ሀገራዊ ምክክሩ ይዞት የሚመጣውን ዕድል በሚገባ መጠቀም ይገባል!

 ኢትዮጵያ በረጅም ዘመናት የታሪክ ጉዞዋ ጥሩም ሆነ መጥፎ ታሪኮችን አሳልፋለች። ጥንታዊና በዓለም ታሪክ ጉዞ ውስጥ የጎላ ስፍራ ከመያዟም ባሻገር የሰው ልጅ መገኛና የነፃነት ዓርማ የሆነች ሀገር ናት። ከዚሁ ጎን ለጎንም የጦርነት፤ የርሃብ፤ የእርዛት፤ የመፈናቀልን ተረክ የያዙ ታሪኮችም ባለቤት ነች።

ስለዚህም ስለ ኢትዮጵያ ስናስብ እነዚህን ሁለት ገጽታዎቿን በአግባቡ መረዳት ይገባል። ይህ መሆኑም ያሉትን ጠንካራ ጎንኖች አጎልብቶ ለማስቀጠልና በሌላም በኩል ጉድለቶቻችንን ለመሙላት ይረዳናል።

እኛ ኢትዮጵያውያን የጀግንነታችንና ለሌሎች ሀገራት ጭምር የነፃነት ተምሳሌት የመሆናችንን ያህል የውስጥ ሰላማችንን በማረጋገጥ ግን ብዙም አልተሳካልንም። በጀግንነትና በሰላም ማስከበር የገዘፈ ታሪክ ያለንን ያህል በሰላም የመኖር ጥበብ የለንም። የኢትዮጵያን ታሪክ መለስ ብሎ ላየው የውስጥ አለመግባባት፤ ግጭትና ጦርነት የበዛበት ነው። በጋራ ታሪኮቻችን ላይ መግባባት ካለመቻላችንም በላይ የግጭትና የጦርነት መንስኤ እስከ መሆን ደርሷል።

ይህ ደግሞ ለተሸጋጋሪ ዘመናት ሀገሪቱን በማያባራ ግጭትና ጦርነት ውስጥ ከቷል፤ ለበርካታ ሰዋዊና ቁሳዊ ኪሳራም ዳርጓል። ለሀገሪቱ ዕድገትም ፈተና ሆኗል። እንደ ሀገርም ያላለቁ የቤት ሥራዎች ያሉብን በመሆኑም በበርካታ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ አልደረስንም። ከሕገ መንግሥት ጀምሮ እስከ ሰንደቅ ዓላማና ሌሎች የማነንት እና የወሰን ጉዳዮች ጭምር ያልተፈቱ የቤት ሥራዎቻችን ናቸው።

እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ ዛሬ የተፈጠሩ አይደሉም። ዘመናትን የተሻገሩና ሲንከባለሉ የመጡ ናቸው። ስለዚህም ዛሬ ባልተፈጠሩ ጉዳዮች መጣላትና ወደ ግጭትና ጦርነት ውስጥ መግባት ትናንትን ካለመመለሱም በላይ ዛሬን ያበላሻል ነገንም ብሩህ ቀን ያጨልማል።

ስለዚህም የግጭት፣የጦርነት፤ ያለመግባባት ታሪካችን ተዘግቶ በጋራ ነገዎቻችን ላይ የምንግባባ፤ ለጋራሀገራችን የምንተጋ፤ ለልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማውረስ የጋራ ዕሳቤ የጨበጥን አዲስ ትውልድ መሆን ይገባናል።

ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በምክክርና በመግባባት ነው። ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባትም እንደሀገር የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል። በእነዚህ ጊዜያትም ምክክሩ የሚመራበትን አቅጣጫ ከመቀየስ ጀምሮ የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮዎችን የመቀመርና በምክክሩ የሚሳተፉ ሰዎችን የመለየት ሥራዎች ተከናውነዋል። በቀጣይም የምክክሩን አጀንዳዎች ከኅብረተሰቡ የመቀበልና ምክክሩን ወደ መሬት የማውረድ ሥራዎች ይከናወናሉ።

ስለሆነም ሀገራዊ ምክክሩ የቀድሞ ችግሮቻችን፤ አሁን ያሉት ችግሮቻችን መፍቻና በቀጣይም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳያጋጥሙን የመፍትሔ አቅጣጫን የሚጠቁመን መድኅን መሆኑን ማመን ይጠበቅብናል። በሀገሪቱም መተማመን የሰፈነበት የፖለቲካ ሥርዓት ለመመስረትም እርሾ ሆኖ እንደሚያግዝ እምነት መጣል ይገባናል።

በቅድሚያ ሁሉም ነገር በንግግር እና በምክክር ይፈታል የሚል እምነት ማዳበር ይጠበቅብናል። የወሰንም ሆነ የማንነት ጥያቄ እንዲሁም ራስን በራስ ማስተዳደር እና የፍትህ ጥያቄዎች በአጠቃላይ የፖለቲካ ጥያቄዎች እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በሙሉ በሀገራዊ ምክክር ሊፈቱ እንደሚችሉ እምነት ማሳደር ይጠበቅብናል።

ሀገራዊ ምክክሩ አሁን ያሉትን አለመግባባቶች አስወግዶ በፍቃደኝነት እና በመግባባት ላይ የተመሠረተች ኢትዮጵያን እውን የማድረግ አቅም አለው። የማይተካ ሚና አለው። ስለዚህም ሀገራዊ ምክክሩ ይዞት የመጣውን ዕድልና ጸጋ መጠቀም የአሁኑ ትውልድ ትልቁ የቤት ሥራ ነው።

ትውልዱ በዚህ ዕድል መጠቀም ካልቻለ ግን ለመጪው ትውልድ ያልተረጋጋች ሀገር እንደምናወርስ ከወዲሁ ግንዛቤ ልንጨብጥ ይገባል። ይህ ማለት ደግሞ የመጪውን ትውልድ መጻኢ ሕይወት ማጨለም ማለት ነው።

ስለሆነም የታሪካችን አንዱ ክፋይ ሆኖ ዘመናትን የተሻገረውን ጦርነትና ግጭትን ለማስወገድና የተረጋጋች፤ ሰላሟ የተጠበቀ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማውረስ ሀገራዊ ምክክሩ ይዞ የመጣውን ዕድል ልንጠቀምበት ይገባል። ይህ ታሪካዊ ወቅትም የነገዋን ብሩህ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የማይተካ ሚና እንዳለው መረዳትና ለተግባራዊነቱም መንቀሳቀስ የዚህ ትውልድ የቤት ሥራ ነው!

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You