
አዲስ አበባ፡- የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጁን በቀጣዮቹ 5 ዓመታት ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ።
የሆስፒታሉ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሮቮስት አቶ ዓለሙ ክብረት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኮሌጁ ከጥቂት አንጋፋ የጤና ተቋማት መካከል አንዱና በየዘመናቱ ለጤናው ዘርፍ የበኩሉን አስተዋፅዖ ሲያደርግ የቆየ ነው። ባለፈው ዓመት 100 ዓመት የሞላው የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ፣ አሁን ደግሞ በተለየ ሁኔታ እድሜውንና ስሙን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት የ10 ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድ አውጥቶ ለስኬቱ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
ኮሌጁን በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ለማደግም በሕክምናና በትምህርቱ ዘርፍ የሚሰጠውን አገልግሎት በየጊዜው በማስፋትና በማዘመን ላይ ነው። ከ13 ዓመታት በፊት በመሠረታዊነት ከሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት በተጨማሪ የሕክምና ሙያ ትምህርትንም እንዲሰጥ የተደረገው ሜዲካል ኮሌጁ፣ የማስተማር አገልግሎቱ ከጀመረ ወዲህ ለጤናው ዘርፍ በርካታ ብቁ የጤና ባለሙያዎችን እንዳበረከተ ጠቁመዋል።
ይህን አገልግሎቱን የበለጠ በማስፋት በየጊዜው በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ተማሪዎችን እየተቀበለና እያስተማረም ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል። ዘመናዊነትን መላበስን ጨምሮ ትኩረት ልንሰጥባቸው የሚገቡ የትኩረት አቅጣጫዎችን ለይተናል ያሉት አቶ ዓለሙ፣ በሕክምናውም ሆነ በትምህርቱ ዘርፍ እያገለገለው ያለው መላው ሠራተኛ ለተቋሙ እድገት የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የሜዲካል ኮሌጁ የድንገተኛና የጽኑ ሕሙማን ስፔሻሊስት ሐኪምና የሕክምና አገልግሎት ምክትል ፕሮቮስት ዶ/ር አንተነህ ምትኩ በበኩላቸው፣ የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ስሙንና እድሜውን የሚመጥን አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ተቋም መሆኑን አንስተዋል።
የሕክምና አገልግሎት ላይ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት የሚያግዙና ሥራን በጥራትና በቅልጥፍና ለማከናወን የሚያስችሉ የተለያዩ ሪፎርሞችን እየተገበረ እንደቆየም አመላክተዋል። እርሳቸው እንዳሉት፣ ሆስፒታል ኮሌጁ 39 የሚደርሱ የሕክምና ዘርፎች ሲኖሩት፣ በዓመት ለ500ሺ ያህል ሰዎች የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል።
በሕክምና ትምህርት ዘርፍም በዓመት እስከ 1500 ተማሪዎችን በሕክምና የመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ እስከ ሰብ ስፔሻሊቲ ድረስ እያስተማረ ሲሆን ይህን አገልግሎት ለመስጠት 2300 የሚደርሱ ሠራተኞች አሉት ብለዋል። ከእነዚህ ውስጥ 1400ው የጤና ባለሙያዎችና የሕክምና አገልግሎቱን የሚያግዙ ሠራተኞች መሆናውንም አብራርተዋል።
ኮሌጁ በሁሉም ዘርፎች የሚሰጠውን አገልግሎት በማስፋትና በማዘመን ጥራቱን የጠበቀና ጊዜውን የዋጀ ዘመናዊ አገልግሎት በመስጠት በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት የማደግ ርዕይ ሰንቆ እየሠራ ይገኛል።
ዮርዳኖስ ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ጥር 22/2016