የአርብቶ አደሩን አካባቢ ልማት በአርብቶ አደሩ እምቅ ሀብት!

 የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ከሚታወቁባቸው ግንኙነቶቻቸው መካከል ድንበር ሳይወስናቸው በሰፊ ስፍራዎች ላይ በሚኖሩት አርብቶ አደሮቻቸው መካከል ያለው ጥብቅ ትስስር ይጠቀሳል፡፡ አርብቶ አደሮቹ ከፍተኛ መጠን ባለው የእንስሳት ሀብታቸው በእጅጉ ይታወቃሉ፡፡

አርብቶ አደሮቹ ለእንስሳቶቻቸው ሲሉ ከቦታ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከአንዱ ሀገር ወደ አንዱ ሀገር በነጻነት እንዲገቡና እንዲወጡ ሲያደርጋቸው ኖሯል፡፡ ይህ ምንም አይነት ቪዛ ሳያስፈልጋቸው እንደ ልብ ከሀገር ሀገር የሚንቀሳቀሱበት መንገድ የአርብቶ አደሮቹ ብቻ ሳይሆን የምሥራቅ አፍሪካም መለያና ትልቅ አቅም ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል፡፡ ይህ ጥብቅ ግንኙነት የፖለቲካ ውሳኔ ከሚፈጥረው ትስስር በላይ በጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ፣ በቀላሉ የማይናወጥና ዘመናትንም የተሻገረ ነው፡፡

አርብቶ አደሮቹ የአካባቢው ትልቅ አቅም የሆነውን የእንስሳት ሀብት በራሳቸው መንገድ እያለሙ ይገኛሉ፡፡ በእዚህ ሀብት ልማት ላይ የአካባቢው ሀገሮች ብዙም የጨመሩት እሴት የለም፤ የአርብቶ አደሩ ከብቶች ጤና የሚጠበቅበት ሁኔታ ብዙም ጠንካራ ባለመሆኑ፤ አርብቶ አደሩ የከብት ግብይት የሚፈጸምበት መንገድ ዛሬም እንደ ጥንቱ በቁሳቁስ ልውውጥ የሚካሄድበት /ባርትሬድ/ ሁኔታ፣ አካባቢው ለድርቅ ያለው ተጋላጭነት ከፍተኛ መሆኑም በዘርፉ ላይ ብዙ አለመሰራቱን ያመለክታሉ፡፡

መንግሥታት ለአካባቢውና ለማኅበረሰቡ ሲሰጡ የቆዩት ትኩረት አናሳ በመሆኑ በአካባቢው ድርቅ፣ ጎርፍ እና የእንስሳት በሽታ ደጋግሞ ይከሰታል፡፡ ባለፉት ዓመታት በድርቅ ሳቢያ በኢትዮጵያ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ያለቁት ከብቶች ብዛት የችግሩን አሳሳቢነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ አርብቶ አደሩ ከእንስሳቶቹ የሚያገኘው ተጠቃሚነት በመሰረተ ልማትና በገበያ እጦት፣ በጤና መታወክና በህገወጥ ግብይት ሳቢያ እዚህ ግባ የማይባል ሆኖ ኖሯል፡፡ የመሰረተ ልማት እጦቱ የአርብቶ አደሩ የእንስሳት ሀብት እንዲባክን እያደረገው ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ለአርብቶ አደሩ ትኩረት ሰጥተው መስራት የጀመሩ ቢሆንም፣ አካባቢው ካለው እምቅ አቅም፣ አርብቶ አደሩ ከሚገኝበት ዝቅተኛ ህይወት አኳያ ሲታይ ብዙ ተሠርቷል የሚያሰኝ አይደለም፡፡ የአካባቢውን በርካታ ትላልቅ ወንዞች ማልማት ባለመቻሉ አርብቶ አደሩ ለእንስሳቶቹ ውሃ ፍለጋ፣ በዚህ ሀብት መኖ በማልማት ከብቶቹን መመገብ የሚቻልበት ዕድል እያለ ዛሬም እንደ ጥንቱ ከአካባቢ አካባቢ፣ ከሀገር ሀገር መንከራተቱን ቀጥሏል፡፡

አርብቶ አደሩን ከዚህ አይነቱ ችግር በማውጣት ሕይወቱን ለመቀየር፣ የአካባቢው ሀገሮችም ከዚሁ አካባቢ ሀብት በሚገባ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ለመፍጠር እንደ ሀገርም እንደ አካባቢም የተጀመሩ ጥረቶች መጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡

ለእዚህም የአካባቢው አርብቶ አደሮች የቆየ ትስስር ያለምንም ቪዛ ከሀገር ሀገር የሚገቡበትና የሚወጡበት መንገድ ፣ አካባቢያቸውን የሚያስተዳድሩበት ሁኔታ አካባቢውን ለመለወጥ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ግብአት ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል፡፡ ልማቱን በጋራ አስተሳስሮ ለማካሄድም ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ከትናንት በስቲያ በሚሊኒየም አዳራሽ የተጀመረው የምሥራቅ አፍሪካ አርብቶ አደሮች ኤክስፖ ትልቅ ስፍራ ሊሰጠው ይገባል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን በኢኮኖሚ በማስተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነትን ማስፈን የኢትዮጵያ የምንጊዜም ፍላጎትና ጥረት መሆኑን መድረኩን የከፈቱት የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ኤክስፖው ትስስራችን ምን ያህል የጠነከረ፣ አጥርና ድንበር የሌለን ወንድማማቾችና እህትማማቾች መሆናችንን በግልፅ የሚያሳይ ነው›› ያሉት አፈ ጉባኤው፣ ይህንን ትልቅ እሴት በኢኮኖሚ በማስተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነትን ማስፈን የኢትዮጵያ የምንጊዜም ፍላጎትና ጥረት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

‹‹አርብቶ አደሩ አጥርም ድንበርም የለውም፤ ይህም የቀጣናችንን ትስስር ለማጠናከር፣ አብሮ ለመበልፀግ እንዴት መጓዝና መደመር እንዳለብን ብዙ ይነግረናል›› ሲሉ የተናገሩትም የአርብቶ አደሩን አካባቢ ለማልማት ከራሱ ከአርብቶ አደሩ ህይወት ብዙ ትምህርት መቅሰም እንደሚቻል ያስገነዝባል፡፡

በእርግጥም ይህን የአርብቶ አደሩን የቆየ እሴት በመጠቀም አካባቢውን ማልማት ይቻላል፡፡ አካባቢው በቂ ሀብት አለው፤ አብሮ መልማት የሚያስችል ዘመናነትን የተሻገረ በቂ አቅምም አለው፡፡ ይህን ማልማት የሚቻልበትን ሁኔታ በመፍጠር አካባቢውን በድርቅና በመሳሰሉት ችግሮች በቀላሉ ከሚጠቃበት ሁኔታ ማውጣት ፣ የአካባቢውን ሀገሮችም ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል፡፡ ምሥራቅ አፍሪካን በንግድ ለማስተሳሰር እየተሞከረ ያለበትን መንገድ በመጠቀምም እንዲሁ አካባቢው በቂ ገበያ እንዲኖረው በማድረግ ከእንስሳት ሀብቱ ሽያጭ በሚገባ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፡፡

ለእዚህም የአርብቶ አደሩን አካባቢ ለማልማት የሚደረገውን ጥረት ይበልጥ ማጠናከር፣ እንደ ቀጣናም መሰል መድረኮችን ቶሎ ቶሎ በማዘጋጀት ከመድረኮቹ የተገኙ ሃሳቦችን ወደ ተግባር በመቀየር ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡

የአርብቶ አደሩን አካባቢ በአካባቢው ሀብት ማልማት ይቻላል፡፡ የአካባቢው ሀብትና የአርብቶ አደሩ ልምድና ተሞክሮ ለእዚህ ትልቅ አቅም በመሆን ያገለግላሉና፡፡ በእዚሀ ትልቅ ሀብት ላይ ጥቂት ሀብት መጨመር ነው የሚያስፈልገው፡፡ ይህ ሲሆን አርብቶ አደሮቹን፣ ሀገራቱንና ሕዝባቸውን ብሎም ቀጣናውን ይበልጥ በማልማት ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል!

 አዲስ ዘመን ጥር 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You