የ«ፀሐይ» ለሀገሯ መብቃት ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው!

ሀገራችን ጥንታዊ ከመሆኗ አኳያ፤ የረጅም ዘመናት የሀገረ መንግሥት ታሪክ፤ የብዙ ሃይማኖቶችና ባህሎች ባለቤት ናት። በዚህም ዘመናት ያስቆጠሩ፤ የብዙዎችን ቀልብ የሚስቡ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ቅርሶችም ባለቤት ነች። በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍያለ እውቅና አትርፋለች።

ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ ከተመዘገቡ አስራ ስድስት ዓለም አቀፍ ቅርሶች በተጨማሪ፤ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቅርሶች ባለቤት ነች። እነዚህን ቅርሶች በአግባቡ አጥንቶ፤ አውቆ እና በተደራጀ መልኩ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ለማዋል ገና ብዙ የቤት ሥራዎች እንደሚቀሩም የዘርፉ ባለሙያዎች የሚስማሙበት ነው።

በተለይም በተበታተነ መንገድ በየቦታው የሚገኙ ቅርሶችን ከተደቀኑባቸው አደጋዎች ታድጎ፤ ዘመኑን በሚዋጅ አስተማማኝ መንገድ ለትውልዶች የሚተላለፉበትን፤ ለሀገር ኢኮኖሚ የተሻለ አቅም የሚሆኑበትን መንገድ ማፈላለግ፤ የዚህ ትውልድ ትልቁ ኃላፊነት እንደሆነም ይታመናል።

ከዚህ ጎን ለጎን በተለያዩ ወቅቶች ያለአግባብ (በስርቆትና በዘረፋ) ከሀገር ወጥተው በተለያዩ ሀገራት ሙዚየሞች እና ግለሰቦች እጅ የሚገኙ የሀገር ቅርሶችን አፈላልጎ ወደ ሀገር የሚመለሱበትን ስትራቴጂክ ዲፕሎማሲ አቅሞችን አጠናክሮ መቀጠል፤ የመላው ሕዝብ በተለይም የመንግሥት ትልቁ የቤት ሥራ ነው።

ከዚህ ቀደም ባሉት ዓመታት ሰፋፊ ሥራዎችና ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በዚህም፤ ለገሐር ባቡር ጣቢያ ቆሞ የሚገኘው የሞአ አንበሳ ሐውልት፣ አጼ ቴዎድሮስ ስለንግሥት ቪክቶሪያ የጻፉላቸው ሁለት ደብዳቤዎች፣ «አፍሮ አይገባ» በመባል የሚታወቀው ከላሊበላ ቤተ-መድኃዓለም ውቅር ቤተክርስቲያን ተሰርቆ በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር የወጣ መስቀል፣ በጣሊያን ወረራ ወቅት ተወስዶ የነበረ «የአፄ ኃይለሥላሴ ዙፋን» ለሀገራቸው ማብቃት ተችሏል።

የአፄ ቴዎድሮስ ዳዊት፣ የዓለማየሁ ቴዎድሮስ ፎቶግራፍ፤ የእቴጌ ምንትዋብ ስንክሳር፣ ከ15 እስከ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተጻፉ የተገመቱና የብራና መጻሕፍትና በዚሁ ዘመን እንደተሠራ የሚገመት ሰይፍ፣ መስቀሎችን፣ ሃይማኖታዊ ስዕሎች፣ የብራና ጽሑፎች፤ በመቅደላ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ ተዘርፎ የሄደ ጽላት፣ የአፄ ቴዎድሮስ አሸንክታብ ለታሪካዊ ባለቤታቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተመልሰዋል።

የአክሱም ሐውልትን ጨምሮ የዐፄ ቴዎድሮስ የጦር መሣሪያዎች፣ በለንደን ለጨረታ ቀርቦ የነበረው የእቴጌ ምንትዋብ ድባብ ለንደን በሚገኘው በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ተገዝቶ ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ተደርጓል። በኬንያ ብሔራዊ ሙዚየም የነበሩ፣ ከዝሆን ቆዳ የተሠራና በብር ያጌጠ ጋሻ፣ ሁለት ጐራዴዎች፣ አራት ጩቤዎች፣ አንድ ሳንጃ፣ የአፄ ቴዎድሮስ፣ ፀጉር፣ የተለያዩ መስቀሎች እና የብራና መጽሐፍትም ለሀገራቸው በቅተዋል።

ይህ ሀገራዊ ጥረት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ተጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህም ብዛት ያላቸው ቅርሶች ወደ ሀገራቸው የተመለሱባቸው መልካም አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል፤ ከእነዚህም ውስጥ የአፄ ቴዎድሮስ ወንድ ልጅ የልዑል ዓለማየሁ የፀጉር ዘለላ እና ከመቅደላ ጦርነት በኋላ በእንግሊዝ ጦር ተዘርፈው የተወሰዱ የተለያዩ ቅርሶች ተጠቃሽ ናቸው።

የልዑል ዓለማየሁ የፀጉር ዘለላ፣ የካፒቴን ስፒዲ ፀጉር፣ የጄኔራል ናፒር ፎቶግራፍ፣ ሁለት በብር የተለበጡ የቀንድ ዋንጫዎች፣ አንድ የቀንድ ዋንጫ፣ ስለ ልዑሉ የተፃፉ ደብዳቤዎች፣ ስለ መቅደላ የተፃፈ መጽሔት፣ በመቅደላ ጦርነት ጊዜ አገልግሎት ላይ የዋለ የጦር ጋሻ፣ ከመቅደላ የተዘረፈ የመድኃኔዓለም ታቦት ለባለቤቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተመልሷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሰሞኑን ፤ በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ መነቃቃት ትልቅ ማሳያ ተደርጋ የምትወሰደው፤ በ1935 ዓ.ም ሄር ሉድዊግ ዌበር በተባለው ጀርመናዊ ኢንጂነር እና የንጉሡ ፓይለት በወቅቱ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የተሠራችው የመጀመሪያዋ «ፀሐይ» በመባል የምትታወቀው አውሮፕላን ከ88 አመታት በባዕድ ሀገር ቆይታ በኋላ ወደ ሀገሯ ተመልሳለች፡፡

የአውሮፕላኗ ወደ ሀገር ውስጥ መመለስ እንደሀገር ቅርሶቻችንን ከያሉበት የማሰባሰብ ጥረት ትልቅ እመርታ ላይ እንዳለ አመላካችና ከፍያለ የዲፕሎማሲ ስኬት ማሳያ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር፣ ለታሪክና ለታሪካዊ ቅርሶች ያላቸውን ከበሬታ በተጨባጭ ያሳየ ጭምር ነው!

አዲስ ዘመን ጥር 24/2016

Recommended For You