ብሪታኒያና የአውሮፓ ህብረት በመካ ከላቸው ለአራት አስርት ዓመታት የዘለቀውን የአንድነት ትስስር ገመድ ለመበጠስ ከሶስት ዓመት በፊት ታሪካዊ ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወሳል።«ከአብሮነት ይልቅ ፍቺ ይሻለኛል» የሚል ጥያቄ ያቀረበችው ብሪታኒያም፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ አማካኝነት የፈለገችውን ለማስፈፀም ላለፉት ዓመታት የተለያዩ ተግባራትን ስታከናውን ቆይታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ የሁለቱ ወገኖች መለያየት ይፋ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ «ከሌሎች በበለጠ እንጠቀምበታለን፤ እናተርፍበታለን» በሚል የሰጡትን የ2016ቱን ድምጸ ውሳኔ ለማስከበርና አገራቸውን ከአውሮፓ ህብረት ለማፋታት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም።
ይሁንና የፍቺው ድርድር ከተጀመረ አንስቶ አገሪቱና ህብረቱ የየቅል ፍላጎታቸውን በማራመ ዳቸውና አንዳንዶቹ ልዩነቶቻቸው ደግሞ ግትር አቋም የሚንፀባረቅባቸው ሆነው መገኘታቸው የታሰበውን ለመፈፀም ብዙ ድካም ጠይቋል።
ይህ ሲሆን በአገሪቱ ታሪክ ሁለተኛዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ሜይ፤የህዝብ ውሳኔ ነው ያሉትን ለማስፈፀምና ብሪታኒያን ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት ያስኬዳሉ የሚባሉ የድርድር ሃሳቦችን ሁሉ በማቅረብ ብዙ ቢደክሙም የተከተሉት መርህ አብዛኞችን መስማማት አልሆነለትም።
በተለይ ይፋዊ የፍቺ ቀጠሮው የሚታወቅበት ቀን እየተቃረበ በመጣበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሯ ለድርድሩ ስኬታማነት ያግ ዛሉ ያሏቸውን የተለያዩ አማራጮች ቢያቀርቡም፤ ውጥናቸው ግን የብራሰልስን ብቻ ሳይሆን የአገራቸውን ህዝብ እንደራሴዎች ሳይቀር ማሳመን አልተቻለውም።ይባስ ብሎ ስልጣና ቸውን እንዲለቁ ጥያቄ እንዲያቀርቡ አድርጓቸዋል።
አተርፍ ባይ አጉዳይ ሆነው ለአገሬው ይበጃል ያሉትን ተፈፃሚ ለማድረግ ብዙ ቢደክሙም ብሪታኒያ ከህብረቱ ጋር በምትለያይበት ጉዳይ ላይ ከፓርላማ አባላት ጋር ከስምምነት መድረስ ያልሆነላቸው ሜይ፤ሁሉን ሞክረው ቢያቅታቸው ከቀናት በፊት ስሜታዊ በሆነ መልኩ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታቸውን እንደሚለቁ አሳውቀዋል።።«ለሀገር ጥቅም ሲባል ቦታውን ለሌሎች መልቀቅ ይኖርብኛል» ሲሉም ተደምጠዋል።
ሜይ ስልጣን እንደሚለቁ ማስታወቃቸውን ተከትሎም አገሪቱ ከህብረቱ ጋር ትቀጥል ወይንስ አትቀጥል የሚለው ቅጡ ባለየበት በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሯን ለመተካት በርካታ ሰዎች ለቦታው ታጭተዋል።የወግ አጥባቂ ፓርቲው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበሩን የሚረከብ እንደመሆኑ የተለያዩ ግለሰቦች የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ለመያዝ እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል።
ከእነዚህ እጩዎች መካከል ደግሞ የቀድሞ የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ዋነኛው ሆነዋል።የ54 ዓመቱ ጆንሰን፤ቀደም ሲል የለንደን ከንቲባ ሆነው የሰሩ ሲሆን፤ባሳልፈነው ዓመት አገራቸው የአውሮፓ ህብረትን ለቃ በምትወጣበት ሂደት ላይ ባላቸው ልዩነት ሳቢያ ስልጣን እስከለቀቁበት ጊዜ ድረስም ብሪታኒያን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለሁለት ዓመት አገልግለዋል።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቁ ጆንሰን ቀደም ሲል በከፍተኛ ሃላፊነት ቦታ ላይ እንደ መስራታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሯን ለመተካት ቀዳሚው ተመራጭና የተሻለ እድል እንዳላቸውም ተመላክቷል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቴሬዛ ሜይን ለመተካት ቦሪስ ጆንሰን ሁነኛ አማራጭ ናቸው ማለታቸው ይታወሳል።
በብሪታኒያና በህብረቱ ፍቺ ሂደት ላይ አፋጣኝ እርምጃዎች መውሰድ የግድ መሆኑን የሚያምኑት ጆንሰን፤ፍቺውን ለዳግም ህዝበ ውሳኔ ማቅረብ አደጋው እጅግ የከፋ ነው፤እናም ብሪታኒያ በስምምነትም ሆነ ያለስምምነት ከህብረቱ መፋታት አለባት የሚል አቋም እንዳላቸው ታውቋል።
ጆንሰን ምንም እንኳን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ወንበር ላይ ለመቀመጥ የተሻለ እድል እንዳላቸው ቢታመንም፤ ከቀናት በፊት ከብሪታኒያ የአውሮፓ ህብረት ፍቺ ጋር ተያይዞ የተደረገውን የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘመቻ የመራው ማርኩስ ቦል የተሰኘ ግለሰብ ክስ አቅርቦባቸዋል።ፍርድ ቤት እንዲቀርቡም መታዘዛቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
ከአውሮፓ ህብረት አባልነት ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ የብሪታኒያን ህዝብ ዋሽተዋል፤ ብሪታኒያ በአውሮፓ ህብረት አባልነቷ በየሳምንቱ 442 ሚሊየን ዶላር እንደምታጣ በመግለፅም የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲፈጠር አድርገዋል በሚል የቀረበባቸው ክስም፤ ምናልባት በተመራጭነታቸው ላይ አሉታዊ ገፅታን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ተገምቷል።
የወቅቱ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀረሚ ሃንትም ጠቅላይ ሚኒስትር ሜይን ይተካሉ ተብለው ከታጩት መካከል ሌላኛው ተጠቃሽ ናቸው።የ52 ዓመቱ ሃንት፤ቀደም ሲል ለስድስት ዓመታት በጤና ሚኒስትርነት ከሰሩ በኋላ ባሳለፍነው ዓመት የቦሪስ ጆንሰንን ከሃላፊነት መነሳት ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅና የንግዱ ሰው መሆናቸው የሚነገርላቸው ሃንት፤ከቢቢሲ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ በፍቺው ሂደት ብሪታኒያ በስምምነት መውጣት እንዳለባት ከዚህ ውጪም ሌላ አማራጭ አለመኖሩን ይህ ካልሆነ አደጋው ከባድ እንደሚሆን ተናግረዋል።አገሪቱ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ፍቺውን እንደምትፈፅም ተስፋቸው እንዳላቸው ጠቁመው፤ ከህብረቱ ጋር ተቀራርቦ መወያየት ግን ሊዘናጋ እንደማይገባው አመላክተዋል።
ሌላኛው የጠቅላይ ሚኒስትሩነቱ ወንበር ላይ ለመቀመጥ የወሰኑት ግለሰብ ዶሜኒክ ራብ ናቸው። የ44ዓመቱ ራብ ቀደም ሲል ብሪግዚት ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤የጠቅላይ ሚኒስትር ሜይ እኤአ በ2017 በተካሄደው ምርጫ ቃል በገባው መሰረት ፍቺውን እያስኬዱት አይደለም የሚል ከአምስት ወራት የሃላፊነት ቆይታ በኋላ ባሳልፍነው ዓመት ስራቸውን መልቀቃቻው ይታወሳል።
የኦክስፎርድ ተመራቂው ራብ፤ከህብረቱ ጋር ያለስምምነት መለያየት ምርጫቸው መሆኑና ጊዜው የለውጥ ነው የሚል አቋም እንዳለቸውም የተጠቆመ ሲሆን፤ ግለሰቡ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታም ሃላፊነቱን ከተረከቡ የአገሪቱንና የህብረቱን የፍቺ ሂደት ሁለቱንም ወገን ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ የማስኬድ ፍላጎት እንዳላቸው አሳውቀዋል።
የቀድሞ የስራና የጡረታ ሚኒስትር ኢስቴር ማክቬይ በአገሪቱ ታሪክ ሶስተኛዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን እድል አላቸው ከተባሉት እጩዎች አንዷ ናቸው።ለንደን ከሚገኘው ኪዊን ሜሪ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁትና የቀድሞው የቴሌቪዥን ፕሮግራም መሪ፤ብሪታኒያን ከህብረቱ በማፋታት ሂደት የጠቅላይ ሚኒስትር ቴሪሳ ሜይ እቅድ አልጣመኝም በሚል ከካቢኔና ከስራ መልቀቃቸው ይታወሳል።
ብሪታኒያ ያለምንም ስምምነት ህብረቱን መልቀቅ አለባት የሚል አቋም እንዳላቸው የሚታመኑት የ51 አመቱ ማክቬይ፣ ሰንዴይ ቴሌግራፍ ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ አገሪቱ አዲስና አስተማማኝ አካሄድ መከተል ያስፈልጋታል፤እናም ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ከህብረቱ መፋታት አለባት የሚል አቋም እንዳላቸውም ታውቋል።
ሌላኛው በጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ወንበር ላይ ለመቀመጥ ተስፋ ያላቸው የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሮሪ ስቴዋርት ናቸው።እኤአ 2010 በፓርላማ የተመረጡት የ46ቱ ዓመቱ ሰው ቀደም ሲል አካባቢ ጠበቃ ሚኒስቴርነትን ጨምሮ በተለያዩ ሃላፊነቶች አገራቸው አገልግለዋል።
ካለምንም ስምምነት ህብረቱን መልቀቅ አይገባም የሚል አቋም እንዳላቸው የሚታመነው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂው ስቴዋርት፤በፍቺው ጉዳይ ለስካይ ኒውስ በሰጡት አስተያየትም፤ለዘብተኛ አቋም እንደሚከተሉ አሳውቀዋል።
የአየር ንብረት ሚኒስትር ማሼል ጎቭ ሌላኛው እጩ ናቸው። የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቁ ጎቭ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቴሪሳ ሜይ፣ካቢኔ አባላት ስኬታማነታቸው ጉልህ መሆኑ ይነገርላቸዋል። በጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ሃላፊነት ለመወዳዳር በተለይ ወግ አጥባቂ ፓርቲውንና የዩኒየን ፓርቲዎችን አንድነት ለማጠናከርና ታላቋን አገር ለመምራት ዝግጁ ነኝ ያሉት ጎቭ፤በፍቺው ሂደትም በጋራ መግባባት ጠቅላይ ሚኒስትር ተሬሳ ሜይ ይከተሉት ከነበሩት የተሻለ አማራጭ እንደሚያራምድ ገልጸዋል።
ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ሃላፊነት የሚጠበቁት ሌላኛው እጩ ማት ሃንኮክ ናቸው። ከእጩዎቹ ዝቅትኛ እድሜ የያዙት የ40 ዓመቱ ሃንኮክ፤ቀደም ሲል የባህልና እንዲሁም የጤና ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን በጋራ ትብብር ላይ መሰረቱን ያደረገ ግንኙነትን መመስረት የሚፈልጉና አገራቸው ከህብረቱ ጋር የሚኖራት ፍቺ ያለምንም ድርድር መቋጨት የለበትም የሚል አቋም እንዳላቸው ተመላክቷል።
አንድሪያ ሊድሰም ሌላኛው የሴት እጩ ናቸው።። እኤአ በ2016 ዴቪድ ካሜሮንን በመገዳደር ዋነኛው የነበሩት የ56ዓመቷ ሊድሰም፤ከወራት በፊትም የአገራቸው መንግስት በፍቺው ሂደት እየተከተለ ባለው አካሄድ እምነት ስለሌላቸው ከመንግስት ሃላፊነታቸው መልቀቃቸው ይታወሳል።
በባንክና በኢንሹራንስ ሙያ የ25 ዓመታትን ልምድ ያላቸውና የዋርዊክ ዩኒቨርሲቲ ምሩቋ ሊድሰ ብሪያኒያ በተቀመጠው የፍቺ ጊዜ ሰሌዳ በስምምነትም ሆነ ካለስምምነት መፋፋት አለባት በማለት ለሰንዴይ ታይምስ ተናግረዋል።
ከእነዚህ እጩዎች በተጓዳኝም፤የቤቶች ሚኒስትሩ ሳጂድ ጃቪድ፤ ጄምስ ክሌቭርሊ፤ አንድሪያ ሌድሰም፤ ኬት ሜልት ሃውስ፤ የተሰኙ ገለሰቦችም ክእጩዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ለማውቅ የተቻለ ሲሆን፤አንዳንዶች ግን ሜይን በመተካት ማንም ይመረጥ ማን ተተኪዎቹ የፍቺውን ሂደት ዳር ለማድረስ የሚጠብቃቸው ፈተና ቀላል እንደማይሆን ከወዲሁ አፅእኖት ሰጥተውታል።
በዚህ ረገድ በኪውን ዩኒቨርሲቲ የአውሮፓ ፖለቲካል ጉዳዮች ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዴቪድ ፊንሞር ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቆይታም፤ እጩዎቹ ድርድሩን እንዴት ማስኬድ እንዳለባቸው በግልፅ የተቀመጠና ተጨባጭ እቅድ እስከሌላቸው መጪው ጊዜም ተመሳሳይ ውጤት ይዞ ይመጣል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2011
ታምራት ተስፋዬ