አሁን ላይ በሀገራችን ብዙ ያደሩ የቤት ሥራዎች ከመኖራቸው የተነሳ ዘላቂ ሠላም በማስፈን ልማትን በሁለንተናዊ መልኩ ለማስቀጠል የሚደረጉ ጥረቶች በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ስለመሆናቸው ተደጋግሞ የሚነሳ፤ በተጨባጭም የተጀመረውን ሀገራዊ የለውጥ ሂደት ክፉኛ እየጎዳ ስለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው ።
ሀገሪቱ ካላት የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ፤ ከዚያም በላይ በየዘመኑ ካስተናገደቻቸው መንግሥታት ባሕሪ፤ እንዲሁም በየዘመኑ ከነበረው የሰላም እጦት አንጻር፤ ችግሮች መኖራቸው የሚጠበቅ ቢሆንም፤ እንደ ሀገር እያስከፈሉን ያለው አላስፈላጊ ዋጋ ግን ከግምት በላይ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።
አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎችም እነዚህን በጊዜያቸው ተሠርተው ያላለቁ የቤት ሥራዎችን የጥፋት አጀንዳቸው ማማሟቂያ በማድረግ፤ አሁን ላይ ሕዝባችን አብዝቶ የሚሻውን፤ ብዙ ዋጋ የከፈለበትን እና እየከፈለበት ያለውን ሠላምና ልማት እውን እንዳይሆን ፤ በከፍተኛ መነቃቃት ለጀመረው ለውጥ ዋነኛዎቹ ፈተናዎች ሆነውበታል።
እነዚህን ችግሮቻችንን ለዘለቄታው ለመፍታት፤ መንግሥት ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በማቋቋም፤ መላው ሕዝብ አሉ በሚባሉ ችግሮች ዙሪያ በግልጽና በነፃነት ተመካክሮ የራሱን የመፍትሔ ሀሳቦች እንዲያስቀምጥ የጠራ አቅጣጫ አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ ነው ።
ኮሚሽኑን ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንዲዋቀር ከማድረግ ጀምሮ፤ ለስኬታማነቱ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን በማድረግ እንደ መንግሥት ያለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ረጅም ርቀቶችን ተጉዟል። እስካሁን እያደረጋቸው ያሉ ተጨባጭ ድጋፎችም ለኮሚሽኑ ተልዕኮ ውጤታማነት ትልቅ አቅም ስለመሆናቸው ተደጋግሞ በኮሚሽኑ በኩል እየተነገረ ይገኛል።
ኮሚሽኑም ወደ ሥራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ፤ ለችግሮቹ መፍትሔ የማፈላለጉ ተልዕኮ ከዛሬ አልፎ በመጪዎቹ ትውልዶች ዕጣ ፈንታ ላይ የሚኖረውን የማይተካ አስተዋፅዖ በአግባቡ በመረዳት በኃላፊነት መንፈስ እየተንቀሳቀሰ ነው። እስካሁን ባለው ሂደትም ተስፋ ሰጭ ሥራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑ የእለት ተእለት ሥራዎቹ ተጨባጭ ማሳያ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑ ከአማራና ትግራይ ክልሎች በስተቀር በክልል ደረጃ ምክክር ለማስጀመር የሚያስችለውን የዝግጅት ምዕራፍ/የተሳታፊዎች ልየታ አጠናቋል፤ በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር የተሳካ ውይይት በማድረግም የጋራ መግባባት ላይ ደርሷል ።
ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉምን ኢትዮጵያውያን የሃሳብና የአመለካከት ውክልና ያካተተ፤ የሃሳብ ብዝኃነትን በማስተናገድ በኢትዮጵያ ውስጥ ሀገራዊ መግባባትን ማምጣት የሚያስችል ዓላማ ያነገበ መሆኑ፤ ያደሩ የቤት ሥራዎቻችንን እንደ ትውልድ በኃላፊነት መንፈስ ሠርተን ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ የተሻለ ዕድል ይዞልን መጥቷል።
ይህንን እድል በመጠቀም ችግሮቻችንን ዘመኑን በሚዋጅ መንገድ/በውይይት ለዘለቄታው ለመፍታት የጀመርነው ጥረት ፤ ድህነትን ታሪክ አድርገን ለማለፍ እንደ ትውልድ የጀመርነውን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ትርክት ስኬታማ ለማድረግ ዋነኛ አቅም እንደሚሆን ይታመናል ።
በተለይም አሁን ላይ እንደ ሀገር ፈተና የሆነብንን የልዩነት ትርክቶች እና ትርክቶቹ እንደ ሀገር እያስከፈሉን ያለውን ያልተገባ ዋጋ በማስቀረት፤ የወል ትርክቶቻችን ትንሣኤ አግኝተው የመላው ሕዝባችን የዘመናት መሻት የሆነውን ብልጽግና እውን ለማድረግ የተጀመረውን መነቃቃት ለማስቀጠል ፋይዳውም ከፍያለ ነው ።
ከሁሉም በላይ መጪው ትውልድ ከትናንት ጎታች ጫናዎች ወጥቶ፤ ዛሬዎቹን በተሻለ መንገድ ተገንዝቦ፤ የራሱን ዕጣ ፈንታ በራሱ በመወሰን፤ ከራሱ አልፎ ለሀገሩ ተስፋ የሚሆንበትን መሠረት መጣል የሚያስችል ትልቅ መነቃቃት ነው!
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም