የአጼ ዮሐንስ ንግሥና

በዚህ ሳምንት ብዙ የታሪክ ክስተቶች አሉ። የአጼ ዮሐንስ አራተኛን የንግሥና ሳምንት ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበራቸውን ሚና እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት ግን ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን እናስታውስ፡፡

ከ62 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 13 ቀን 1954 ዓ.ም ኢትዮጵያ በታሪኳ እስካሁን ድረስ ብቸኛ የሆነውን የአፍሪካ ዋንጫ አሸነፈች፡፡

ከ14 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 15 ቀን 2002 ዓ.ም 90 ሰዎችን (82 መንገደኞችንና 8 ሰራተኞችን) ይዞ ከቤሩት፣ ሊባኖስ፣ ራፊቅ ሃሪሪ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ እየበረረ የነበረው የበረራ ቁጥሩ ET409 የሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-8AS አውሮፕላን ሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ወደቀ፤ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት ሁሉም ሰዎች ሞቱ፡፡

ከ100 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 16 ቀን 1916 ዓ.ም የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ባለውለታ የነበሩት ዶክተር ካትሪን ሐምሊን ተወለዱ፡፡ እነሆ ዘንድሮ 100ኛ ዓመታቸው ሆነ፡፡

ከ53 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 17 ቀን 1963 ዓ.ም በዓለም ታሪክ ከታዩ አምባገነን ገዢዎች መካከል አንዱ እንደነበር የሚነገርለት ኢዲ አሚን ዳዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚልተን ኦቦቴን በመፈንቅለ መንግሥት ገልብጦ የኡጋንዳን ስልጣን ጨበጠ፡፡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚልተን ኦቦቴ በሲንጋፖር በሚካሄደው የጋራ ብልጽግና ሀገራት ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ነበር፡፡ ኢዲ አሚን ዳዳ እነሆ በታሪክ ውስጥ የአምባ ገነን ምሳሌ ተደርጎ ይታወሳል፡፡

ከ137 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 18 ቀን 1879 ዓ.ም በጀግናው ራስ አሉላ እንግዳ (አሉላ አባነጋ) የተመራው የኢትዮጵያ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው የመጡትን ጣሊያኖችን ‹‹ዶጋሊ›› በተባለ ቦታ ላይ ገጥሞ ዶጋ አመድ አደረጋቸው፡፡

ከ33 ዓመታት በፊት ጥር 18 ቀን 1983 ዓ.ም ኢትዮጵያን በግፍ የወረሩት፤ ሦስተኛው የሶማሊያ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት የነበሩት ሜጀር ጀኔራል መሐመድ ዚያድ ባሬ ከስልጣን ተባረሩ፡፡

ከ79 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 19 ቀን 1937 ዓ.ም ናዚ ጀርመንና ተባባሪዎቻቸው በርካታ ሰዎችን፤ በተለይም አይሁዶችን ሲያሰቃዩበት የነበረውና ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን (960 ሺህ አይሁዶች፣ 74 ሺህ አይሁድ ያልሆኑ ፖላንዳውያን፣ 21 ሺህ ሩማንያውያን፣ 15 ሺህ የሶቭየት ኅብረት ምርኮኛ ወታደሮች እንዲሁም 15 ሺህ ሌሎች አውሮፓውያን) የገደሉበት ‹‹የኦሽዊትዝ ካምፕ›› በሩስያ ቀዩ ጦር ነፃ ወጥቶ ተዘጋ፡፡

አሁን ደግሞ ከ152 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆነው የነገሡት ወደ አጼ ዮሐንስ 4ኛ ታሪክ እንለፍ፡፡

አጼ ዮሐንስ 4ኛ የተንቤንና የእንደርታ ባላባቶች ከነበሩት ወላጆቻቸው ሐምሌ 5 ቀን 1825 ዓ.ም ‹‹ማይ በሀ›› (ተምቤን) በሚባል ሥፍራ ተወለዱ። ከመንገሣቸው በፊትም ‹‹ርዕሰ መኳንንት ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ›› በመባል ይታወቁ ነበር። በወቅቱም በትግራይ መኳንንት እግር ተተክተዉ የአካባቢዉ ገዢ ሆነዉ ቆይተዋል።

በሰሜን በኩል በወደቡ አቅራቢያ መገኘታቸውም ከአውሮፓውያን ቆንሲሎች ጋር ወዳጅነት እየመሰረቱ መጠነኛ የትጥቅ ድጋፍ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። ደጃዝማች ካሳ ምርጫ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት እንደሚሆኑ እርግጠኛ ስለነበሩ ‹‹ደጃዝማች›› ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ራሳቸውን ለውጭ ሀገራት መንግሥታት በደብዳቤ ያስተዋውቁ ነበር።

ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ከሞቱ በኋላ ለሦስት ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የነበሩት አፄ ተክለጊዮርጊስ፣ ደጃዝማች ካሳን ሊያስፈራሩ አንድ ስልቻ ጤፍ አስቋጥረው ‹‹የሰራዊቴ ቁጥር እንደዚህ የበዛ ነውና አትችለኝም፤ ስለዚህ ገብር!›› ብለው ላኩባቸው፡፡ ደጃዝማች ካሳ ደግሞ በምላሹ የተላከውን ጤፍ አስቆልተው ‹‹የእኔ ሰራዊት ደግሞ ያንተን ሰራዊት እንደዚህ ይቆላዋል›› ብለው ላኩላቸው፡፡ የተናገሩት አልቀረም፤ ደጃዝማች ካሣ አፄ ተክለ ጊዮርጊስን ዓድዋ አካባቢ ‹‹አሰም›› በሚባል ሥፍራ ላይ ሐምሌ 5 ቀን 1863 ዓ.ም ተዋግተው ድል አደረጓቸው፡፡

ከድሉ በኋላም ለበዓለ ንግስናቸው የሚያስፈልገውን ሁሉ ሲያደራጁ ቆይተው ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም በእለተ እሁድ በአክሱም ፅዮን ቤተ ክርስቲያን በጳጳሱ አቡነ አትናቴዎስ እጅ ተቀብተው ‹‹ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ግርማዊ ዮሐንስ ራብዓዊ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ፅዮን ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ነገሡ።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ለሀገራቸውና ለሃይማኖታቸው ባላቸው ቀናኢነት የሚታወቁት አጼ ዮሐንስ 4ኛ፣ አንዲት ጠንካራ ሀገር እውን እንድትሆን ያለ ዕረፍት ሲተጉ ኖረዋል። በተለያዩ አቅጣጫዎች ሀገር ለመውረር ከመጡት ከግብጾች፣ ከቱርኮች፣ ከጣሊያኖችና ከደርቡሾች (መሐዲስቶች) እና ከሌሎች የውጭ ኃይሎች ጋር ተደጋጋሚ ጦርነቶችን አድርገው ነፃ ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ያስረከቡ ትጉህ ንጉሥ እንደሆኑ የታሪክ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡

የአጼ ዮሐንስ አራተኛ ታሪክ ሲነሳ በብዙዎች ዘንድ ቶሎ የሚታወሰው ለሀገራቸው ክብር መስዋዕት የሆኑበት የመተማ ጦርነት ነው፡፡ የዚህን ጦርነት ክስተቶች እናስታውስ፡፡

አጼ ዮሐንስ ገላባትን፣ ብሎም አምድሩማንንና ካርቱምን በመያዝ የድርቡሽን መንግሥት ለመገርሰስ ዝግጅት መጀመራቸው ሱዳን ውስጥ ጭምጭምታ ተሰማ። አጼ ዮሐንስ በዋነኞቹ የጦር መሪዎች በእነ ራስ አርአያ ድምፁ፣ ራስ ሚካኤል (መሐመድ አሊ)፣ ራስ ኃይለማርያም ጉግሳ፣ ራስ አሉላ፣ ስልሕ ሻንቆ እና ሌሎችም ታላላቅ የጦር አዛዦች የሚንቀሳቀሱ ክፍለ ሠራዊቶችን በመምራት በቅድሚያ ገላባትን ለመያዝ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸው ወሬው በደርቡሽ ዘንድ ተሰማ።

የገላባቱ ምሽግ ዋና አዛዥ ሸክ በኪ ጡማል በመምጣት ላይ ያለውን ጠላት ከምሽግ ውስጥ ሆኖ መዋጋት ወይስ ገና ከመንገድ ላይ መቁረጥ የትኛው እንደሚሻል አማካሪዎቹን አወያየ። ካለምንም ማወላወል ምሽጋቸውን ማጠናከር አማራጭ የሌለው ዘዴ መሆኑ እርግጥ ነበር። እንደማዕበል የሚነጉደውን የኢትዮጵያ ሠራዊት ከምሽግ ወጥቶ መመከት የማይታሰብም የማይሞከርም ነበር።

አጼ ዮሐንስን ለመግጠም የተመደበው የዘኪ ጥምር ጦር 80‚000 ደርሷል። ከቁጥሩ በላይ ጦሩ ምሽጉን አጥብቆ በመያዝ የመጣበትን ጦር ለመመከት ቁርጠኛ ነበር። አዋጅ ነጋሪዎች በገጠር በከተማው እየዞሩ ሱዳናዊ ሁሉ የዕለት ተግባሩን ትቶ ጠብመንጃውን አንግቶ፣ ጎራዴውን ታጥቆ ሀገሩን እንዲከላከል የመሪያቸውን ትዕዛዝ አሰሙ። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የዘመቻ ዝግጅት ከተነገረው በላይ ተጠናክሮ መቀጠሉን የድርቡሽ ወታደራዊ ምንጮች ገለፁ። እነዚህ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት መረጃዎችን ያሰባስቡ የነበሩ ሰላዮች የኢትዮጵያን ሠራዊት እንቅስቃሴ በሚከተለው መልክ አቀረቡት።

‹‹የሀበሻ ሠራዊት እንደሰማይ ከዋክብት እንደባህር አሸዋ ህልቆ መስፈርት የለውም። ሠራዊቱ ሲርመሰመስ ለዓይን እይታ የሚታክት፣ መጨረሻው ከአድማስ ባሻገር የሆነ፣ የዘመቻው ንቅናቄ በሚያስነሳው ምድራዊ ደመና ጸሐይን ያጠቆረ አስፈሪ ኃይል ነው››

ይህ ደማቅ ወታደራዊ ዘገባ የድርቡሾች ዋና ከተማ የነበረችውን አምድሩማንን ከወዲህ ወዲያ በሽብር አናወጣት። ከዕለታት አንድ ቀን ሱዳን በሀበሻ እንደምትተፋ፣ የንጉሡ ፈረስም ኮቴው በፈሰሰው ደም ተውጦ፣ እንደ ወሬ ነጋሪ ከጥፋት በተረፈችው አንዲት ዛፍ ጥግ ታስሮ እንደሚታይ እንደ ትንቢት የሚነገረው አፈ ታሪክ ጊዜው መድረሱና ትንቢት የተነገረለት የሀበሻ ንጉሥ ዮሐንስ እንደሆነ ትንቢት ተናጋሪዎች አስረዱ።

በ1881 ዓ.ም ወርሀ የካቲት መጨረሻ ላይ ንጉሠ ነገሥቱ አጼ ዮሐንስ 4ኛ ጎንደር ከተማን ለቀው በመውጣት ሕዝብን ለማጥፋት የተነሳውን ቁርጠኛ ጠላት ለመደምሰስ ሠራዊታቸውን በረድፍ በረድፍ አስከትለው ወደ ገላባት ተመሙ። ከከተማዋ አቅራቢያ እንደደረሱ አጼ ዮሐንስ እንዲህ አሉ፡፡

‹‹እንደ ሌባ ተሽሎክልኮ መጣ እንዳትለኝ፤ ለፍልሚያው ተነስቻለሁና ተነስ!›› ብለው ለድርቡሹ አዋጊና የጦር አዛዥ መልዕክት ሰደዱለት፡፡ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ከወንዶቹ ሌላ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወይዛዝርት አብረው ተሰልፈዋል። እነዚህ ሴት ዘማቾች የትዳር ጓደኞቻቸውን፣ የእጮኞቻቸውን፣ የወንድሞቻቸውንና የአባቶቻቸውን የሞትና የመከራ ጽዋ ለመቅመስ ኑሯቸውን በትነው፣ ጎጇቸውን ዘግተው ወደ ጦር ሜዳ የዘመቱ ናቸው።

ቅዳሜ መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም አፄ ዮሐንስ የገላባትን ምሽግ ማጥቃት ጀመሩ፡፡ ሠራዊታቸው መሪውን እየተከተለ ከምሽጉ ውስጥ በፉከራና በቀረርቶ እየዘለለ ገባ። ከጦር አውድማው የሚነሳውን አቧራ አውሎ ነፋሱ ሲያነሳው እሽክርክሪት እየሰራ በውጊያው መሀል ሰይጣናዊ ጭፈራውን አቀለጠው። ከወዲያም ከወዲህም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለዘመን ፍጻሜ የሚዋደቁ የሚመስሉ ወታደሮች አንዱ ሌላውን ለመለየት በማይቻልበት ሁኔታ ወደቁ፡፡ የሞትና ሽረት ትግሉ የቀኑን ብርሃን ጽልመት አለበሰው።

ንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሐንስ ጦርነቱ መሐል ገብተው ሲዋጉ ያየው የኢትዮጵያ ወታደር መንፈሱ በአንዳች ወኔ እየተፈነቀለ ግስጋሴውን ቀጠለ። የድርቡሾች ጠንካራ ምሽግ መላላትና መሳሳት ጀመረ።

ከድርቡሾች ሰይፍና የጥይት አረር ይልቅ የኢትዮጵያ ጦርን የከበደው ቢኖር በአገር ምድሩ የበቀለው እሾህማ ጥቅጥቅ የቆላ ግራር ነበር። ለደርቡሾች ተደራቢ ምሽግ ሆነላቸው። ሀበሾቹ ግራሩን ግራ ቀኝ ረግጠው እየዘለሉ፣ አንዳንድ ጊዜም እያቃጠሉ ወደ ዋናው የደርቡሽ ማዘዣ ጣቢያ ዘልቀው ለመግባት ሲዋጉ የድርቡሽ ሠራዊት አጋጣሚውን በመጠቀም ጥይቱን አርከፈከፈው። በዚህ የትንቅንቅ ሰዓት ነበር ከማህዲ ሰፈር አምልጠው ለኢትዮጵያ ሠራዊት እጃቸውን የሰጡ ትኹሪሮች (ደቡብ ሱዳናውያን) ጠቃሚ መረጃ የሰጡት።

በደርቡሾች የጦር ሰፈር ደካማው የውጊያ ግንባር ያለበትን ምርኮኞቹ ተናገሩ። የኢትዮጵያ ሠራዊት ለመጨረሻው የሞት ሽረት ድል ወጊያውን አፋፋመ፡፡

በሁለቱም ወገን ከተከፈለ ከባድ የሕይወት መስዋዕትነት በኋላ የኢትዮጵያ ሠራዊት እንደ ውቅያኖስ ማዕበል እያስገመገመ ከፊት ለፊቱ የቆመውን ሁሉ እየደመሰሰ የደርቡሾችን ወታደራዊ እምብርት ዘልቆ በመግበት የበላይነቱን ተቀዳጀ። ድልን ጨብጦ በመገስገስ ላይ የነበረውን ኃይል በተመለከቱ ጊዜ ከኋላ ሆነው ‹‹ግፋ በለው›› እያሉ እልል ሲሉ የዋሉት በሺዎች የሚቆጠሩ የደርቡሽ ሴቶች ልብ የሚነካ እዬዬና ዋይታ ያሰሙ ጀመር።

የኢትዮጵያ ጦር አሁንም ማጥቃቱን በመቀጠልና ያገኘውን ድል በማጠናከር የድርቡሾችን ምሽግ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ። ይህ ግስጋሴ ሀበሾችን ወደ ፍፁም ድል በር የሚያደርሰው ወሳኝ እርምጃ ነበር።

የገላባት (መተማ) ጦርነት ከዚያም ከዚህም የሰው ልጅ እንደ ቅጠል ቢረግፍበትም ድል ፊቷን ወደ ዮሐንስ ማዞሯ አጠራጣሪ አልነበረም። ሐበሾች የደርቡሽን የትጥቅና ስንቅ ማከፋፈያ ማዕከልን ተቆጣጠሩ። የጦር አዛዡ አቡ አንጋ ጦርነቱን ይመራ የነበረው ከዚሁ ሠፈር ሆኖ ነበርና የዮሐንስ ወታደሮች የማዘዣ ጣቢያው መደምሰስን ተከትሎ የደርቡሾችን የሬሳና የቁስለኛ ክምር በማገላበጥ የራሱን የአቡ አንጋን አስክሬን ለማግኘት ፍለጋ ጀመሩ።

ከማዘዣ ጣቢያቸው ሙሉ በሙሉ መደምሰስና ትጥቅና ስንቃቸው በኢትዮጵያ ሰራዊት መማረክ በኋላ የድርቡሾች ወኔ ሟሸሸ። የደርቡሽ ጦር በእጁ የያዘው ጥይትና ሌላ አስፈላጊ የውጊያ መሣሪያ አልቆ መዋጋት በማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ የዮሐንስ ዘማች ኃይል አሸናፊነት እርግጥ ሆነ።

ደርቡሾች ተሸንፈው ‹‹እግሬ አውጭኝ›› እያሉ በሚሸሹበት ሰዓት ንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሐንስ በአንዲት ጥይት ተመትተው መውደቃቸው በኢትዮጵያውያን ሰፈር ተሰማ። ወሬው እየተቀጣጠለ ጦሩን ግራ አጋባው፡፡ በድርቡሽ ቆራጥነት ያልተፈቱት ሀበሾች በድል አፋፍ ላይ ቆመው የድርቡሽን ሽሽት አሻግረው በሚመለከቱበት ሰዓት በንጉሠ ነገሥታቸው መመታት ድንጋጤ ጥርጣሬና ተስፋ መቁረጥ ወረራቸው። ከድል በኋላ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ በተተኮሰችው ጥይት ምክንያት የኢትዮጵያውያኑ ሠፈር ተስፋ መቁረጥና ትካዜ ገባበት። ካለ መሪ ካለ አስተባባሪ የቀረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ፊቱን ወደ አገሩ በማዞር ጉዞ ጀመረ። ድል ፊቷን ወደ ኢትዮጵያውያን ብታዞርም እንደገና ወደ ድርቡሽ ዞረች፡፡

የተበታተኑት የድርቡሽ ሠራዊቶች እየተሰበሰቡ ወደ ተደመሰሰው ምሽጋቸው መመለስ ጀመሩ። በዚህ ሁኔታ ድል የቀናው የድርቡሽ ሠራዊት የአጼ ዮሐንስ አራተኛን ራስ ቆርጦ ለመውሰድ ዕድል አገኘ፡፡

የአፄ ዮሐንስ ራስ በአምድሩማን አደባባይ ለዕይታ ቀርቦ እንደበቃ በቆዳ ተለብዶ ወደ ደንጎላ (ዳርፉር ግዛት) ከዚያም አልፎ እስከ ግብጽ ድንበር ድረስ በግመል ተጭኖ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡ እነሆ ዛሬ ድረስ ይህ ታሪክ በጠላትም ሆነ በወዳጅ ወገን ይነገራል፡፡

አጼ ዮሐንስ 4ኛ ከነገሥታቱ ለየት የሚያደርጋቸውም ይህ ታሪካቸው ነው፡፡ ንጉሥ ሆነው ልክ እንደ ተራ ወታደር ሲዋጉ ነው የሞቱት። እንደ አገር ባላቸው ታሪክ ደግሞ ኢትዮጵያ አገራቸውን የማያስደፍሩ ጀግኖች አገር መሆኗን አሳይተዋል፡፡ የጀግኖችን ታሪክ የምናስታውሰውም ለዚህ ነው፡፡

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ጥር 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You