ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሀገሪቱን በሁለንተናዊ መልኩ ወደ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ለማሻገር በመንግሥት በኩል ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው። በዚህም እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ከሀገር አልፈው የዓለም አቀፍ እውቅና ምንጭ እየሆኑ ነው፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች ሀገር ደምቃ እንድትታይ መልካም አጋጣሚዎችን እየፈጠሩ ነው።
አስቻጋሪ በሆኑ ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ውስጥ እየተተገበሩ ያሉ እነዚህ ስኬታማ የልማት ክንውኖች፤ መንግሥት ለልማት ያለውን ቁርጠኝነት ከማሳየት ባለፈ፤ በችግር ወቅት ሀገርን መታደግ የሚያስችል ስትራቴጂክ የአመራር አቅም/ብቃት ባለቤት እንደሆነ በተጨባጭ ማሰየት ያስቻሉ ተሞክሮዎች ናቸው ።
ከዛም በላይ ሕዝብና መንግሥት ተናብበው እና ተደማምጠው በሙሉ አቅማቸው መንቀሳቀስ ከቻሉ፤ እንደ ሀገር ያሉ ፀጋዎችን አውቆ በማልማት፤ የሀገርና የሕዝብን ነገዎች ብሩህ ማድረግ፤ የትናንት ስብራቶችን መጠገን እና መራመድ የሩቅ መንገድ ጉዞ እንዳልሆነ አመላካች ናቸው ።
በተለይም መንግሥት ከትናንት ጥቋቁር ታሪኮቻችን በመነሳት በምግብ እህል እራስን ለመቻል የጀመራቸው ስትራቴጂክ ጥረቶች፤ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆነው ስኬታማ የመሆናቸው እውነታ ለሕዝባችን አንድ የእፎይታ ምንጭ ከመሆን ባለፈ ፤ የዓለም አቀፍ እውቅና ምንጭ መሆን ከጀመሩ ውለው አድረዋል።
በምግብ እህል በተለይም በበጋ የስንዴ እርሻ እየተመዘገበ ያለው ስኬት፤ አሁን ላይ እንደ ሀገር ያጋጠመንን የድርቅ አደጋ መቋቋም የሚያስችል አቅም መፍጠር አስችሏል፤ እንደ ሀገር በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል የጀመርነው ጥረት አዲስ የታሪክ ትርክት ይዞ እየመጣ ስለመሆኑ አመላካች ሆኗል።
ሀገሪቱ ለስንዴ እርሻ ያላትን መሬት፣ የውሀ ሀብት፣ ቴክኖሎጂና የሰው ኃይል በማቀናጀት በጥቂት ዓመታት ውስጥ በመቶ ሚሊዮን ዶላር ከውጪ ይገባ የነበረውን የስንዴ ምርት በማስቀረት ብሎም እንደ ሀገር በዓለም አቀፍ የስንዴ ገበያ ውስጥ መግባት የሚያስችል ተስፋ ሰጭ ጅማሬ ላይ ትገኛለች ።
በገበታ ለሀገር እየተሠሩ ያሉ ሀገራዊ ሥራዎችም በጅምር ደረጃ የሚታዩ ቢሆኑም፤ በዚህ ደረጃ ያላቸው ውጤታማነት፤ እንደ ሀገር በምግብ እህል ራስን ከመቻል ባለፈ፤ ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ፤ በዚህም ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጭ አቅም ናቸው ።
ይህ ሀገራዊ ፀጋዎችን ለይቶ፤ ወቅቱን በሚዋጅ ውጤታማ ስትራቴጂ እየታገዘ ተግባራዊ በመሆን ላይ ያለው በምግብ እህል ራስን የመቻል ሀገራዊ ንቅናቄ፤ ከዚህ ትውልድ ባለፈ የሚመጡ ትውልዶችን ከምግብ እህል ጠባቂነት የሚታደግ፤ በረሀብ የጎደፈውን የትናንት ታሪካችንንም የሚያድስ ነው።
በመንግሥትና በመላው ሕዝባችን ቅንጅት ውጤታማ እየሆኑ ያሉ ሥራዎች፤ ሰላማዊ በሆነ ሀገራዊ ዓውድ ውስጥ መተግበር የሚያስችል ዕድል ቢያጋጥማቸው የውጤታማነታቸው ደረጃ ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል፤ በዓለም አቀፍ መድረኮችም የበለጠ ደምቀን እንድንታይ አቅሞች ይሆኑን እንደነበር ለመገመት የሚከብድ አይደለም።
በምግብ እህል ከጠባቂነት ወጥተን እራሳችንን እንድንችል የጀመርነው ሀገራዊ ጥረቶቻችን፤ አሁን ከደረሱበት በላይ ብዙ እርምጃዎችን መራመድ የሚችሉበት፤ እኛም እንደሀገር የበለጠ ቀና ብለን የምንሄድባቸውን የተሻሉ ዕድሎች መፍጠር የሚያስችሉ እንደሆኑም ይታመናል ።
ይህንን ሀገራዊ ተጨባጭ እውነታ በአግባቡ በመረዳት፤ የስኬቱ ባለ ራዕይ ለሆኑት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳሊያ መሸለሙ ተገቢ እና ተጠባቂ ጭምር ነው። ለጀመርነው በምግብ እህል ራስን የመቻል ሀገራዊ መነቃቃት ስኬት ትልቅ አቅም የሚሆን ነው።
ሽልማቱ በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ራዕይ፣ አመራር እና ቁርጠኝነት፣ ብሎም ፈጣን፣ ተለዋዋጭ እና ፈታኝ በሆነው ከባቢያዊ ሁኔታ በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል በተከተሉት ፈጠራዊ መፍትሔ ዕውቅና ለመስጠት የተበረከተ መሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ራዕይ ያከበረ ትጋት በአግባቡ ያገናዘበ ነው!።
አዲስ ዘመን ጥር 21/2016