አቶ ፋካንሰ ገመቹ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ
መንግሥት ከመቼው ጊዜ በላይ ለቱሪዝም ሴክተሩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ለዚህም ዋና ማሳያ የሚሆኑት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ክልሎች “ገበታ ለሀገር” በሚል መርሕ እየተገነቡም እየተመረቁም ያሉ ፕሮጀክቶችን ናቸው።
ከእነዚህ አንዱ በቅርቡ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመረቀው እና የገበታ ለሀገር አካል የሆነው የወንጪ ሐይቅን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። አዲስ ዘመንም በኦሮሚያ ክልል በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኘውን የወንጪ ሐይቅን አስመልክቶ እና በዞኑ ስላሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች ጋር ተያይዞ ያለውን ሁኔታ እንዲገልጹልን ከዞኑ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፋካንሰ ገመቹ ጋር ያካሔደውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- በዞኑ ዋና ዋና የቱሪዝም መዳረሻ ናቸው የሚባሉት መስሕቦች የትኞቹ ናቸው ?
አቶ ፈካንሰ፡- ዞናችን በቱሪዝም የታወቀ ነው። በእርግጥ ቱሪዝም ሲባል ጽንሰ ሐሳቡ ሰፊ ነው። ብዙ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ እንዲሁም ባሕላዊ እና ታሪካዊ፣ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ የሆኑ የቱሪዝም መስሕቦች አሉን። ከእነዚህ መካከል እንደዞናችን ለየት ብለው የሚታዩ ደግሞ ሦስት ትልልቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች ሲኖሩ፣ አንደኛው በቀርሳ ማሌማ በሚባል ወረዳ የሚገኘው አዳዲ ቤተክርስቲያን ነው።
አዳዲ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ቤተክርስቲያን ነው። አሠራሩ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ከሚገኙት ከእነላልይበላ ጋር የሚመሳሰል ሲሆን፣ ዋና ማሳያውም ከአንድ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራ ቤተ ክርስቲያን መሆኑ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የሚያመሳስላቸው በአንድ ዘመን የተሠሩ መሆናቸው ነው። ቤተ ክርስቲያኑ አስር ክፍሎች 24 መስኮቶች አሉት። ሙሉ በሙሉ የሚሰጠው አገልግሎት የእምነት ነው። እንደ ቱሪዝም መዳረሻ ስናየው ደግሞ ዋና የዞናችን የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ እያገለገለ ነው።
ሁለተኛው የቱሪስት መዳረሻ አዋሽ መልካ ቁንጥሬ ሲሆን ይህ ስፍራ በጣም ታዋቂም ነው። የሰው ቅሪት አካል የሚገኝበት የአርኪዮሎጂ ሳይት ነው። ይህ ቦታ እንደአፍሪካም ሲታይ ብቸኛው ክፍት የአፍሪካ ሙዚየም ተብሎ ይጠራል። ስፍራው ሙዚየም እና አራት ቤቶችም አሉት። አራቱም ቤቶች በአካባቢው የአኗኗር ስልት የተሠሩ ናቸው። ከእነዚህ ክፍሎች ውስጥ አንዱ የአፍሪካን ቅድመ የሰው ልጅ ታሪክ መረጃ የሚሰጥ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ለሚታወቁ አርኪዮሎጂስቶች ሙሉ መረጃ የሚሰጥ የመጀመሪያው ስፍራ ነው። በተጨማሪም የሰው ልጅ ከቅድመታሪኩ በፊት የሚጠቀምበት ከተለያየ ግብዓት የተሠራ ቁስ ያለበት ሲሆን፣ ሌላኛው ክፍል ደግሞ የሰውም የእንስሳትም አጥንት ያለበት ትልቅ ሙዚየም ነው።
ከእነዚህ መዳረሻዎች በተጨማሪ ወቅታዊ የሆኑ ፏፏቴዎች አሉ። ፏፏቴዎቹ መስከረም እና ጥቅምት አካባቢ አወራረዳቸው በጣም አስገራሚ እና ልዩ ውበት ያለው ነው። በጋ ሲገባ ግን በአወራረዳቸው እየቀነሱ የሚሄዱ ናቸው። እነዚህ ፏፏቴዎች በዞናችን አመያ ወረዳ ውስጥ በርከት ብለው ይገኛሉ።
ትንሽ ለየት የሚያደርገው ሌላው የዞናችን የቱሪስት መዳረሻ የሆነውና ብዙ ሥራም ያልተሠራበት በርካታ ዋሻዎች መኖራቸው ነው። ይሁንና በእነዚህ ዋሻዎች ዙሪያ እስካሁን ጥናት በአግባቡ አልተካሔደበትም። ለምሳሌ ከእነዚህ ዋሻዎች አንዱ አራሬ ዋሻ የሚባል ሲሆን፣ አንድ ግለሰብ መፀዳጃ ቤት ሲቆፍር የተገኘ ዋሻ ነው። ይህ ቦታ ቶሌ ወረዳ ውስጥ ባንቱ በምትባል ከተማ አካባቢ የሚገኝ ነው።
ከአዳዲ ማርያም ጋር ተያይዞ በርካታ ዋሻዎች አሉ። ለምሳሌ ቡርቂቱ የሚባል ዋሻ በዚያ ስፍራ ከሚገኙት መካከል ተጠቃሽ ነው። ሌላው ደግሞ ግብዝና የሚባል ዋሻ ነው። በዋሻ በኩል ዞናችን የሚታወቀው ወንጪ ውስጥ በሚገኘው ስላሴ ዋሻ ነው። በጥቅሉ ዞናችን በሰው ሠራሽም ሆነ በተፈጥሮ ዋሻ በዚህ ደረጃ የሚታወቅ ነው።
ሌላው ትክል ድንጋይ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ቦታውን ለማጥናት ይመቸው ዘንድ ከልሎትም ነበር። ትክል ድንጋዮቹ በእጅጉ የእድሜ ባለፀጋ የሆኑ ናቸው። የተለያየ ምልክት የተጻፈባቸውና የተለያየ ቅርጽም ያላቸው ናቸው። ይህ ትክል ድንጋይ ያለው በቀድሞው ደቡብ ክልል ሶዶ ዳቺ በምትባል ወረዳ አካባቢ ነው። ሶዶ ዳቺ የሚባለው ስፍራ በቀድሞው ደቡብ ክልል አዋሳኝ የሆነ ቦታ ነው። ከጢያ ከተማ ጋር የሚዋሰን ሲሆን፣ ጢያ ትክል ድንጋይም መገኛው እዛው አዋሳኙ ቦታ ነው። በእኛ ዞን ውስጥም ልክ እንደ ጢያ ትክል ድንጋይ ምልክቱ ያለበት አይነት ትክል ድንጋይ ይገኛል። ለምሳሌ ከምልክቶቹ መካከል ቦራቴ (ትራስ)፣ ጎራዴ ፣ ታቶ እና መሰል ናቸው።
ይሁንና ዋናው ቁም ነገር የትክል ድንጋዮቹ በዞናችን ውስጥ መኖር ብቻ አይደለም፤ ትልቁ እና አሳሳቢው ነገር ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑ ነው። እነዚህ በአርሶ አደሩ ማሳ ውስጥ ያሉ ትክል ድንጋዮች ጉዳት እየደረሰባቸው ነው። ትክል ድንጋዮቹ ማንም በፈለገው ሰዓት ለተለያየ አገልግሎት ሊያውል የሚችል አይነት ሁኔታ ውስጥ ናቸው። እንዲህ አይነቶቹ ብዙ ጥንቃቄ የሚያሻቸው የሀገር ቅርሶች ሲሆኑ፣ በርከት ያለ ጥናት ቢካሔድባቸው ተጨማሪ መረጃና የሚያስገኙም ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ትክል ድንጋዮቹ በትክክል እየደረሰባቸው ያለው ጉዳት ምንድን ነው? ኃላፊነቱንስ የሚወስደው አካል ማን ነው?
አቶ ፈካንሰ፡- ትክል ድንጋዮቹ ከሚገኙባቸው አንዱ ቶሌ ወረዳ ሃርሙፎሶሌ ቀበሌ ውስጥ ነው። ድንጋዮቹ የተለያየ ቅርጽና ቁመት ያላቸው ናቸው። ይሁንና ትክል ድንጋዮቹ ያሉበት ወይም የተተከሉበት ቦታ የግለሰብ መሬት ነው። ግለሰብ ደግሞ ቦታውን ለእርሻም ለግጦሽም ይፈልገዋል። ወረዳው ደግሞ ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመት ውስጥ በፀጥታ ሁኔታው ችግር የተነሳ ወደስፍራው ሰው ሔዶ መሥራት አልቻለም።
ብዙ ጊዜ ወደስፍራው ስልክ በመደወል ስለትክል ድንጋዮቹ እከታተላለሁ። ይህንን የማደርገው ኃላፊነት ስላለብኝ ነው። ክትትል የሚያስፈልግበት አንዱ ምክንያት አንዳንዴ አርሶ አደሩ ትክል ድንጋዮቹን ከማሳው ውስጥ በማውጣት ዳር ላይ ሊያስቀምጥ ስለሚችል ነው። እንዲሁም ደግሞ እያረሱ ባለበት ጊዜም ጉዳት እያደረሱበት ነው።
በእርግጥ እስካሁን የተሰበረ የለም፤ ነገር ግን ወደፊት በዚህ አይነት አካሔድ ምን ሊያጋጥም እንደሚችል አይታወቅም። የእኛም ክትትል ከዚህ ስጋት የተነሳ ስለሆነ የምንፈልገው ትኩረት እንዲሰጠው ነው። ነገ አርሶ አደሩ ሊሰብረውና ለተለያየ አገልግሎት ሊያውለው ይችላል። ስለዚህ አርሶ አደሩም ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል። በእርግጥ ቅርስ የሚመዘገብበት የራሱ የሆነ ቅጽ አለው። በዚያ ላይ መዝግበው እና ኃላፊነቱን ሰጥተን ወጥተዋል።
አንዳንዱን ደግሞ እዛው ባለበት አምስት ያህል ቆርቆሮ ዙሪያውን ያጠርንበት አለ። ከዚህ ባሻገር የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በትክል ድንጋይ እንደቱሪዝም መዳረሻ ብቻ ሳይሆን እንደ ምርምር ማዕከልም ሆኖ የሚያገልግል አቅም ያለው ዞን ነው ማለት ይቻላል። ትክል ድንጋዩ በቁጥር ብዙ ነው። ለምሳሌ ቶሌ ወረዳ ውስጥም ሶዶ ደጬ ውስጥ ያለው በርከት ያለ ነው።
ይሁንና የፀጥታ ጉዳይ ሲታይ አሁን ካሉ ዘርፎች ውስጥ በጣም ጥንቃቄ የሚፈልገው ዘርፍ የቱሪዝም ዘርፍ እንደመሆኑ በፀጥታው ጉዳይ ትኩረት ቢሰጠው መልካም ነው። በተለይ የውጭ አገር ቱሪስቶች ፍሰት የቀድሞውን ያህል አይደለም። አልፎ አልፎ ቢመጡም እምብዛም ምቾት አይሰማቸውም። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ ዞናችን እንደክልልም ሆነ እንደ ሀገር አቀፍ ታዋቂ የቱሪዝም መዳረሻነቱ በብዙ ተጠቃሚ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው የወንጪ ሐይቅ በዞኑ ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በምን ያህል ደረጃ ያሳልጠዋል ተብሎ ይጠበቃል?
አቶ ፈካንሰ፡- የወንጪ ሐይቅ በዓለም አቀፍ ደረጃም እኤአ በ2021 ወርልድ ቤስት ቱሪስት ቪሌጅ ተብሎ የተሰየመ የሀገር ሀብት ነው።
በመሠረተ ልማት በኩል ሲታይ ዋናው የቱሪስት መዳረሻ ሀብቱ መኖሩ ብቻ ሳይሆን ያለንን ሀብት ማስተዋወቅ ሲቻልም ጭምር ነው። ቀደም ሲል ዘርፉ እንደ አነስተኛ እና ተፈላጊ እንዳልሆነ ይታይ ነበር። ዘርፉን እንዲመሩ እድሉ የሚሰጣቸው አመራሮችም የቅጣት ቦታ ያህል አድርገው ይቆጥሩትም እንደነበር ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት ግን መንግሥትም ለዘርፉ የሰጠውን ያህል ትኩረት ለማንም አልሰጠም። ሰው ግብርና፣ የበጋና የመስኖ ስንዴ ይበል እንጅ ለቱሪዝም ዘርፉ የተሰጠው ብልጫ ያለው ነው ባይ ነኝ።
ከዚህ አኳያ ኅብረተሰቡ አካባቢም ያለው አመለካከት ይቀየር ዘንድ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ ሲሆን፣ ይህም ሥራ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ አካባቢዎች ላይ የውስጥ ለውስጥ መንገድ በራሱ በኅብረተሰቡ ተነሳሽነት ለመሥራት የሚያስችል ነው። ዋናው ችግር የመሠረተ ልማት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ መንገድ ዋናው ነው። የምንከተለው ፍልስፍና ማኅበረሰቡን መሠረት ያደረገ ኢኮቱሪዝም ነው። ይህ በአግባቡ ከተሠራ፣ ለወጣቱ የሥራ እድል መፍጠር ከቻለ እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ከጠቀመ፤ ራሱ ሕዝቡ አገልግሎቱን ሲያይ ሀብቱን ወደመጠበቅ እና መንከባከብ ይሔዳል። ያንን ካላደረገ ግን መጎዳቱ አይቀርም።
በእኛ በኩል ወደ 78 የሚሆኑ የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ ማፒንግ አድርገን ከመሬት አስተዳደር ጋር በመሆን የባለቤትነት ወረቀት ወስደናል። ይህ ቀደም ሲል ያልተለመደ ነው። አሁን ማንም የአባቴ፣ ቅድመ አያቴ መሬት ነው ብሎ ማሰብ አይችልም። እኛ በአሁኑ ወቅት የማኅበረሰብ ተሳትፎ ላይ አመያ እና ሰደንሶዶ ወረዳ ላይ በብዙ ሠርተናል። ከዚህ የተነሳ ወደ 78 የሚሆኑ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ላይ የባለቤትነት ወረቀት ይዘናል። እንዲህ ሲባል የቱሪዝም ቦታዎችን ብቻ ሳይሆን የተከበሩ የሚባሉ ቦታዎች ጭምር ነው።
ይሁን እና እንደ ወንጪ መሠረተ ልማቱ ተሟልቶለት ባይሆንም በእኛ አቅም መሥራት ያለብንን ነገር ሠርተናል ብዬ ብዙ መናገር አልችልም። የጀመርናቸው ነገሮች ግን አሉ። ነገር ግን ወደ ወረዳ አካባቢ በሚኬድበት ጊዜ ከፀጥታው ችግር የተነሳ የምንቀሳቀሰው አንዳንዴ በእጀባም ጭምር ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዞኑ ውስጥ ያሉትን የቱሪዝም መዳረሻዎች በአግባቡ ለመስሕብነት ይበቁ ዘንድ ከዞኑ ባሻገር በክልል ደረጃም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ ፈካንሰ፡- የቱሪዝም ባለድርሻ የሚባለው ሁሉም ሴክተርና ግለሰብም ጭምር ነው። ሚዲያም እንዲሁ በባለድርሻ ነው። በእርግጥ ሚዲያው የሚቀረው ነገር ቢኖረውም የራሱን ሥራ እየሠራ ነው። ለዚህ ምክንያቱ እኛ ዞን ያለው የቱሪዝም መዳረሻን ሰው ማወቅ የቻለው ሚዲያውም በሠራው ሥራ እንጂ እኛ እየደወልን ስለነገርን አይደለም።
በመንግሥት በኩል ያለበት ድርሻ ብዬ የምለው ለዘርፉ ትኩረት መስጠት ነው፤ ይህን ደግሞ እያደረገው ይገኛል። መንግሥት ከአምስቱ ምሰሶዎች ውስጥ ቱሪዝም አንዱ ነው ብሎ ሪፎርም ሠርቷል። በእርግጥ ዘርፉ መሠረተ ልማት እንደ ውሃ እና መንገድ ያስፈልገዋል። ይህ ደግሞ የሚሠራው በመንግሥት እንጂ በኅብረተሰብ አይደለም፤ ኅብረተሰቡ ደግሞ በተለይ ድርሻው የሆነው አካባቢውን ጠብቆ ሠላማዊ በማድረጉ በኩል መሥራት ይጠበቅበታል።
ለምሳሌ በቅርቡ ለምረቃ የበቃው የወንጪ አካባቢ አካባቢውን ጠብቆ ለዚህ ያበቃ ኅብረተሰብ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል። አካባቢውን መንጥሮ ለግብርና ሥራ ለማዋል ባለመነሳሳቱም ሊመሰገን ይገባል፡። አካባቢውን ጠብቆ ለዚህ አይነት መስሕብ እንዲበቃ ማድረግ ችሏልና። ኅብረተሰቡ አገር በቀል የሆኑ ትልልቅ ዛፎችን “ለከሰል ይጠቅመኛል” ብሎ አክስሎ ሸጦ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ወንጪን በዚህ አይነት ሁኔታ ላናገኛት እንችል ነበር።
አንዳንድ ቦታ ግን አካባቢያቸውን ያለእውቀት የሚያጠፉና ያጠፉ አሉ። እነርሱ ያንን ያደረጉት በእውቀት እጥረት የተነሳ ሊሆን ሰለሚችል ኅብረተሰቡን መውቀስ ከባድ ነው። ሕዝቡ ዛሬ አደራጅተነው የዚህን አካባቢ መንገድ ማውጣት አለብህ ብንለው ያለምንም ማቅማማት ያንን የሚፈጽም ነው። በዚህ ምንም ችግር የለበትም። ስለዚህ ለሕዝቡ በመጀመሪያ መረዳት እንዲኖረው ግንዛቤ መስጠት ነው፡። በእርግጥ አንዳንድ ቦታ በተለይም እንደወንጪ አይነት ቦታዎችን ላይ ለጉብኝት የሚመጡ ፈረንጆችን እያዩ ስላደጉ የቱሪዝም ግንዛቤው ይኖራቸዋል። በዞናችን ወደሌላ ወረዳ ላይ ያለው መዳረሻ ላይ ግን የቱሪዝም ጽንሰ ሐሳቡን በራሱ አያውቁምና ግንዛቤው ሊፈጠርላቸው የሚገባ ነው።
ከዚህ ቀደም እኔ በዘርፉ ኤክስፐርት ሆኜ በሠራሁባቸው ጊዜያት ለዘርፉ የነበረው ተቀባይነት ያን ያህል ነበር። በዘርፉ አመራር የነበሩትም የተገባቸውን ያህል አልሠሩበትም። ነገር ግን ዘርፉ ብዙ የሚስብና የሚሠራ ነገር ያለው መሆኑ የሚታወቅ ነው።
ቱሪዝም ጭስ አልባ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ስለመሆኑ ብዙ ተብሎለታል። ስለሆነም በኢኮኖሚ ውስጥ የራሱ የሆነ ድርሻ ይኖረዋል። ከዚህ ጎን ለጎን የሥራ ዕድልም ይፈጥራል። በሌሎች ሀገራት ቱሪዝምን እንደ ሀብት ቆጥሮ ለ24 ሰዓት ሲያስተዋውቀው ይታያል። በእኛ ሚዲያ ግን ምን የመሳሰለ የቱሪዝም ሀብት ሀገራችን እያላት በአግባቡ ማስተዋወቅ ሲገባው ምናልባት ከቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል ለዜና መዳረሻ ይሆን ዘንድ ብልጭ ከማድረግ የዘለለ ነገር እምብዛም አይታይም። ጥልቅ የሆነ የማስተዋወቅ ሥራ ላይ ገና ብዙ መሥራት ይቀረናል የሚል አስተያየት አለኝ። በየሚዲያው ትኩረት ተሰጥቶበት ቢተዋወቅ ባለሃብትም በዘርፉ ልማት ላይ ይሰማራል።
አዲስ ዘመን፡- የወንጪ ሐይቅ በቅርቡ ተመርቆ ሥራ መጀመሩ ይታወቃል፤ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ምን አይነት የቱሪስት ፍሰት ነበረው?
አቶ ፈካንሰ፡- አንድ ትልቅ ችግር ነው የሚባለው ከቱሪስት የተገኘውን ገቢ እንዴት ነው የሚለካው የሚለውን ስናይ አንዳንድ ቱሪስት ሀገራችን ኢትዮጵያ መጥቶ ገብተው እስከተመለሱበት ድረስ ያለው ምን ይመስላል የሚለውን ለመለየት እንደ ሀገር አቀፍ ወጥ የሆነ ስሌት የለም። አንድ የውጭ አገር ዜጋ ሀገር ውስጥ መጥቶ አንድ ቦታ ደርሶ ለመመለስ የሚያወጣው ገንዘብ ይኖራል። እንደ ሀገር ግን ከአየር መንገዳችን ጀምሮ መዳረሻው ቦታ ደርሶ ተመልሶ ደግሞ ሒልተን ወይም ኢሊሌ ሆቴል አርፎ ሲሄድ የገንዘብ ዝውውሩ የሚለካው በዚህ ሁሉ ውስጥ ነው። ለቱሪዝም ብቻ ብሎ ይዞ የመጣውን ገንዘብ የሚገመተው በእኛ ገበያ ውስጥ የተዘዋወረው ስንት ነው? ተብሎ ነው።
እኛ ዘንድ ያለው ቁጥር አይተን የማናውቀው ነው ማለት ብር ገቢ ነው። ወንጪ ከተመረቀ ጀምሮ ከ20 ሺ 500 ከሚሆነው የሀገር ውስጥ ጎብኚ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ሰብስበናል። ወንጪን በሚመለከት የሳምንቱ መዳረሻ ቅዳሜ እና እሑድ ላይ መግቢያ ላይ ብቻ ከ200 ሺ እስከ 500 ሺ እያስገባ ይገኛል። አንድ ጎብኚ ወደ ውስጥ ገብቶ ደግሞ ፈረሱን፣ መርከቡን በመጠቀም ሲዝናና ሌላ ገቢ ይሆናል። ይህ ወንጪ ከመመረቁ ሁለት ሳምንት አስቀድሞ የነበረ ገቢ ነው። ከተመረቀ በኋላ ደግሞ የዚህን አምስት ስድስት እጥፍ ይሆናል ብለን እናምናለን።
አዋሽ መልካ ቁንጥሬን በተመለከተ ባለፈው እኛ ከዩኔስኮ ኤክስፐርቶች ጋር ነበርን። ስለ መልካ ቁንጥሬ የተደራጀ መረጃ ሰጥተናቸዋል። እሱን አይተው ለጉዳዩ እውቅና ለመስጠት ነው የመጡት። አዋሽ መልካ ቁንጥሬ በዩኔስኮ የመመዝገቡ ሁኔታ በቅርቡ ለሀገራችን ሰበር ብሥራት ይሆናል ብለን እናስባለን። ከዚህ ባሻገር ወደአዳዲ ማርያም የውጭ አገር ጎብኚዎች በብዛት መጥተው የሚጎበኙት አንዱ መዳረሻችን ነው። የሀገር ውስጡን ቱሪስት ከተመለከትን ደግሞ ኅዳር 25 ቀን የሚመጣው ብቻ ቁጥሩ በርካታ ስለሆነ አይታወቅም።
በእርግጥ እኛ በሀገር ውስጥ ጎብኚ ምንም ችግር የለብንም። በሳምንቱ መጨረሻ ቀርቶ በአዘቦቱ ቀን መተላለፊያም የለውም። መንግሥት በወንጪ አካባቢ የሠራው ሥራ በጣም ላቅ ያለ ነው።
በዞናችን በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመርቆ ሥራ የጀመረው ወንጪ በትንሹ አንድ ሺ 943 የሚሆን የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። በአካባቢው ያሉ ወጣቶችን አደራጅተን የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። ሌላው የሥራ ዕድል መፍጠር ብቻ ሳይሆን የኅብረተሰቡ የአኗኗር ዘይቤ በራሱ እንዲቀየር አድርጓል። ይህንን ማምጣት የቻለው ቱሪዝሙ ነው።
ወንጪን እንደ ዞን መግለጽ ማለት ወንጪን ማሳነስ እንዳይሆንብኝ እሰጋለሁና እንደ ሀገር ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ ነው። ከዚህ ቀደም ወንጪ የአፍሪካ ሲውዘርላንድ ብለን የምንጠራት አካባቢ ናት። አንዳንዶች ደግሞ በተለያየ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ኢስታንቡል ይሏታል። በእኔ አተያይ ከሁለቱም ዓለም አቀፍ ቦታዎች ወንጪ ይበልጣል። ምናልባትም ሀገራቱ የገንዘብ ችግር ስለሌለባቸው ሰው ሠራሽ ማሳመሪያ አድርገው አሳመሩት እንጂ ልክ እንደ ወንጪ ተፈጥሯዊ ውበት የተላበሰ ቦታ አይደለም። እኛ ደግሞ ተፈጥሮ በዛ መልኩ የለገሰችን ነን። ይሁንና ለአሁኑ ገንዘብ በእጃችን ስለሌለ የዚያን ያህል መዋዕለ ንዋይ ገና አላፈሰስንበትም። በጥቅሉ ግን የወንጪን ውበት አሁን ለመግለጽ በጣም ከባድ ነው። እኔ መንግሥት ለቱሪዝም በዚህ መልኩ ትኩረት በሰጠበት በዚህ ዘመን እዚህ ወንጪ አካባቢ በመገኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። በወንጪ አካባቢ ቀንና ማታ ሳንል ስንሠራ የነበረው ለሁለት ዓመት ያህል ነው።
እንደ ዞንም ወጣቶችን ከማደራጀት ይልቅ ወደ 700 ሺ የሚሆን ብር አውጥተን 36 ያህል ሳይክል ገዝተንላቸዋል። ይህን ያደረግነው በአንድ በኩል የሥራ ዕድል በሌላ በኩል ደግሞ ቀጣይነት ያለው ፕሮጀክት ለምሳሌ የቱሉ ቦሎ ቡድን እንደ ኢትዮጵያ ሆነ እንደ አፍሪካም እየተወዳደረ ያለ ቡድን ነው። ከዚህ የወንጪ ደንዲ ባይስክል ቡድን ፕሮጀክት ለማድረግ እየሠራን ነው። በእርግጥ የቤት ሥራችን ከእኛም ከፍ ያለ ነው፤ እኛ የምንሠራው እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ወንጪን የት ለማድረስ አቅዳችኋል?
አቶ ፈካንሰ፡- ዞናችንን ኦሮሚያ ላይ ሆነው ሲያስቡ በአንድ በኩል በአዋሳኙ አካባቢ ምክንያት ይቆጠር የነበረው እንደ ደቡብ ነው። የዞኑ የኋላ ታሪክ ጉራጌ እና ጨቦም ነበር። ይህ ዞን በሀገሩ የሚኮራ እና ለሀገራቸው ሲሉ ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች የፈለቀበት ነው።
በጥቅሉ እኛ አሁን እየሠራን ያለነው ወንጪ ቱሪዝም ሆኖ ቱሪስትን አምጥቷል። ይህ የቱሪዝም ዘርፉ ድርሻ ነው። የባሕሉ ድርሻስ? ባሕሉን ወደኢኮኖሚ እንዴት እንቀይር የሚለውን ገና ነው። ስለዚህ እቅዳችን የኦሮሞ አልባሳትና ባሕላዊ እቃውን እና መገለጫውን የያዘ አንድ ጋለሪ በማቋቋም ያንን ለቱሪስት ማሳየት ነው። ዓመትን ጠብቆ ፌስቲቫል ማዘጋጀትና ወጥቶ መጨፈር ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዘርፍ እንዲሆን ባሕላችንን እንዴት መሸጥ አለብን የሚለውን እንደ ፕሮጀክት ወንጪ ላይ ይዘናል። ስለዚህ የወንጪ ፕሮጀክት በሂደት ያደገ የሚሄድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
አቶ ፈካንሰ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም