ሰላም ልጆችዬ፣ እንዴት ናችሁ? ሰላም ናችሁልኝ? ‹‹በጣም ደህና ነን። ›› እንደምትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ልጆችዬ፣ ትምህርታችሁን ስትከታተሉ የነበራችሁ ተማሪዎች የመጀመሪያውን መንፈቅ ዓመት፤ ወይም አንደኛ ሴሚስተር ፈተና ወስዳችሁ እንዳጠናቀቃችሁ ይታወቃል።
ልጆችዬ፣ ታዲያ ዝግጅታችሁ ምን ይመስል ነበር? ፈተናውስ እንዴት ነበር? ቀለላችሁ፣ ወይስ ከበዳችሁ? መቼም ልጆችዬ፣ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ጊዜያችሁን በጥናት እና በንባብ እንዳሳለፋችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም። ልጆችዬ፣ ሁልጊዜም እንደምንላችሁ ጥናት የሚጀመረው ፈተና ሲደርስ ብቻ አይደለም። ስለዚህም ሁሌም ማጥናት፤ ሁሌም ማንበብ ይኖርባችኋል።
አንዲት ጎበዝ ተማሪ እናስተዋውቃችሁ። ተማሪ ኑሀሚን ከተማ ትባላለች። የአራተኛ ክፍል ተማሪ ናት። በትምህርቷ ጎበዝ ስትሆን ባለፈው ዓመት ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው። ዘንድሮም የበለጠ ውጤት ለማምጣት በርትታ እያጠናች እና ትምህርቷን እየተከታተለች ትገኛለች።
እስካሁን በተፈተነቻቸው ፈተናዎች «ጥሩ» የሚባል ውጤት ለማምጣት ችላለች። ባሳለፍነው ሳምንት ፈተና ተፈትነው እንዳጠናቀቁ የምትናገረው ኑሀሚን፤ እረፍቷን የተለያዩ መጻሕፍትን በማንበብ፣ አልፎ አልፎ ደግሞ ቤተሰብ በመርዳት በማሳለፍ ላይ እንዳለች ትናገራለች። ልጆችዬ፣ እናንተም እንደሷ እንዳቀዳችሁ፣ በእቅዳችሁ መሠረትም እያሳለፋችሁ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ።
ልጆችዬ፣ እረፍቱ አልቆ ወደ መደበኛ የትምህርት ገበታችሁ ተመልሳችሁ የፈተና ውጤታችሁን ስትቀበሉ የመጀመሪያ ሥራችሁ ሊሆን የሚገባው ምን መሰላችሁ? ራሳችሁን መመዘን። እንዴት ነበር ያጠናሁት? በክፍል ውስጥ የነበረኝ ተሳትፎ ምን ይመስላል? ለፈተና ያደረኩት ዝግጅት ምን ይመስላል? በማለት ራሳችሁን መጠየቅ አለባችሁ። ይህ ማሻሻል ያለባችሁን ነገር እንድታሻሽሉ ያግዛችኋል። በጣም ጥሩ ውጤት ባመስመዘገባችሁት የትምህርት ዓይነቶች ላይ ከዚህ በፊት ታደርጉትን የነበረውን የጥናትም ይሁን ትምህርታችሁን የምትከታተሉበትን መንገድ ማስቀጠል ይኖርባችኋል።
ጥሩ ውጤት ካላመጣችሁ ደግሞ ለምን ብላችሁ ጠይቁ። ስላልገባኝ ነው? መምህራን በክፍል ውስጥ ሲያስተምሩ ከልቤ ስላልተከታተልኩኝ ነው? ያልገባኝን ስላልጠየኩኝ ነው? ወይስ ፈተና ስፈተን መመሪያ እና ትዕዛዞችን በሚገባ ባለማንበቤ ተሸውጄ ነው? የሚሉትን እና ሌሎችን ጥያቄዎች በመጠየቅ ራሳችሁ መፈተሽ ይኖርባችኋል።
ሌላው ደግሞ ልጆችዬ፣ በትምህርታችሁ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ከፈለጋችሁ ሁልጊዜ ከማጥናት ባሻገር መምህራን በክፍል ውስጥ ሲያስተምሯችሁ አጠገባችሁ ካለው ተማሪ ጋር ማውራት የለባችሁም። መረበሽም አያስፈልግም። እናም ልጆችዬ፣ በክፍል ውስጥ በንቃት መምህሮቻችሁ ምን ማስተማር እንደፈለጉ በንቃት በመሳተፍ፣ በመከታተል፣ ያልገባችሁን በመጠየቅ ማሳለፍ ይገባል።
በትምህርት ቤት ውስጥ ያላችሁን ትርፍ ሰዓት ደግሞ በጨዋታ ብቻ ከማሳለፍ ወደ ቤተ መጻሕፍት በማቅናት ብታጠኑ በትምህርታችሁ ውጤታማ ለመሆን ያግዛችኋል። በተጨማሪም ከትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁ ጋር በጋራ በማጥናት እና ስለ ትምህርት በመጠያየቅ ማሳለፍ ይኖባችኋል።
ልጆችዬ ጥሩ ውጤት አላመጣሁም ብሎ መጨናነቅ ግን ተገቢ አይደለም። ከዚያ ይልቅ ‹‹እንዴት ላሻሽል?›› ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። አንደኛ ሴሚስተር ወደ ሌላው ምዕራፍ እንድትሸጋሩ ዕድልን የሚሰጥ መሆኑን መቼም ታውቃላችሁ አይደል? እናም የዓመቱን ጥሩ ውጤት ለማምጣት በጥንካሬያችሁ መቀጠል ሲኖርባችሁ፤ ከድክመታችሁ ለመሻሻል ደግሞ የመምህራን፣ የወላጅ (አሳዳጊ)፣ እንዲሁም የእናንተ ድርሻ ከፍተኛ ነው።
ልጆችዬ፣ ለሁሉም ነገር ጊዜ፣ ወቅት እና ልክ አለው አይደል? ‹‹በትክክል›› እንዳላችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም። ስለዚህም እናንተ የምትገኙበት ዕድሜ የትምህርት መሆኑን በማሰብ ሙሉ ትኩረታችሁ ትምህርት እና ትምህርት ላይ ብቻ ማድረግ ይኖርባችኋል።
ሌላው ልጆች፣ በእረፍት ጊዜያችሁ ቴሌቪዥን፣ ታብሌት፣ ሞባይል እና መሰል ነገሮች ላይ ጊዜ የምታጠፉ ከሆነ በትምህርታችሁ ጥሩ ውጤት እንዳታስመዘግቡ እንቅፋት ይፈጥርባችኋልና ከዚህ ድርጊት ራሳችሁን አርቁ፤ እሺ ልጆች። ይህ ብቻ እንዳይመስላችሁ ልጆችዬ? በጤናችሁ ላይ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑን በመገንዘብ ከእንዲህ ዓይነቶቹ፣ ጤናን ከሚጎዱ ነገሮች ራሳችሁን ማራቅ ይኖርባችኋል።
ወላጆች እና አሳዳጊዎችም ይህንን በመገንዘብ ልጆቻችሁ የእረፍት ጊዜያቸውን በንባብ፤ እንዲሁም ትምህርት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይኖርባችኋል። በተጨማሪም ጥናት እና ሌሎች ነገሮች የሚከውኑበትን ሰዓት (ፕሮግራም) በማውጣት ልጆቻችሁ በእቅድ እና በፕሮግራም እንዲመሩ ያግዛቸዋል።
ከተቻለም በአካባቢ ወደ´ሚገኙ ቤተመጻሕፍት እንዲሄዱ በማድረግ የእረፍት ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማበረታታት ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ የተለያዩ እውቀቶችን እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል። ታዲያ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ አደጋ እንዳያጋጥማቸው በጥንቃቄ እንዲሆን ከእናንተ እገዛ በተጨማሪ የሌሎችንም ርዳታ እንዲጠይቁ ማድረግ ይቻላል፤ ለምሳሌ የቤተመጻሕፍት ባለሙያዎችን።
ልጆችዬ ለዛሬው በዚህ እናብቃ አይደል? በአጠቃላይ ግን ፈተና ጨርሳችሁ አይደል? የሚኖራችሁን እረፍት በንባብ፣ ቤተሰቦቻችሁን በመርዳት፣ እንደ ሙዚቃ፣ ቴአትር፣ የፈጠራ ሥራ እና ሌሎች ችሎታ ካላችሁ ደግሞ እነሱን ለማዳበር እንደምትጠቀሙበት ተስፋ አደርጋለሁ። ልጆችዬ ሳምንት ደግሞ በሌላ ርዕሰ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ በማድረግ፤ መልካሙን ሁሉ ለእናንተ እንመኛለን።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን እሁድ ጥር 26 ቀን 2016 ዓ.ም