የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ለረጅም ዓመታት ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ በሆኑ ችግሮች በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያልተገባ ዋጋ በመክፈል ለማለፍ የተገደዱ፤ ዛሬም ቢሆን እስከ ችግሮቻቸው፣ ነገዎቻቸውን ተስፋ አድርገው ለመጠበቅ በተመሳሳይ ፈተናዎች ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
አካባቢው ካለው ጂኦ – ፖለቲካል ስትራቴጂ እና የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ በፈጠራቸው ተግዳሮቶች፤ በአካባቢው የሚገኙ ሕዝቦች ካላቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ የጠበቀ መስተጋብር አንጻር የሚጠበቀውን ያህል አንድነት ፈጥረው ለጋራ ፍላጎታቸው በጋራ መንቀሳቀስ ሳይችሉ ቀርተዋል። ከዚህ ይልቅ ቀጣናውን ተሻግረው በሚመጡ የውጭ ኃይሎች ፍላጎት እና ፍላጎቶቹ በፈጠሯቸው ሴራዎች፤ አካባቢው የግጭት ማዕከል ሆኗል።
ሌላው ቀርቶ ተፈጥሮ ያደለቻቸውን ጸጋዎች አውቀውና አልምተው ድህነትንና ኋላ ቀርነትን መሻገር ሳይቻላቸው ቀርቷል። የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እና አስተሳሰቡ የወለደው የልዩነት ትርክት፤ በብዙ መልኩ ተመሳሳይ የሆነውን ሕዝብ፤ ስለ ራሱ ዕጣ ፈንታ ቁጭ ብሎ እንዳይነጋገር፤ ተነጋገሮ እንዳይግባባ፤ ተግባብቶ ለዘለቄታው ችግሮቹን በጋራ መቋቋም እና መሻገር የሚያስችል አቅም እንዳያዳብር አድርጎታል።
ይህም ቀጣናው ካለው ጂኦ ፖለቲካል ስትራቴጂክ ጠቀሜታ በተጨማሪ የብዙ የተፈጥሮ ጸጐች ባለቤት እየሆነ ባለበት ሁኔታ የድህነትና የኋላቀርነት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል። ከሁሉም በላይ በአካባቢው የሚገኘው የአርብቶ አደር ማኅበረሰብ የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ሆኗል።
የአካባቢው አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ የመልማት ፍላጎትም በብዙ ተግዳሮቶች ምክንያት እውን አለመሆን፤ ማኅበረሰቡ ዛሬም ለእንስሳቱ ውሃና ግጦሽ ለማግኘት ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ እየተንቀሳቀሰ እንዲኖር አስገድዶታል። ይህ ደግሞ እንደ ድርቅ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ አደጋው የሚፈጥረው ጥፋት ሕይወትን አንድ ብሎ እንዲጀምር እስከ ማድረግ የሚደርስ ነው፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚኖረው ኑሮ ነገን በተስፋ መጠበቅ የሚያስችል አቅም የተላበሰ አይደለም። መጪዎችን ትውልዶች አስቦ ለተሻሉ ነገዎች በተስፋ መትጋት የሚያስችል መነቃቃት የሚፈጥርም አይደለም።
የዚህ አካባቢያዊ ችግር በዋናነት የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰው ሀብት ወይም የኢንቨስትመንት ችግር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለጋራ ዕድገትና ተጠቃሚነት በጋራ ማሰብ የሚያስችል እሳቤ አለመኖር ነው። ዕጣ ፈንታን በጋራ መሥራት የሚያስችል መናበብ መፍጠር አለመቻልም ነው። ይህ በቅኝ ግዛት እሳቤ ምክንያት የተፈጠረ ክፍተት፤ በቅኝ ግዛት ዘመን እንደሆነው ሁሉ የአካባቢው ሕዝቦች በአንድም ይሁን በሌላ የሀብታቸው ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። የሀብት ችግር ሳይኖርባቸው የቅኝ ገዥዎቻቸውን ዳረጎት እንዲጠብቁና በእነሱ በጎ ፈቃድ እንዲኖሩ እያስገደዳቸው ነው።
በብዙ መስዋዕትነት፤ ውድ ሕይወታቸውን ገብረው ያገኙት የፖለቲካ ነፃነት፤ ባልተገባ ልዩነት በሚፈጠር ጠላትነት የቅኝ ገዥዎቻቸው የኢኮኖሚ ባርያ በመሆን፤ ነፃነታቸው ሙሉ ትርጉም እንዳይኖረው ሆኗል። በዚህም ዛሬም ቀና ብለው የሚሄዱበትን ልብ መፍጠር ተስኗቸዋል። የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች ከዚህ ያልተገባ የልዩነት ትርክት ከፈጠረው መከፋፋል እና መከፋፈሉ ከፈጠረው አለመተማመን፣ አለመተማመኑ ከፈጠረው ጥርጣሪ ወጥተው፤ ነገዎቻቸውን በእጆቻቸው ባሉ መልካም ዕድሎች ብሩህ ለማድረግ ዛሬ ላይ ቆም ብለው በሰከነ መንፈስ ለጋራ ተጠቃሚነት ማሰብ ይጠበቅባቸዋል።
አካባቢው ያለውን ሰፊ የውሃ ሀብት፣ የሚታረስ መሬት፣ ተስማሚ የአየር ሁኔታ፣ ማዕድናት፣ የባሕር ወደቦች …ወዘተ ሀብቶች አቀናጅተው ቀጣናውን አዲስ የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ አቅም ሆኖ መውጣት ወደሚያስችል የታሪክ ምዕራፍ ማሸጋገር ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የጀመረችው አካባቢያዊ ጸጋዎችን አቀናጅቶ በጋራ የማደግ አስተሳሰብ እንደ መልካም አጋጣሚ ሊወስድ የሚገባው ነው ፤ አስተሳሰቡ ዘመኑን የሚዋጅ፤ በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ የተቃኘና አፍሪካዊ ወንድማማችነትን ወደ ላቀ ደረጃ ማሻገር የሚያስችል ነው፡፡
የአካባቢው ሀገራት ከመጡበት የችግር መንገድ፤ መንገዱ እስከዛሬ እያስከፈላቸው ካለው ያልተገባ ዋጋ አንፃር፤ አንድነታቸውን በማጠናከር ፤ ነገዎቻቸውን በጋራ ብሩህ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይህ በእጃቸው ያለ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ትልቁ አቅማቸው ነው!
አዲስ ዘመን ጥር 23/2016