የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ቡሀሪ ባሳለፍነው ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ አገሪቱን ለመምራት ቃለ መሃላ ፈፅመዋል፡፡ በቃለ መሃላው ወቅት ምንም አይነት የተጋነነ ፕሮግራም እና የተጠሩ የአለም አገራት መሪዎች አልነበሩም። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ባለፈው ዓመት የናይጄሪያ መንግስት ካቢኔ የዴሞክራሲ ቀን ሲከበር እአአ 1993 ሰኔ 12 የአካዳሚ ሽልማት አሸናፊ የነበረውን ማኮ አቢኦላ ለማክበር እንዲውልና የቡሀሪም ቃለመሀላ ይህንን ቀን አስመልክቶ ያለምንም ግርግር እንዲከናወን በመወሰናቸው ነው፡፡ አቢኦላ በቀድሞ አምባገነን መሪ ኢብራሂም ባባንጊዳ እንዲታሰር ተደርጎ ማረሚያ ቤት ውስጥ እንዳለ ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል፡፡
እንደአልጀዚራ ዘገባ ምንም አይነት ግርግር ያልታየበት የቃለ መሀላ ፕሮግራም በተጨማሪምነት ቡሀሪ በቀጣይ አራት ዓመት ምን እንደሚጠበቅባቸው ያመላከተ ነበር፡፡ ባለፉት የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲወድቅ ያደረጉ፣ የአመራር ብቃታቸው የወረደ እና ለውጥ ያመጣ ስራ አለመስራታቸው ይጠቀሳል፡፡ በዝቅተኛ መንገድ ፕሮግራም ማዘጋጀት የተፈለገው እአአ 2023 ላይ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመልቀቅ ዝግጅት ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ተበራክተዋል፡፡ ይህንንም ጉዳይ ቡሀሪ በቅርቡ ተጠይቀው አምነዋል፡፡ ነገር ግን በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ምን ቃል ገብተው ነበር፡፡ በቅስቀሳው ወቅት ሙስናን ለማጥፋትና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማስተካከል እንዲሁም የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ ምን እሰራለሁ ብለው ነበር፡፡ በመጀመሪያ የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው በጉዳዮቹ ላይ ምን አከናውነዋል፡፡
ሙስና
ቡሀሪ ገና ከመመረጣቸው በሙስና የሚጠረጠሩ ባለስልጣናትን ማሳደድ ጀምረዋል፡፡ በተለይ በህዝብ አስተዳደር ላይ የነበሩ ሰዎች እንዲታሰሩ እያደረጉ ነው፡፡ በቅርቡ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ሳምቦ ዳሱኪ በጦር መሳሪያ ግዢ ስምምነት ሁለት ቢሊዮን ዶላር አጭበርብረዋል ተብለው ተከሰዋል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ በቡሀሪ ሁለተኛ የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ተቃዋሚዎቻቸው በሙስና በኩል ጥያቄ እንዳያነሱባቸው ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። በአሁን ወቅት ቡሀሪ በሙስና እንዲታሰሩ ዝርዝር ያወጡላቸውን ሰዎች በሙሉ በቁጥጥር ስር አውለዋል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ቡሀሪ የራሳቸውን ባለስልጣናት በአግባቡ እንዲጠየቁ ላያደርጉ ይችላሉ ብለው ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ቀዳማዊት እመቤት አሂሻ ቡሀሪ 16 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት የትንኝ መከላከያ አጎበር በማህበራዊ ኢንቨስትመንት ፕሮግራም ስም እንዲገዛ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን አጎበሩ የት እንደገባ አይታወቅም፡፡ ቀዳማዊ እመቤቷ ቃል በተገባው መሰረት አጎበሮቹ ለድሆች ሊሰራጭ ያልቻለው አካባቢዎቹ ምቹ ባለመሆናቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ዋናው ጉዳይ ቡሀሪ በጉዳዩ ላይ እጃቸው እንደነበረ አምነዋል፡፡ በቀጣይ አራት ዓመት ፕሬዚዳንቱ በመጀመሪያ ዘመናቸው የሰሩትን ስህተት ሊያርሙ ይችላሉ፡፡ በዋናነት ደግሞ ሙስናን በመከላከል ረገድ ሰፊ ስራ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ኢኮኖሚ
ናይጄሪያውያን በቡሀሪ የመጀመሪያው የፕሬዚዳንትነት ዘመን ኢኮኖሚያቸው ዝቅ ብሏል፡፡ ስልጣን ከያዙ ከአንድ ዓመት በኋላ የአገሪቱ ብሄራዊ ባንክ ኢኮኖሚው አደጋ ውስጥ መሆኑን ተናግሮ ነበር፡፡ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ባሳለፍነው ወር መጨረሻ ላይም አስተላልፏል፡፡
ዋነኛው ችግር ቡሀሪ ኢኮኖሚውን ለማስፋት ቃል ቢገቡም አሁንም የአገሪቱ ኢኮኖሚ የተመሰረተው በነዳጅ ገቢ ላይ ነው፡፡ ለናይጄሪያ በአሁን ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው እየቀነሰ የመጣውን ነዳጅ ኢኮኖሚያቸውን ይበልጥ እንዳይጎዳው አማራጭ መፈለግ ይጠበቅባቸዋል። በሌላ በኩል የኤሌክትሪክ አቅርቦት ዋነኛ የአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች መፈጠርና በገበያው መቆየት ዋጋ አለው፡፡ ነገር ግን በቡሀሪ መጀመሪያ ፕሬዚዳንትነት ዘመን ሊሳካ አልቻለም፡፡
እአአ 2023 ቡሀሪ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከነዳጅ ያላቅቃሉ ተብሎ አይገመትም፡፡ ምክንያቱም ፕሬዚዳንቱ ለዚህ ትክክለኛ መልስና ሰው ስለሌላቸው ነው፡፡ ቀስ በቀስ የአገሪቱ ብሄራዊ ባንክ በህዝቡ ሊተዳደር ይችላል፡፡ ከሶስት ሳምንት በፊት የባንኩ የአንድ ክፍል ኃላፊ በባንኩ ጉዳይ የተደረገ ውይይት ድምፅ በድረገፅ አውጥቶ ነበር። ተቀርፆ በወጣው ድምጽ ውስጥ ያለአግባብ የባከነውን አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በምን አይነት መንገድ ሊስተካከል እንደሚችል የተደረገ ውይይት ይገኝበታል፡፡
ቡሀሪ ለሁለተኛ ጊዜ ከተመረጡ በኋላ ስራቸውን በጀመሩበት በመጀመሪያዎቹ ቀናት እንደዚህ አይነት ወሬዎች መሰማታቸው ከባድ ቢሆንም የባንኩ ዋና አስተዳዳሪ ጎድዊን ኢምፍሊ የቡሀሪ አስተዳደር በቀጣይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት በሚል የውሸት የሂሳብ ሪፖርቶች ሊያዘጋጅ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ደህንነት
እውቅና መሰጠት ያለበት ቦታ ላይ እውቅና መስጠት ግዴታ ነው፡፡ በአሁን ወቅት ቦኮሀራም ከአራት አመት በፊት የነበረው ተፅዕኖ በአሁን ወቅት የለም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ባይጠፉም ቡሀሪና የጦር አዛዡ መሪ ቱኩር ቡራታሪ ለቦኮሀራም መቀነስ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ የቦንብ ጥቃቶች እና ከፍተኛ የሆነ እገታ በፊት ከነበረው ቀንሷል። ነገር ግን አልፎ አልፎ ከፍተኛ የሆኑ ወታደራዊ ጥቃቶች ይሰነዘራሉ፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት በደረሰ ጥቃት 25 ወታደሮች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ቡሀሪ ቀሪ ስራዎች እንዳሉባቸው ነው፡፡
በሁለተኛው ዙር ጥቃቶቹ መሻሻሎች ይኖራቸዋል፡፡ ይህ መጠን የሚወሰነው ከሚመጣው የሕግ አውጭው አካል ጋር አብሮ ለመስራት ሲዘጋጁ ነው፡፡ ቀድሞ የነበረው የርስበርስ ግንኙነት የተፈረካከሰ በመሆኑ አሁን የተለየ እንቅስቃሴ ሲደረግ ብዙዎች ፍራቻ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የፀረ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት አንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጋቸው ብዙዎችን አስፈርቷል ።
ነገር ግን በአገሪቱ ጭቆና እንዳይኖር ለማድረግ በተሰራው ስራ ቡሀሪ ውጤታማ አልነበሩም።የሽግግርና የእገታ እንቅስቃሴዎች በሁሉም አገሪቱ አካባቢዎች እየተባባሱ ይገኛሉ። ይህ ሁኔታ በዋና ከተማዋ አቡጃም እየተስተዋለ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም አጥፍቶ መጥፋት አደጋዎች እየታዩ ነው፡፡
እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ታይተው የነበሩት ከቦኮሀራም ጋር እየተደረገ በነበረው ጦርነት ወቅት ነበር፡፡ በአሁን ወቅት እንደዚህ አይነት ችግሮች የተባባሱት ቡሀሪ በተሻለ መንገድ የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ ባለመስራታቸው ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ለተከታታይ ወር የተለያዩ የሽብርተኝነት ጥቃቶችን ለማስቆም በተደረገ እንቅስቃሴ የፖሊስ መሪ የሆነውን ኢብራሂም ኢድሪስ ተጎድቶ ነበር፡፡ ጉዳቱ የደረሰበት ጓደኛው የሆነውን አቡበከር አዳሙን ለመከላከል ሲሞክር ሲሆን ለጉዳዩ ቡሀሪ ምንም አይነት ትኩረት አልሰጡም ነበር፡፡ ቡሀሪ ለመረጡት ዜጎች ታማኝ ለመሆን ፍላጎት የላቸውም። የአገሪቱን ደህንነት አጠባበቅ ካለበት መቀየር አይፈልጉም። ምክንያቱም የአገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት ተቋም አጠራጣሪ ውስጥ በመሆኑ ነው፡፡ እንዲሁም ሥራቸውን እንዳይቀይሩ ለማድረግ ጫና የማያሳድርባቸው እስከሌለ ድረስ የናይጄሪያ የደህንነት ፈተና በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ባለበት ይቀጥላል፡፡
የሚያስገርመው ነገር ከአራት ዓመታት በኋላ ቡሀሪ ስለ አገሪቱ ደህንነት ከሀሳብ የዘለለ ምንም አልሰሩም፡፡ በአገሪቱ ብሄራዊ መገናኛ ብዙሀን ድንገተኛ ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ቡሀሪ በአገሪቱ እየተባባሰ ስለመጣው እገታ ሲጠየቁ እአአ 1999 እስከ 2014 ድረስ ምን ተፈጥሮ እንደነበረ እያሰቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደሳቸው አባባል፤ አብዛኛው ጉዳይ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ነው፡፡ ወታደሩና ህግ አስከባሪው አካላት ተጠያቂነት ጥርጣሬ ውስጥ ገብቷል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ የተቀመጡት ጉዳዮች በቀጣይ በቡሀሪ ቀጣይ አራት ዓመት የስልጣን ጊዜ እንዲስተካከሉ የሚጠበቁ ናቸው። ፕሬዚዳንቱ አሁን ካሉበት የማሰቢያ ጊዜ ወጥተው ወደ ተግባር መግባት ይገባቸዋል። የአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ የፀጥታና የሙስና ችግር እስከ እአአ 2023 ድረስ ባሉበት እንደሚቀጥሉ መገመት ቀላል ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ለሁለተኛ ጊዜ የፕሬዚዳንትነት ጊዜ ችግር እንዳይሆንባቸው መጠንቀቅ ይገባቸዋል ሲል አልጀዚራ ዘገባውን አጠቃሏል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2011
መርድ ክፍሉ