ኢትዮጵያ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት የባሕር በር ሳይኖራት፣ ለብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫናዎች ተጋላጭ ሆኖ ቆይታለች። ከዚህም ባለፈ በአካባቢው ለዘመናት የነበራት ስትራቲጂክ አቅሞች ተዳክመው፣ በወደብ እና በባህር ጉዳይ የበይ ተመልካች ለመሆን ተገዳለች።
ሀገሪቱ እንደ ሀገር የወደብ ባለቤት እንዳትሆን ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጨምሮ ብዙ የውጪ ጫናዎችን አስተናግዳለች። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከአንድም ሁለት ወደብ ባለቤት የመሆኗ ታሪክ ተለውጦ፤ ዛሬ ላይ የገቢ ወጪ ንግዶቻችንን ማስተናገድ የሚያስችል አስተማማኝና ቀልጣፋ የወደብ አማራጮችን ማግኘት ሳትችል ቀርታለች።
በሀገሪቱ ከሚታየው የሕዝብ ቁጥር ዕድገት፤ ዕድገቱ ሊያስከትለው ከሚችለው ሁለንተናዊ ጫና እና ሀገሪቱ አሁን ላይ እያስመዘገበችው ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አኳያ፤ አስተማማኝና ቀልጣፋ የወደብ አማራጭ ጉዳይ ነገ ላይ የሕልውና ጥያቄ ሊሆን እንደሚችል በማጤን ጉዳዩ ትልቅ አሁናዊ ሀገራዊ አጀንዳ ሆኗል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕር ሕግ አንቀጽ 69 ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 5 የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ካለው ባሕር የተፈጥሮ ሀብት እኩል የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ ይህም፣ ዓሣ ማጥመድን እና በባሕር ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ፍለጋን ጨምሮ ሌሎች ከባሕር ተፈጥሮ ሀብት ጋር የተያያዙ ሀብቶች ተጠቃሚነት መብትን ያካትታል፡፡
የዚሁ ሕግ አንቀጽ 125 ንዑስ አንቀጽ አንድ፤ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ያለውን ባሕር የመጠቀም እና የመሸጋገር ዓለም አቀፍ መብት አላቸው። ይህ መብት የባሕር በር በሌለው ሀገር፣ የባሕር በር ባለቤት በሆነው ሀገር እና በቀጣናው መካከል በሚደረግ ስምምነት ሊፈጸም እንደሚገባ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ሁለት ላይ ተመላክቷል፡፡
አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ፤ እነዚህ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በስምምነት ከተደረገ የተለየ የአገልግሎት ክፍያ ከሌለ በስተቀር ለተገለገሉበት ባሕር ምንም ዓይነት የትራፊክ ታክስ ወይንም ሌላ ክፍያ እንደማይጠየቁ ይደነግጋል፡፡
የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በምስረታ ቻርተሩ መግቢያ ላይ፤ በባሕር ሕግ ጉዳዮች ላይ ባሰፈረው ሀተታ የአፍሪካ ሀገራት የባሕር በር ያላቸውን ጨምሮ ከባሕር ሊያገኙት የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ እንዳልሆነ አመልክቶ፣ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ከባሕር የመጠቀም መብታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ እና ይህም ከዓለም አቀፍ መርህ አንጻር ሊታይ እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡
በእነዚህ ዓለም አቀፋዊ የሕግ ድንጋጌዎችና ኢትዮጵያ ለውሃ አካላት ካላት ቅርበት አንጻር፤ የባሕር በር የማግኘት መብት አላት። የባሕር በር ጥያቄና ፍላጎቷም በሃይማኖት፣ በሞራል ሆነ በሌሎች የሥነ ምግባር ሕግጋት ተቀባይነት ያለውና ምክንያታዊ ነው፡፡ የባሕር በር ባለቤት መሆኗም ከራሷ አልፋ ለሌሎችም የሚያተርፍ እንደሚሆን ይታመናል፡፡
ሀገሪቱ አስተማማኝና ቀልጣፋ የወደብ አማራጮችን ለማግኘት እየተጓዘችበት ያለው የፖለቲካ እሳቤ ሰጥቶ በመቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ፣ አብሮ ማደግና መልማትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ፤ ከሁሉም በላይ የአካባቢው ሀገራት ያላቸውን የተፈጥሮ ጸጋዎች አቀናጅተው ለሕዝቦቻቸው የጠሸሉ ነገዎችን ለመፍጠር የተሻለ ዕድል የሚፈጥር ነው።
በቅርቡ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረሰበት የመግባቢያ ስምምነት፤ የዚህ ትልቅ ቀጣናዊ ራዕይ አንድ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው፤ ከዛሬ ስድስት አስርት ዓመታት በፊት የነበሩ አፍሪካውያን አባቶቻችን እውን ሊያደርጉት ብዙ ዋጋ የከፈሉበት የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ተግባራዊ መገለጫ ጭምርም ነው።
ድህነት እና ኋላ ቀርነት፤ ግጭት እና ጦርነቶች፤ የተደጋገመ የድርቅ አደጋ እና ረሀብ፤ ሞት፣ ስደት የኑሮ ሰቆቃ በዝቶ በሚስተዋልበት በዚህ ቀጠና እነዚህን ችግሮች ለዘለቄታው አሸንፎ መሻር የሚለው፤ በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ጸጋዎች አቀናጅቶ በጋራ ተጠቃሚነት መንቀሳቀስ ሲቻል ብቻ ነው።
ተገማች ያልሆኑ ችግሮች በየወቅቱ የዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ትኩረት እየሳቡ ባለበት ሁኔታ፤ የቀጠናው ሀገራት ሕዝቦች በሚጠበቀው መልኩ ዓለም አቀፍ ትኩረት አግኝተው ለችግሮቻችው ዘላቂ መፍትሄ ያገኛሉ ብሎ ማሰብና አካባቢው ባለፉት ስድስት አስርቶች የነበረበትንና አሁን ላይ ያለበትን ሁኔታ በአግባቡ ማጤን ተገቢ ነው!
አዲስ ዘመን ጥር 27/2016 ዓ.ም