የአንድ መሪ ስኬታማነት መመዘኛው ለሚመራው ሕዝብና ሀገር የሚጨበጥ ለውጥ በማምጣት የተሻለ ተጠቃሚነትን ማስፈን ነው። ለዚህም ነው በምርጫ ሰሞን የተፎካካሪ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ በአብዛኛው ብትመርጡኝ ይህን እና ይህን አደርጋለሁ! ፤ ይህን እና ይህን እለውጣለሁ ! .. ወዘተ በሚሉ ንግግሮች የተሞሉ የሚሆኑት ።
ምርጫ አማራጮችን መሠረት አድርጎ የሚከናወን ከመሆኑ አንጻር በሂደቱ የሚደረጉ የምረጡኝ ቅስቀሳዎች ልብ አማላይና በተስፋዎች የተሞሉ መሆናቸው የሚጠበቅ ነው። መራጩም ሕዝብ የምርጫ ካርዱን የሚጥለው ተስፋው ተጨባጭ ነው ብሎ ላመነበት ብቻ ሳይሆን፤ ቃሉን የመፈጸም አቅም አለው ብሎ ለሚያምነውም ጭምር ነው።
በእኛም ሀገር የዛሬ ሦስት ዓመት ከምርጫ ጋር በተያያዘ አዲስ ታሪክ መፍጠር ያስቻለ ክስተት ተፈጥሯል። የለውጥ ኃይሉ ራሱን የለውጥ መንግሥት አድርጎ ለማስቀጠል ባደረጋቸው የምረጡኝ ቅስቀሳዎች ብዙ ሀገር አሻጋሪ ተግባራትን በመሥራት ሀገርና ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ቃል ገብቷል። የገባቸው ቃሎችም በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ስፍራ በማግኘታቸው በምርጫው አሸንፎ ወደ ሥልጣን መጥቷል።
ለውጡ እንደ አንድ ሀገራዊ ትርክት ለዋጭ ለውጥ፤ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ የተገደደበት ሁኔታ ተፈጥሯል ፤ ፈተናው ለውጡን ብቻ ሳይሆን ሀገርን እንደሀገር የሕልውና ፈተና ውስጥ እስከ መክተት የደረሰ አደጋ ሆኖ የተከሰተበትም እውነታ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው ።
ይህን አደጋ ለመቀልበስ የተደረጉ ጥረቶች ከፍ ያለ ቁርጠኝነትና የዓላማ ጽናትን የጠየቁ፤ የለውጥ ኃይሉን በሁለንተናዊ መንገድ የፈተኑ ናቸው፤ ከውጪም ከውስጥም የተፈጠሩ ጫናዎች ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ሳይቀር እንደ አንድ ትልቅ ታሪካዊ አጋጣሚ ተወስደው ከፍ ያለ ርብርቦሽ የተደረገባቸው ናቸው።
የለውጥ ኃይሉ ይህንን በብዙ መልኩ ከተገማችነት ያለፈ ፈተና ለመሻገር በአንድ በኩል ለራሱ፤ በሌላ በኩል ለሕዝብ የገባውን ቃል ተጨባጭ ለማድረግ ብዙ የተጎረባበጡ መንገዶችን፤ ለጉዞ የማይመቹ ኮረብታዎችን ለመጓዝ ተገድዷል። ጉዞው ከሚፈጥራቸው ፈተናዎች በመማርም ራሱን እያበቃ ዛሬ ላይ ደርሷል ።
ለዚህም የለውጡ አርክቴክት የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአመራር ብቃት መተኪያ የሌለው እንደሆነ፤ የለውጥ ኃይሉ ከቃል ባለፈ በየወቅቱ እያስመዘገበ ካለው ሀገራዊ ስኬትና ስኬቱ እንደ ሀገር እየፈጠረ ካለው ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብዙ የሚከብድ አይደለም። አብዛኛው ዜጋ የሚስማማበት ከዚያም ባለፈ ዓለም አቀፍ እውቅና እየተቸረው ያለ ነው ።
ለዚህ ከሁሉም በላይ ሀገርን ከሕልውና ስጋት መታደግ፣ ጠንካራ የመከላከያና የፀጥታ ተቋማትን የመገንባት ተስፋ ሰጭ ጅማሬ፤ የዓባይ ግድብን ከነበረበት ተስፋ አስቆራጭ ምዕራፍ አውጥቶ ዛሬ የደረሰበት ከፍያለ የተስፋ ምዕራፍ ላይ ማድረስ ፣ የገበታ ፕሮጀክቶች፤ አማራጭ አስተማማኝና ቀልጣፋ የወደብ አገልግሎት ለማግኘት እየተሄደበት ያለው መንገድ፤ በምግብ እህል ራስን ለመቻል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች እና አሁናዊ ስኬቶቻችውን ወዘተ ማንሳት ይቻላል።
እነዚህ ስኬቶች ሀገር እንደሀገር በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆና የተገኙ ብቻ ሳይሆኑ፤ ፋታ እና ዕረፍት በሌለው የአመራር ቁርጠኝነት የተገኙ ናቸው። ስኬታማነታቸውን ስናስብም ብዙ ተደክሞባቸው፤ ተለፍቶባቸው፤ ዋጋ ተከፍሎባቸው መሆንን በአግባቡ በመገንዘብ ተገቢውን እውቅና በመስጠት ሊሆን ይገባል ።
ከዚህ አንጻር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ራዕይ፣ አመራር እና ቁርጠኝነት፣ ብሎም ፈጣን፣ ተለዋዋጭ እና ፈታኝ በሆነው ከባቢያዊ ሁኔታ በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል በተከተሉት ፈጠራዊ መፍትሔ ዕውቅና በመስጠት የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት የአግሪኮላ ሜዳሊያ በመሸለማቸው እንኳን ደስ ያለዎት ለማለት እንወዳለን።
ሽልማቱ ሀገርና ሕዝብ ዳግም በዓለም አቀፍ መድረክ ደምቀው የታዩበትን ታሪካዊ አጋጣሚ የፈጠረ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩና በአጠቃላይ የለውጥ ኃይሉ ለሕዝባችን የገቧቸውን ቃሎች ተጨባጭ በማድረግ ለሀገርና ለሕዝብ የበለጠ የሚያገለግሉበትን አቅም የሚያሳድግ ትልቅ ዓለም አቀፍ ምስክርነት ነው!
አዲስ ዘመን ጥር 22/2016