ያለንበት የታሪክ ምዕራፍ ነገን ብሩህ አድርጎ ማሰብን የሚጠይቅ ነው!

ሀገር በብዙ ስብራቶች ፈተና ውስጥ በገባችበት ወቅት ወደ ሥልጣን የመጣው የለውጡ መንግሥት ላለፉት አምስት ዓመታት ከፍ ባሉ ተግዳሮቶች የማለፉ እውነታ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፤ ከሆነም ለጥያቄ ሊቀርብ የሚችለው እንዴት እነዚህን ተግዳሮቶች ተሻግሮ ሀገርን እንደሀገር ማቆምና ማጽናት ቻለ የሚለው ነው።

በለውጡ ዋዜማ ሀገሪቱ በብዙ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ እንደነበረች ለየትኛውም ኢትዮጵያዊ የተሰወረ አይደለም። የችግሮቹ ደረጃ እና ጥልቀት ምን ያህል ለሕዝባችን ፈተና እንደሆነ፤ ለለውጥ ንቅናቄው ከእርሾነት ባለፈ የለውጡ ትልቁ አቅም እንደሆነም የአደባባይ ምስጢር ነው።

በለውጡ ማግስትም የለውጡ መንፈስና የቆየው የፖለቲካ ባህል አንጎበር ያልለቀቃቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች፤ ለውጡን ለማኮላሸት የሄዱበት ረጅም ርቀት፤ የሀገርን ህልውና አደጋ ውስጥ እስከመክተት የደረሱበት ክስተት ተፈጥሯል። በዚህም እንደሀገር ለመክፈል የተገደድነው ዋጋ ከፍያለ ነው።

ዛሬ ላይ ላለንበት እና ሕዝባችን ያልተገባ ዋጋ እየከፈለባቸው ለሚገኙ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው። ከለውጡ በፊት ከነበሩ ሀገራዊ ስብራቶች ላይ ተደምረውም ለውጡ በተጠበቀው ፍጥነት እንዳይጓዝ መሰናክል ሆነውበታል፤ በሕዝቡ ውስጥ የነበረውንም የለውጥ መንፈስ አቀዛቅዘውታል።

ከዚህ በተጨማሪም በለውጡ ማግስት የተከሰቱትና ዓለምን የተፈታተኑት ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የኮቪድ ወረርሽኝ፤ ተገማች ያልሆኑ ዓለምአቀፍ ችግሮች፤ ባልተገባ መልኩ በመንግሥትና ሕዝባችን ላይ የተፈጠሩ ዓለምአቀፍ ጫናዎች … ወዘተ የለውጡን ግለት በብዙ ተፈታትነውታል።

መንግሥት ከለውጡ በፊት ሆነ ከለውጡ በኋላ የተፈጠሩ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ስብራቶችን በተገቢው መንገድ በመገንዘብ፤ ሊታከሙ የሚችሉበትን የተለያዩ አማራጮችን ተግባራዊ በማድረግ፤ ስብራቶቹ እንደሀገር ሊፈጥሩ የሚችለውን ጥፋት መቀነስ፤ ለዘለቄታው የሚፈወሱበትን መንገድ ቀይሶ መንቀሳቀስ ችሏል።

በዚህም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በውስጥና በውጭ፤ በሀገር እና በሕዝብ ላይ የሚነገሩ ሟርቶችን በመቀልበስ የሕዝባችንን ነገዎች ብቻ ሳይሆን፤ የመጪው ትውልድን ዕጣ ፈንታ ብሩህ የሚያደርጉ ተስፋ ሰጪ ተግባራትን አከናውኗል። በዚህም በዓለምአቀፍ ደረጃ ዕውቅና እና ከበሬታ አትርፏል ።

በባህሪው ፈታኝ በሆነው የሽግግር ወቅት ፖለቲካዊ ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ፤ በለውጥ እሳቤና እሳቤው በወለደው ቁርጠኝነት፤ ከሽግግር ወቅት ፈተናዎች በላይ በመሆን ሕዝባችን እንደ ሕዝብ የሚመኘውን የበለጸገች ሀገር የመገንባት ራዕይ እውን ማድረግ የሚያስችል የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል።

የትናንትም ሆነ የዛሬ ስብራቶችን መጠገን የሚያስችሉ፤ በጎ ኅሊና ያላቸው፤ ዓይናቸውን ከፍተው ለማየት የታደሉ ዜጎቻችን በልበ ሙሉነት በድፍረት የሚመሰክሩላቸው ተጨባጭ ተግባራትን አከናውኗል። በዚህም ብዙ ዜጎቻችን ነገዎቻቸውን መለወጥ የሚችሉበትን መነቃቃት ማትረፍ ችለዋል።

ይህ የአምስት ዓመት የለውጥ ጉዞ የተፈተነበት ፈተና፤ ከፈተናው በላይ መሆን በሚያስችል የለውጥ አስቤ ባይገዛ ኖሮ ፤ ከፈተናው እና ከተዋንያኑ ብዛት እና ዓይነት አኳያ፤ ሀገር እንደሀገር ዕጣ ፈንታዋ ምን ሊሆን፤ እንደሀገር ቆመን የመጽናታችንም ትርክት ምን ሊመስል እንደሚችል ለመገመት የሚከብድ አይሆንም።

አሁን ያለንበት የታሪክ ምዕራፍ፤ እንደሀገር ከመጣንበት የስብራት ጉዞ ሆነ፤ አሁን እየሄድንበት ካለው የለውጥ /ስብራትን የመፈወስ ጉዞ፤ ከፍያለ ጥንቃቄ የሚጠይቅ፤ ትናንቶችን በደንብ መረዳት፤ ዛሬ ላይ ዘመኑን በሚዋጅ እሳቤ መቆምን እና ነገን ብሩህ አድርጎ ለራሥና ለመጪዎቹ ትውልዶች ማሰብን የሚጠይቅ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ትናንት ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጧቸው ምላሾች፤ የአስተሳሰብ መሠረታቸውም ይኸው ነው። ይህ ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈ፣ ለሀገር፣ ለሕዝብ እና ለትውልዶች ተቋርቋሪ ነኝ የሚል ግለሰብ፣ ቡድን ከዛም ባለፈ የመላው ሕዝባችን የአስተሳሰብ መሠረት ሊሆን ይገባል!

 አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You