ለሚወዱት ሰው አቅም በቻለ መጠን ስጦታ ማበርከት የተለመደ ነው። ኧረ እንዲያውም ለወደዱት ከቁሳቁስም ባለፈ መተኪያ የሌለው ውድ ህይወትም ይሰጣል። እንደ «የፍቅረኛሞች ቀን» ባሉት ዕለታት ደግሞ ከምንጊዜውም በላይ ጥንዶች ስጦታ ይለዋወጣሉ። በዚህ ወቅት ታዲያ ከአበባ እና የመልካም ምኞት መግለጫ እስከ ትልልቅና ውድ ስጦታዎች ለተወዳጁ ሰው ይቀርባሉ።
ከሌላው ዓለም በተለየ የፍቅረኛሞች ቀን በግንቦት ወር ከሚከበርባት ቻይና፤ የስጦታ ልውውጡን ተከትሎ አስደናቂ ታሪኮች እየተሰሙ ይገኛሉ። «ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ ሳይሰጠኝ ቀረ» በሚል የጥፊ ውርጅብኝ በፍቅረኛዋ ላይ ያወረደችው ወጣት መነጋገሪያ ሆና ቆይታለች። ከሰሞኑ ደግሞ በዚያው በቻይና አስደናቂ እና ያልተለመደ ስጦታ በዓሉን ተከትሎ መበርከቱ ነው የተነገረው።
አንዲት ወጣት ፍቅረኛዋ ያበረከተላትን ገጸበረከት በማህበራዊ ድረገጾች «እዩልኝ» ስትል በለጠፈችው መሰረት መነጋገሪያ መሆኗንም ነው ኦዲቲ ሴንትራል ያስነበበው። አስደናቂው ስጦታም በ210 ሄክታር መሬት ላይ የተንጣለለ ውቅያኖስ ነው (ግራ አያጋባ ይሆን?)። ዣንግ የተባለው ይህ አፍቃሪ ፍቅረኛውን ላስደነቀበት ስጦታ መግዢያም 99ሺ ዶላር ማውጣቱ ነው የተዘገበው።
ውቅያኖሱ ቼኒሻን ከተባለ ደሴት በቅርብ ርቀት የሚገኝ ሲሆን፤ ዳርቻውንም በሻንዶንግ ያደረገ ነው። ቀድሞ በአንድ አሳ አጥማጅ ስራ የተሰማራ ድርጅት ንብረትም ነበር፤ ውቅያኖሱ። ታዲያ በዘንድሮው የፍቅረኛሞች ቀን፤ ጓደኛዋ ለባለታሪኳ ምንም ስጦታ እንዳልገዛላት ነበር የነገራት በዚህም ወቅሳዋለች።
ነገር ግን ወደዚያው ወስዷት የውቅያኖሱ አንድ ክፍል የእርሷ እንደሆነ የነገራት መሆኑንም ነው ወጣቷ በማህበራዊ ድረ ገጿ ያጋራችው። የባለቤትነት የምስክር ወረቀቱን፣ በጨረታው አሸናፊ በመሆን የተከፈለው የገንዘብ መጠን እንዲሁም ባለቤት የሆነችበትን የውቅያኖስ ክፍል ካርታም በፎቶ ማያያዟም በዘገባው ተወስቷል።
ብዙዎች ይህንን ዜና ከሰሙ በኃላም የተለያዩ ሃሳቦችን በማንሳት ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ አንዳንዶች ባለማመን «እንዴት ውቅያኖስ ይሸጣል?» የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል። ዘገባውም በምላሹ «ይቻላል» ሲል፤ መቀመጫውን በቤጂንግ ያደረገ ዣንግ ዢናን የተባለ አንድ የህግ ባለሙያም ወጣቷ በማሳያነት ያቀረበቻቸው መረጃዎች ህጋዊ መሆናቸውን ማረጋገጣቸውንም ለጥርጣሬው ህጉን አስደግፎ ምላሽ ተሰጥቷል።
የህግ ባለሙያው አክለውም «በሃገሪቷ የሚገኙ ውሃማ አካላት ሊሸጡም ሆነ ሊገዙ እንደማይችሉ ህጉ ያመላክታል። ነገር ግን ለግለሰቦችም ሆነ ተቋማት የማስተዳደርና የተጠቃሚነት መብትን ይሰጣል» ብለዋል። በውሃማው አካል ላይ መብት ያለው አካልም (ገዢው)፤ ለሌላ ሰው ማስተላለፍ፣ ማከራየት አሊያም በተለያዩ መንገዶች ግልጋሎት ላይ ማዋል ይችላል።
አሁን የውቅያኖሱ ባለቤት የሆነችው ሴት ግን ምን ልትሰራበት እንዳሰበች እንዲሁም ፍቅረኛዋ ምን አስቦ እንደገዛላት እስካሁን አልታወቀም። ወሬው የደረሳቸው በማህበራዊ ድረገጾች ተጠቃሚዎች አስተያየት እየሰጡ ሲሆን፤ አንድ ግለሰብ «የዚህ ስጦታ አላማ ምንድነው? ፍቅረኛው የባህር ምግቦችን ስለምትወድ አሳ እንድታጠምድበት ይሆን?» ሲልም ጠይቋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2011
ብርሃን ፈይሳ