የወጣቶች አዕምሮ ጤና እና የዲጂታል ሚዲያ ተጽዕኖ

የአዕምሮ ጤና ሲቃወስ፤ የግለሰብን የየዕለት ተግባር በማዛባት፣ ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት እና የሰውነት ሁኔታ ላይም የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ዕድሜ፣ ጾታን፣ የገቢ ሁኔታን ወይም ዘር ሳይለይ ሁሉም ሰው ለአእምሮ ጤና መታወክ በሽታ የሚጋለጥበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

ማኅበራዊና የገቢ ሁኔታ፣ ጥሩ ያልሆኑ የልጅነት ልምዶች፣ አፈጣጠርና መሰረታዊ የጤና ሁኔታዎች የአንድን ሰው የአእምሮ ጤንነት ሊወስኑ እንደሚችሉም ነው የሚነገረው። አብዛኛው የአእምሮ ጤና መታወክ ያለባቸው ሰዎች በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ የጤና ችግር እንደሚኖርባቸውም መረጃዎች ይጠቁማሉ። እንደመረጃዎቹ የአእምሮ ሕመም ዓይነቶች ጭንቀት፣ የስሜት መለዋወጥ (መቃወስ) እና ስኪዞፍሬኒያ (ከእውነታው ዓለም መዛባት) ናቸው፡፡ ጭንቀት፥ የተለመደ የአእምሮ ሕመም እንደሆነም ይገለጻል፡፡ ይህ የአዕምሮ ጭንቀት ያጋጠማቸው ሰዎች ከአንዳንድ ነገሮች ወይም ሁኔታዎች ጋር የተያያዘ ከፍተኛ ፍርሃት ወይም ጭንቀት ያጋጥማቸዋል።

የጭንቀት ምልክቶች ከሚባሉት ውስጥ እረፍት ማጣት፣ ድካም፣ ትኩረት አለማድረግ፣ የጡንቻ ሕመምና የተቆራረጠ እንቅልፍ ይጠቀሳሉ፡፡ የስሜት መለዋወጥ (መቃወስ)፥ ከፍተኛ ደስታና ከፍተኛ ጭንቀት ሲፈራረቅ የሚስተዋል የአዕምሮ ሕመም ዓይነት ነው፡፡ በአዕምሮ ሕመም ተፅዕኖ በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰሩ ጥናቶች ያሳያሉ። ከዓለም የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር ተያይዞ ዲጂታል ሚዲያው በአዕምሮ ጤና ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ ብዙዎች ያነሳሉ።

አቶ ሳሙኤል ቶሎሳ የአዕምሮ ጤና ባለሙያና በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ የአዕምሮ ሕክምና ሆስፒታል የተመላላሽ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ናቸው። እሳቸው እንደሚናገሩት፤ ዲጂታል ሚዲያው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እያደገ እና ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ በቢሊዮን በሚቆጠሩ የዓለማችን ስዎች ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ይህ ማለት ደግሞ እራሱን የቻለ ማኅበራዊ፣ ስነልቦናዊና አዕምሮአዊ ከፍተኛ ጉዳት ይዞ የሚመጣ ነው ይላሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ አምስት ቢሊዮን የሚሆን የዓለማችን ሕዝብ የዲጂታል ሚዲያ ተጠቃሚ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ የሚሉት አቶ ሳሙኤል፤ በኢትዮጵያም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዜጋ የዲጂታል ሚዲያ ተጠቃሚ እንደሆነና ከሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘውና በዚህ የሚዲያ ተፅዕኖ ውስጥ የሚገኘው ወጣት መሆናቸውንና እንደ ሀገር ጉዳቱ ቀላል አለመሆኑንም አስረድተዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የአብዛኛው ወጣት የዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀሙ ተቀራራቢ ወይም ተመሳሳይ መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያው፤ ቴክኖሎጂ ይዞት የሚመጣው ጥሩ ዕድል እንዳለ ሆኖ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

‹‹ከጤና አንፃር ከ10 እስከ 19 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት አዕምሮአቸው የሚያድግበት ግዜ ነው። ይህ ጊዜም ታዳጊዎች ነገሮችን ማየት የሚጀምሩበትና የአዕምሮ ክፍላቸውም የሚሰፋበት ወቅት ነው›› የሚሉት የአዕምሮ ሕክምና ባለሙያው አቶ ሳሙኤል፤ ስሜቶቻቸው፣ ከሰው ጋር ያላቸው መግባባት፣እያንዳንዱ ባህርያቸው የሚቀየርበት ወቅት እንደሆነና ትልቅ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት የዕድገት ደረጃ እንደሆነ አመልክተዋል።

“የወጣትነት ዕድሜ በውስጣችን ያለውን የሚሰማንን ነገር ሁለት ጊዜ ሳናስብ የምናወጣበት ወቅት ነው” የሚሉ አቶ ሳሙኤል፤ በባህርይ የእኔነት ወይንም የግለኝነት ስሜት የሚንጸባረቅበት፣ በትንሽ ነገር ቶሎ መደሰትና መበረታታት፤ በዛው ልክ ደግሞ በትንሽ ነገር መከፋት የሚስተዋልበት ዕድሜ በመሆኑ ይህንን ተረድቶ ማለፍ የሚያስፈልግ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

የማኅበራዊ ሚዲያው የንግድ ሀሳብ ይዞ፣ ብዙ ሰዎች ይሳተፉበታል የሚለውን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተመሰረተ እንደሆነ ይታወቃል የሚሉት አቶ ሳሙኤል ይህ በማኅበረሰቡ ውስጥ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል ብለዋል። የሚዲያው ዋና ዓላማ ገንዘብ ማግኘት እንደሆነና ለዚህም ተደራሻቸው ወጣቱ እንደሆነ አመልክተዋል።በአጠቃላይ የሚሰጠው ጥቅም እንዳለ ሆኖ የሚያስከትለው ችግርም ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ።

‹‹አንድ ወጣት በማኅበራዊ ሚዲያ ቀርቦ እያወራ ወይም ፎቶግራፉን እያጋራ በሚገኝበት ወቅት፤ ያለ ገደብ ማንኛውም ሰው ሊያየው ይችላል፡፡ በመሆኑም ተመልካቹ ያንን ሰው ሊያበረታታውም ወይንም ሊጎዳው የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ለምሳሌ ሴት ብትሆን መልኳ ወይንም ሰውነቷ እንደማያምር አስተያየት ሊሰጣት ይችላል›› የሚሉት አቶ ሳሙኤል፤ ይህ ከፍተኛ መጨናነቅ፣ ድብርት፣ አለፍ ሲልም እራስን እስከማጥፋት የሚደርስ የስነ ልቦና ጫና ሊያስከትልባት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ይህች ሴት ሁሌም ቆንጆ ሆና ለመታየት ከአቅሟ በላይ በሆኑ ነገሮች ላይ ግዜዋን እንድታጠፋ ሊያደርጋት ይችላል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ሳሙኤል ገለጻ፤ ባደጉት ሀገራት ላይ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አንዱ የድብርት ስሜት ነው። ይህም የሚፈጠረው የእኔን ፖስት ብዙ ሰው አየልኝ ወይም ወደደው፣ ወይም ብዙ ሰው አልተመለከተውም የሚለው ነገር ነው፡፡ ሁኔታው ወጣቶቹን በጣም ሊያስጨንቃቸውና ውድድር ውስጥም ሊከታቸው ይችላል፡፡ በመሆኑም የራሳቸው ማንነት ያልሆነውን ግን ሰዎች ሊወዱት ይችላሉ ብለው የሚያስቡትን ነገር ማሳየት ይጀምራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ድባቴ ውስጥ በመክተት እራሳቸውን እንዲጎዱ ይገፋፋቸዋል፡፡ ለአእምሮ ጤና ችግርም ይጋለጣሉ፡፡

ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ኮምፒውተር እና የእጅ ስልካቸውን በመጠቀም ነው። ይህን እንደልማድ በመውሰዳቸው ምግብ ሲመገቡ እንኳን አያቋርጡም፡፡ በዚህ የተነሳም የአመጋገብ ስርዓት መዛባት እያስከተለባቸው ነው፡፡ ለከፋ የአዕምሮ ጤና ችግሮች ተጋላጭም እያደረጋቸው ይገኛል።

በዚህ ጊዜ ለረዥም ሰዓት እንቅልፍ ሳያገኙ የሚቆዩ ወጣቶች ቁጥርም ከፍተኛ እየሆነ ነው፡፡ “አዕምሯችን በተፈጥሮ እንቅልፍ የሚተኛበት ሰዓት ጨለማ ወይም ብዙ ብርሃን በማይኖርበት ሰዓት እንደመሆኑ፤ ማኅበራዊ ሚዲያው ደግሞ አዕምሯችን መተኛት ባለበት ሰዓት ላይ ጠብቀን እንዳንተኛ ስለሚያደርገን ሕይወታችን እንቅልፍ ማጣትን ተከትሎ ለሚመጡ የጭንቀት፣ የስሜት መረበሽ፣ የሀዘን ስሜቶች ወይም ሕመሞች ተጋላጭ ያደርገናል›› ሲሉም አቶ ሳሙኤል አስረድተዋል።

በተጨማሪም ወጣቶች ለብዙ ሰዓት በአንድ ቦታ ተቀምጠው ስለሚውሉ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረጋቸውን ተከትሎ በሚመጣ የጤና ችግርም እንደሚጋለጡ እና ይህም እንደ የልብ ሕመም አይነት በሽታዎች ተጋላጭ ይሆናሉ ብለዋል። እንደ አቶ ሳሙኤል ማብራሪያ፤ እንቅስቃሴ ካላደረግን ደም አይዘዋወርም። የአዕምሮአችንም አይነቃቃም። በዚህም ጫናዎች ተደራራቢ ይሆናሉ፡፡ የጤና ችግሩም በአዕምሮ ውስጥ ደም መፍሰስ ሊያስከትል የሚችልበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡

በሌላ በኩል ወጣቶችና ሕፃናት አብዛኛውን ሰዓት ትምህርታቸውን ከማንበብ ይልቅ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስለሆነ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት፤ ትምህርት ቤት ሄደውም በተመሳሳይ በማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ስር ስለሚሆኑ ትምህርታዊ በሆነው ነገር ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ ውስን ነው፡፡ ይህ እጅግ አደገኛ በመሆኑ የሚያስከትለው ጉዳት እንደ ሀገር በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡

የዲጂታል ሚዲያውን መቆጣጠር የምንችለው አይደለም የሚሉት የስነአዕምሮ ባለሙያው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ሀገራት የሚቸገሩበት ጉዳይ ነው። ታዳጊ ሀገር ላይ ደግሞ ተፅዕኖው ከፍተኛ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ወላጆች ስለዲጂታል ሚዲያው ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ እንደሆነና ጉዳትና ጥቅሙን በትክክል የመገንዘብ ችግር የሰፋ ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡

ይህንን ችግር ለመቀነስ እንደ ሀገር ፖሊሲ ሊኖር ይገባል የሚሉት አቶ ሳሙኤል፤ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ፖሊሲ ኖሮ በተለይ ሕፃናት በቀላሉ እንዳይጠቀሙ ወይም ዕድሜያቸውን ባገናዘበ መልኩ መጠቀም እንዲችሉ እንደ ሀገር መመሪያዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡ ከሌሎች ሀገራት ልምድ በመውሰድ ተደራሽ መሆን የሌለባቸው የዲጂታል ሚዲያ አማራጮች እንዲገደቡ መንግሥት ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዳይጠፋ መስራት አለበት ሲሉም ገልጸዋል።

እንደ አቶ ሳሙኤል ገለጻ፤ ቤተሰብ ወይም አሳዳጊ ከልጅ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ይኖርበታል። በተቻለ ጉዳቱን ማሳየት፣ ምን አይነት ችግር ይዞ እንደሚመጣበቸው ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል፡፡ አደገኛ የሆነ በተለይ ማየት የሌለባቸውን ነገር ማየት እንዲችሉ ሆኖ ስለሆነ የተዘጋጀው በዚህ ረገድ ቤተሰብ የጋራ መግባባት በመፍጠር የቁጥጥር ስርዓት ማበጀት ይኖርበታል።

ዲጂታል ሚዲያው ስዎች በማንነታቸው፣ በቆዳ ቀለማቸው፣ በአፈጣጠራቸውና ባላቸው ተፈጥሮ የሚሰደቡበትና የሚንቋሸሹበት መድረክ በመሆኑ፤ ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የስነልቦና ተፅዕኖ ያሳድራል። ይህንን ለመከላከል እንዲያስችል ሁለት ወገኖች ማለትም ወላጅ እና ልጅ በስምምነት ስለ ጉዳትና ጥቅሙ መወያየት አለባቸው፡፡ በዚህ መንገድ ቴክኖሎጂው የሚያደርሰውን ከፍተኛ የሆነ ዘርፈ ብዙ ጉዳት መቀነስ ይቻላል።

በስም ከሚታወቁ የማኅበራዊ ሚዲያዎች አማራጮች በተጨማሪ በይፋ የማይታወቁ ነገር ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተከታይ ያላቸው የበይነመረብ ሚዲያዎች አሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የተቃኙት ሕፃናትና ወጣቶችን መሠረት በማድረግ ስለሆነ የሚለቋቸው የምስል፣ የድምፅና የቪዲዮ መረጃዎች ዕድሜን የማይመጥኑ ናቸው፡፡ ብዙ ሰዎች ያላቸው የሚዲያ አጠቃቀም ከቁጥጥር ውጭ የወጣና ለስነአዕምሮ ሕመም ተጋላጭ የሚያደርጋቸው ነው፡፡

በቤት ውስጥ በማኅበራዊ ሚዲያ ተገድቦ የሚኖር ልጅ ምን እየሰራ እንደሆነ ወላጆች አብረው ሆነው በየቀኑ በግልፅነት የሚያወሩበት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ከዚህ ውጭ ወላጆች ልጆቻቸው በአካል ሄደው ከሰዎች ጋር ማውራት፣ መጫወት እንዲችሉ መንገድ መፍጠር አለባቸው፡፡ ከጎረቤት ልጆች ጋር ወይም ከትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ጋር አብረው ጊዜ እንዲያሳልፉም ማበረታታት ይኖርባቸዋል፡፡

በተጨማሪም ወላጆች ወጣት ልጆቻቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ስለሚያጋጥሟቸው ነገሮች በግልፅ ከቤተሰብ ጋር እንዲያወሩ ማድረግ ይጠበቃል። ውይይቱ ታዳጊዎችንም ሆነ ወጣቶችን ካላስፈላጊ ነገር ለመታደግ ያግዛል፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ዲጂታል ሚዲያን ተጠቅሞ የሚፈፀም ጥቃት እያደገ የሚሄድ እንጂ የሚቀንስ ባለመሆኑ በዚህ ረገድ መንግሥት የተለያዩ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፎችን በማውጣት ያሉትን ደግሞ በማጠናከር የተጠያቂነት ስርዓት እንዲኖር መስራት ያስፈልጋል ሲሉም ባለሙያው ምክረሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ በሌላ በኩል ለሕፃናት ብቻ የሚሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች ሀገር ውስጥ በማበልፀግ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ሥራዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡

‹‹ያለ አዕምሮ ጤና የለም›› የሚሉት ባለሙያው፤ ከዲጂታል ሚዲያው ጋር ተያይዞ የሚመጡ የአዕምሮ ሕመሞችን ቀድሞ ለመከላከልና እንደ ሀገር ወጣቱን ትውልድ ለማትረፍ በመጀመሪያ አሳዳጊ ወላጅ በተጨማሪም መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት በከፍተኛ ትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ጥር 24/2016

Recommended For You