ፅናትና ታታሪነት ለስኬት ያበቁት ሁለገቡ ወጣት

አንዳንዶች ገንዘብን ገና በወጣትነታቸው ያገኙትና ልጅነት ይዟቸው፣ ማስተዋል አጥሯቸው ያገኙትን ገንዘብ ያለአግባብ አባክነውት የጉልምስና ዕድሜያቸውንም በችግርና በትካዜ ያሳልፉታል:: እነዚህ ሰዎች ገንዘባቸው ልባቸውን ቀድሞት በመሄዱ፣ ገንዘባቸውን በጥሩ ልብ መምራት ሳይሆንላቸው ቀርቶ ‹‹ምነው ያኔ ከገንዘቡ ጋር ልቡም ኖሮኝ ቢሆን?!›› እያሉ ለገንዘብ ቅርብ፣ ለልብ ግን ሩቅ ሆነው ያሳለፉትን ዘመናቸውን በቁጭት የሚያስታውሱ ናቸው::

ጥቂት ቢሆኑም ሀብትንም ብስለትንም በአንድ ጊዜ፣ ያውም በጠዋቱ፣ የሚጨብጡትና ይዘው የሚያቆዩት አስደናቂ ሰዎችም አሉ:: እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሕይወት ገና በጠዋቱ ብዙ ያስተማረቻቸው፣ የሕይወትን ትምህርትና ልምድ በማስተዋል የተገበሩ፣ ያላቸውን ለሌሎች በማካፈል በፅኑ የሚያምኑ እና ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች መሆን የሚችሉ አርዓያዎች ናቸው:: ገንዘባቸው ልባቸውን ሳይቀድም የሚመጣላቸውና ልባቸውን ለገንዘባቸው መምሪያና ማስተዳደሪያ በብቃት የመጠቀም ችሎታ ያላቸውም ናቸው:: እነዚህ ሰዎች ለገንዘብ ቅርብ የሆኑትን ያህል ለልብም ቅርብ ናቸው::

የ‹‹ጣዝማ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› መስራችና ባለቤት አቶ ሰርፀሚካኤል ጉችማ ሀብታምነትንና ልባምነትን አስማምተው ከያዙ ወጣቶች መካከል የሚመደብ የስኬት ምሳሌ ነው:: ሰርፀሚካኤል የተወለደው በ1981 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን፣ መርሐቤቴ ወረዳ፣ ዓለም ከተማ ነው::

ገና በልጅነቱ ወላጆቹን በሞት የተነጠቀው ሰርፀሚካኤል፣ አባቱ በወታደራዊው መንግሥት (ደርግ) ዘመን ሀገራቸውን በውትርድና ሲያገለግሉ ቆስለው ስለነበር በ1988 ዓ.ም አረፉ:: ሰርፀሚካኤልን ብቻቸውን የማሳደግ ኃላፊነትን የተረከቡት እናቱም ብዙም ሳይቆዩ በ1992 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ:: ይህ አሳዛኝ አጋጣሚ የታዳጊውን የሰርፀሚካኤልን ሕይወት ገና በለጋነቱ መራራ ገፅታ እንዲጋፈጥ አስገደደው:: ሰፊ በሆነው የወላጆቹ ቤት ውስጥ ብቻውን መኖርን ጨምሮ፣ ለመኖር የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ፍላጎቶቹን ለማሟላት ተቸገረ::

ሰርፀሚካኤል የሕይወትን ፈተናዎች ለማሸነፍ ትግሉን ጀመረ:: ለትምህርት ያለው የጋለ ፍላጎትና የትምህርት አቀባበሉም ጠንካራ ከሚባሉ ተማሪዎች ተርታ የሚያሰልፈው ስለነበር፣ አቅሙ የፈቀደውን ሥራ እየሠራ ትምህርቱን ለመቀጠል ወሰነ:: ፀጉር ቤት ከፍቶ ፀጉር እያስተካከለና ሌሎች ሥራዎችን እየሠራ በሚያገኘው ገቢ ሥራንና ትምህርትን ጎን ለጎን ማስኬድ ቻለ::

‹‹ለትምህርት የሚያስፈልገኝን ወጪ መሸፈኛ ገንዘብ አጣሁ ብዬ ትምህርቱን ማቋረጥ አልፈለግኩም›› የሚለው ሰርፀሚካኤል፣ የእናቱ ቃል ተጨማሪ ብርታት እንደሆነው ይናገራል::‹‹እናቴ ብቻዋንም ሆና በትምህርቴ እንድበረታ ታግዘኝ ነበር:: ስትሞትም ‹የልጄን ትምህርት አደራ› ብላ ተናግራ ነበር:: ቃሏን ለማክበርም ትምህርቴን መቀጠል ነበረብኝ›› በማለት ያስታውሳል:: ይህ ጥንካሬውም የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን (ከ1ኛ-8ኛ ክፍል) በዓለም ከተማ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአርበኞች ሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ ትምህርት ቤት ተምሮ እንዲያጠናቅቅ አስችሎታል::

የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በመርሐቤቴ ወረዳ ማስታወቂያ ጽሕፈት ቤት ፖስተኛ ሆኖ ተቀጠረ:: በወቅቱ የክልሉ መንግሥት ወጣት ለሆኑ፣ ፈጣን የትምህርት አቀባበል ለነበራቸው እና የተሻለ የሥራ አፈፃፀም ላሳዩ ሠራተኞች የትምህርት ዕድልና የሥራ ኃላፊነት ይሰጥ ስለነበር ሁሉንም መስፈርቶች ማሟላት የቻለው ሰርፀሚካኤል፣ የትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ ሆኖ ቀድሞ ከነበረባቸው የሥራ መደቦች ከፍ ባሉ ኃላፊነቶች ላይ ማገልገል ችሏል፤ ምስጉን የሥራ አፈፃፀሙ ቡድን መሪ እስከመሆን አደረሰው:: ቀን እየሠራ ማታ በ‹‹አልማዝ በም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ›› በኮምፒዩተር ሳይንስ ተምሮ በደረጃ አራት (Level 4) በዲፕሎማ የተመረቀው በዚህ ወቅት ነበር::

ያልተቋረጠ ማደግና መሻሻል ከሕይወት መርሆቹ መካከል አንዱ ነውና ለተሻለ ሕይወት ወደሰፊዋ አዲስ አበባ መግባት እንዳለበት አምኖ የትምህርትና የሥራ ልምድ ማስረጃዎቹን ይዞ በ2004 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጣ:: አዲስ አበባ ያደረገችለት አቀባበል ግን ሌላ የፈተና ምዕራፍ ሆነበት:: እርሱም ቢሆን ይህ ዓይነቱ ፈተና እንደሚገጥመው ቀድሞ ያውቅ ስለነበር ለዋና ከተማዋ የሕይወት ፈተና ራሱን አዘጋጅቶ እንደለመደው የለውጥ ትግሉን ተያያዘው:: በዚያ ጊዜ ለሥራ ፍለጋ ከአዲሱ ገበያ እስከ ቃሊቲ ድረስ በእግሩ ለመጓዝ ይገደድ ነበር::

የሰርፀሚካኤል የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ‹‹ምሥራቅ ድል ትምህርት ቤት ›› ላወጣው የሰው ኃይል አስተዳደር ባለሙያ የሥራ መደብ የሚመጥን ስለነበር፣ ውድድሩን አልፎ በዚሁ ሥራ መደብ የትምህርት ቤቱ ሠራተኛ ለመሆን በቃ:: 1ሺ295 ብር ወርሃዊ ደመወዙ ለኑሮው በቂ ስላልነበር ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት እንዳለበት አመነ:: እናም ጠዋት ሥራ እስከሚገባ ድረስ እና ማታ ከሥራ ከወጣ በኋላ የሚኖረውን ጊዜ ተጨማሪ ሥራ ሊሠራበት ወሰነ::

‹‹መንጃ ፈቃድ ስለነበረኝ ከመደበኛው ሥራዬ በተጨማሪ ጠዋትና ማታ ታክሲ አሽከርካሪ ሆኜ እሠራ ነበር:: ጠዋት ቢሮ ከመግባቴ በፊት እስከ አውቶቡስ ተራ፣ ከሥራ ከወጣሁ በኋላ ከቀኑ 11 ሰዓት እስከ ምሽት ሦስት ሰዓት እስከአያት ድረስ እሠራ ነበር:: ከጓደኞቼ ጋር የሚኖረኝ የመዝናኛ ሰዓት ራሱን የቻለ ፕሮግራም አለው:: እንደዚያ ባላደርግ ኖሮ የኑሮ ጫናዎችን መቋቋም አልችልም ነበር›› በማለት የሚባክን ጊዜ እንዳልነበረው ያስታውሳል::

ሰርፀሚካኤል ቀደም ሲል ይታወቅበት የነበረው ትጋቱና የላቀ የሥራ አፈፃፀሙ በምሠራቅ ድል ትምህርት ቤት ከ2004 ዓ.ም መጨረሻ እስከ 2007ዓ.ም መጀመሪያ ድረስ በነበረው ቆይታም አብሮት ዘልቋል:: ይህም ለተሻለ ኃላፊነት አበቃውና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ ተመድቦ እንዲሠራ አስችሎታል::

በእነዚህ የኃላፊነት ቦታዎችም ላይ ብቃት ያለው ባለሙያና መሪ መሆኑን በማስመስከሩ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ሆኖ በ2011 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በከተማ መሬት አስተዳደርና ኢንፎርሜሽን ሲስተም የትምህርት መስክ (Urban Land Use Management and Information System) የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ:: በየትኛውም አጋጣሚ ከሥራ ውጪ መሆን የማይፈልገው ሰርፀሚካኤል፣ ትምህርቱን እየተማረም ሆቴል ከፍቶ ይሠራ ነበር:: በወቅቱ አዋጭ የነበረው ይህ ሥራው ለወደፊት እቅዱና ጉዞው ስኬት ጠቅሞታል::

በሀገሪቱ የግንባታ ሥራ ዘርፍ ላይ ለውጥ የሚፈጥርና ለዘርፉም እድገት የራሱን አስተዋፅዖ የሚያበረክት የግንባታ ተቋም የማቋቋም የረጅም ጊዜ እቅድ የነበረው ሰርፀሚካኤል፣ ይህ እቅዱ እውን የሚሆንበት ጊዜ መድረሱን በማመኑ፣ የትምህርት ዝግጅቱና የሥራ ልምዱ በሚፈቅድለት አግባብ መሠረት፣ በ2012 ዓ.ም በ150ሺ ብር መነሻ ካፒታል ‹‹ጣዝማ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር››ን አቋቋመ::

ድርጅቱን ‹‹ጣዝማ›› ብሎ የመሰየሙ ምክንያትም የድርጅቱ ሥራዎች ተመራጭ፣ ጥልቅና ጠንካራ ሆነው በግንባታው ዘርፍ ለሚታዩ ችግሮች እንደጣዝማ ማር ተፈላጊና ፍቱን መድኃኒት እንዲሆኑ ከመሻትና ከማቀድ የመነጨ እንደሆነ ሰርፀሚካኤል ይገልፃል:: ‹‹የጣዝማ ማር በቀላሉ የሚገኝ አይደለም:: ማሩን ለማግኘት ብዙ መልፋት ይጠይቃል:: ማሩ ለብዙ በሽታዎች ፍቱን መድኃኒትም ነው:: ‹ጣዝማ ኮንስትራክሽን›ም ሥራዎችን በጥረትና በልፋት በማከናወን በዘርፉ ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔ ለመሆን ይተጋል:: ድርጅቱን ‹ጣዝማ› ብለን ስንሰይመው ተግባራችንን እንዲገልፅ ከመፈለግ በመነጨ ስሜት ነው:: ‹ጣዝማ› የሚለው ስም ጥረታችንን ሊያጎላ ይችላል ብለን እናምናለን›› በማለት ድርጅቱ ‹ጣዝማ› ተብሎ የተሰየመበትን ምክንያት ያስረዳል::

አቶ ሰርፀሚካኤል እንደሚገልፀው፣ ‹‹ጣዝማ ኮንስትራክሽን›› የግለሰብ ቤቶችን፣ አብያተ ክርስቲያናትን፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን፣ ኮብልስቶኖችን፣ ድልድዮችንና ሌሎች ግንባታዎችን በታቀደላቸው የግንባታ ጥራት፣ ዋጋና ጊዜ መሠረት ያከናውናል:: ከሥራዎቹ መካከል በቦሌ አራብሳ፣ አያት፣ የካ አባዶ፣ ፒያሳ (እሪ በከንቱ) አካባቢዎች የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የማጠናቀቂያ (ፊኒሽንግ) ሥራዎች ይጠቀሳሉ:: ድርጅቱ በርካታ የግለሰብ ቤቶችን፣ የግል ተቋማትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሕንፃዎችን ሠርቶ አስረክቧል:: ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪም የሚያከናውናቸው የግንባታ ሥራዎች አሉት:: ከግንባታ ሥራ በተጨማሪ የግንባታ ሥራ ለሚሠሩ አካላት ጠጠር፣ ብሎኬት፣ አሸዋና ሌሎች ግብዓቶችንም ያቀርባል::

አሁን በስፋት እየሠራበት ባይሆንም የሲልካሳንድ ማዕድንን (Silica Sand) ለብርጭቆና ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ያቀርባል:: በመርሐቤቴ ወረዳ፣ ዓለም ከተማ ላይ ባለአራት ኮከብ ሆቴል ለመገንባት የሚያስችለውን ፈቃድም አግኝቷል:: ቦታ ተረክቦ ግንባታውን ለመጀመር በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የሚስተዋለው የፀጥታ መደፍረስ እስከሚስተካከል ድረስ ብቻ እየጠበቀ ይገኛል:: ‹‹ጣዝማ ኮንስትራክሽን›› ከግንባታና የግንባታ ግብዓቶችን ከማቅረብ ሥራዎቹ በተጨማሪ የፈጣን መልዕክት አገልግሎት ይሰጣል:: የራሱ ንብረት በሆኑና በተከራያቸው ሞተሮች አማካኝነት መልዕክቶችን ለባለጉዳዮች ያደርሳል::

‹‹ግንባታዎችን የምንሠራው በተመጣጣኝ ዋጋ ነው፤ በሀገራችን ብዙ የሰው ኃይል አለ፤ብዙ ሥራዎችን በመሥራት በረጅም ጊዜ ትርፍ ለማግኘት (ከብዙ ሥራ ብዙ ትርፍ ማግኘት) እንጂ ከአንድ ሥራ ብዙ ትርፍ ለማግኘት አንሠራም:: ብዙ የግንባታ ባለቤቶችና የሥራ ተቋራጮች ግንባታዎች በጊዜያቸው ባለመጠናቀቃቸው ምክንያት አለመግባባት ውስጥ ሲገቡና ሲካሰሱ እናስተውላለን:: እኛ አቅማችንና ሕጉ በሚፈቅድልን አሠራር ብቻ ተወስነን ስለምንሠራ እስካሁን እንዲህ ዓይነት ቅሬታ ቀርቦብን አያውቅም:: ጥሩ የሥራ አፈፃፀም ታሪክ ስላለን ሥራዎችን ለማግኘት አንቸገርም:: ብዙ እውቅናዎችና ምስጋናዎችም ተችረውናል:: በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት በሚያስችል መልክ እየሠራን እንገኛለን›› ይላል::

ይሁን እንጂ ሥራውን ሲጀምር በርካታ መሰናክሎች እንደነበሩ ያስታውሳል:: በቂ ልምድ አለመኖርና የግንባታ ባለቤቶችን ሙሉ እምነት ለማግኘት መቸገር እና የፋይናንስና የግንባታ ዕቃዎች እጥረት ዋናዎቹ ፈተናዎች እንደነበሩ ገልጾ፣ ድርጅቱ የመጀመሪያ ሥራዎቹን በታቀደው ጊዜና ጥራት አጠናቆ ማስረከብ ቢችልም ኪሳራ እንዳስመዘገበ ያስታውሳል:: ‹‹ጣዝማ ኮንስትራክሽን›› በመጀመሪያዎቹ ሥራዎች ኪሳራ ቢያስመዘግብም ሥራዎቹን በተሰጠው ጊዜና በተቀመጠላቸው የጥራት ደረጃ አጠናቅቆ ማስረከቡ በግንባታ ባለቤቶች ዘንድ እምነት አትርፎለት ለቀጣይ ሥራዎቹ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮለታል:: በ150ሺ ብር ሥራውን የጀመረው ‹‹ጣዝማ ኮንስትራክሽን››፣ ዛሬ የበርካታ ሚሊዮን ብሮች ባለቤት መሆን ችሏል::

ሰርፀሚካኤል በወጣትነቱ የገንዘብ ሀብታም መሆን የቻለ ሰው ብቻ አይደለም፤ ገና በወጣትነቱ ልባምነትንም የታደለ ነው:: ልባም ለመባል ያበቃው ሀብት እንዲያፈራ ያስቻለው ትጉህ ሠራተኛነቱ ብቻ ሳይሆን ያለውን ሀብት ለሌሎች የማካፈል ባህርይው ነው::

ድርጅቱ ‹‹ጣዝማ ኮንስትራክሽን›› ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ በርካታ ተግባራትን ያከናውናል:: ‹‹ዞን ስድስት›› የሚባለው የአያት አካባቢ በክረምት ወራት የሰፈሩ መንገድ አስቸጋሪ ሲሆን አሸዋና ጠጠር በማቅረብ የመንገድ ጥርጊያ ሥራ ያከናውናል:: ለአብያተ ክርስቲያናትና ለመስጊዶች ድጋፍ ያደርጋል፤ ይህም ሰፈሩ ሰላማዊና የኅብረተሰቡም መስተጋብር ጠንካራ እንዲሆን አድርጓል::

በበዓላት ወቅት የማዕድ ማጋራት ሥራ ያከናውናል:: ለአብነት ያህል በዘንድሮው ገና በዓል ለክፍለ ከተማው ከ200 ሊትር በላይ ዘይት እንዲሁም ለወረዳው ደግሞ በርካታ በጎችና ዶሮ ገዝቶ አበርክቷል:: የድሃ ድሃ ተብለው ለተለዩ ዜጎች ቤታቸውን ያድሳል::

አቶ ሰርፀሚካኤልም በግለሰብ ደረጃ በሚኖርበት አካባቢ (አያት፣ ዞን ስድስት) ውሃና መብራት እንዲገባ የኮሚቴ አባል በመሆን እንዲሁም የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል:: የአዲስ አበባ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በመሆንም በነፃ እያገለገለ ይገኛል::

‹‹አቅማችን በፈቀደ መጠን ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፤እያደረግንም እንገኛለን፤ወደፊትም እንቀጥላለን:: በእኛ ሀገር ችግር የሆነው አቅም በፈቀደው ልክ አለመረዳዳት ነው:: ሰውንና ተቋማትን መርዳት በፈጣሪ ዘንድ ዋጋ ሊያሰጥና የመንፈስ እርካታ ሊያስገኝ የሚችል በጎ ተግባር ነው:: የጣዝማ አንዱ የስኬት ምክንያትም ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን በመወጣታችን የምናገኘው በረከትና ምርቃት ነው›› በማለት ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣትን አስፈላጊነትና አስደሳችነት ያስረዳል::

ዛሬ በስኬት ጎዳና ላይ የሚገኘው አቶ ሰርፀሚካኤል ጉችማ፣ በአንድ ወቅት ወደ ቤቱ ለመድረስ ለትራንስፖርት የሚሆን ሁለት ብር አጥቶ እንደነበር እንዲህ ያስታውሳል:: ‹‹ከዓለም ከተማ ወደ አዲስ አበባ መጥቼ፣ ከአዲሱ ገበያ እስከ ፒያሳ ድረስ በታክሲ ተጓዝኩ:: ከዚያ በኋላ ምንም ገንዘብ ስላልነበረኝ ከፒያሳ እስከ መገናኛ ድረስ በእግሬ ሄድኩ:: መኖሪያ ሰፈሬ አያት አካባቢ ስለነበር ሁለት ብር ከፍዬ በአውቶቡስ ለመጓዝ ተቸገርኩ:: በወቅቱ የነበረኝ አማራጭ ስልኬ ውስጥ ያለውን ካርድ ሸጬ በአውቶቡስ መጓዝ ስለነበር፣ የአየር ሰዓት (ካርድ) ወደ ሌላ ሰው አስተላልፌ ባገኘሁት ብር በአውቶቡስ ሰፈር ደረስኩ::

አቶ ሰርፀሚካኤል ችግሮችን የምሬትና መሰናክል ምንጭ አድርጎ ከማየት ይልቅ የጥንካሬ መመዘኛና የብቃት መፈተኛ አድርጎ ይመለከታቸዋል። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ‹‹ብዙ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ዋናው ቁም ነገር ለችግሮችና ለፈተናዎች አለመበገርና በፅናት ታግሎ ማሸነፍ ነው:: ችግር ባጋጠመን ጊዜ የበለጠ ጠንካራ በመሆን አሸናፊ መሆን ያስፈልጋል›› ብሎ የሚናገረው።

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ሥራ ላይ ብቻ የመወሰንና ለስምንት ሰዓታት ብቻ የመሥራት ልምድ ሊቀየር ይገባል›› በማለት በአፅንዖት የሚናገረው አቶ ሰርፀሚካኤል፣ ሥራን ለነገ ብሎ አለማሳደሩ፣ ውሳኔ ለመወሰን አለመቸገሩ እና በአንድ ጊዜ ብዙ ሥራዎችን መሥራቱ ለስኬት እንዳበቁት ይገልፃል:: አቶ ሰርፀሚካኤል በርካታ ፈተናዎችን አልፎ ዛሬ ለሚገኝበት ትልቅ ደረጃ መብቃቱ ‹‹የስኬት ጫፍ ላይ ደርሻለሁና ይበቃኛል›› ብሎ እንዲቀመጥ አላደረገውም፤ድርጅቱን አሁን ካለበት ደረጃ የተሻለ የማድረግ ዓላማና ራዕይ አለው።

 አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ጥር 18/2016

Recommended For You