ረመዳን ከእስልምና ሃይማኖት ምሶሶዎች አንዱ ነው። በእስልምና አቆጣጠር ዘጠነኛው ወር በሆነው በዚህ ወር ለ29 ወይም ለ30 ቀናት ይፆምበታል። ረመዳን ከማለዳ እስከ ጨረቃ መውጪያ ባሉት ሰዓታት የሚፆምበት ወር ነው። በሻዕ ባን ወር መጨረሻ ምሽት የሚጀምረው ፆሙ የሚጠናቀቀው በረመዳን ወር መጨረሻ ምሽት ነው።
በጤንነት እክልና በነፍሰጡርነት ላሉ፣ ለሚያጠቡ ሴቶች፣ ረጅም መንገድ ለሚሄዱ እና አረጋውያን የመሳሰሉት ብቻ ፆሙን የማይገደዱ ቢሆንም ለወጣትና ጎልማሳ ሙስሊሞች ግን ፆም የሃይማኖቱ ግዴታ ነው። በምሽት የሚቀርቡ ምግቦች ሽዑር የሚባሉ ሲሆን፣ ልክ ፀሐይ እንደጠለቀች የሚቀርበው ፆም ለመፍታት የሚቀርበው ምግብ ሾርባና የመሳሰሉት ኢፍጠር ተብሎ ይጠራል፤ አንዳንድ ሰዎች የረመዳን እራት ይሉታል።
በረመዳን ወር መፆም ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ አስተዋፅዖ ማበርከት ይጠበቃል። ስለዚህ ሙዕሚኑ ጊዚያቸው በፀሎትና በስግደት (በዱኣና በሶላት) ፣ ቁርኣን በመቅራት፣ በጎ ተግባራትን በማድረግ ያሳልፋሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ረመዳን ሙስሊሞች ራሳቸውን በስነምግባር የበለጠ እንዲያንፁ፣ እንዲቆጣጠሩ፣ መስዋዕትነት እንዲከፍሉ፣ ለምስኪኖች ሀዘኔታን እንዲያሳዩ፣ የልግስና ተግባራትን እንዲያበረታቱ እና ዘካ በማውጣት መለገስንም የሚያስተምር ነው።
ምጽዋት በእስልምና በጣም አስፈላጊ ነገር ሲሆን ረመዳን ወር ሲመጣ ደግሞ አስፈላጊነቱ እጅግ በጣም ይጨምራል። ዘካት ወይም ልግስና ከእስልምና አስትምህሮ ምሶሶዎች አንዱ ነው። አንድ ሰው ከቆጠበው የተወሰነ መቶኛውን በረመዳን መጨረሻ ለድሆች መስጠት ይኖርበታል ።
ሰደቃ ደግሞ ሙስሊሞች ለድሆችና ለጦም አዳሪዎች መስጠት ከሚጠበቅባቸው መቶኛ (ከዘካ ) በላይ በፍቃደኝነት የሚሰጡት ልግስና ነው።
በእስልምና በዓመቱ ውስጥ ካሉት ወራት ይበልጥ በረመዳን መልካም ተግባራት ሁሉ ማድረግ ጥሩ ዋጋን ያሰጣል። ስለዚህም ብዙዎች ይህንን የረመዳን ወር ካላቸው ላይ ብዙ ሰደቃዎችን በማውጣት በመጨረሻው ፍርድ ቀን የሚያገኙትን ሽልማት ለመጨመር ይፈልጋሉ።
ረመዳን በኢትዮጵያ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ከሙስሊሞች ጋር በጋራ ሆነው እንኳን አደረሳችሁ ብለው ድፎ ዳቦም ሆነ ኬክ ይዘው የሚያከብሩት በዓል ነው።
በርግጥ በኢትዮጵያ እስልምና ረጅምና ልዩ ታሪክ ያለው ሃይማኖት ነው። ነቢዩ ሙሐመድ በነቢይነት ሲነሱ በመካ ቁረይሾች በተቃውሞ ተነሱባቸው። ተከታዮቻቸውንም በ615 ዓ.ም ወደ አቢሲኒያ የምትባለው የክርስቲያን ሀገር እንዲሸሹ አዘዙዋቸው። በዘመኑ የነበረውም አርማኅ የሚባለውም የኢትዮጵያ ንጉሥ ለፍትሕ ቆሞ የእስልምና ስደተኞቹን ተቀብሎ በትግራይ ውቅሮ ነጋሽ መጠለያ ሰጣቸው።
በእስልምና ታሪክና ትውፊት ኢትዮጵያ “የመጀመሪያው ሂጅራ ስደተኞች መጠለያ” ተብላ ትታወቃለች። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች መካከል ያለው ወዳጅነት ረጅምና ጥልቅ ያደርገዋል።
እስልምና በኢትዮጵያ ከገባበት ዘመን ጀምሮ የክርስትናና የእስልምና ተከታዮች እንደ አንድ ማኅበረሰብ በአንድነት የሚኖሩ ናቸው ። በሕዝቦች መካከል ምንም መለያየት የለም። ይህ ባህልና ደማቅ ግንኙነት የበለጠ ጎልቶ የሚታየው ደግሞ በረመዳን ወር ነው። በተለይ በአፍጥር ሰዓት ማኅበራዊ ግንኙነቱ ይጠነክራል። በረመዳን ወር ዕለት ዕለት ሾርባ ለመጠጣት ሙስሊም ወዳጆቻቸው ቤት የሚሄዱ ብዙ ክርስቲያኖች አሉ ።
በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ክርስቲያን አማኞች የእስልምና ተከታይ ከሆኑ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋራ ዘወትር በረመዳን ምሽት ፆም ሲፈታ ሙስሊም ወዳጆቻቸው ቤት ሄደው የረመዳን ሾርባና እራትም አብረው ይበላሉ ደስታውን ይካፈላሉ።
የ28 ዓመቱ አቤል በላይ ለዚህ አንዱ ምሳሌ መሆን ይችላል። ከልጅነቱ ጀምሮ በአዲስ አበባ ኮልፍ ቀራንዮ ከሚገኙት ሙስሊም ጎረቤቱ በረመዳን ፆም መፍቻ ምሽት እራት እየበላ ሾርባውን እየወሰደ ደስታና ፍቅርን ሸምቶ ተጫውቶ ወደ ቤቱ ይመለሳል።
ጎረቤቱ አቶ ሙሐመድ ክርስቲያን ጎረቤታቸው በአፍጥር ሰዓት ሲመጣ ሁልጊዜ እንደሚደሰቱ ይናገራሉ። አቤል በበኩሉ” እኔ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ተከታይ ነኝ በየዓመቱ ረመዳን ሲመጣ ሾርባውን በጉጉት እጠብቃለሁ።” ይላል።
በረመዳን ወር ሙስሊሞች ሰደቃ የበለጠ ያወጣሉ። አቶ ሙሐመድ አሊ እንደሚናገሩት “አብዛኛዎቹ ሙስሊሞች በአፍጥር በዓል ላይ ብዙ ሰዎች እንዲቀላቀሉዋቸው ይጠራሉ። ምክንያቱም በዚህ ከአላህ መንፈሳዊ ዋጋ ስለሚያገኙ ነው።”
አቶ ሙሐመድ እንዳሉት ክርስትና ተከታዮች በረመዳን ወቅት ሙስሊሞችን በብዙ ነገር ይረዳሉ። በተለይ በገጠራማ አካባቢዎች ክርስቲያኖች የእርሻ መስኮቻቸውን በመጠበቅ ከብቶቻቸውን በማሰማራት የሚሰበሰቡ እህሎችም ካሉ በመሰብሰብ ለብዙ ዓመታት ሲረዱዋቸው ቆይተዋል ። “ይህ ለብዙ ዓመታት የዘለቀ ባህላችን ነው።”ይላሉ።
በብዙ የሀገራችን ክፍሎች የረመዳን ወር ብቻ ሳይሆን ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ርዕስ በርዕስ ይረዳዳሉ። መረዳዳቱ ደግሞ በረመዳን ወር ብቻ ሳይሆን በሌሎቹ ወራት የሚታይ ነው ። አሁንም ውሃ ቀጠነ እያሉ በሃይማኖት እየከፋፈሉ ሊለያዩንና ሊያጋጩን የሚፈልጉ አድርባዮችን ሁሉም ሊያውቅባቸውና ሊርቃቸው ይገባል። አስበው ሳይሆን በአጋጣሚ የራሳቸውን ምቾት ሊያመቻቹ የሚፈልጉ ናቸው ። ዒድ ሙባረክ!
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር