እኛ ኢትዮጵያውያን ነፃነታችንን አስከብረን ዘመናትን መሻገር የቻልነው ለሀገራችን ካለን መተኪያ የሌለው ፍቅር፣ ፍቅሩ በየዘመኑ ከፈጠረው የመስዋዕትነት ገድል እንደሆነ ታሪካችን በስፋት የሚዘክረው እውነት ነው። ለፍትህ እና ለነፃነት ያለን ቀናኢነትም የዚሁ ታሪካዊ እውነታ አካል እንደሆነም ይታመናል።
የቀደሙት አባቶቻችን በየዘመኑ የተነሱብንን፤ በኃይል አስገዝተው የባርነት ቀንበር ሊጭኑብን የተነሱ የውጭ ኃይሎችን አሳፍረው በመመለስ እስከዛሬ ትውልዶች ቀና ብለው የሚሄዱበትን ታሪክ በደማቸው ጽፈው አልፈዋል። በዚህም ኢትዮጵያዊነት የነፃነትና ቀንዲል የሆነበትን ዓለም አቀፍ ትርክት ፈጥረዋል።
በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶችም የአባቶቻቸውን ፈለግ በመከተል ሀገር እንደ ሀገር ጸንታ ትቆም ዘንድ፤ የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል። የአሁኑም ትውልድ የዚሁ ሀገራዊ ትርክት አካል በመሆን ከፍያለ መስዋዕትነት እየከፈለ፤ ሀገሪቱ ከተጋረጠባት አሁናዊ ስጋቶች በብዙ መስዋዕትነት እየታደገ ይገኛል።
በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሀገር እንደሀገር፤ የህልውና ስጋት ውስጥ በገባችበትና የውስጥና የውጭ ኃይሎች ተናበው እና ተቀናጅተው፤ በጋራ በተንቀሳቀሱበት ወቅት ትውልዱ፤ እንደቀደሙት አባቶቹና አያቶቹ ከፍ ባለ የሀገር ፍቅር ስሜት ፤ ሀገራዊ አደጋዎችን በመቀልበስ አደራ ተረካቢነቱን በተግባር አስመስክሯል።
ከመንግሥት የቀረበለትን ሀገርን የመታደግ ጥሪ ሳያቅማማ በመቀበል፤ በግዳጅ ወረዳዎች ራሱን እያበቃ፤ መስዋዕትነት በሚፈጥረው ጠንካራ ስብዕና ራሱን እያጸና፤ ስለ ሀገሩ ያለውን የማይናወጥ አቋም አሳይቷል። በሀገር ጉዳይ መደራደር እንደማይቻል እራሱን ለመስዋዕትነት በማቅረብ ጭምር በተጨባጭ አስመስክሯል።
በሀገር ጉዳይ ላይ የማይናወጥ አቋም ከፍ ያለ መስዋዕትነት በሚጠይቁ የግዳጅ ቀጣናዎች በመዝለቅ ለሕይወቱ ሳይሳሳ፤ ሀገርን በመታደግ የራሱን ታሪክ በደሙ ጽፏል፡፡ የአባቶቹ ልጅ በመሆን፤ የተንሰላሰለው የትውልዶች የጀግንነት ታሪክ አካል እንደሆነም አረጋግጧል።
መንግሥትም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሀገሪቱን የመከላከያ ኃይል አቅም በሁለንተናዊ መልኩ ለማሳደግ እየሄደበት ያለው ስትራቴጂና እየተመዘገበ ያለው ስኬት የዚሁ እውነታ አንድ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። በቀጣይም የሠራዊቱን አቅም ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶች መሠረታቸው ይኸው ትውልዱ ለሀገሩ በክብር ለመሰዋት ያሳየው ቁርጠኝነት እንደሚሆን ይታመናል።
ትናንት የመከላከያ ሠራዊቱ ፈተናዎች ውስጥ በነበረበት ወቅትም ሆነ አሁን ደግሞ የመከላከያ ሠራዊቱን አቅም ለማሳደግ ሠራዊቱን በስፋት እየተቀላቀለ፤ የተለያዩ ሥልጠናዎች እየወሰደ፤ ራሱን ለግዳጅ ዝግጁ እያደረገ ያለው ወጣት ትውልድ የዚህ እውነታ አካል ነው።
ሕገመንግሥቱንና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ከመጠበቅ አንስቶ፤ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች እንደሀገር የፈጠሩብንን የሰላም እጦት በመቀልበስ ሕዝባችን በሰላም ወጥቶ የሚገባበትን፤ የዕለት ተዕለት ሕይወቱን ያለ ስጋት የሚመራበትን ሀገራዊ አውድ ከመፍጠር አኳያ ብዙ የሚጠበቅበትና ሕዝባችንም ተስፋ የሚያደርግበት ነው።
ከዚህም ባለፈ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ሆኑ፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ከፍ አድርገን ከያዝናቸውን ትላልቅ ሀገራዊ ራዕዮቻችን ጋር በተያያዘ ሊያጋጥሙን የሚችሉ ስጋቶችን በመቀልበስ፤ እንደ ሀገር ብሩህ ነገዎችን ሠርተን አዲስ የታሪክ ትርክት ለመፍጠር ለጀመርነው ሀገራዊ ንቅናቄ መድህን ነው።
ይህ የሀገርን ህልውና እና ተስፋ፤ የሕዝብን ሰላም ለማስከበር በተለያዩ ሙያዎች በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ በስፋት እየተካተተ፤ እየሰለጠነና ራሱን እያበቃ ያለ ትውልድ፤ የሀገርን ህልውና አደጋ ውስጥ የከተቱ ትናንቶች በሁለንተናዊ አቅማቸው በድጋሚ እንዳይከሰቱ ማስተማመኛ ሀገራዊ አቅም ነው።
ቀደም ባሉት ጊዜያትም ሆነ ትናንት በሁርሶ ኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ማዕከል/ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ሰልጥነው የተመረቁ ዕጩ መኮንኖችን፤ ራሳቸውን የአንድ ትልቅ የተንሰላሰለ ታሪክ አካል አድርገው ማየት፤ ራሳቸውን ለታሪክ ሠሪነት ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል!
አዲስ ዘመን ጥር 26/2016