መንግስት ለፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ትግበራ ያሳየው ቁርጠኝነት የሚመሰገን ነው!

 የሰላም እጦት ከለውጡ ማዜም ጀምሮ ሀገራችንን እንደ ሀገር እየተፈታተነ ያለ ትልቅ ተግዳሮት ነው። የለውጡ እሳቤና ተጨባጭ አካሄድ ያልተመቻቸው የውጪና የውስጥ ኃይሎች በተናጠልና በተቀናጀ መንገድ የለውጡን ጉዞ ለማደናቀፍ በስፋት ተንቀሳቅሰዋል። በዚህም የተፈጠረው የሰላም እጦት የመላውን ሕዝባችንን የዕለት ተዕለት ሕይወት እየተፈታተነ ይገኛል።

በተለይም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሕወሓት ብዙ የሰላም አማራጫችን ረግጦ በቀሰቀሰው ግጭት ሀገርን ለሁለንተናዊ ቀውስ መዳረጉ የሚታወስ ነው። በዚህም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ለሞትና ለአካል ጉዳት፤ በቢሊየን የሚቆጠርም የሀገር ሀብት ለውድመት ተዳርጓል። የችግሩ ሰብአዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠባሳም ዛሬም ሀገርን ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ነው።

መንግስት ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ ይፈታ ዘንድ ይዞት የነበረውን የቀደመ የጸና አቋም ታሳቢ በማድረግ፣ ”ለአፍሪካዊ ችግር በአፍሪካዊ መፍትሄ ” በሚል ከወዳጅ ሀገራትና ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በመሆን በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ በስምምነት እንዲቋጭ ትልቁን ኃላፊነት ወስዶ ተንቀሳቅሷል።

ብዙ ሰላምን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶችን በቋርጠኝነት በመሻገር፤ ግጭቱ በሰላም ስምምነት መፍትሄ እንዲያገኝ ረጅም ርቀቶችን ተጉዟል። በዚህም በአካባቢው የሰላም አየር እንዲነፍስ አድርጓል። ለሰላም ያለውን የጸና አቋም በድጋሚ ለመላው ሕዝባችንና ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በተጨባጭ ማሳየት ችሏል።

በስምምነቱ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ በማድረግ፤ በግጭቱ ምክንያት መልከ ብዙ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ዜጎቻችንን ሕይወት ለመታደግ እና ወደቀደመው የተረጋጋ ሕይወታቸው እንዲመለሱ፤ የተገኘውን ሰላም የሚገዳደሩ ፈተናዎችን በሆደ ሰፊነት ለመሻገር ረጅም ርቀት ተጉዟል፤ ለዚህም ብዙ ዋጋ ከፍሏል።

በተለይም የትግራይ ሕዝብ፤ ጦርነቱ ከፈጠረው የስነልቦና ስብራት እንዲያገግም፤ በእለት ተእለት ሕይወቱ ላይ የተደቀነውን የከፋ አደጋ ለመቀልበስ፤ የሀገሪቱ አሁነኛ አቅም ሊፈቅድ የማይችለውን ከፍተኛ ሀብት በመመደብ ለሕዝቡ ያለውን አጋርነት አሳይቷል። ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ወደ አካባቢው በመላክ አጋርነቱን አሳይቷል፡፡

ሕዝቡ የባንክ፣ የቴሌኮም፣ የመንገድ፣ የጤና፣ የትምህርትና ..ወዘተ መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ሰፊ ጥረቶችን በማድረግም፤ የፕሪቶርያ ስምምነት በተፈረመ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ በጀትና ባለሞያዎችን በመመደብ በክልሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ አድርገዋል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የክልሉን የዘርፍ መሥሪያ ቤት ለማጠናከር ከተወሰዱ ርምጃዎች ባሻገር ለካፒታል በጀት 4.9 ቢልዮን ብር፤ ለመደበኛ በጀት 11.4 ቢልዮን ብር፣ እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 400 ሚልዮን ብር፤ በድምሩ 16.7 ቢሊዮን ብር በ2015/16 ለክልሉ ሰጥቷል፡፡ በክልሉ ለሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች 5.1 ቢልዮን ብር ሰጥቷል፡፡ በልማት አጋሮች በኩል የ1.7 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለትግራይ ክልል እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በቻናል አንድ 1.7 ቢሊዮን እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስቴር በክልሉ ባቋቋመው ጽ/ቤት በኩል፣ በትግራይ ለሚከናወኑ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች እና ለአየር ንብረት ለውጥ ፕሮጀክቶች በድምሩ ከ565 ሚልዮን ዶላር በላይ ፈሰስ ተደርጓል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ፕሮጀክትም 65 ሚሊዮን ብር ለክልሉ ተላልፏል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በክልሉ የሚገኙ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶችንና ተቋማትን ለማብቃት ሥልጠና ሰጥተዋል፤ ቁሳቁስ አሟልተዋል፤ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጾታን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶች የምላሽ አገልግሎት የሚውል ከ7 ሚልዮን ዶላር በላይ ለክልሉ ድጋፍ ተሰጥቷል፡፡

በጦርነቱ የተጎዱ ድልድዮችን በጊዚያዊነት ለመጠገን እንዲቻል ሁለት ተገጣጣሚ ድልድዮች የተለገሱ ሲሆን አራት ድልድዮችን ለመገንባት ጨረታ ወጥቷል፡፡ በጦርነቱ ወቅት የተቋረጡ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችንም በልዩ ፕሮግራም የክልሉ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ለዘጠኝ ከተሞች የፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ የሚውል ከ409 ሚሊዮን ብር በላይ እና ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለክልሉ ተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርም ለደመወዝና ለሥራ ማስኬጃ እና ለመንገድ ፕሮጀክት ጥገና ከ418.6 ሚልዮን ብር በላይ ወደ ክልሉ ልኳል፡፡ ለትግራይ ገጠር መንገድ ጥገና ከመንገድ ፈንድ ከብር 107 ሚልዮን ብር በላይ፤ የ2026 በጀት ቅድመ ክፍያ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ተልኳል፡፡ በፕላንና ልማት ኮሚሽን በኩል ደግሞ በጠቅላላው የ4.2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል፡፡

ድጋፉ ከሁሉም በላይ የትግራይ ሕዝብ ወደቀደመ ሰላማዊ ሕይወቱ እንዲመለስ በመንግስት በኩል ያለውን እና የነበረውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ለፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈጻሚነት፣ ምን ያህል ከስምምነቱ በላይ ምን ያህል ረጅም ርቀት እየተጓዘ እንዳለ በተጨባጭ የሚያመላክት ነው።

በዚህ ደረጃ ከፍ ባለ ሕዝባዊና ሀገራዊ ኃላፊነት እየተንቀሳቀሰ ያለው የፌደራል መንግስት፤ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አንዲተገበር የነበረው ዝግጁነትና ያሳየው አፈጻጸም በማንኛውም ሚዛን ቢለካ እውቅና ሊሰጠው የሚገባና የሚያስመሰግነው ነው!።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You