በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካን፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ እና ኢትዮጵያ ኤምባሲ ባልከፈተችባቸው ጭምር በተለያየ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከፍተኛ ነው። በጥናት የተደገፈ መረጃ ማቅረብ ባይቻልም፤ በቁጥር ደረጃ እጅግ ከፍተኛ የሚባል እንደሆነ ይነገራል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ከሀገራቸው ወጥተው በስደት በሌላ ሀገር ለመኖር ሲመርጡ የተለያዩ ምክንያቶች አሏቸው፡፡ አንዳንዱ ሀገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ አልመች ብሏቸው፣ ሌሎች ደግሞ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ፣ የተቀሩት ደግሞ ተምሮ እራስን ለማሻሻል በሚል አላማ ከሀገር ይወጣሉ፡፡
ኢትዮጵያውያኑ የሄዱበትን ዓላማ ለማሳካት ሌትከቀን በሥራ፣ በትምህርት፣ ኑሮን ለማሸነፍ ይደክማሉ፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ለስኬት ለመብቃት ሌተቀን ሲደክሙ ግን ሀገራቸውን በልባቸው ይዘው ነው፡፡
በሀገራዊ ወቅታዊ የፖለቲካ አለመመቸት ምክንያት አኩርፈው ከሀገራቸው የወጡ ቢሆኑም ለመኖር ብለውም በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት የውጭ ሀገር ለመሆን ቢገደዱ እንኳን አካላቸው እንጂ በሀሳብ ውሎና አዳራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ይህንንም እውነታ ባገኙት አጋጣሚ በተለያየ መንገድ ሀሳባቸውን ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ ስኬታቸውም ለግላቸው ብቻ እንዳልሆነ በተለያየ መንገድ በሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ይገለጻል፡፡
በተለያየ ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ያላቸው ድጋፍ ቤተሰብን ከመርዳት ይጀምራል፡፡ ለቤተሰባቸው የሚልኩት የውጭ ምንዛሪ ደግሞ በተዘዋዋሪ በሀገር ምጣኔ እድገት ላይ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ከዚህ አልፎ ደግሞ በሚኖሩበት ሀገር ያገኙትን ትምህርት፣ የሥራ ክህሎት፣ ቴክኖሎጂ በትውልድ ሀገራቸው ውስጥ በመተግበር፣ ልምድና ተሞክሮአቸውንም በማካፈል የማይናቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡
ከፍ ሲልም በተለያየ ኢንቨስትመንት በመሰማራት መዋዕለነዋያቸውን በሀገራቸው ያፈሳሉ፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ከሀገራቸው ርቀው ቢገኙም በዚህ መልኩ ሀገራቸውን እያገዙ ይገኛሉ፡፡
በተወሰነ ጊዜም ሀገራቸው በመምጣት የሀገራቸውን ወቅታዊ ሁኔታ በማየት የሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ ሚናቸውን የሚወጡ እንዳሉም ይታወቃል፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ከሀገራቸው ከወጡ ጀምሮም ያልመጡም ይኖራሉ፡፡
በተለያየ ምክንያት ወደ ሀገር ያልመጡና በውጭ ተወልደው ስለሀገራቸው የማያውቁትን መንግሥት ጥሪ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም ውጭ ሀገራት ተወልደው ኢትዮጵያን በአካል የማያውቋት የሁለተኛው ትውልድ አባላት ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መንግሥት በማበረታታት ላይ ነው፡፡
እኛም የዳያስፖራው ማህበረሰብ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ እያደረገ ስላለው ተሳትፎ እንዲሁም በዲፕሎማሲው ስላለው አበርክቶ ከዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እድሪስ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም የንባብ ጊዜ፡፡
አዲስ ዘመን፦ በቅድሚያ ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያለው ሀገራዊ ተሳትፎ ምን ይመስላል ከሚለው ብንጀምርስ ?
ዶክተር መሐመድ፤ የዳያስፖራውን ሀገራዊ ተሳትፎ በሶስት መንገድ ወይንም ማዕቀፍ መግለጽ ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ከዳያስፖራው ስብጥር ወይንም አይነት የሚመነጭ ተሳትፎ ነው፡፡ አንዱ የኢኮኖሚ ዳያስፖራ ብለን የምንወስደው ነው። ዳያስፖራዎች በሚኖሩበት ሀገር ያፈሩትን ሀብት ወይንም ጥሪት ሀገራቸው ውስጥ በማዋል ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸው እንዲጠቅም እንዲሁም ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር በአጠቃላይ ለሀገር እድገት እንዲውል የማድረግ ፍላጎት ያላቸው ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ያሉት ደግሞ የእውቀት ዳያስፖራ ናቸው፡፡ እነዚህ ዳያስፖራዎች ትምህርታቸውን በሀገር ቤት ተከታትለው ከጊዜ በኋላ ወደ ውጭ ሀገር የሄዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ወይንም ደግሞ በስደት በሚኖሩበት ሀገር ውስጥ ተምረው እውቃታቸውን አሻሽለው የተሻለ ክህሎት ያላቸው ናቸው፡፡ በዚህኛው ዘርፍ እውቀትና ክህሎት ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሰራው ሥራ ይጠቀሳል፡፡
ስብጥሩ በነዚህና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ በፖለቲካው ዘርፍ፣ በሁለተኛ ትውልድ፣ በሚሉ የሚገለጽ ሲሆን፤ የነዚህ ሁሉ ስብጥር የሚስተዋልበት የዳያስፖራ ተሳትፎ ነው በሀገር ውስጥ ያለው። ለአብነትም ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ዘርፍ በአነስተኛ፣ በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ የሚገለጽ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ በተለያየ የኢንቨስትመት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያለው ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
በአነስተኛ ኢንቨስትመት ላይ የተሰማሩትን ትተን ዋና ዋና ወይንም ከፍተኛ በሚባለው፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ ከአምስት መቶ በላይ የዳያስፖራ ባለሀብቶች በተለያየ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ በመሰማርት ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ አነዚህ ባለሀብቶች ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረው፣ ምርትም አምርተው ወደ ገበያ በመግባት ውጤታማ በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ በ2015ዓ.ም ብቻ ከ264 በላይ የሚሆኑ ዳያስፖራ ባለሀብቶች በሀገራቸው ኢንቨስት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡
በእውቀትና በቴክኖሎጂ ሽግግርም በተመሳሳይ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ ከሰባት መቶ በላይ የሚሆኑ የዳያስፖራ የእውቀት፣ የክህሎትና የቴክሎጂ ሽግግር ፕሮግራሞች ተከናውነዋል፡፡ ፕሮግራሞቹ የጤና፣ የስልጠና፣ የትምህርት፣ ኮምፒውተር ሳይንስ፣ ውሃና መሰል ፕሮግራሞች ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ፤ አንዱ ፕሮግራም ብቻም እስከ አንድ መቶ ዳያስፖራዎችን ሊያሳትፍ ይችላል፡፡ ተሳትፎው እንደየይዘቱ አነስተኛ ቁጥር ወይንም በዛ ያለ ተሳታፊ ሊኖረው ይችላል። በዚህ መልኩ ነው የዳያስፖራውን ስብጥር ታሳቢ ያደረገ ሥራዎች በመከናወን ላይ የሚገኙት፡፡
ሌላው ከስብጠሩ ማእቀፍ የሚመነጨውና የትኩረት አቅጣጫ የሆነው፤ ሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ላይ የሚሰራው ሥራ ነው፡፡ ሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራዎች ሀገራቸውን እንዲያውቁ ለማስቻል የሚደረግ ጥረት ሲሆን፤ በዚህ ረገድ ደግሞ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር በማድረግ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት ያስችላል፡፡ እንዲሁም የሀገር ገጽታን ለመገንባት የሚሰራ ሥራ ነው፡፡ በተለያየ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራዎች በቤተሰብ፣ ጓደኛሞች በቡድን ሆነው ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ ነው የሚበረታቱት፡፡
ዳያስፖራውን የተመለከቱ ጉዳዮች በአምስት ዓመትና በአስር ዓመት መሪ እቅዶች የሚመራ ነው። እነዚህን እቅዶች መሠረት በማድረግ ዳያስፖራውን በቋሚነት የምናሳትፍበት ዘርፎች አሉ፡፡ ሆኖም ግን ሀገር ከዳያስፖራው ምን ትፈልጋለች? ዳያስፖራውስ ከሀገር ምን ይፈልጋል ? የሚሉ ሃሳቦች ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል፡፡
በተለይም ሀገር ከዳያስፖራው ምን ይፈልጋል ለሚለው፤ በዚያኛው ወገን ወይንም በዳያስፖራው በኩል ያለውን አቅርቦት ታሳቢ ያላደረገ፣ ሀገር ቤት ውስጥ ያለውን ፍላጎት ብቻ መሠረት ያደረገ እቅድ አቅዶ መነሳት ፈተና ውስጥ ይከተናል፡፡ ስለዚህ ዳያስፖራው ምን ይፈልጋል ስንል፣ ዳያስፖራው ምን አይነት አቅም አለው፣ ከአገልግሎት አንጻርስ ምን ይፈልጋል፣ የሚለው መለየት ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ዳያስፖራው ከሚፈልገው ማዕቀፍ በመነሳት ሥራዎች ሊሰሩ ይገባል፡፡
ዳያስፖራው፣ የቤት ልማት ፕሮጀክት ሊፈልግ ይችላል፡፡ የቤት ልማት ፕሮጀክት መሠረተ ሀሳቡ ለዳያስፖራው ቤት መስጠት አይደለም፡፡ ዳያስፖራው የውጭ ምንዛሪውን በሀገር ቤት በማስቀመጥ ሀገር ውስጥ ላሉ የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋራጮች ሥራ መፍጠር ነው፡፡ እንዲህ ያለው እንቅስቃሴ ለሀገር የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል፡፡ በዚህ መልኩ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝም የሚመጡ ዳያስፖራዎችን ፍላጎት በመጨመርና እድሉን በማስፋት ተጠቃሚ መሆን ይቻላል።
ዳያስፖራው በውጭ ያካበተውን ልምድ፣ ያገኘውን ሙያና ትምህርት መሠረት በማድረግ በሙያው ሀገሩን ማገልገል ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ በትምህርት፣በጤና፣በአጠቃላይ በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የእውቀት ክህሎት ሽግግር ምን አይነት ምቹ ሁኔታ ያስፈልጋል በሚለው ላይ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡
ሌላው ወቅታዊ ሁኔታ የሚያመጣው ወይንም የሚፈጥረው የዳያስፖራው ተሳትፎ ነው፡፡ ወቅታዊ ሁኔታዎቹ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ለአብነትም እንደ ታላቁ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ፣ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለትውልድ ያሉ በመንግሥት እየተከናወኑ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ። ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የዳያስፖራው ተሳትፎ ከ70 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይሆናል፡፡ ገበታ ለሀገር የመጀመሪያው ፕሮጀክት ላይም ወደ 29 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ተሳትፎ ተደርጓል። ለገበታ ለትውልድ ደግሞ ወደ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ነው ተሳትፎው፡፡ በተለይ ደግሞ አስቸጋሪ ናቸው በሚባሉ ወቅቶች ለምሳሌ፤ ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ተከስቶ በነበረበት ወቅት፣ በጦርነት ፣ በተለያየ ምክንያት ሰዎች ከቄያቸው ተፈናቅለው ለችግር ሲዳረጉ፣ ዳያስፖራው በተቻለው አቅም በመረባረብ በገንዘብና በተለያየ መንገድ ይሳተፋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ባስፈለገበት ወቅትም እንዲሁ ድጋፍ ከማድረግ አልተቆጠበም፡፡ በ2015ዓም ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ወደ ስድስት ሚሊዮን ዶላር በማሰባሰብ ለተቸገሩ ኢትዮጵያውያን እንዲውል ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም በአይነት ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ሊያወጡ የሚችሉ ድጋፎች ተደርገዋል። በገንዘብም በአይነትም የተደረገው ድጋፍ ከፍተኛ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከዳያስፖራው ስብጥር የሚመነጩ ተሳትፎዎችን ስንመለከት የዳያስፖራው ማበህረሰብ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካ ያደረገው ተሳታትፎዎችን በመጠን ለመለካት የራሱ የሆነ ሥራ የሚያስፈልገው ቢሆንም፤ ድርሻው ከፍተኛ ወይንም ሰፊ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡
አዲስዘመን፦ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያላቸው አበርክቶ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር መሐመድ፦ የውጭ ግንኙነት ሥራ ተቀዳሚ ዓላማ ተደርጎ የሚቀመጠው፤ የአንድን ሀገር ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ነው፡፡ ብሄራዊ ጥቅም ደግሞ አንድ ትልቅ አጀንዳ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በመሆኑም ብሄራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ በአንድ ተቋም ሥራ ብቻ ይሳካል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ምንም እንኳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ ሀገራት ኢትዮጵያን የመወከል ሥራ ቢሰጠውም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ የበርካታ ተቋማትና የሁሉም ዜጎች ርብርብ ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አንጻር የዳያስፖራው ማህበረሰብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደ አንድ ባለድርሻ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ድርሻ አለው፡፡
ወደ ዝርዝር ጉዳይ ስንመጣ ግን ፤እራሱ የውጭ ጉዳይ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሥራ እንዲያሳካቸው የሚፈልጋቸውን ሥራዎች ብንመለከት አንደኛው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሥራ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሥራ በአንድ በኩል በውጭ ሀገር ያለን ሀብት ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት የሀገር ውስጥ መዋዕለ ነዋይ ፍሰትን መጨመር፣ የሥራ እድልን ማሳደግ እንዲሁም የእውቀትና የክህሎት ሽግግርና መጨመር ነው፡፡ በዚህ በኩል የዳያስፖራው ማህበረሰብ ቀጥተኛ የሆነ ድርሻ አለው፡፡
አንድም ዳያስፖራው እራሱ በውጭ ሀገር ካፈራው ሀብት፤ ሁለትም በውጭ ሀገራት ካለው የተለያየ አማራጭ የፋይናንስ እድል ሲሆን፣ ዳያስፖራው ከሚኖርበት ሀገር የገንዘብ ብድር የማግኘት እድልም አለው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ በተለያዩ የውጭ ሀገር ከሚገኙ ባለሀብቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር፣ የሚያደርገው ጥረት በሀብት ፍሰት ላይ የሚኖረው ሚና ይጠቀሳል። ስለዚህ ዲፕሎማሲን ለማሳካት ከሚያስችሉ ነገሮች አንዱና ቁልፍ ተዋናይ ተደርጎ የሚወሰደው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ነው፡፡
የዚህ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሌላው መገለጫ፤ በንግድ ዘርፍ ያለው ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ምርቶች ገበያ መፍጠር ነው፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት መጥተው የሚፈጥሩት ቢዝነስ ወይንም ንግድ ብቻ ሳይሆን፤ በውጭ ሀገራትም በርካታ የንግድ ተቋማትና እንቅስቃሴዎች አሏቸው፡፡ የኢትዮጵያን ንግድ ወዳሉበት ሀገር በመውሰድ እሴት ጨምረው መሥራት ይችላሉ፡፡
ስለዚህ ዳያስፖራዎች አዳዲስ ምርቶችን ያስተዋውቃሉ፡፡ የምርት መዳረሻም ሆነው ያገለግላሉ፡፡ የኢትዮጵያን ምርትም ገዥ ናቸው። የተለያዩ የኢትዮጵያ ምርቶች የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) በሰንጠረዥ ብናስቀምጣቸው፤ በተለይም ዋና ዋና የሚባሉት ላይ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ፤ልምሳሌ በቡና የወጪ ንግድ ላይ ወደ አምስት መቶ የሚሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል። ትልልቅ የሚባሉ የኢትዮጵያ የወጪ ምርቶችም በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ስኬት ላይ ቁልፍ ሚና አላቸው ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲያሳካ የሚጠበቅበት፤ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ነው፡፡ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ በዋነኛነት ኢትዮጵያና ሌሎች አቻ ሀገራት የሚኖራቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ በሌሎች ባለብዙ ወገን ግንኙነቶች ላይ ተደማጭነቷ እንዲጨምር ማድረግ ነው፡፡
በዚህ በኩልም ዳያስፖራው እራሱን የቻለ፣ በቁመቱ ልክ የተመጠነ ሚና አለው፡፡ ቀደም ሲል እንዳነሳሁት የዲፕሎማሲ ሥራ በአንድ አካል ወይንም ተቋም ላይ ብቻ የሚወድቅ፣ የሚገኘው ስኬትም ሆነ ውድቀት እንዲሁ የአንድ አካል ብቻ መሆን እንደሌለበት ሁሉ ዳያስፖራውም በፖለቲካ ዲፕሎማሲውም በራሱ ልክ የተለካ ሚና አለው ማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ከማስከበር አንጻር ዳያስፖራው እያደረገው ያለውን አስተዋጽኦ ቢያብራሩልን ?
ዶክተር መሓመድ -በሁሉም የዓለም ሀገራት ባንል እንኳን በጣም ብዙ በሚባሉ ሀገራት ውስጥ ዜጎቻችን ይኖራሉ፡፡ ይህ ማለት የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ተደራሽ ባልሆኑባቸው ሀገራት ጭምር ማለት ነው። ስለዚህ ዜጎቻችን አምባሳደሮቻችን ናቸው ማለት ነው። ስለኢትዮጵያ የማሳወቅ፣ የመናገር፣ ኢትዮጵያን የመምሰል ተልእኮ ይወጣሉ። በሳይንስና ምርምር እንዲሁም በጣም ትላልቅ በሚባሉ ዓለምአቀፍ ተቋማትና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ ብዛት ያላቸው ትውልደ ኢትዮያውያን አሉ፡፡ ዜጎቻችን በሚኖሩባቸው ሀገራት ውስጥ በሚገኙ በነዚህ ትላልቅ ተቋማት ውስጥ መሥራታቸው በራሱ ውክልና አለው። በመኖራቸው ደግሞ ሌላ የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ አለ ማለት ነው፡፡
ከዚያ አለፍ ብሎ ደግሞ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ የሚፈለጉ አጀንዳዎች ሲኖሩ፤ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያው ተሰላፊ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ የትኛውም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ጉዳይ በተለያየ መንገድ ስለሆነ የሚሰራው ዳያስፖራው የራሱን ድርሻ ይይዛል ማለት ነው፡፡
አንድን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ፤ ከአንድ ሀገር ጋር መደራደር ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ዳያስፖራው በሚኖርበት አካባቢ መራጭ፣ ወይንም ተመራጭ ነው፡፡ ሰራተኛም ሊሆን ይችላል፡፡ ወይንም በጋራ በሚፈጥራቸው አደረጃጀቶች የራሱን ድምጽ ለማሰማት የሚችልበት እድል አለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ለማሳካት ዳያስፖራው በራሱ ልክ የተሰፈረ ድርሻ አለው፡፡
በሌላ በኩል የፖለቲካ ዲፕሎማሲያችንን እንዲያሳካ የሚጠበቅበት፤ የባህልና የገጽታ ግንባታ ሥራ ነው፡፡ ይሄ ከውጭ ግንኙነት ሥራችን አንዱ እንደመሆኑ መጠን፤ ዳያስፖራው በባህል፣ በገጽታ ግንባታ፣ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በኩል ትልቅ የሚባል አሻራ አለው፡፡ ሌሎች ያሉትን ተሳትፎዎች እንኳን ትተን በዚህ ዘርፍ ብቻ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ በገንዘብ ቢለካ፣ በተቋም ደረጃም ቢሆን እንስራ ብንል የማይቻል ከፍተኛ የሆነ ስኬት ነው፡፡
ዳያስፖራው የሚያንቀሳቅሳቸው የባህል ሬስቶራንቶችና መዝናኛዎች፣ ዳያስፖራው በሚኖርባቸው የውጭ ሀገራት ውስጥ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸው የሚያከብራቸው የኢትያጵያን ባህል፣ ወግና ሥርዓት የሚያንፀባርቁ በዓላት የሀገር ገጽታ ግንባታ ማሳያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ አፍ አውጥተው የሚናገሩ በተግባር የሚታዩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ናቸው፡፡
እነዚህን በጀት መድቦ ለመሥራት ቢሞከር በቢሊዮን የሚቀጠር ገንዘብ ይጠይቃል። ዳያስፖራው ገንዘብ ሳይጠይቅ የሚወጣው ተግባር ነው፡፡ መለያ ወይንም ብራንድ ማድረግ ላይ ክፍተት ሊኖር ይችል እንደሆን እንጂ በተለያየ መንገድ የሚወጡት ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ከፍተው በሚሰሩባቸው ሬስቶራንቶችና ምግብ ቤቶች ውስጥ ከኢትዮጵያውያኑ በላይ ነጮቹ ናቸው የሚጠቀሙት። በተለይም በአሜሪካን የተለያዩ ግዛቶች የሚታየው ሀቅ ይህ ነው፡፡
የአትክልት ምግብ (ቬጂቴሪያን) የሚባለው ሥጋ ተመጋቢ ላልሆነ ሰው ከሚያቀርቡት ምግብ ጀምሮ ተመራጭ የሆነ ስብጥር ያለው ምግብ በማቅረብም ይታወቃሉ፡፡ በዚህ በኩል ብራንዲንግ ላይ ብንበረታ እራሱን የቻለ ለገጽታ ግንባታ መዋል ይችላል፡፡
ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ስንሄድ ቋንቋቸውን የሚናገሩ፣ የኢትዮጵያን ባህል ደግሞ የሚያውቁ፣ በተለያየ ምክንያት የተረሱ ባህሎቻችንን፣ታሪኮቻችንን፣ በራሳቸው ቋንቋ የሚናገሩ፣ የሚያስተጋቡ፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስራችንን የሚያጠናክሩ፣ ሥራዎችን የሚሰሩ ዲያስፖራዎች በርካታ ናቸው፡፡
በውጭ ዲፕሎማሲ እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ልናሳካው የሚገባው የምንፈልጋቸውን ዘርፎች ዳያስፖራው በቁመቱ ልክ ይወስዳል፡፡ ትልቅ የሆነ ሚናም ይጫወታል፡፡ የእከሌ ሥራ ነው ወይንም የአንድ አካል ተልእኮና ተግባር ነው ተብሎ የሚነሳ ጉዳይ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፦ በቆይታችን ያላነሳናቸው ያልተገለጹ ነገሮች ካሉ ቢጨምሩ
ዶክተር መሐመድ፦ አንዳንዴ እኛ በምናስበው ልክ ዳያስፖራውን የመሳል ሁኔታ አለ። በአንዳንድ ወቅት የዳያስፖራ ተሳትፎ ገንዘብ ላይ እንዲያተኩር ሊፈለግ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ዘመቻው፣ እንቅስቃሴው፣ አጀንዳው በአብዛኛው ወደዚያ ያተኩሩና የማህረሰቡም የዳያስፖራውም ተሳትፎ እዛ ላይ ሊታሰር ይችላል። በሀገር ቤትም በውጭ ሀገር የሚኖሩ አንዳንዶች ጉዳዩን ያልተረዱ ጉዳዩን ላልተገባ የፖለቲካ ፍጆታ ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ይሄ ስህተት ነው፡፡
በሌላ ጊዜ ደግሞ የገጽታ ግንባታ ሥራ ወይ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ወይንም በፖለቲካ ዲፕሎማሲ በዲጂታል ንቅናቄዎች አካባቢ በጣም አንገብጋቢ ይሆንና፣ እዚህ ላይ ሰፊ የዘመቻ ሥራ እንሰራለን። ሙሉ ባለድርሻ አካላትን እዛ ላይ እናሳትፋለን። ዳያስፖራዎቻችን፣ ኤምባሲዎቻችን ሙሉ ትኩረታቸውን እዛ ላይ እንዲያደርጉ እንሰራለን። እዚህ ላይ በሚሰራው ሥራ ደግሞ የዳያስፖራው ተሳትፎ የድጋፍ ሰልፍ ከመውጣት ጋር ይተሳሰርና ድጋፍና ተቃውሞ ከዚህ ጋር ይተሳሰራል።
ይሄን ጉዳይ የማነሳው የዳያስፖራውን ተሳትፎ በሁለተናዊ መልክ ካላየነው፤ ከሁሉም ህብረተሰብ ወይንም የዳያስፖራ አቅም ከሁሉም ለማምጣት፤ ሀገርንም ዳያስፖራንም መጥቀም አለብን ብለን ካላሰብን፤ ስለዳያስፖራ ያለው አመለካከት ወይንም ተሳትፎ ወቅታዊ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ አንዱን ዘርፍ ብቻ እንይዝና እቅዳችን፣ ሀብታችን፣ የሰው ኃይላችን፣ የተግባቦት ሥራችንም በዛው ላይ ይታጠራል፡፡ የዳያስፖራ ዲፕሎማሲ ሲባል ጠቅለል ተደርጎ በስፋት መታየት አለበት፡፡
ለምሳሌ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ትልቅ ተነሳሽነት(ኢኒሼቲቭ) ነው፡፡ ነገር ግን ወደ አተገባበር ሲመጣ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፤ አጀንዳ ላይ በአብዛኛው ሰፍኖ የሚታየው፤ የተጎዱ ዜጎችን ከውጭ ሀገር ማስመለስ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣የዲፕሎማሲ ዓላማ በራሱ፤ ብሄራዊ ጥቅሞቻችንን በማስጠበቅ በሀገር ውስጥም በውጭም ሀገር የሚገኙ የዜጎቻችንን ጥቅም ማስጠበቅ ነው፡፡ ሁለተኛው ዜጋህን እንደዲፕሎማት ተጠቅመህ የምታሳካው ዲፕሎማሲ ነው፡፡
ሦስተኛ የዜጎችን ክብር ማስጠበቅ ነው፡፡ አራተኛ እያልክ የምትዘረዝራቸው በርካታ አመለካከቶች አሉና በነዚህ ላይ በሰፊው መሥራት ካልተቻለ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በአንዱ ዘርፍ ላይ ብቻ ሊያተኩር ይችላል። እቅድህ ተግባቦትህ ሪፖርትህ እዛ ላይ ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የዳያስፖራውም ተሳትፎ ልክ እንደዚያው ነው እና ሙሉ ቅርጹንና ይዘቱን ካሰብን ብዙ እንደ ሀገር በርካታ ጥቅሞችን ይዞልን ይመጣል።
አዲስ ዘመን፦ ለሰጡን ማብራሪያ በጣም እናመሰግናለን።
ዶክተር መሐመድ ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም