ትምህርት – የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ልዩ ትኩረት

እንደ ማንኛውም ጊዜ፣ ዘንድሮም የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እዚህ፣ የአህጉሪቱ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ይካሄዳል። በመሆኑም፣ መዲናዋ አዲስ አበባም እንደ ምንጊዜውም እንግዶቿን ለመቀበል፣ ተቀብላም በጥሩ ሁኔታ ለማቆየት፤ አቆይታም በኋላም ለመሸኘት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ትገኛለች።

በዚህ በኅብረቱ ጽሕፈት ቤት በሚካሄደው 47ኛው (ከፌብሯሪ 17 – 18) የኅብረቱ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ በርካታ የአህጉሪቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች ተነስተው፣ ውይይት ተደርጎባቸውና ውሳኔ ተላልፎባቸው ወደ ተግባር ይቀየራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከእነዚህም መሠረታዊና ሕዝባዊ ጉዳዮች መካከል ፊት መሪው ትምህርት እና በትምህርት ዙሪያ የሚገኙ ጉዳዮች መሆናቸው ታውቋል።

የኅብረቱ (African Union) ድረ ገጽን ጨምሮ በርካታ መገናኛ ብዙኃን እንዳሰራጩት የዘንድሮው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ትኩረት ሰጥቶ የሚነጋገረው በቀዳሚነት አፍሪካ ተኮር ትምህርት እና ሥልጠና ላይ ሲሆን፣ የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው በአህጉሪቱ የሚሰጡ ትምህርቶችና ሥልጠናዎች አፍሪካን የሚመጥኑ፣ የአፍሪካን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘቡ፣ ለአፍሪካ ተስማሚ የሆኑና የአፍሪካን ችግሮች ሊፈቱ በሚችሉ መልኩ እንዲሰጡና አፍሪካዊ አስተሳሰብን የተረዳ ትውልድ መፍጠር ላይ ያተኮረ መሆኑ ነው።

እንደሚታወቀው አህጉረ አፍሪካ ሳይቸግራት የተቸገረች፤ ሳታጣ ያጣች አህጉር ነች። በመሆኑም ይሄው እስከ ዛሬ እዛው ነች። በተለይ ሠላምና ጦርነትን፣ የእርስ በርስ ግጭቶችንና በሠላም አብሮ መኖርን በተመለከተ ዛሬም በጣም በጣም እዛው ነች። ዘመናዊ እውቀትንም ሆነ ቴክኖሎጂን በተመለከተም እንደዛው።

ወደ ትምህርቱ ዓለም ስንመጣ አፍሪካን የምናገኛት በከፍተኛ ደረጃ ተጎድታ ነው። እንደ ዩኔስኮ (በ26/02/2020 ይፋ የተደረገ) ጥናት ከሆነ ከሳሐራ በታች ብቻ ባሉ ሀገራት እድሜያቸው ከ6 እስከ 11 ከሆኑ ልጆች መካከል ከአንድ አምስተኛ (1/5) በላይ የሆኑት የትምህርት ቤት ደጃፍን ያልረገጡ ናቸው። እድሜያቸው ከ12 እስከ 14 ከሆኑት መካከል ከ1/3 በላይ የሆኑትም እንደዛው። በአጠቃላይ አህጉሪቱ እድሜያቸው ከ15 እስከ 17 ከሆኑት መካከል ከ60% በላይ የሆኑት ምንም ዓይነት የትምህርት እድል የማያገኙ ወይም ያላገኙ፤ በአጠቃላይ በቀጣናው 64 ሚሊዮን በላይ (34 ሚሊዮን ልጃገረዶችን ጨምሮ) መማር የሚገባቸው ዜጎች ከትምህርት ውጪ ናቸው (በ2023 በተደረገ ጥናት መሠረት)።

ችግሩ በዚህ የማይበቃ መሆኑን ጠቅሰን ወደ ተነሳንበት እንመለስ።

በተለይ የራስን ማንነት መሠረት ባደረገ መልኩ ትውልድን ከመቅረፅና በእውቀትና ክሂሎት ማስታጠቅ ላይ ሲሠራባት የኖረው ሸፍጥ እራስ አስይዞ የሚያስጮህ ነው። በተለይ “እንግሊዝኛ ተናጋሪ“ እና “ፈረንሳይኛ ተናጋሪ″ ተብላ ለሁለት መከፈሏ፤ የየሀገራቱም ሥርዓተ ትምህርቶች ይሄንን ክፍፍል ተከትለው መቀረፃቸው አህጉሪቱን ዋጋ አስከፍሏት እዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ዘፍቀዋታል።

በተለይ “ፈረንሳይኛ ተናጋሪ“ በሚለው ምድብ ስር የተካተቱት ሀገራት ከማንነታቸው የመነቀል ያህል እስኪቆጠር ድረስ ፈረንሳይኛን ሲጋቱ ነው የኖሩት። ሙሉ የሥርዓተ ትምህርቱ ዝግጅት በፈረንሳዮች (ፈረንሳይ በሠለጠኑ አፍሪካውያን) ሲዘጋጅ ነው የኖረው። ይህ ምንን አስከተለ፤ እነ ማሊ እና የመሳሰሉት ፈረንሳይኛን ከብሔራዊ ቋንቋነት የመሰረዝ እርምጃን እንዲወሰድ ከበቂ በላይ ምክንያት ሆኗቸዋል።

በእነዚህ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሀገራት ውስጥ ብዙ ነገሮች ተበለሻሽተው የኖሩ ሲሆን፣ በተለይ ከትምህርት ጋር፣ በተለይ በተለይ ከእውቀትና ክሂሎት ጋር በተያያዘ ሲፈፀም የነበረው ግፍ ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም። ለእውቅናና ሽልማት ሳይቀር የሚታጩና የሚሸለሙት በፈረንሳይኛ ቋንቋ የፃፉ እንጂ በሀገራቸው ቋንቋ ለሕዝባቸው የደረሱቱ አይደሉም። “ጎሽ″ የሚባሉት በፈረንሳይኛ ያቀነቀኑ እንጂ በራሳቸው ቋንቋና ባሕል ያዜሙ ድምፃዊያን አልነበሩም። ታዲያ ከዚህ በላይ ምን በደል አለ፤ ምንስ ግፍ ይኖራል?

ከእነዚህ ሁሉ በደሎች በመነሳት ይመስላል የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ መሪ ቃል በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካን የመጠነ ትምህርትና ሥልጠና፤ ችግሮችን መቋቋምና ማሸነፍ የሚችል ሥርዓተ ትምህርትን በመገንባት የትምህርትን ተደራሽነት፣ ጥራት፣ አካታችነት፤ እንዲሁም ዘላቂነት እውን ማድረግ መሆኑን “Educating an Africa fit for the 21st century: building resilient education systems for increased access to inclusive, qualitative, lifelong and relevant learning for Africa.″ በማለት ያስቀመጠው።

የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበሩ ሙሳ ፋቂ “Our theme for the Year 2024 is devoted to pondering over an in-depth reform of education in Africa, with the prospect of training young people endowed with intellectual, scientific and ethical capacities to serve the transformation of our continent to make it a comfortable and productive living space” በማለት እንዳስቀመጡት፤ የዚህ ዓመት የኅብረቱ መሪዎች ጉባኤ መሪ ቃል በአህጉሪቱ ውስጥ ጥልቅ የሆነ የትምህርት ሪፎርም (ለውጥ) ማድረግ ላይ ያተኮረ፤ ይህም ከሥልጠናዎች ጀምሮ ወጣቱን ትውልድ በእውቀት፣ ሳይንሳዊ አስተሳሰብና ሥነምግባር አቅሙን በማጎልበት አህጉሪቱ እያደረገች ያለውን ሽግግር እንዲያግዝ ማድረግ ነው።

እንደ አሁኑ የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ (Moussa Faki Mahamat) ጠበቅ ያለ ንግግር አፍሪካ እንደ አህጉር ለመቀጠል ያሏት ሀብቶች ሁለት ሲሆኑ፣ እነሱም አንድነት እና ኅብረት (Unity and Solidarity) ናቸው። ያለ እነዚህ ሁለቱ መሠረታውያን አፍሪካ የትም ልትደርስ አትችልም። እንደየወቅቱ ሊቀመንበር አስተያየት አህጉሪቷ ዛሬ ላይ ከገጠሟት ፈታኝ ፈተናዎች ለመውጣት እነዚህ ሁለቱ ለአፍታም ቸልና “ለነገ″ ሊባሉ የሚችሉ ጉዳዮች አይደሉም።

ሙሳ 47ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ላይ በአፅንዖት እንዳስተላለፉት መልእክት ከሆነ፣ በአሁኑ ሰዓት አህጉሪቱ ወደ ተሻለ የእድገትና ብልፅግና እንድትሸጋገር፣ መቻቻል፣ መተባበር፣ በጋራ መልማት፣ የጋራ ሠላምና ፀጥታን ማስፈን፣ የሠለጠነ ዜጋ መፍጠር እና የመሳሰሉት ነባር እሴቶች እጅጉን ያስፈልጓታል። እንደ አህጉር፣ እነዚህን የራስ ማድረግ ካልተቻለ፤ የወጣቱን እምቅ እውቀትና ኃይል መጠቀም ካልተቻለ (#Youthcharter ይጎብኙ) ኅብረቱ የተመሠረተበትን 100ኛ ዓመት (1963) መሠረት አድርጎ ይደረስበታል የተባለው “አጀንዳ 2063″ የሚደረስበት አይሆንም።

እንደ ዘንድሮው የኅብረቱ የመወያያ አጀንዳ ቅደም ተከተል ከሆነ ቅድምና የተሰጠው ለትምህርት ሲሆን፤ ይህም፣ በተለይ ይህንን አጀንዳ እና የኅብረቱ መዋቅራዊ ሪፎርም እንዲሳካ ጨምሮ ለወጣቱ ማስተማርና ግልፅ ማድረግ፤ ፓንአፍሪካኒዝምን ጨምሮ ሙሉ ግንዛቤ እንዲኖረው ማስቻል ይገባል።

ኅብረቱ እንደማንኛውም የጉባኤ ዘመን (የኅብረቱ የ2021 መሪ ሃሳብ “የምንፈልገውን አፍሪካን ለመገንባት ሥነ-ጥበባት፣ ባሕል እና ቅርስ ምሰሶዎች ናቸው″ የሚል ነበር)፣ ዘንድሮም ከላይ የጠቀስነውን መሪ ሀሳብ ያነገበ ሲሆን፣ ለዚህም አባል ሀገራቱ በጉዳዩ ላይ በሚገባ መክረውና ዘክረው ወደ ተግባር ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያን ተሞክሮ አበርክቶ እንደሚታወቀው፣ ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ለአጠቃላይ አህጉረ-አፍሪካ ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ እንደ ነበረ በግልፅ የሚታወቅ ነገር ነው። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ሰነዶችን እንኳን ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንፈትሽ ስለ አጠቃላይ አፍሪካ፣ በተለይም ስለ አፍሪካ የትምህርት ሁኔታ በርካታ ጥናቶች ተካሂደው ነው የምናገኘው። ለአፍሪካ ወደ ፊት መራመድ፣ ከተለያዩ ችግሮች መላቀቅ፣ ሠላምና ፀጥታ፣ ወንድማማችነት፤ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብት ወዘተ ሁሉ በብዛት ተጠንቶ በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ክፍሎች (ቤተ መጽሐፍቶቹን ጨምሮ) ውስጥ ይገኛል። ይህ አህጉር አቀፍ ኢትዮጵያዊ እንቅስቃሴ መሐል ላይ የተቀዛቀዘ ቢመስልም አሁን አሁን መልሶ እያንሰራራ ያለ ስለ መሆኑ ቀጥለን የምንመለከታቸው ማስረጃዎች ማሳያ ናቸው።

በኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር (በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2021) ተደርጎ የነበረ አንድ ዓውደ ጥናት (Validation Workshop) የሚነግረን ዐቢይ ጉዳይ ቢኖር የዚህኑ ለአፍሪካ ችግሮች መፈታት አፍሪካዊቷ ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለው አስተዋፅዖ ሲሆን፣ አንዱም የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራምን እውን ማድረግን የተመለከተው ነው።

ከላይ በጠቀስነው ዓመት በትምህርት ሚኒስቴር ድረ-ገፅ ላይ “የትምህርት ሚኒስቴር በአፍሪካ ደረጃ የሚተገበረውን ሀገር አቀፍ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም መመሪያ እየገመገመ ይገኛል፡፡″ በሚለው ዘገባ ስር:-

1) በወርክሾፑ ሀገር አቀፍ የትምህርት ቤት የምገባ ፕሮግራም ውጤታማነት ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ መመሪያው መገምገሙ 2) መድረኩ በሀገር አቀፍ የትምህርት ቤት ምገባ መመሪያ ላይ ውይይት በማድረግ ግብዓት ለመሰብሰብ ያቀደ መሆኑ 3) የትምህርት ቤት ምገባ በትምህርት ቤቶች እንዲተገበር መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን እና መመሪያውንም ወጥ እና ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ 4) አጠቃላይ በአፍሪካ ደረጃ የሚተገበረውን ሀገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ መመሪያ ላይ ለተሳታፊዎች ማብራሪያ መሰጠቱ 5) የሀገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ መመሪያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ55ቱም የአፍሪካ ሀገራት ወጥነት ባለው መልኩ ለመተግበር የሚያስችል መሆኑ 6) የሀገር በቀል ትምህርት ቤት ምገባ የትምህርትን ተደራሽነትና ጥራት ለማሻሻል የአፍሪካ ሀገራት የትምህርት ሚኒስትሮች ቀጣናዊ መግባባት ላይ መድረሳቸው 7) ይህን በአፍሪካ ደረጃ የሚተገበረውን ሀገር አቀፍ የትምህርት ቤት ምገባ መመሪያ እንዲገመግሙ ከተመረጡ 16 የአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗ ተዘርዝሮ ይገኛል።

ከዚህ የምንገነዘባቸው በርካታ ቁም ነገሮች ቢኖሩም በዋናነት ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ ችግሮች መፍትሔዎችን ከማፈላለግ ባሻገር፣ በራሷ ተግብራ አዋጭ ሆኖ ያገኘችውን ሁሉ ለተቀሩት የአህጉሪቱ አባል አገራት ማካፈሉ ላይ ችላ ብላ የማታውቅ መሆኑን ነው።

ኢትዮጵያ ለየአፍሪካ ኅብረት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ኮሚሽነርነት በእጩነት አቅርባቸው የነበሩት ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በወቅቱ ባካሄዱት የምረጡኝ ቅስቀሳ (ዘመቻ) ወቅት በአመራር ጥበባቸው ለኅብረቱ የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ኮሚሽን እሴት እንደሚጨምሩ እምነታቸውን ሲገልፁ የነበሩት ፕሮፌሰሯ “በአፍሪካ አካታችና ጥራት ያለው ትምህርት ለማዳረስ እሠራለሁ፤ በትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን እሞላለሁ” ማለታቸውን፤ ዓለም የተለያዩ የአብዮት ደረጃዎችን በማለፍ በአሁኑ ወቅት የቴክኖሎጂ አብዮት ላይ እንደምትገኝ በማስረዳት አፍሪካም እኩል መሄድ እንዳለባት በአፅዕኖት ሲናገሩ የነበረ መሆኑን፤ ለዚህም የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ያላቸውን ፋይዳ በመዘርዘር በአፍሪካውያን ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሠሩ ማብራራታቸውን፤ በአፍሪካ አካታችና ጥራት ያለው ትምህርት እውን በማድረግ የአህጉሩን እምቅ የወጣት ሃብት መጠቀም ላይ የመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን መግለፃቸውን እዚህ ጋ በመጥቀስ የኢትዮጵያን ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ አቋም አጠናክሮ ማሳየት ይቻላል።

በአጠቃላይ፣ የእስከ ዛሬውን በደልና ግፍ ትተን በዛሬይቱ አፍሪካ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ብንመለከት በትምህርት ብቻም ሳይሆን በብዙ መልኩ ኋላ ቀርነት አለ። ለዚህ ችግር መቀረፍ ደግሞ፣ ማንንም እንደሚያስማማው፣ መፍትሔው እውቀት ነው። የእውቀት መገኛ መንገዱ ደግሞ ትምህርት እንጂ ሌላ አይደለም። ከዚህ አኳያ የአፍሪካ ኅብረት በዘንድሮው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ልዩ ትኩረቱን ትምህርት እና ሥልጠና ላይ በማድረግ ወጣቱን ለማብቃት መወሰኑ፤ የትምህርት ሥርዓቱም ፍፁም አፍሪካዊ መሠረት እንዲኖረውና የ21ኛዋ ክፍለ ዘመን አፍሪካን የመጠነ እንዲሆን ለመሥራት መነሳቱ፤ አባል አገራትም ይህንን ተግባራዊ ያደርጉ ዘንድ ከወዲሁ እያሳሰበ መሆኑ ሊያስመሰግነው ይገባል።

መልካም የመሪዎች ጉባኤ እንዲሆን እንመኛለን!!!

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You