ምርታማነትንና የግብይት ሠንሰለትን ውጤታማ የሚያደርግ ፕሮጀክት

በኢትዮጵያ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባሮች ምርትና ምርታማነት እያደገ መጥቷል:: ምርትና ምርታማነቱን ከዚህም በላይ ሊያድግ እንደሚችል ታምኖበት እየተሰራ ይገኛል::

የምርትና ምርታማነት ማደግ ብቻውን ግን አርሶ አደሩንም ሀገርንም ተጠቃሚ ሊያደርግ አይችልም:: ከዚሁ ጎን ለጎን ግብይት ላይ መስራት ወሳኝ ነው:: ግብይት ላይ በሚፈለገው ልክ አለመሰራቱን ተከትሎ ከምርቶቹ የበለጠ ተጠቃሚ እየሆነ ያለው አርሶ አደሩ ሳይሆን ነጋዴውና ደላላ መሆኑ ይታወቃል:: ይህን ችግር ለመፍታት ምርታማነትን በማሳደግ እና ምርት ተገቢውን የገበያ እሴት ሰንሰለት ጠብቆ ለግብይት እንዲቀርብ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረቶች ሲደረጉ ይታያል።

በቅርቡም በኢትዮጵያ እና በጀርመን መካከል እንዲሁም በፈጻሚነት ደግሞ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከጂአይዜድ ጋር በመተባበር ምርትና ምርታማነት ማሳደግና የግብይት እሴት ሰንሰለትን በጠበቀ መልኩ ለገበያ የማቅረብ ሂደት እንዲኖር ማድረግ የሚስችል አሰራር የሚተገበርበት ፕሮጀክት በቅርቡ ይፋ ተደርጓል:: ይህ በአቮካዶ፣ ሽንኩርትና አኩሪ አተር ምርቶች ላይ የሚተገበር ፕሮጀክት በሙከራ ደረጃ የሚተገበር ሲሆን፣ የእነዚህን ምርቶች የእሴት ሰንሰለት ማሳደግ ላይ ያለመ ነው፤ ለ14 ወራት የሚተገበር ፕሮጀክት ሲሆን፣ በሌሎች ምርቶች ላይም በቀጣይ እንደሚተገበር ተጠቁሟል::

የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ ውቤ መንግስቱ በኢትዮጵያ እና በጀርመን መካከል የተደረገው የዚህ ፕሮጀክት ስምምነት በቅርቡ በተካሄደበት ወቅት እንዳስታወቁት ፤ ፕሮጀከቱ በአማራ፣ በኦሮሚያና ሲዳማ ክልሎች ላይ ያተገበራል። ክልሎቹ የተመረጡትም ምርቱን በማምረት ባላቸው አቅም መሰረት ነው::

በተወሰኑ ምርቶች፣ ለተወሰኑ ወራት እና በተወሰኑ ክልሎች የሚከናወን ሲሆን፣ እየሰፋ ሊሂድ የሚችልም ነው። ከፍተኛ መጠን ያለው የአኩሪ አተር ምርት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ይመረታል፤ በሲዳማ ክልል ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው አቮካዶ ይመረታል። አማራ ክልል እና በኦሮሚያ ክልሎች ሸንኩርት በስፋት ይመረታል። ስለሆነም ክልሎቹ ለምርቶቹ ያላቸው የማምረት አቅም ታይቶ ለፕሮጀከቱ በሙከራነት የተመረጡ መሆናቸውን ዋና ጸሐፊው ይናገራሉ።

ፕሮጀክቱ ከፕሮጀክቱ ለጋሽ ጋር በመነጋገር የሚከናወን መሆኑን አቶ ውቤ ጠቅሰው፣ የምክር ቤቱን አቅም በማሳደግ፣ በእርሻና ንግድ ስራዎች ላይ የማማከር ስራዎች እንዲሁም በፖሊሲ መፍትሄዎች ላይ በጋራ ለመስራት እንደሚያስችልም አስታውቀዋል። የሽንኩርት፣ አቮካዶ እና አኩሪ አተር ምርታማነትን ለማሳደግና የገበያ ሰንሰለትን ለመፍጠር ያለመው ይህ ፕሮጀክት በሶስቱ ክልሎች ለሚገኙ አንድ ሺህ ያህል የግል አምራቾች ዘርፈ ብዙና ተከታታይ ድጋፍ የሚደረግበት መሆኑንም አመላክተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ እና በአማራ ክለሎች ላይ በአሾካዶ፣ አኩሪ አተር (ሶያ ቢን) እና ሽንኩርት ማምረት ስራ ላይ ከተሰማሩ አምራቾች አንስቶ ከታች ወደ ላይ ወይም ከማምረት እስከ ግብይት ድረስ ያለውን የእሴት ሰንሰለት በመደገፍ ምርታማነታቸውን ለማሻሻል ያግዛል። የማምረቻ ቴከኖሎጂ አጠቃቀማቸውን ለመሻሻል፣ የገበያ መዳረሻቸውን ለማስፋት እና ተደራሽነታቸውን ለመጨመር ታስቦ የሚከናወን ነው።

ለፕሮጀከቱ ማከናወኛ የተያዘው የገንዘብ መጠንም 553 ሺህ ዩሮ መሆኑን ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል። ይህም በአቮካዶ፣ በአኩሪ አተር እና በሽንኩርት ንግድ ላይ የተሰማሩትን ሴቶችና ወጣቶችን ጨምሮ የተለያዩ የንግድ ማህበረሰብ አባላትን የንግድ ትርኢት ተሳትፎ በማሳደግ የገበያ ይዘትን መማር እንዲችሉ እንዲሁም ከአቻዎቻቸው ጋር በመወያያት እውቀት መለዋወጥ የሚያስችላቸውን ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችሉ ሰፊ ስራዎች ይሰሩበታል።

በተለይም በማምረት ስራና በአመራር ላይ የሚገኙት ልምዳቸውን የሚያጋሩበትና ልምድ የሚቀስሙበት፣ ልምድ በመቀመር የተሻለ ምርታማ እንዲሆኑ የሚታገዙበት የውጭ እድል ጭምር የተካተተበት ፕሮጀክት መሆኑን ይናገራሉ። በፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት ሂደትም በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ያሉ የፀጥታ ችግሮች እየተወገዱ ሲሄዱ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ይደረጋል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም አስታውቀዋል::

እንደ አቶ ውቤ ገለጻ፤ ፕሮጀከቱ ለ14 ወራት ይካሄዳል:: እንደ ኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ባሉት አስራ አንድ የስራ ዘርፎች ውስጥ ሁሉም የስራ ዘርፎች የየራሳቸው ሥራ እንዲኖራቸው በማድረግ ይደራጃል። ምርታማነትን እንዲሁም የምርት ውጤታማነትን በማሻሻል ረገድ ፕሮጀክቱ እንደ አንድ መነሻ ሥራ ሊታይ ይችላል። ከዚህ ፕሮጀክት በመቀጠልም እየሰፋ በመሄድ ወደ ሁሉም አምራች ለመድረስ የሚኬድበት አሰራር ይቀጥላል።

ፕሮጀክቱን በዘለቄታዊነት ለማስቀጠልም ይሰራል ያሉት አቶ ውቤ ፤ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ተረክቦ እየደገፈ የሚሄድበት አሰራር ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መላኩ አዘዘው (ኢ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፣ የግሉ ዘርፍ ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በመቀናጀት ባለፉት ዓመታት በእርሻ ምርታማነት ዘርፈ- በዙ ስራዎችን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፤ የሌሎችን ተሞክሮ ከመውሰድ ጀምሮ የእርሻ ሥራዎችን ዘመናዊ ማድረግ በሚያስችሉ ጥናቶች እና ቴክኖሎጂዎች ላይ ኢንቨስት አድርጓል፤ እነዚህ ጥረቶችም በዘርፉ የተሰማሩ ተዋናዮችን አቅም ለማጠናከር፣ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ እና የገበያ አቅርቦትን እና የዘርፉን አጠቃላይ እድገት ለማረጋገጥ አቅም የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች ነበሩ።

በዚህ ፕሮጀክት በሙከራ ደረጃ ተመርጠው ተግባራዊ የሚደረጉት የአቮካዶ፣ የአኩሪ አተር እና የሸንኩርት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እንዲሁም በገበያ ሰንሰለት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሌላ በኩል ደግሞ የገበያ ሰንሰለቶችን በመዘርጋት የሀገር ውስጥ ገበያው እንዲረጋጋ እገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። ምርቶቹ በዓለም ገበያ ያላቸው ተፈላጊነት እንዲጨምር ያደርጋል ሲሉም አስታውቀዋል:: ፕሮጀክቱ የምክር ቤቱ ዕቅድ ውጤታማ እንዲሆን እንደሚያግዝ ጠቅሰው፤ ለተግባራዊነቱ እና ለውጤታማነቱ ምክር ቤቱ የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

ከማህበረሰቡ እና ከግሉ ዘርፎች እንዲሁም እንደ ጂአይዜድና ከመሳሰሉት ጋር በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ ስራዎች የተቋማት አደረጃጀቶችን አቅም ማሳደግ፣ የአሰራር ሂደቶችን ማሻሻል እና የገበያ ሰንሰለቱን ውጤታማ ማድረግ እንደሚያስችሉም ተናግረዋል።

የእሴት ሰንሰለት እውቀትን በማሻሻል እና የፈጠራ ስራዎችን በማስፋፋት፣ ፖሊሲዎችን በሚገባ ተገንዝቦ ተግባራዊ በማድረግ፣ ዘላቂ ስራዎችን ቅድሚያ በመስጠት በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ የተመረጡትን የአቮካዶ፣ የአኩሪ አተር እና የሽንኩርት ምርቶችን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማሳደግ እንደሚቻል ያመላከታሉ።

የፕሮጀክቱ ቀዳሚ ዓላማም በአቮካዶ፣ አኩሪ አተር እና ሽንኩርት ምርታማነት እና የገበያ ሰንሰለት ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን ከተገቢ ክህሎት እና እውቀት ጋር መስጠት መሆኑንም አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ይህን ትልቅ ቅንጅታዊ ሥራ በኃላፊነት በመቀበል እና ተግባራዊ በማድረግ ኃላፊነቱን በቁርጠኝነት እንደሚወጣም ገልጸዋል::

ፕሬዚዳንቱ እንዳብራሩት ፤ ቀደም ሲልም ምክር ቤቱ ከልማት ባንክ ጋር በመተባበር ለ110 ሺህ ነጋዴዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ስልጠናዎችን ተደራሽ ለማድረግ ችሏል:: ከእነዚህም በንግዱ ዘርፍ ለመሰማራት ለሚፈልጉ አካላት ንግድ በምን መልኩ መጀመር እንደሚገባቸው፣ በገቢ ማስቀመጥ እና የንግድ ፕላን አዘገጃጀት፤ የሰው ሀብት፣ የገበያ አስተዳደር እና የፋይናንስ አስተዳደር ላይ ስልጠናዎችን ሰጥቷል፤ ይህንን ስልጠና የሰጠውም 228 አሰልጣኞችን በመላ ሀገሪቱ በማሰማራት ነው:: አሁንም ከጂአይዜድ ጋር በመተባበር በሚሰራው በዚህ ፕሮጀክት ምክር ቤቱ ለወደፊቱ በጋራ የሚያከናውነውን ሥራ ለማሳካት የሚያስችል አቅም ይፈጠራል።

ጂአይዜድ ባለሙያዎች እና ግብአቶችን በማቅረብ ለምክር ቤቱ የሚያደርገው ድጋፍ ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለሚያከናውናቸው ተግባሮች ፋይዳ እንዳላቸው አመላክተዋል። ፕሮጀክቱ ለታለመለት አላማ እንዲውልና ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻልም የክልል መንግሥታት፣ የንግድ ምክር ቤቶች፣ ማህበራት እና በተመረጡት የምርት ዘርፎች የተሰማሩ አካላት በኩል የሚኖረው ትብብር የራሱ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል።

የጂአይዜድ ተወካይ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሚሳ እንደተናገሩትም፣ ፕሮጀከቱ በሽንኩርት፣ በአኩሪ አተር እና በአቮካዶ ምርታማነት እና የገበያ እሴት ሰንሰለት ላይ ማሻሻሎች እንዲታዩ ያግዛል። የእነዚህን ምርቶች ምርታማነት ለማሳደግ ፕሮጀከቱ በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ በሚደረግባቸው የኦሮሚያ፣ አማራ እና ሲዳማ ክልሎች አቅም የሚያጎለብቱ ውጤታማ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን በመስራት እና ከክልሎቹ ጋር የፖሊሲ ምክክር በማድረግ አዎንታዊ ለወጦችን ለማምጣት ያስችላል።

ጂአይዜድ የግሉን ዘርፍ አቅምና ምርታማነት የሚያሳድጉ የቴክኒክ እና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ የሚያስችለውን ይህን ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በመተግበር አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ምርታማነታቸውን የሚያሳድጉ ስራዎችን እንዲሰሩና ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ያለውን የግሉ ዘርፍንም በመደገፍ ለማበረታታት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የኮሙኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ አበበ እንደሚገልጹት፤ በዋነኛነት ፕሮጀክቱ የሚያተኩረው የግብርና የእሴት ሰንሰለትን ማጠናከር በሚለው ላይ ነው፤ ፕሮጀክቱ በአቮካዶ፣ በአኩሪ አተር እና በሸንኩርት ምርት ላይ ያሉ መሰረታዊ አቅሞችን በመለየት እና ምርቶቹን ለውጭ ገበያ ጭምር ካላቸው ተፈላጊነት አንፃር መሰራት ያለባቸው ስራዎች የሚለይበት ነው። የእሴት ሰንሰለቱም ከማምረት ጀምሮ ለገበያ ቀርቦ ለተጠቃሚው እስከሚቀርብ ድረስ ከጥራትና ከምርት ብዛት አንፃር እንዲሁም ምርቱ በአግባቡ ተመርቶ የገበያ ትስስር ተፈጥሮ ተጠቃሚው ዘንድ እስከሚደርስ ድረስ ተገቢ የአሰራር ሥርዓት የሚፈጠርበት ነው።

እነዚህ ምርቶች በሙከራ ደረጃ ለፕሮጀክቱ ሥራ የተመረጡበትም ምክንያት በሀገሪቱ በስፋት በመመረታቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ ለውጭ ገበያ ሊቀርቡ የሚችሉ መሆናቸውም ሌላው ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዚህ አንፃር በሶስቱም ምርቶች ምርታማነት ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ የመንግሥት የፖሊሲ ስትራቴጂ አቅጣጫዎች የሚወጡበትን ሁኔታ ሊያመቻቹ የሚችሉ ጥናቶችን ለማከናወን እንደሚያስችል አስታውቀዋል።

ከፖሊሲ ግንዛቤ ጀምሮ የሚከናወኑ ተግባሮችን የመደገፍ፣ የምርምር እና የንግድ አካባቢዎችን የማጥናት እና በመንግሥት እና በግሉ ዘርፎች ምክክር የሚካሄድባቸውን ሰነዶችና መድረኩን እንዲሁም ሥልጠናዎችንና የአቅም ግንባታ ስራዎችን ማዘጋጀት በስፋት የሚከናወኑበት መሆኑንም ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በፕሮጀከቱ የተመረጡት እነዚህ ምርቶች በዋነኛነት ያሉባቸው ማነቆዎች ከተፈቱ፣ ምርቶቹን በጥራት እና በብዛት ለማምረት እና በተሻለ ሁኔታ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በሚያስችል ደረጃ /ስታንዳርድ/ ማምረት ከተቻለ፣ ትልቁ ሥራ የሚሆነው እነዚህን ምርቶች ለዓለም ገበያ የማስተዋወቅ ሥራ ይሆናል።

ከዚህ አንፃርም በዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶች ላይ በመሳተፍ ምርቶቹ እንዲታወቁ የማድረግ ስራዎችን ይሰራሉ ያሉት አቶ ደበበ ከዚህ አንጻር በሶስቱ ክልሎች 900 የምርቶቹ አምራቾች ተጠቃሚ የሚሆኑበት የፕሮጀክት እቅድ ተዘጋጅቷል ብለዋል። ከሥልጠና ጋር በተያያዘም በዋነኛነት በግዢ ዘርፉ ላይ የተሰማሩ እና ውሳኔ የሚሰጡ አካላት የስልጠና አቅማቸው እንዲጠነክር የማድረግ ሥራዎች እንደሚከናወኑም አስታውቀዋል።

በኃይሉ አበረ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You