መልካም ዓይኖች – ትናንትን ላለፉ፣ ነገን ለሚያሻግሩ እጆች

1996 ዓም፡፡ ተመሳሳይ ስሜትና ፍላጎት፤ አንድ አይነት ዓላማና ግብ ያላቸው ወገኖች ስለ አንድ ወሳኝ ጉዳይ በአንድ ሆነው ሊመክሩ ተገናኙ፡፡ እነሱን መሰል ወገኖች መስራት እየቻሉ የሰው እጅ እያዩ ነው፡ ዕውቀት ችሎታው እያላቸው ዕድል፣ አጋጣሚን ስላጡ ብቻ አስታዋሽ ዓይን አላገኙም። ይህ እውነት በበርካቶች ውስጠት የኖረ ሀቅ ነው፡፡ አሁን ለዚህ እንቆቅልሽ መልስ ለመሻት አንድነት ኃይል ሊሆን እነሆ ጊዜው ደርሷል፡፡

በርካቶቹ አካል ጉዳተኞች ባለባቸው ችግሮች ምክንያት ለበዙ መከራዎች ይጋለጣሉ፡፡ ሰርቶ ለማደርና፣ ቤተሰባቸውን በወጉ ለማስተዳደር አመቺ ሁኔታ ባለመኖሩም፣ የሰው እጅ በማየት ለልመና የሚዳረጉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ይህን እውነት እየኖሩት ካሉት በርካቶች መሀል ‹‹ችግር ይብቃን፣ ራሳችንን እንቻል›› ያሉ ሰብሰብ ብለው ስለነጋቸው መከሩ፣ ተማከሩ፡፡ ውሎ አድሮ የምክሩ ሀሳብና ዓላማ የገባቸው ሌሎች ተቀላቀሏቸው። ሁሉም ከዕለት ገቢያቸው እየነጠቁ፣ ያላቸውን እየቆጠቡ፣ ለቁምነገር ተዘጋጁ፡፡ የቻሉ ጥርሳቸውን ነክሰው ቁጠባቸውን ቀጠሉ።

ኑሮና ህይወት ያንገዳገዳቸው ደግሞ ጅምር መንገዳቸው ተቋረጠ፡፡

ከበረቱት ጥቂቶቹ የሀሳባቸው ጉልበት በርትቶ፣ የኪሳቸው አቅም ዳበረ፡፡ ይህኔ ዓላማቸውን ከግብ ሊያደርሱ፣ ሀሳብ ህልማቸውን ሊፈቱ ጥያቄ ይዘው አቀረቡ፡፡ በወቅቱ ከቤት ከጓዳቸው፣ ከልጆቻቸው አፍ እየነጠቁ የቆጠቡት በቂ ጥሪት በእጃው ነበር። ጥያቄው የቀረበለት የመንግሥት አካል ሀሳባቸውን ያስረዱ ዘንድ ዕድሉን ሰጣቸው፡፡

ብርቱዎቹ አካል ጉዳተኞች ውጣ ውረድ የበዛበትን አስቸጋሪ ህይወታቸውን ለማሳየት እማኝ አላሻቸውም።

ፈታኙን ኑሮ የሚለውጥ፣ ታሪካቸውን የሚቀይር ራስን የመቻል ሀሳብ መሰነቃቸውን በዝርዝር አስረዱ፡፡ ለዚህ እቅዳቸው የሚመጥን የመስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸውም ጠየቁ።

በወቅቱ የነበሩ የወረዳ ኃላፊዎች የእነሱን ሀሳብ ላለመቀበል ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› አሉ፡፡ በ‹‹አናውቃችሁም›› ሰበብ ፊት ሊያዞሩባቸው ሞከሩ። ይባስ ብሎ ለመሰብሰብና ተገናኝቶ ለመወያየት እንዳይችሉ ገደብ ጣሉባቸው።

ብርቱዎቹ አካል ጉዳተኞች ግን በተስፋ መቁረጥ ዝም አላሉም፡፡ በየዕለቱ በግንባር ተገኝተው ሀሳቡን በሀሳብ ሞገቱ። እንደ ዜግነታቸው መብታቸው ተከብሮ፣ ሊደራጁ፣ ቦታ ሊሰጣቸውና የሥራ ዕድል ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ አስረዱ፡፡

የጀመሩት ጉዳይ በወረዳው ላይ ብቻ አልቀረም። ከፍ ብሎ ክፍለ ከተማ የሚያደርሳቸው ሆነ፡፡ አሁንም በስፍራው ሲገኙ የያዙትን ዓላማና የሰነቁትን በጎ ተስፋ ለሚመለከታቸው አካላት አንድ በአንድ ዘረዘሩ፡፡ ሰርቶ በመለወጥ የሚተገብረውን ዕቅድና ያላቸውን አቅም አሳይተው ምላሹን ጠበቁ፡፡

ውሎ አድሮ ሀሳብ ፍላጎታቸው ከልብ ገባ፣ መልካም ዓይኖች በትኩረት አስተዋሏቸው። ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶም የተነፈጉት የመሰብሰብ ዕድል ተፈቀደላቸው። የዓመታት ህልማቸውን ዕውን ሊያደርጉ ሌት ተቀን ባዘኑ። በወቅቱ ጥቂት በጎ አድራጊ ድርጅቶች ዓላማቸውን ደግፈው ከጎናቸው ቆሙ፡፡

1996 ዓ∙ም መገናኛ አካባቢ የሚገኝ የማምረቻ ቦታን በሊዝ ተረክበው ሥራ ሲጀምሩ ‹‹ብሩክ፣ ሀብታሙና ጓደኞቻቸው›› የስጋጃ አምራች ማህበር በሚል ስያሜ ሆነ። በተረፋቸው ገንዘብ የማምረቻ ማሽኖችንና የተለያዩ ቁሶችን አሟሉ፡፡ የልፋታቸው ዋጋ ለተጨማሪ ወገኖች ዋርካ ሆኖ ብዙኃንን አሰባሰበ፡፡

ማህበሩ አካል ጉዳተኞች በራሳቸው አቅም ሰርተው እንዲያድሩ፣ ከልመናና፣ የሰውን እጅ ከማየት ልማድ እንዲላቀቁ ተምሳሌት ሆነ፡፡ በወቅቱ ከሰላሳ በላይ አባላት የነበሩት ይህ ማህበር በእኔነት ስሜት ተመስርቷልና ትርጉሙ ዋጋ አላጣም፡፡ ሁሉም ዕውቀት ጉልበቱን ሰጥቶ የማህበሩን ምሰሶ ሊያቆም ታገለ፡፡

ያለአንዳች ብድርና የመንግሥት እርዳታ ሥራ የጀመረው ማህበር አንዱን ከአንዱ እየሞላ በእንቅስቃሴው ተጓዘ፡፡ መንገዱ ዕዳ ላለመግባትና ላለመክሰር ጥንቃቄ ያለበት ነበር፡፡ እንቅስቃሴው ያለ ማንም ድጋፍና የገንዘብ እገዛ ነበርና በአቅም ማጣት መንገዳገዱ አልቀረም፡፡

የማህበሩ የሥራ ልፋትና የሌት ተቀን ድካሙ የታሰበውን ያህል አልሆነም፡፡ የገበያ ትስስሩና፣ የማቴሪያል አቅርቦቱ ዋጋ መናር ችግር ያስከትል ያዘ። የሚገኘው ገቢ ማነስ ለውጥን ለሻቱት ብርቱዎች ተስፋ አስቆረጠ፡፡ ውሎ አድሮ ችግሩን መቋቋም ያልቻሉ አባላት ከማህበሩ ራቁ፡፡ ሌሎችም በሞት ተለዩ፡፡ ይህ አጋጣሚ የማህበሩን አባላት ቁጥር ዝቅ ማድረጉ አልቀረም፡፡

የማህበሩ ህልውና ግን ከእርምጃው አልተገታም። ከነችግሮቹም ቢሆን መስመሩን ይዞ በጥንካሬ ተጓዘ፡ ፡ ከሚያመርታቸው የስጋጃ ውጤቶች ባሻገር መወልወያ፣ መጥረጊያና ቡሩሽን በተለየ ጥራት እያዘጋጀ በጠባብ ዕድልም ቢሆን ለገበያ ማቅረብ ያዘ፡፡ የሻወር ቤቶችን በመስራት፣ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ለገቢ ምንጩ ታተረ፡፡ ሱቆች ከፍቶ የእጆቹን ጥበብ ‹‹እነሆ››አለ፡፡

አቶ ብሩክ መልካሙ የማህበሩ መስራችና ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ባለ ትዳርና የሰድስት ልጆች አባትም ናቸው። ድርጅቱ በ1996 ዓ∙ም ሲቋቋም ዓላማ አድርጎ የተነሳው አካል ጉዳተኛ ወገኖችን ራስን ለማስቻልና ለልጆቻቸውና ለቀጣዩ ትውልድ የሞራል ስብራት ላለመሆን እንደነበር ይናገራሉ፡፡

በዚህ ሂደት በነበረው ጉዞም ሥራና ተግባራቸው ለሌሎች ጭምር አርአያ መሆኑን ማሳየት ጥረታቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እንደ አቶ ብሩክ ዕምነት አካል ጉዳተኞች ዕድልና አጋጣሚውን ካገኙ ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ የሚያግዳቸው አይኖርም፡፡

በአሁኑ ጊዜ ማህበሩ የተለያዩ አካል ጉዳት ያለባቸውን ወገኖች በአባልነት አቅፎ ይገኛል፡፡ አቶ ብሩክ ደጋግመው እንደሚሉት፤ ይህ ሀሳብ ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡ በአስቸጋሪ የኑሮ ፈተና ውስጥ የሚገኙ በርካታ አካል ጉዳተኞች በየቤታቸው ያሉ በመሆኑ እነዚህ ወገኖች በማህበሩ ታዛ ስር ቢካተቱ ምኞታቸው ነው፡፡

አግኝቶ ማደር፣ ሰርቶ መለወጥ የብሩክ፣ ሀብታሙና ጓደኞቻቸው ትጋትና ህልም ነው፡፡ ማንም አካል ጉዳተኛ ባለበት ተጽዕኖ ምክንያት ከቤት መዋልና መቸገር አይኖርበትም ፡፡ ይህን እውነት ከግብ ማድረስ ዓላማው የሆነው ማህበር እስካሁን የራሱን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

በማህበሩ ሰርቶ ለመለወጥ፣ አግኝቶ ለማደር የሚተጉ ነፍሶች ሌት ተቀን መልፋት ልምዳቸው ነው። አንዳንዴ ግን ይህ ልፋት ድካማቸው በአንድ እጅ የማጨብጨብ ያህል ጎዶሎ ይሆናል፡፡ እነዚህ ወገኖች ጥረታቸው ቢቀጥልም ምርቶቻቸውን የሚጎበኝላቸው፣ ለሽያጭ የደረሱትን አይቶ ‹‹ልግዛችሁ›› የሚላቸውን ጠያቂ አላገኙም፡፡

ትናንት ብዙ ዋጋ ከፍለው ያቋቋሙት ማህበር ዛሬ በዚህ የኑሮ ውድነት አቅም ሊሆናቸው ሲገባ ሆድ ያስብሳቸው ይዟል፡፡ ባላቸው አቅም ተፍጨርጭረው የሚያመርቷቸው ውጤቶች በበቂ ሁኔታ የገበያ ትስስሩን ዕድል አላገኙም፡፡

በዓመት ለጥቂት ቀናት የባዛር ዕድል ቢኖርም በሚገኘው ገንዘብ ዕቃ ከመግዛት የዘለለ ደሞዝ ይሉትን አያውቁትም፡፡ አብዛኞቹ ጧፍ በመሸጥ፣ ቤተሰቦቻቸውን ያኖራሉ፡፡ የማህበራቸው መቆም ህልውናቸው ነውና ዛሬም ከስፍራው አልራቁም። ይህ እውነት በብዙ እየፈተናቸው ያለው ወገኖች አሁን ላይ የብዙኃንን ትኩረት ይሻሉ፡፡

አቶ ብሩክ እንደሚሉት የማህበራቸው መቋቋም ዋና ዓላማ ለጥቂት ሰዎች ብቻ አይደለም፡፡ በብዙ ችግሮች ውስጥ ለሚገኙ በርካታ አካል ጉዳተኞች ጭምር እንጂ፡፡ ያሰቡት ተሳክቶ የልባቸው ቢሞላ ድርጅታቸውን ይበልጥ አስፋፍተው ብዙኃንን የማሳተፍ ውጥን ነበራቸው፡፡

ዛሬ ላይ በዚህ ማህበር በህይወት የተለዩትን ጨምሮ በተስፋ መቁረጥና አቅም ማጣት የራቁት አባላቶች ጥቂቶች አይደሉም፡፡ እንዲህ ለመሆኑ ዋንኛ ምክንያት ከማህበሩ የሚገኘው ገቢ በቂ አለመሆኑና ቋሚ የደመወዝ ተከፋይነት ልምድ አለመኖሩ ነው፡፡

አቶ ብሩክ በሀገራችን በርካታ ባለሀብቶች ስለመኖራቸው ያስታውሳሉ፡፡ በጎ ልቦና ያላቸው ሰዎችም ጥቂቶች አይደሉም ባይ ናቸው፡፡ እነሱ ወደ እነዚህ ወገኖች ቀርበው ማህበሩን ቢጎበኙና የቻሉትን አስተዋጽኦ ቢያደርጉ ድርጅቱ ስብራቱ ተጠግኖ የሚያገግምበት አጋጣሚው የሰፋ ነው፡፡

ይህ ማህበር በዋንኛነት የአካል ጉዳተኞችን ያሰባሰበ ቢሆንም ጉዳት አልባ የሆኑ ጭምር በሙያና በጉልበታቸው ያግዙታል፡፡ እንደ ማህበሩ መስራቾች ዕምነት ድርጅቱ በታሰበው ልክ ቢሰፋ ኖሮ ለበርካታ ወገኖች የገቢ ምንጭ ለመሆን በቻለ ነበር፡፡

አቶ ሀብታሙ አሰፋ የማህበሩ ምክትል ሰብሳቢ ናቸው፡ ፡ በድርጅቱ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች የእጅ ጥበብ ለሌሎች በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እንደሳቸው አባባል በመረሳት ላይ ያለውን የስጋጃ ሥራ ጨምሮ ሌሎችም ምርቶች ባህልና ቅርስን በማቆየት ድርሻቸው የላቀ ነው፡፡ ድርጅቱ በነበረው ጠንካራ እንቅስቃሴ ከሌሎች ወረዳዎች በተሻለ ሞዴል ሆኖ ሲመሰገን ቆይቷል፡፡

እንደ አቶ ሀብታሙ አገላለጽ በአሁኑ ጊዜ ማህበሩ በቀድሞ ማንነቱ እንዳይቀጥል ሌላ ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ አካባቢው ለመንገድ ልማት በማስፈለጉ ምክንያት የግቢው ግማሽ ይዞታ እንዲፈርስ ሆኗል። የይዞታው መፍረስ ደግሞ የነበሩ እሴቶችን ጭምር በማክሰም የገቢ ምንጮችን አስቀርቷል፡፡

ይህ ስፍራ በርካታ ጉድለቶችን የሚሞላ፣ ገቢን የሚደጉምና ሰፊ ዕቅድ የታያዘበት ነበርና ብዙ አጉድሏል። እንዲህ መሆኑ ቀድሞ በነበረ ችግር ላይ ሌላ ችግር እንዲደረብ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡

ለአካባቢው ማህረበረሰብ ጥቅም ይውሉ የነበሩ የመሸጫ ሱቆች፣ ዘመናዊ የመጸዳጃና የሻወር ቤቶች የማህበሩን ጎን በመደጎም ላቅ ያለ ድርሻ ነበራቸው። እነዚህ ቤቶች በሚገነቡ ጊዜ ከፍተኛ የሚባል ወጪ ተደርጎባቸዋል፡፡ በርከት ያሉ የባህር ዛፎችን ጨምሮ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችም በከተማ ግብርና ዕውቅና የተቸራቸው የማህበሩ ሀብት ንብረቶች ነበሩ፡፡

እንደ አቶ ሀብታሙ አባባል እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም የማህበሩ አባላት የአካባቢውን መልማትና ማደግ የሚቃወሙ አይደሉም፡፡ በመጣው ለውጥና ግንባታ ከልብ ደስተኞች ናቸው፡፡ ነገን በተሻለ ለመራመድ የስፍራው መለወጥ በጎ ስለመሆኑ በጽኑ ያምናሉ፡፡

ማህበሩ በራሱ አቅምና በሌሎች አጋርነት ለመስራት ያሰባቸውን ስራዎች ለመከወን ግን ይህ አጋጣሚ ጊዜ የማይሰጥ ፈተና ጋርጦበታል፡፡ ቀድሞ የነበረውን የአቅም ማነስ ለማዳከምም አስተዋጽኦው ቀላል አይደለም። በወቅቱ ከሚመለከተው አካል ዳግም ለመስራት ቃል የተገባላቸው ቢሆንም እስካሁን የተጀመረ ውጥን ባለመኖሩ ሀሳብ ላይ ወድቀዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የብዙዎችን ህይወት የሚፈትነው የኑሮ ውድነት የእነሱንም በር እያንኳኳ ነው፡፡ ለገቢና ትርፍ ሳይሆን የማህበሩን ህልውና ለማቆየት የሚታገሉት አባላት ዛሬም በሌላቸው በቂ አቅም በጥረታቸው መጓዙን ቀጥለዋል፡፡

ሁሉም አባላት በከፍተኛ ድካምና ጥንቃቄ በዓይነሰውራን እጆች የሚሰሩ ምርቶች ገበያ አግኝተው ገቢ ይኖራቸው ዘንድ ይሻሉ፡፡ ባለሀብቶችን ጨምሮ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ባሉበት ደርሰው ቢጎበኝዋቸው የከበዱ ሸክሞቻቸውን ለማቅለል ይቻላቸዋል፡፡ አቶ ሀብታሙም ይህን መልዕክት ለሚመለከታቸው ሁሉ ‹‹ይድረስልን ››ይላሉ፡፡

አቶ ካሳዬ ደገፋው በማህበሩ የሂሳብ ሹም በመሆን ያገለግላሉ፡፡ ይህ ድርጅት ዓላማ ቀርጾ ሲቋቋም በርካታ ዕቅዶችን ሰንቆ እንደሆነ ያስታውሳሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ አባላቱ በገቢ ማነስ፣ በማህበሩ ይዞታ መፍረስና በገበያው ውድነት ምክንያት ፈተና ላይ ወድቀዋል፡፡

ችግሮቹ እንዳሉ ሆኖ ጊዜያዊ መፍትሄ ለመሻት ሁሉም የአቅሙን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ባለው ቦታ ላይ የጓሮ አትክልት በመትከል፣ ገቢ ለማግኘት የሚደረገው ሙከራ እንዳለ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ምርቶችንም ለሽያጭ የማቅረብ ዝግጁነቱ አልተቋረጠም፡፡

አቶ ካሳዬ እንደሚሉት የችግሮቹን ቀዳዳዎች ደፍኖ ለማለፍ የሚደረገው ጥረት በሁሉም የማህበሩ አባላት ዘንድ በጽኑ ፍላጎት መከወኑን ቀጥሏል፡፡ ይህ የአንድ ወገን ጥረት ግን ብቻውን ለውጥ አያመጣም። አሁን ላይ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ህብረተሰቡ ‹‹የት ናችሁ? ምን ጎደላችሁ? ቢላቸው ፍላጎታቸው ነው፡፡

አቶ ካሳዬ ማህበሩ ይህን ጥሪ ሲያቀርብ ትኩረት እንጂ እርዳታን እየጠየቀ አለመሆኑን አጽንኦት ይሰጡታል። እንደሳቸው ዕምነት ሌሎች ወገኖች ቀረብ ብለው ምርቶቻቸውን ቢገዙ፣ ‹‹አይዟችሁ፣ አለን›› ቢሏቸው ስለነገው ሞራላቸው ይገነባል፡፡ በርካታ የሥራ ዕድል ያላገኙ፣ በጎዳናና በቤታቸው የዋሉ ሌሎች አካል ጉዳተኞች ጭምር ይጠቀማሉ፡፡

የአራት ልጆች አባት የሆኑት አባወራ ማህበሩን በሙያቸው ከመደገፍ ባሻገር ለዕለት ጉርሳቸው በየበአላቱ ጧፍ በመነገድ፣ በጓሯቸው ዶሮ አርብተው ዕንቁላሉን በመሸጥ ይተዳደራሉ፡፡ የማህበራቸው ህልውና ግን ዘወትር ከሀሳባቸው ርቆ አያውቅም። እንደ ትናንቱ ጅማሬ ነገን አብቦና ፈክቶ ለፍሬ መድረሱን ይመኛሉ፡፡

ብሩክ፣ ሀብታሙና ጓደኞቻቸው የስጋጃ አምራች ማህበር እንደተቋም ተመስርቶ ስራውን ሲጀምር ታላቅ ራዕይ አንግቦ ነው፡፡ በርካታ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሌሎች ወገኖችን በማቀፍ ውጤት ያለው ተግባር ማከናወንም ቀዳሚ የሚባል ዕቅዱ ነበር፡፡

ይህ ማህበር ዛሬ ላይ ባሉበት ተደራራቢ ችግሮችና መሰል ምክንያቶች ህልውናው አደጋ ላይ ይገኛል፡፡ ይህን ስጋት ለመቅረፍና መፍትሄ ለመሻትም ለአባላቱ ጥረት ጊዜ መስጠት የግድ ይላል፡፡ ዛሬ ትናንትን በጽናት ያለፉ፣ ነገን በብርታት የሚያሻግሩ ጥበበኛ እጆች ትኩረትን ይሻሉ፡፡

የገበያ ትስስሩን በማቀላጠፍ፣ ምርቶች ለሽያጭ እንዲቀርቡ፣ ገቢው እንዲዳብርና የላብ ፣ የልፋት ዋጋ ከግምት እንዲገባ የሁሉም አካላት ትብብርና የትኩረት ዓይኖች ሊገለጡ ይገባል፡፡ እንዲህ ከሆነ የጥበብ እጆች አይነጥፉም፤ የሚሮጡ እግሮች አይዝሉም፡፡

ፎቶመልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You