ተሠርተው ካላለቁ ፈርሰው ቢያልቁ!

አንዳንድ ሙያዊ ነገሮች ለተራው ዜጋ ግልጽ አይሆኑም። ከእነዚህ ሙያዊ ነገሮች በተደጋጋሚ ጥያቄ የሚፈጥርብኝ የመንገዶች ግንባታ ነገር ነው። አንዳንድ መንገዶች ሲፈርሱ ሳይ በተሻለ ጥራት በአዲስ መልክ ሊሠሩ ነው ብዬ አስባለሁ። ከዛሬ ነገ የሚያልቁበትን ጊዜ እየጠበቅኩ የተቆፋፈሩ መንገዶችን በተስፋ አልፋለሁ። ምክንያቱም በታዳጊ ሀገር ውስጥ የተሻለ ነገር ለማግኘት የግድ ዋጋ መከፈል አለበት።

እዚህ ላይ ታዲያ በተደጋጋሚ የምታዘበው ነገር ተሠርተው አለማለቃቸውን ሳይሆን ፈርሰው አለማለቃቸውን ነው። የመጀመሪያው ዙር ማፍረስ የሥራው ባሕሪ ነው ብዬ አልፈዋለሁ። ከዚያ የሆነ ነገር ሲነጠፍበት ወይም ሲለብስ አየዋለሁ። ከቀናት ወይም ሳምንታት በኋላ ደግሞ ያ የተነጠፈው ወይም የለበሰው ነገር ሲፈርስ ይታያል። እንደገና ይቆፈራል። አሁንም ሌላ ጊዜ የተቆፈረው ነገር የሆነ ነገር ይሠራበታል። በቃ ተሠርቶ ሊያልቅ ነው ሲባል እንደገና ደግሞ ይፈርሳል። በዚህ የመሥራትና የማፍረስ መፈራረቅ ውስጥ መንገደኛ እየተጉላላ ነው። ይሄኔ ነው እንግዲህ ተሠርቶ ማለቁ ባይሳካ እንኳን ፈርሶ ማለቁን የምንመኘው። ምክንያቱም ቢያንስ በአቧራው ላይ እንኳን ለመሄድ ፈርሶ ማለቅ አለበት።

እንደዚያ የሚያደርጉበት ምክንያት ይኖራቸው ይሆናል። ምናልባትም በተደጋጋሚ የዲዛይን ስህተት እያጋጠማቸው ይሆናል። ወይም መሠራት በሌለበት መንገድ ስለተሠራ እንደገና አፍርሱት እየተባሉ ይሆናል። ይህን ሁሉ ግን ተራው ዜጋ ሊያውቀው አይችልም። ነዋሪው ለረጅም ጊዜ መጉላላቱን ብቻ ነው የሚያስብ። ስለዚህ እንዲህ አይነት የመንገድ ሥራዎች ሲሠሩ በቂ ጥናት ተደርጎ፣ መጀመሪያ ዲዛይኑ አልቆ፣ በቂ ክትትል እየተደረገበት መሆን አለበት።

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እንዲህ ይሆናል። ማፍረሱም ሆነ መሥራቱ ይቆምና በፈረሰበት ወይም ሥራው በተጀመረበት ይቆማል። እነዚያ አካፋና ዶማ ይዘው የሚታዩ ሠራተኞች፣ እነዚያ የሚቆፍሩ ተሽከርካሪ ማሽኖች ልክ ሥራ እንደጨረሱ ሁሉ ይጠፋሉ። ‹‹በቃ በዚሁ ሊቀር ነው!›› እያልን ስንጨናነቅ ከሳምንታት ወይም ወራት በኋላ ደግሞ ብቅ ይላሉ። በዚህ ሁሉ ክፍተት ውስጥ መንገደኛው እየተጉላላ፣ በተለይም አካል ጉዳተኞች እየተቸገሩ ነው።

እርግጥ ነው ሀገራችን ድሃ ናት። ነገሮች በታሰበው ልክ አይሄዱም። መንግሥትም ቢሆን በታሰበው ልክ ቢሄድለት አይጠላም። ሥራዎች የሚጓተቱት በሀገሪቱ የዕድገት ደረጃ ሁኔታ መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም ግን የክትትል ችግርም አለ። ለምሳሌ አንድ ሥራ ተቋራጭ የሆነ መንገድ ሲጀምር በተከተታይ ጊዜ ሊሠራ መሆን አለበት። በታሰበው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሊጨርስ መሆን አለበት። በተባለው ጊዜ ውስጥ ካልጨረሰ ወይም በመሐል ሥራውን የሚያቋርጥ ከሆነ መጠየቅ ሊለመድ ይገባል።

የአሁኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚመሰገንባቸው ነገሮች አንዱ የጀመረውን ፕሮጀክት በፍጥነት መጨረስ ነው፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ከታሰበው ጊዜ ቀድሞ በመጨረስም ነው። ከፕሮጀክቶች ሁሉ ግን የመንገድ ጥገናዎች ላይ አሁንም የመጓተት ችግር አለ። ለምሳሌ፤ እንደ ላምበረት ያሉ አገር አቋራጭ መናኸሪያዎች አካባቢ ያሉ መንገዶች አሁንም እንደፈራረሱ ናቸው። አንድ ክረምት ጨርሰው እነሆ አሁንም ሌላ የዝናብ ጊዜ ሊመጣ ነው። የተቆፈረው አቧራ በተሽከርካሪዎች ጎማ ሲነካ አካባቢውን አቧራ በአቧራ ያደርገዋል። ይህ ከሚሆን ሥራው የሚጀመርበት ጊዜ ሳይወሰን ማፍረሱ ባይቀድም ጥሩ ነበር።

አራት ኪሎ ከትምህርት ሚኒስቴር እስከ አራዳ ክፍለ ከተማ ድረስ ያለው የእግረኛ መንገድ መፍረስ ከጀመረ ቆይቷል። እስከ አሁን ግን በተደጋጋሚ ሲሠራና ሲፈርስ እንጂ ሲያልቅ አይታይም። ይቆፈራል፤ የሆነ ነገር ይደረግበታል፤ ከዚያ እንደገና ይቆፈራል። በመሐል ደግሞ ማፍረሱም መሥራቱም ይቆማል። እንዲህ እንዲህ እያለ የዝናብ ጊዜ ከመጣ አሁንም አስቸጋሪ ሆኖ ይቆያል ማለት ነው።

ይህ እንግዲህ የግንባታ ሂደት ስለሆነ መጓተት ነው ብለን እንለፈው፤ ቢያንስ የሆነ ጊዜ ያልቃል። ከዚህም በላይ ችግር የሚሆነው ግን አንዱ አካል ሠርቶ ሲሄድ ሌላው አካል አፍርሶ የሚተወው ነገር ነው። ይህ ለብዙ ዓመታት የቆየንበት መጥፎ ልማድ ነው። መንገድ ሠሪው አካል ሠርቶ ይሄዳል። ሌላው አካል ደግሞ የሚቀብረው ወይም የሚያነጥፈው ይኖረኛል በሚል አፍርሶ ይቀብራል። ለመዘርጋት የተቆፈረው ጉድጓድ ግን እንደ ነገሩ ለበስ ለበስ ተደርጎ ይተዋል። የእሱ ሥራ የተፈለገውን ነገር መዘርጋት ብቻ ነው። ለመዘርጋት አስፋልቱ ሲቆፈር የሚወጣው አፈር ግን ከዳርና ከዳር ተቆልሎ ይቀራል። ያ አፈር በበጋ አቧራው፣ በክረምት ጭቃው የአካባቢውን ገጽታ ያበላሻል።

ሌላው የምንታዘበው ደግሞ የጥራት ችግር ነው። ለምሳሌ ‹‹ቴራዞን›› የሚባለው የእግረኛ መንገድ ንጣፍ በብዙ ቦታዎች ላይ ሲያስቸግር ይታያል። የተነጠፈው ንጣፍ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ መነሳት ይጀምራል። ይህ ሲሆን በተለይም በዝናብ ወቅት በውስጡ ውሃ ይይዛል። በውስጡ የተጠራቀመው ውሃ ንጣፉን ከአንደኛው ጫፍ ሲረግጡት ውሃው ወደ ላይ ይረጫል። ይሄኔ በልብስ ላይ ወይም በሰውነት ላይ ያርፋል ማለት ነው። ስለለዚህ ብዙ ሰው እየተሳቀቀ ነው የሚረግጠው፤ ወይም ላለመንካት ዳር ዳር ሲል ከተሽከርካሪ ጋር ሊጋጭ ይችላል።

በዚሁ እግረ መንገድ ግን አንድ ትዝብት እንጨምር። አንዳንድ ቦታዎች ላይ የእግረኛ መንገዶች በተሽከርካሪ ይያዛሉ። ለምሳሌ፤ መገናኛ እስራኤል ኤምባሲ አካባቢ ያለው የታችኛው የእግረኛ መንገድ በተሽከርካሪዎች የተያዘ ነው። ሰዎች የሚሄዱት በዋናው አስፋልት ላይ ከተሽከርካሪ ጋር እየተጋፉ ነው። ይህ ደግሞ ለአደጋ ያጋልጣል ማለት ነው።

አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ የእግረኛ መንገዱ በግንባታ ምክንያት ይታጠራል። ይህ ሲሆን እግረኛ በዋናው አስፋልት ጥግ ጥግ በኩል ያልፋል። እዚህ ላይ ታዲያ የሚያጋጥመው ችግር ብዙ አሽከርካሪዎች የእግረኛ መሄጃው ላይ ተሽከርካሪ አቁመው ይጠፋሉ። ለምሳሌ፤ ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳ በሚወስደው መንገድ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ያለውን ልብ በሉ። እግረኛ የሚሄደው ከተሽከርካሪ ጋር እየተደበላለቀ ነው። የእግረኛ ማለፊያዋን ከጫፍ እስከ ጫፍ ተሽከርካሪ ይቆምበታል። ባለቤቶች በውስጡ አይታዩም። እነዚህ ባለመኪኖች ግን ቢያንስ ለንብረታቸው ደህንነት አይሰጉም?

በእንዲህ አይነት ድርጊቶች ላይ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል። በበዓል ወይም የሚመረቅ ነገር ሲኖር መንገድ ሲዘጋ ብቻ ነው ‹‹ለአጭር ጊዜም ሆነ ለረጅም ጊዜ ተሽከርካሪ ማቆም የተከለከለ ነው›› የሚል ክልከላ የምንሰማው። ተሽከርካሪ መቆም የሌለበት ቦታ ላይ መቼውንም ቢሆን ሊቆም አይገባም። በተለይም የእግረኛ መንገድ ዘግቶ መቆም ሊከለከል ይገባል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You