በድሮው አዲስ ዘመን ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ አንባቢያኑ አንባቢ ብቻም ሳይሆኑ ተሳታፊም ነበሩ፡፡ ዛሬ ላይ ይህን ናፍቀን “ለምን?″ ብንል፤ ምናልባትም የቴክኖሎጂና የሚዲያውን መብዛት ሰበብ እናደርግ ይሆናል፤ ምክንያት ግን አይደለም፡፡ አውቶብሱን በእንቅልፍ ሰመመን፤ የመነጥሩ ጣጣ፤ ይድረስ ለ”ኮንዶም” ተጠቃሚዎች፤ ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ፤ ስሜን ሰረቀና ለፈገግታ … ልዩና የማይዘነጋ የአንባቢያን የሀሳብ ባሕር አለ፡፡ የዛሬው ዓምዳችንም ከእነዚሁ የአዲስ ዘመን ተሳታፊና አንባቢያን ደብዳቤዎች ላይ ያርፋል፡፡
አውቶብሱን በእንቅልፍ ሰመመን ሲነዳ
“ከጠጡ አይንዱ” የሚለው የማስጠንቀቂያ አባባል የቆየና በየአጋጣሚው የሚሰማ ጠቃሚ ማሳሰቢያ ነው፡፡
…
ሐምሌ 14 ቀን 1979 ዓ.ም ከጅማ ወደ አዲስ አበባ የተጓዘውን የጎን ቁጥር 768 የሆነውንና በልማድ “አይናፋር” በመባል የሚታወቀውን የአንበሳ አውቶብስ ያሽከረክሩ የነበሩት ሾፌር ይታይባቸው የነበረው አስጊ ሁኔታ ነው፡፡ ሾፌሩ ከሚዛን ጅማ ገብተው አዳር ሲሆን ማምሻውን ጠጥተው እንደነበርና በቂ እንቅልፍ አለማግኘታቸውን፤ ከብዙ ፈተና በኋላ በዕለቱ ወሊሶ ደርሰን ለዕረፍት በቆየንበት ቦታ ራሳቸው ሲናዘዙ ሰምቻለሁ፡፡ በጉዞ ላይ የእንቅልፍ ፍላጎት እያናወዛቸው በተደጋጋሚ ከአደጋ አፋፍ ላይ ሲያደርሱን ነገሩ ያሰጋቸው ረዳትና ተቆጣጣሪ ቀዝቃዛ ውሃ፣ ዙርባ ጫትና ሲጃራ ቢያቀርቡላቸውም ብዙ ሳይረዳቸው በመቅረቱ ተሳፋሪው በጭንቀት እንደተዋጠ ወሊሶ ሊደርስ ችሏል፡፡
ከሁሉም ይበልጥ የሚያሳዝነው ከተሳፋሪዎች መካከል በሹፌሩ ላይ ይታይ ስለነበረው ድካምና የእንቅልፍ ስሜት አንስተው ሲያሳስቡ እንዴት ተነካሁ በሚል እልህ መሪውን ከወዲያ ወዲህ እያሉት በበቀል ስሜት ተሳፋሪውን ማስጨነቃቸው ነው፡፡ በአጠቃላይ መታየት ያለበት በዕለቱ ደህና መግባታችን ሳይሆን ሾፌሮች ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡ ምክር ሊሰጣቸው ይገባል ነው፡፡
(አዲስ ዘመን፣ ሐምሌ 19 ቀን 1979 ዓ.ም)
የመነጥሩ ጣጣ
በኒውዮርክ ክፍለ ግዛት የሮችስተር ከተማ ነዋሪ የሆኑት ፔርሲ እርር ድብን ያደረገቻቸውን ባለቤታቸውን ጥላቸው ስትሔድ አሳደው ከመንገድ ላይ በጥይት ይገድሏታል፡፡ ከዚያም ወደ ዘመዶቻቸው ቤት ሔደው ፖሊስ ጠርተው እጃቸውን ለመስጠት ይወስናሉ፡፡ ፖሊሶቹ ሲደርሱ ባለቤታቸውን የገደሉ መሆኑን ቢያስታውቁም የገደሏት ሴት ግን ባለቤታቸው ሳትሆን ሌላ ሴት መሆኗ ታውቋል፡፡ ድርጊቱን ከፈጸሙ በኋላ ፔርሲ ከፖሊሶች ለቀረበላቸው ጥያቄ “…በጣም አዝናለሁ፡፡ መነፅሬን ቤት በመርሳቴ ልሳሳት ችያለሁ” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
(አዲስ ዘመን፣ የካቲት 10 ቀን 1975 ዓ.ም)
ይድረስ ለ”ኮንዶም” ተጠቃሚዎች
በተለያዩ አገሮች ቀሳፊው በሽታ ማለትም ኤድስ እየተስፋፋ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ ቢሆንም አንዳንድ ጠበብት እንደሚያስረዱት፤ ይሄንን ቀሳፊ በሽታ ለመከላከል ወንዶች “ኮንዶም” መጠቀም አለባቸው፡፡
ነገር ግን አንዳንድ ግለሰቦች የተጠቀሙበትን ኮንዶም የትም ስለሚጥሉት የነገ ሀገር ገንቢ የሆኑት ውድ ሕጻናት ይህን ኮንዶም በመጫወቻ መልክ እንደፊኛ በትንፋሻቸው በመንፋት ሲጫወቱ ተመልክቻለሁ፡፡ እውን ይህ ነገር በሕጻናቶች ላይ የጤና ችግር አይፈጥርምን?
ከተማሪ ደሳለኝ ተሾመ (ከፍቼ)
ከአዘጋጁ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያትቱ በርካታ ደብዳቤዎች እየደረሱኝ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ፤ ከአሥመራ፤ ከናዝሬት፤ ከድሬዳዋ… ፡፡ ይኸው አሁን ደግሞ ከፍቼ!
ስለ ኮንዶም አንስቼ ዶክተር ጥበበ የማነ ብርሃንን አነጋግሬ ነበር፡፡ ስለ አጠቃቀሙ የነገሩኝን ለጊዜው ልተወው፡፡ ግለሰቦች ከተጠቀሙ በኋላ ግን በተቻለ መጠን ሕጻናት ከማያገኙበት ቦታ መጣል አለባቸው፡፡
(አዲስ ዘመን፣ ታኅሣሥ 15 ቀን 1994 ዓ.ም)
ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ
*አዳምና ሔዋን ገላቸውን በጨርቅ ያልሸፈኑት ለምንድነው?
አብደላ መሐመድ (ከናዝሬት)
-ያኔ ጨርቅ ስላልተፈጠረ ነው፡፡
*በአርሲ ጠቅላይ ግዛት ያሉት አንዳንድ ከበርቴዎች አዲስ ልብስ ሲገዙ በቅቤ ሳያጥቡ አይለብሱም ለምንድነው?
ዘካርያስ መንበሩ (ከጊቢ)
-በልማድ የመጣ የሀብታምነት መገለጫ ምልክት ነው፡፡
( አዲስ ዘመን፣ ጥር 20 ቀን 1969 ዓ.ም)
“ስሜን ሰረቀ”
*የዛሬ ስድስት ዓመት የመሠረተ ትምህርት ፈተና ስፈትን ሸማኔው ሳምቢ “ጋሼ! ጋሼ!” እያለ ጣቱን ወደላይ ቀሰረ፡፡
ምንድነው ጋሼ ሳምቢ? ብለው፤ አጠገቡ ወደተቀመጠው ሰው ዞሮ “ይሄ ሰውዬ… ስሜን ሠረቀ” ብሎ በክፍሉ ውስጥ ያሉትን ሰዎች በሙሉ አሳቀ፡፡
ሳምቢ አልተሳሳተም ነበር፤ አጠገቡ ያለው ጎልማሳ ሰው የፈተናው መልስ መስሎት የሳምቢን ስም አብሮ ኮርጆ ኑሯል፡፡
(አዲስ ዘመን፣ ጥር 4 ቀን 1982 ዓ.ም)
ለፈገግታ
ሰውየው ጥንብዝ እያለ በመስከር ባለቤቱን ያሰለቸታል፡፡ ሚስት በዘመድ አዝማድ አስመክራ ስላልተሻለው ቢቸግራት ወደ ዶክተር ትሔድና “ዶክተር ባለቤቴ ሁል ጊዜ ማታ ማታ መጠጥ እየተጋተ ሙትት ብሎ እየገባ አስቸግሮኛል” ትለዋለች፡፡
ዶክተሩም ሙትት ብሎ ሲመጣ ጥሪኝ ብሎ ያሰናብታታል፡፡ ሰውየው እንደለመደው ምሽት ጠንብዞ በሸክም ይመጣና አልጋ ላይ ሲወድቅ ሚስት ስልክ ደውላ ሁኔታውን ለዶክተሩ ትነግራለች፡፡
ዶክተሩም ይመጡና ሲያዩት እውነትም ሕይወቱን የማያውቅ ሆኖ ያገኙታል፡፡ ወዲያው የሬሳ ሳጥን ያስመጡና ከነነፍሱ ተሸክመው በመክተት ይቆልፉበታል፡፡ እዚያው ከሳጥኑ ላይ አድሮ ንጋት ላይ ዶክተሩ ተመልሰው መጥተው ከሳጥኑ ውስጥ እንቅስቃሴ ሲጠባበቁ፤ ብንን ብሎ ቢወራጭ ሳጥኑ ሊያንቀሳቅሰው አልቻለም፡፡ በደንብ ሲያስብ በሬሳ ሳጥን መግባቱን ይገነዘባል፡፡ “ወይኔ ትላንትና ማታ ሞቻለሁ ማለት ነው” እያለ ከራሱ ጋር በማውራት ቀደም ብሎ የሞተውን ጓደኛውን ስም ያሰላስልና ጮክ ብሎ “ገብሬ ገብሬ” ሲል ዶክተሩ ወይ ይሉታል፡፡ እባክህ እኔም ትናንትና ማታ ሞቼ አንተ ወዳለህበት ስለመጣሁ እባክህን እዚህ አካባቢ መጠጥ ቤት ካለ ብታሳየኝ በማለት እየጮኸ ሲናገር “አዝናለሁ ባልሽ እንኳንስ በሕይወት እያለ ቢሞትም እንኳን መጠጥ ስለማይተው ልረዳሽ አልችልም” ብለው ዶክተሩ ወደቤታቸው ሔዱ፡፡
( አዲስ ዘመን፣ ኅዳር 13 ቀን 1989 ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም