«ሀገራት በቀይ ባሕር አካባቢ ይዞታቸውን እያጠናከሩ ኢትዮጵያ ላይ ጥያቄ መነሳቱ አስገራሚ ነው» -አዳፍረው አዳነ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መምህር

ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን የመልማት ጥረቷን የምታቋርጥ አገር አይደለችም፡፡ ትናንት የተፈጥሮ ሀብቷን በአግባቡ ተጠቅማ ለመልማት የሔደችበት መንገድ የማንንም ሉዓላዊ መብት እንዳልተጋፋ ሁሉ ዛሬም ያንኑ በመድገም የማንንም አገር ሉዓላዊ መብት ሳትነካ ያቀደቻቸውን የልማት ትልሞች ከማሳካት ወደኋላ አትልም፡፡ ይህን የምታደርገው ግን እቅዷን ሊያቆረፍድና ሊያዘገይ የሚፈልግ አካል ሳይኖር በመቅረቱ አይደለም፡፡

ከአንድ ወር በፊት ለልማቷ መሳለጥ የጀርባ አጥንት የሆነውን የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከራስ ገዟ ሱማሌላንድ ጋር መፈራረሟን ተከትሎ ተፈጥሮ ጠላቶች የሆኑ ሀገራት ላይ ድንጋጤን መፍጠሩ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁንና ዛቻም ሆነ ማስፈራሪያ የማያስበረግጋት ኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞዋን ቀጥላለች፡፡

ከሰሞኑን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን ለመስክ ዘገባ ወደተለያዩ ክልሎች መውጣቱን ተከትሎ አዲስ ዘመንም ወደ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጎራ በማለት በዩኒቨርሲቲው በስነ ዜጋ እና ስነ ምግባር ትምህርት ክፍል የመልካም አስተዳደርና ልማት መምህር የሆኑትን መምህር አዳፍረው አዳነን ከዚሁ ከባሕር በር ስምምነቱ ጋር አያይዞ ቃለ ምልልስ አድርጎ ተከታዩን አጠናቅሯል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

 አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሱማሌላንድ ጋር ያደረገችው የባሕህር በር ስምምነት አንዳንድ ሀገራትን ያስደነገጠበት ምክንያቱ ምንድን ብለው ያስባሉ?

መምህር አዳፍረው፡– ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሱማሌላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት እንደ አገር ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ በስምምነቱ ዙሪያ ብዙ የሚንጸባረቁ የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም የተኬደበት መንገድ ግን የአገራችንን የወደፊት እጣ ፈንታ እና በአፍሪካ ቀንድ አገራት መካከል የሚኖረውን የግንኙነት መስመር ሊወስን የሚችል መስመር አድርጌ የምወስደው ስምምነት ነው፡፡

በእርግጥ ስምምነቱ ከራስ ገዟ ሱማሌላንድ ጋር መሆኑ አንዳንድ ጩኸቶችን አስተናግዷል፡፡ ይህ ደግሞ ከተለያዩ ምክንያቶች ሊመነጭ ይችላል፡፡ አንደኛው ብዙዎቹ ሱማሌላንድ ዓለም አቀፍ የሆነ እወቅና የተሰጣት አገር አይደለችም የሚል መነሻ ነጥብ ያነሳሉ፡፡ ነገር ግን ከተባበሩት መንግስታት እውቅና ባይሰጣትም እንኳን ከ1991 ጀምሮ ረዘም ያለ ዓመታትን እራሷን ስታስተዳድር ቆይታለች፡፡

ከዚህም የተነሳ ራስ ገዝ የሆነች አገር ናት። ከዚያ ወዲያ የተለያዩ ምርጫዎችን ያካሔደች እና የራሷ የሆነ የመንግስት ስርዓት ያላት መሆኑ የሚካድ አየይደለም፡፡ በተጨማሪም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ያሏት አገርም ናት፡፡ የራሷ የሆነ መገበያያ ገንዘብ ያላት አገር ናት፡፡ ዜጎቿ ከአገር አገር የሚንቀሳቀሱበት እና የሚዘዋወሩበት የራሷ የሆነ ፓስፖርት ያላት አገርም ጭምር ናት፡፡

በአንድ ወቅት በ2005 አካባቢ ሱማሌላንድ ከአንድ ያልተወከለው የብሔሮች እና ሕዝቦች ድርጅት (Unrepresented Nations and Peoples Organization) ከሆነ ዓለም አቀፍ ተቋም (ተቋሙ ባልተወከሉ ሕዝቦች ዙሪያ የሚሰራ ነው) ወይም ደግሞ የሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለማስጠበቅ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነውና እሱንም ተቀላቅላለች፡፡ ከዚህ የተነሳ አንድ እርምጃ ወደፊት የሄደች አገር ናት ማለት እንችላለን፡፡

ትልቁ ነገር እና በአብዛኞቹ የሚነሳው የእውቅና እና የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡ የእውቅና ጉዳዩ እንደ ትልቅ ጉዳይ የሚነሳው ወይም እንደ ትልቅ ጉድለት የሚነሳው ኢትዮጵያ ላይ ብቻ መሆኑ ነው ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳው፤ ወይም ደግሞ ትልቅ ጥያቄ ያስነሳል ብዬ የማስበው ኢትዮጵያ እና ሱማሌላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ላይ ሲሆን መጉላቱ ነው፡፡ ለምን ቢባል ሱማሌላንድ በተደጋጋሚ ጊዜ ምርጫ ስታካሒድ ቆይታለች፡ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ታዛቢዎችን ሲልኩ የነበሩ አካላት አሉ፤ በዋናነት የአውሮፓ ኅብረት ታዛቢዎችን ልከው ምርጫ ታዝበዋል፡፡ ይህን ይህን ነገር ሁሉ ሲያደርጉ የዚያን ያህል የጎላ ነገር አልነበረም፡፡ የጎላ ኮሽታም አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ ያደረገችው ስምምነት ላይ ግን የዚያን ያህል መጉላቱ በራሱ አጠያያቂ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ሀገራት በቀይ ባሕር አካባቢ ይዞታቸውን እያጠናከሩ ኢትዮጵያ ላይ ጥያቄ መነሳቱ አስገራሚ ነው፡፡

ሌላው ይህን ጩኸት ያጎላው ነገር ነው ብዬ የማስበው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለውን የእድገት ጎዳና እንደ ስጋት የሚያዩ አገራት በመኖራቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ጎረቤት አገር ሱዳንና ግብጽ የሚሔዱባቸው ርቀቶች የኢትዮጵያን የጋራ ተጠቃሚነት ፍላጎት ወደጎን በመተው ለማዳፈን ነው፡፡ በዋናነት አሁን ግብጽን ከወሰድን የቅኝ ግዛት ሰነዶችን የማስቀጠል ፍላጎት ያላት ናት፡፡ ከዚህ የተነሳ የኢትዮጵያን የመልማት ጥያቄ በበጎ ጎኑ ሳይሆን በክፉ ጎኑ የምትመለከት አገር ናት፡፡

ከእርሷ ጎን የሚሰለፉም አገራት አሉ፡፡ ይህ ከጂኦፖለቲክሱ ጋርም ይያያዛል ብዬ አስባለሁ፡፡ እናም ኢትዮጵያ ባለንበት ቀጣና ወይም በአፍሪካ ቀንድ ላይ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በሌሎችም አቅጣጫዎች ላይ ጎልታ እንድትወጣ አይፈለግም፡፡ ይህ ደግሞ የጎረቤት አገሮች ፍላጎት ብቻም ሳይሆን (ጎረቤት አገሮች ስል ሁሉንም ማለት አይደለም) የሌሎችም ሀገራት ስጋት ሊሆን ይችላል፡፡ ከእነዚህ አገራት በተጨማሪ ደግሞ ኃያላን የሚባሉ አገራት ፍላጎትም ሲታከልበት ኢትዮጵያን በዚህ መንገድ ጎልቶ መታየት ወይም ደግሞ በዚህ ጎዳና ላይ የመንቀሳቀስ ጅማሮዎችን በበጎ የሚያዩትም እንዳሉ ሁሉ በመጥፎ ጎን የሚመለከቱ አገራትም ይበዛሉ፡፡

ይህ የዓለም ስርዓት ባሕሪም ነው፡፡ በእርግጥም ቋሚ የሆነ ወዳጅ የለም፤ ቋሚ የሆነ ጠላትም የለም፡፡ ሁሉም አገር የአንድን አገር እድገት የሚፈልገው ከእርሱ አገር ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚሔድ ከሆነ ነው፡፡ የአንድ አገር እድገት ከእነርሱ ወይም ደግሞ ከእነርሱ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚጻረር ከሆነ እና መስሎ ከታያቸው ያንን ነገር ለማደናቀፍ የማይኬድበት ርቀት የለም፡፡ እንደ ማሳያ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በድጋሚ መውሰድ እንችላለን፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ እርዳታም ድጋፍም እንዳታገኝ እና ነገሮች እንዲጓተቱ የሚደረግ ጣልቃ ገብነቶች የዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ አሁንም ያለንበት የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የምትችልበት ሰነድ መፈራረም በጣም የጎላ ተቃርኖዎችን እና ጩኸቶች ሊያስተናግድ የቻለው በእነዚህ ምክንያቶች ነው፡፡

 አዲስ ዘመን፡- የባሕር በር ስምምነቱን ተከትሎ የወጡ መግለጫዎች ሲጤኑ ከሱማሊያ ጎን የቆሙ የሚመስሉ ይሁኑ እንጂ ኢትዮጵያን ፊት ለፊት የተጋፈጡ አይደለም የሚሉ አሉ፤ በእርግጥ ይህ ምንን የሚያመላክት ነው?

መምህር አዳፍረው፡– ልክ ነው፤ እስካሁን እየወጡ ያሉ መግለጫዎች ስናያቸው ኢትዮጵያን በግልጽ የኮነነ ሳይሆን በተዘዋዋሪ ነካ ለማድረግ የሚሞክሩ አይነት መግለጫዎች ናቸው፡፡ የሱማሊያን ሉዓላዊነት በተመለከተ ይህን ሁሉ ዓመት ራስ-ገዝ ሆና ስትቀጥል የራሷ መንግስት፣ ገንዘብ፣ የመንግስት ስርዓት ኖሯት ስትቀጥል ለሱማሊያ ሉዓላዊነት እንደ አገር ካሰብነው ትርዒት ነው የሚሆነው፡፡ ማለትም የሱማሊያ የሉዓላዊነት ጉዳይ አሳሳቢ ሆኖ ቢሆን እና ሱማሌላንድ የእኔ ናት የሚባል ከሆነ አቤቱታው መሰማት የነበረበት በእነዚህ ሒደቶች ውስጥ ነበር፡፡

ስለዚህ አንድ ግዛት በእኛ ሁኔታ ምናልባት እንደ ክልል ልንወስደው የምንችለው አይነት ግዛት የራሱ የሆነ መንግስት፣ የራሱ የሆነ ገንዘብ፣ የውጭ ጉዳይ ግንኙነት እያደረገ እንቅስቃሴ ከጀመረ ለማዕከላዊ መንግስቱ ፈተና ነው የሚሆነው በለን ስለምንደመድም ከወዲሁ የራሱ የሆነ መንግስት፣ የራሱ የሆነ ገንዘብ፣ የውጭ ጉዳይ ግንኙነት እያደረገ እንቅስቃሴ እንዳይጀምር በመጀመሪያ ነው ሊሰራበት ይገባል የምንለው፡፡ ምክንያቱ እሱ የአገር ሉዓላዊነት ላይ የሚመጣ ፈተና ነውና ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ከሆነ ሱማሌላንድ ከ25 ዓመት ወደዚህ ምርጫ አድርጋለች፡፡ ከዛ በፊት የነበሩ ዓመታትን ደግሞ ስንጨምር ወደ 33 ዓመታት በራሷ ኖራለች፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ ግን የጎላ ነገር አልሰማንም፡፡

አገራቱ ኢትዮጵያ ላይ ስለምንድን ነው በግልጽ ተቃውሞ ያልገለጹት የሚለው ነገር በጣም ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ ምናልባትም እንደ ዓለም አቀፍ ሕግ ስናየው (ዓለም አቀፍ ሕግ በእርግጥ ተፈጻሚነቱን ካየነው በጣም ደካማ የሚባል የሕግ አይነት ነው) ሕጉ አገም ጠቀም ነው፡፡ ከአገር ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ አገራት ሁሉ የሚወዳደሩት ብሔራዊ ጥቅማቸውን አስቀድመው ነው፡፡

የአንድን አገር ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል ያደረገ አይነት የዓለም አቀፍ ሕግ ተፈጻሚነትን እስከዛሬ አላየንም፡፡ እንኳን የአንድን አገር አይደለም፤ የዓለም የጋራ የሆኑ ችግሮችንም ለመፍታት የዓለም አቀፍ ሕጎች ቶሎ አይፈጸሙም፤ ወይም ደግሞ ቀላል የሆነ የማስፈጸሚያ ዘዴ የላቸውም፡፡

በኢትዮጵያ ላይ ስምምነቱን ተከትለው የሚወጡ መግለጫዎች በቀጥታ ኢትዮጵያ ያልጠቀሱበት ምክንያት የራሱ የሆነ ክፍተት የሚያመጣ በመሆኑ ነው፡። እስከ ዛሬ ድረስ ያሉ ክፍተቶችም አሉ፡፡ የዓለም አቀፍ ስርዓቱም ይታዘበዋል፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅብረሰብም ይታዘበዋል፡፡ አሁን ሁሉም የዓለም ማኅብረሰብ አንድ አይነት አመለካከት አይኖረውም፡፡

ግብጽና እና ሱዳንን ጨምሮ እንዲያውም ግብጽ በሱማሊያ ሰሜኑ አካባቢ ላይ የራሷ የሆነ የወታደራዊ ቤዝ ያላት አገር ናት፡፡ ስልጠናዎችን ትሰጣለች፡፡ ወታደራዊ ድጋፍ ትሰጣለች፡፡ መሰል ነገሮችም ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን በቀጥታ ኢትዮጵያን ለመኮነን ያልደረፈሩበት ምክንያት ምናልባት ምስጢራዊ ሊሆን ይችላል፡፡ የዓለም አቀፍ ሕጎችን ስናያቸው ተፈጻሚነታቸው ደካማ ነው። እና የሱማሊያ ሉዓላዊነት ተደፍሯል ለማለት የትኛውን ሕግ ልንጠቀም እንችላለን? ምክንያቱም ቀደም ብሎ የነበሩ ታሪኮችን ስናይ በቅኝ ግዛትም የተለያዩ ቦታ ላይ የነበሩ አገራት ናቸው፡፡ አንደኛዋ በጣሊያን ስር፣ ሱማሌላንድ ደግሞ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበረች አገር ናት፡፡ አንድ ላይ ለመዋሃድ ሙከራዎች የነበሩትም ከነጻነት በኋላ ነው፡፡ ይሁንና መልሰው የተለያዩ አገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ እነዚህ ክፍተቶችም ምናልባት እንደ ክፍተት የሆኑ ይመስለኛል፡፡ በቀጥታ ኢትዮጵያን ላለመኮነን ምክንያቶች ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከሱማሌላንድ ጋር ስምምነት ማድረጓ ቀጣናው እንዳይረበሽ ያሰጋናል የሚሉ አካላት አሉ፤ ተስማምቶ አካባቢን ለማልማት የሚደረግ ሙከራ ጦርነት ማወጅ የሆነው ከመቼ ጀምሮ ነው?

መምህር አዳፍረው፡- የጦርነት ስጋቶች ይኖራሉ፡፡ አገራትም እነዚህን ስጋቶች ያንጸባርቃሉ። ነገር ግን የተፈረመው ስምምነት ጦርነት ሊያመጣ ይችላል ወይ የሚለው ነው ዋናው ቁም ነገር፡፡ ምክንያቱም የተደረገውን ስምምነት በቀና መንገድ ካየነው የጦርነት መንስዔ ይሆናል ብዬ አላስብም። ነገር ግን እውነት ለመናገር ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ላይ ሲሆን ነገሮች ይበረታሉ። እንዲያም ሆኖ ግን በተደረሰበት ስምምነት ምክንያት ነገሮች ጦዘው ወደጦርነት ሊያመራ ይችላል የሚል ግምት ላስቀምጥ አልችልም፡፡፡ ነገር ግን ስጋቶች አሉ፡፡ በእርግጥ ስምምነቱ የጦርነት መነሻ ሊሆን ይችላል ወይ? የሚለውን ካየን ግን ሊሆን አይችልም ባይ ነኝ፡፡

ምክንያቱም የአንድ አገር በኢኮኖሚ መበልጸግ በማንም ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ነው ብሎ መደምደም የሚያስኬድ አስተሳሰብ አይደለም። በአንድ ቀጣና ውስጥ ወይም በአንድ የአፍሪካ ቀንድ ላይ የአንድ አገር መልማት የሌላውም አገር መልማት ነው፡፡ የአንድ አገር በኢኮኖሚ ከፍ ማለት ለሌላውም የኢኮኖሚ መተሳሰሮችን የሚፈጥር ነው፤ እንዲያውም አፍሪካ አንድ ወጥ የሆነ የኢኮኖሚ ስርዓት እና የግብይት ስርዓት የምትፈጥርበት ሒደት ነው፡፡ ይህ አይነት እሳቤ ባለበት ሒደት ውስጥ የአፍሪካ አገራት እርስበእርሳቸው አንዱ ለሌላኛው እንቅፋት የመሆን እንቅስቃሴዎች መታየታቸው አሁንም ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ አለመውጣታችንን የሚያመላክት ነው፡፡ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ አልወጣንም የሚል እሳቤም እንድናነሳ ያደርገናል፡፡

ምክንያቱም እኔ የአፍሪካን እድገት የማይ ፈልጉት አፍሪካውያን አይደሉም የሚል አተያይ አለኝ፡፡ አፍሪካ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በሌሎችም ረገዶች እንዳትበለጽግ የሚፈልጉት ቀድሞ ቅኝ ሲገዙ የነበሩ አገራት ናቸው፡፡ እስካሁንም ደግሞ ኒኮሎኒያሊዝም የምንለው ሒደት ውስጥ ከአፍሪካ የራሳቸውን የሆነ ጥቅም ማስጠበቅ የሚፈልጉ አገራት ናቸው፡፡

እነርሱ ይህን ውዥንብር ሊነዙት ይችላሉ። በተጨማሪም ደግሞ ይህንን አጀንዳ ተቀብለው የሚያስፋፉትና የሚነዙት አፍሪካ አገራትም አሉ፡፡ ጎረቤት አገራትም አሉ፡፡ ብዙ ያልተስማማንባቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ የሕዳሴ ግድቡን መውሰድ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ከጎረቤት አገራት ጋር ጦርነት እንድትገባ መንስዔ ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን አሰላለፎችን ስናይ ሌላው ቀርቶ ጎረቤት አገራት ያላቸው አሰላለፍ አንደኛው ከሌላኛው ጋር ጎራ ሲይዝ የባላንጣነት አይነት ነጸብራቆች ናቸው ያሉት፡፡ ምናልባት እነዚህ ነገሮች ሊያጦዙ እና ወደጦርነት ሊያመሩ ይችላሉ የሚሉ ስጋቶች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ራሱ ጉዳዩ የጦርነት መነሻ ምክንያት ይሆናል የሚል እሳቤ አይኖረኝም፡፡

አዲስ ዘመን፡- የባሕር በር ስምምነቱ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ የሚያደርገው ከምን አንጻር ነው?? ሕዝቡስ የሚጠቀመው ምንድን ይላሉ?

መምህር አዳፍረው፡– የባሕር በር ለማግኘት የተደረገው ስምምነት በሒደት ከጥቅም አንጻር ያየነው እንደሆነ ያሉት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ናቸው፡፡ የባሕር በር እንደ ጽንሰ ሀሳብ ወይም እንደ አንድ ትልቅ ጉዳይ ከወሰድነው ለአንድ አገር የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ እድገት ትልቅ መሰረት ሊጥል የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለንበት የዓለም ስርዓት አንድ አገር እንኳን ኢትዮጵያን የሚያህል የሕዝብ ብዛት ያለው አገር ቀርቶ በጣም አነስተኛ ቁጥር የሕዝብ ብዛት ያለው አገር አንኳን ወደብ አልባ ሆኖ የሚቆይበት ከተቀረው ዓለም ጋር ለመገናኘት ትልቅ ዋጋ የሚከፍልበት እና ራስን ነጥሎ የሚቆይበት ነገር የማይታሰብ ነው፡፡

ስለዚህ የዓለም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ስርዓት እየተሳሰረ ያለ ነው፡፡ ወደፊት ደግሞ ከዚህ የባሰ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የምናገኛቸው ነገሮች ምንድን ናቸው ከተባለ አንደኛው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ነው፡፡ በዚህ መንገድ አገሪቷ ልታስመዘግብ የምትችለው ወይም ደግሞ ልታተርፍ የምትችለው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ኢኮኖሚው ላይ ብቻ የሚቀር አይደለም፡፡

ምናልባት የሰላም መሰረትም አንዳንድ ጊዜ ኢኮኖሚ እንደ ትልቅ ዋልታ የሚወሰድ ጉዳይ ነው። ስለሆነም ሕዝቦች መሰረታዊ ጥያቄዎቻቸው ከተመለሱና የኦኮኖሚ ጥያቄዎቻቸው ከተመለ ሰላቸው፤ ሕዝቦች ወደሰላም እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቻቸው ይመለሳል የሚል አስተሳሰብ ይኖራቸዋል፡፡

ስለሆነም ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ሰላም የምንላቸው ነገሮች የሚነጣጠሉ አይደለም። አንድ አገር በኢኮኖሚ እያደገች ስትሔድ ጥሩ መሪ ካላት እየሰፈነ የሚሄደው ሰላማዊ የሆነ መስተጋብር ነው፡፡ በዚህ መንገድ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካዊና በማኅበራዊው በስነ ልቦናውም ረገድ የተሻለ ነገር ይዞ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡

ስለዚህ እኛ የባሕር በር የመጠቀም እድል አለን ማለት ትልቅ ነገር ነው፡፡ እኛ ቀይ ባሕር ጎረቤታችን ሆኖ መጠቀም አለመቻላችን ከስነ ልቦና ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ምናልባትም እንደ ሕዝብ የተሻለ መነቃቃትን ይፈጥራል የሚል ግምት አለኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የባሕር በር ስምምነቱን ተከትሎ ብዙዎች የየራሳቸውን ፍላጎት የሚያሳብቅ አይነት መግለጫ እንዳለው ሁሉ አንዳንድ ኢትዮጵያውያንም ስምምነቱን ሲቃረኑ ይስተዋላል፤ ለእነዚህ ሰዎች ያልዎት አመለካከት ምንድን ነው?

መምህር አዳፍረው፡– ይህ ከምን ይመነጫል የሚለውን አስቀድሞ ማየቱ ጠቃሚ ነው። በእርግጥም ስምምነቱን የደገፉ እንዳሉ ሁሉ የተቃወሙ እና የተለያዩ ድምጾችን ያሰሙ ግለሰቦችም ቡድኖችም አሉ፡፡ ነገር ግን ለዚህ ምንጮቹ ምንድን ናቸው? የሚለውን ማየት አግባብ ነው፡፡ ምናልባት ምንጩ ነው ብዬ የማስበው በአሁኑ ወቅት አገራችን ላይ የሚታዩ ነገሮች አንደኛው አለከመረጋጋት መስተዋሉ ነው። ግጭቶች ይስተዋላሉ፡ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ተብሎ የሚታሰቡ ነገሮች አሉ፡፡ እዚያም እዚህም የድርቅ ችግር አለ፡፡

ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ የሆኑም ችግሮች አሉና ምናልባትም ሕዝቡ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚችሉ ነገሮች እያሉ ሌላ ተጨማሪ ግጭት መጥመቅ እና ሌላ ጦርነት መጥራት ለምን አስፈለገ የሚሉ ነገሮች ላይ ይነሳሉና ምናልባትም መነሻ ምክንያቶቹ አገራችን አሁን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ልክ ነው አይደለም የሚለው በእርግጥ አወዛጋቢ ሊሆን ይችላል፡፡ አጠያያቂም ሊሆነ ይችላል፡፡ ነገር ግን እኛ በውስጥ ጉዳያችን ወይም በውስጥ ፈተናዎቻችን ተተብትበን ነው ያለነው ብለን ማግኘት ያለብንን ጥቅም ማለትም ውጪያዊ ጥቅም ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባቸዋል የሚል አቋም አይኖረኝም፡፡ እና አንድ ላይ ማስኬድ እንችላለን ወይ ለሚለው አዎ! ማስኬድ እንችላለን ነው መልሴ።

የውጪ ጉዳዮቻችንን በተሻለ መንገድ ወይም የተሻለ የዲፕሎማሲያዊ አካሄድን በተከተለ መንገድ እነሱን ማሳካት እንችላለን፡፡ ሁሌም በውስጥ ችግሮቻችን ብቻ ታጥረን የምንቆይ ከሆነ ከዚያ አዙሪት ውስጥ ላንወጣ እንችላለን። የአገራችን ችግር ብዙ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው።አንዳንድ ጊዜ መሻሻሎች የሚታዩ ሲሆ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የሚብሱ ነገሮች አሉና በዚህ ሒደት ውስጥ የምንቀጥል ከሆነ ወደተሻለ ከፍታ ከመሄድ ይልቅ ወደ አዘቅት ውስጥ ልንወርድ እንችላለን፡፡ ስለዚህ ባሉብን ችግሮች ብቻ ታጥረን መቆየቱ እና እነርሱን ብቻ ነው እናስተካክል ማለቱ አዋጭ አይደለም። በቀጣይ ማድረግ ያለብን ወይም ቅድሚያ መስጠት ያለብን የሚለው ነገር ምናልባት እንደ አገር ካየነው ፈተና ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ፈተና ሊሆንም ይችላል፡፡

ከተቻለ ለአገራችን የሚበጃት ውስጣዊ ችግሮቻችንን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት ጠቃሚ ነው፡፡ በእርግጥ ደግሞ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተጀመሩ ስራዎች እንዳሉ እሙን ነው። አሁንም እኔ የተሻለ ነው ብዬ የማስበው እነዚህ ውስጣዊ ናቸው ምንላቸው ችግሮች ራሳችን የፈጠርናቸው ችግሮች ናቸው፡፡ ተፈጥሯዊ ችግሮ ሳይሆኑ ሰው ሰራሽ ችግሮች ናቸው፡፡ ሰው ሰራሽ ችግሮቻችንን እኛው የፈጠርናቸው ችግሮች ናቸውና ልንፈታቸው እንችላለን፡፡ በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር ልንፈታቸው እንችላለን፡፡ ነገር ግን እነዚህ ችግሮች ስላሉብን አገራችን ማግኘት የተጋባትን ጥቅም መጠየቅ የለባትም የሚለው አስተሳሰብ ጨለምተኝነት የሚታይበት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የመግባቢያ ሰነዱ ተፈርሟል፣ መመሪያዎችና ደንቦችም ይዘጋጃሉ ተብሎ ሲነገር ቆይቷል፤ በቀጣይስ ምን መሆን አለበት ይላሉ? ከዜጋውስ ምን ይጠበቃል?

መምህር አዳፍረው፡– እንደ መንግስት መሰራት ያለበት የተጀመረው ትልቅ ነገር ከዳር ማድረስ ነው፡፡ ይህን ትልቅ ነገር ውጤታማ በሆነ መንገድ ጫፉ ላይ ለማድረስ ደግሞ የሕዝብ ድጋፍ እና ይሁንታ ሊኖረው ይገባል። በተቻለ መጠን አስተሳሰብ ላይ መስራት እና ግንዛቤ ለመፍጠር መጣር ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር ሚዲያው ትልቁን ሚና መጫወት ይጠበቅበታል። በተለይ ሚዲያው የአመለካከት ክፍተት ላይ ሊሰራ ይገባል፡፡

እንደ ሕዝብ ሲታሰብ ደግሞ አሁንም ቢሆን ነገሮችን ሆደ ሰፊ ሆኖ ማየት ጠቃሚ ነው የሚል አተያይ አለኝ፡፡ የማይካዱ ነገሮች አሉ፤ የምናያቸውም ፈታኝ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከሰላምም ሆነ ከኢኮኖሚ አንጻር ሲታይ በአሁኑ ወቅት አገራችን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ሕዝቡን የሚፈትነው እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ በእርግጥ የሚሰሩና እየተመዘገቡ ያሉ ነገሮች መልካም የሚባሉ ናቸው፤ ነገር ግን ገበያውን ልናይ ይገባናል። የኑሮ ውድነቱና የመሳሰሉ ነገሮችን ስናይ ሕዝቡን እንደ ሕዝብ ወደዳር ሊገፉት የሚችሉ ምክንያቶች ናቸው፡፡ መንግስት እነዚህ ነገሮች ላይ የመስራት፣ ጣልቃ የመግባት እና በተቻለ መጠን የማረጋጋት ስራዎችን እየሰራ በጎን ደግሞ ስለ ባሕር በሩ ሊሆን ይችላል ስለሌሎች አገራዊ ጉዳዮችም ሊሆን ይችላል ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች ላይ መስራት ይጠበቅበታል፡፡

ከሕዝቡ የሚጠበቅ ነው ብዬ የማስበው ነገሮችን ሆደ ሰፊ ሆኖ መመልከት ነው፡፡ እርስ በእርስ የሚያጋጩን ነገሮች መቀነስ ነው፡፡ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ በሚታዩ ነገሮች አንዱ ከሌላው ጋር የሚቆራቆዝበት ጉዳይ ከማድረግ መቆጠብ ነው፡፡ ነገሮችን እያጦዙ ያሉት የማኅበረሰብ አንቂ ከሚባሉት መካከል ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያውን የምንጠቀምና ተማርን የምንል ሰዎች ነን፡። አንዳንድ ጊዜ ግጭትን የምንጠምቀው እኛው ራሳችን ነን ብዬ አስባለሁ፡፡ ምሁራን ናቸው ብለን የምንጠራቸው ደግሞ ነገሮችን ማርገብና ሰላማዊ ሒደቶችን መፍጠር ላይ ቢጠመዱ ሕዝቡን ወደ ተሻለ አስተሳሰብ ሊመሩ የሚችሉ ናቸው፡፡ የተሻለም ሰላም ማምጣት ይቻላል ብዬ አሳስባለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

መምህር አዳፍረው፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ጥር 27/2016  ዓ.ም

Recommended For You