ሲያከብሩን እንከበር!

በዚህ ሳምንት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ስም በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሲታወስ ነበር:: በተለይም ‹‹ሲጂቲኤን›› የተባለው ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሰፋ ያለ ሐተታ ሠርቶ ነበር:: ሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ዜናውን ሠርተውታል:: ይህ ሁሉ ሲሆን የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ግን ያሏት የመገናኛ ብዙኃን የውጭዎችን ያህል እንኳን አልሠሩበትም:: በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በዓለም አቀፉ እንግሊዘኛ ቋንቋ የሠራውን ዜና ግን ማመስገን ያስፈልጋል::

ኬንያ የአንድ ፈጣን መንገድ የተሽከርካሪ መውጫ የኢትዮጵያ መሪ በነበሩት አጼ ኃይለሥላሴ ስም ሰይማለች:: ከዚህ በፊትም በኃይለሥላሴ ስም ጎዳና እንደሰየመች ሲነገር ቆይቷል:: ይህ የፈጣን መንገድ የተሸከርካሪ መውጫ ደግሞ የበለጠ የመታየት እና ልብ የመባል ዕድሉ ሰፊ ነው:: ጽሑፉ ከላይ በትልቁ ስለሚታይ በዚያ መንገድ ያለፈ ሁሉ “HAILE SELASSIE›› የሚለውን የእንግሊዘኛ ጽሑፍ ያነባል ማለት ነው:: ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩ መሆናቸውን ያስባል ማለት ነው:: በዚሁ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ትታወሳለች ማለት ነው:: ሀገር የሚተዋወቀው ደግሞ በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ነው::

አፍሪካውያን ለአፍሪካውያን እንዲህ ሊተሳሰቡ ይገባል:: ኬኒያ ኢትዮጵያን ማክበሯ ያስከብራታል። ሊከባበሩ የሚገባቸው ራሳቸው የአህጉሪቱ ሀገራት ናቸው:: ራሱ ያላከበረውን ማንም ሊያከብርለት አይችልም:: ዳሩ ግን በአፍሪካ ውስጥ ይህ ሲደረግ ብዙም አይስተዋልም:: ይህ በመሆኑ ይመስላል ከአፍሪካ መሪዎች ውስጥ የነፃነት ታጋይ እና የመብት ተሟጋች የሌለ እስከሚመስል ድረስ የአፍሪካ መሪዎችን በሙሉ ጭራቅ አድርጎ የመሳል ትርክት ሥር ሰዷል::

ብዙዎቻችን የአፍሪካ መሪዎችን ከማድነቅ ይልቅ አንድ የምዕራባውያን አምባገነን መሪ ማድነቅ ይቀለናል:: ምዕራባውያን በጻፉልን ታሪክ ስለምንመራ የራሳችንን ሰዎች ጭራቅ አድርገን የእነርሱን ደግሞ ቅዱስ አድርገን በልቦናችን ቀርጸናቸዋል:: እንደ ፓትሪስ ሉሙምባ ያሉ የነፃነት ታጋዮች የተገደሉት በእነ አሜሪካና እንግሊዝ ሴራ በቅኝ ገዥዋ ቤልጂየም ነው::

የቀድሞዋ ዛየር (በዛሬው ስሟ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ) እንደ ፓትሪስ ሉሙምባ ያሉ የነፃነት ታጋዮች ነበሯት:: ዳሩ ግን ለበዝባዦቹ ምዕራባውያን አልተመቻቸውምና አስገደሉት:: እንዲህ አይነት የአፍሪካ መሪዎችን በማስወገድ የዛየርን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ለማጥረግረግ ተመቻቸው! ስለፓትሪስ ሉሙምባ የነፃነት ታጋይነት ከመናገር ይልቅ የዛየር አምባገነን መሪ ስለነበረው ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ ብዙ ዘገባዎችን፣ ብዙ ትንታኔዎችን እና ብዙ ዘጋቢ ፊልሞችን ሠርተዋል::

እነርሱ ለጥቅማቸው ነውና በሚፈልጉት መንገድ አደረጉት እንበል! እኛ አፍሪካውያን ግን የራሳችንን ጀግኖች የማድነቅና የማመስገን ችግር አለብን:: በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ውስጥ ፒያሳ ጊዮርጊስ አካባቢ በፓትሪስ ሉሙምባ ስም የተሰየመ አነስተኛ ሆቴል አለ:: እንዲህ በጥቂቱም ቢሆን መታወሳቸው ይበል የሚያሰኝ ነው:: ከስያሜ ባሻገር ግን አፍሪካ እንደነ ፓትሪስ ሉሙምባ ያሉ መሪዎች የነበሯትና ያሏት መሆኑ መታወስ አለበት::

እርግጥ ነው ብዙ የአፍሪካ መሪዎች አምባገነኖች ናቸው:: ሥልጣን የሚለቁት በተፈጥሮ ኃይል ወይም በመፈንቅለ መንግሥት ነው:: ዳሩ ግን ለዓለም አርዓያ የሚሆን ሥራ የሠሩትንም የሚያመሰግናቸው የለም:: ለምሳሌ፤ የታንዛኒያ መሪ የነበሩት ጁሊየስ ኒሬሬ ሥልጣን የለቀቁት በራሳቸው ፈቃድ ነው:: በ21ኛው ክፍለ ዘመን የዓለም የሥልጣኔ እና የዴሞክራሲ ቁንጮ ናት የምትባለው አሜሪካ ብዙ የምርጫ ማጭበርበር ሲወራባት፤ የአፍሪካዊቷ አገር ታንዛኒያ መሪ ጁሊየስ ኒሬሬ ግን በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ሥልጣን በራሳቸው ፈቃድ ለቀው ለዓለም ምሳሌ ሆነዋል::

ሆኖም ግን አፍሪካ ውስጥ የሚደረግን በጎ ነገር ማመስገን የማይቀናቸው ምዕራባውያን ጁሊየስ ኒሬሬን ያላመሰገኑ ኢዲ አሚን ዳዳን እንዲያመሰግኑ አይጠበቅም:: እነ ዘጋርዲያን ይሠሩት የነበረው ሰፋፊ ሐተታ፤ ኒሬሬ በአገሩ ሕዝብ የማይወደድ፣ ሶሻሊዝምን አሰርጻለሁ ብሎ ሀገሩን ድህነት ላይ እንደጣላት የሚያስመስል ነበር:: እውነታው ግን ኒሬሬን የሀገሩ ሕዝብ ‹‹ሙዋሊሙ›› እያለ ይጠራው እንደነበር ነው:: ሙዋሊሙ ማለት በእስዋሂሊ ‹‹መምህራችን፣ አባታችን›› እንደማለት ነው::

‹‹ዴሞክራሲ በራስህ አገር ዓውድ የምታዳብረው እንጂ እንደ ኮካ ኮላ ከውጭ የምትገዛው አይደለም›› በሚለው ንግግሩ የሚታወቀው ኒሬሬ ግን ሶሻሊዝምን እንደ ወረደ መቀበል ሳይሆን ከታንዛኒያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም ያደረገ በመሆኑ በሀገሩ ሕዝብ ይመሰገናል::

እነ ኔልሰን ማንደላ፣ ኩዋሜ ኒኩሩማህ፣ ጆሞ ኬንያታ፣ ሴዳር ሴንጉር፣ ኬኔት ካውንዳ የመሳሰሉት የአፍሪካ መሪዎች የውጭ ወራሪን በመታገል ለአፍሪካ አገራት ነፃነት ውለታ የዋሉ ናቸው:: እንደነ ሳሞራ ማሼል፣ ሮበርት ሙጋቤ የመሳሰሉት በአገዛዛቸው አምባገነን የነበሩ ቢሆንም ሀገራቸውን ከውጭ ብዝበዛ ነፃ ለማድረግ ግን ሲጋፈጡና ሲታገሉ የነበሩ ናቸው:: እንደነ ቶማስ ሳንካራ የመሳሰሉት ‹‹አፍሪካዊ ቼ ጉቬራ›› የሚል ቅጽል ስም የሚሰጣቸው አብዮተኛ ነበሩ::

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የአፍሪካን ታሪክ የጨለማ ታሪክ፣ የአፍሪካን መሪዎች ጭራቅ መሪዎች ማድረግ የምዕራባውያኑ ዘላቂ ሥራ ነው:: አሳዛኙ እሱ አይደለም:: እነርሱ ገናና ሆነው ለመታየት ሌላው ዓለም የኋላቀር ወካይ መሆን ስላለበት ሥራቸው በሙሉ አፍሪካውያንን በሙሉ ማጠልሸት ነው:: የሚያሳዝነው ግን አፍሪካውያን ራሳቸው ለራሳቸው ክብር የማይሰጡ መሆኑ ነው::

አሁን ወደ ሀገራችን እንመለስ:: ኢትዮጵያ የአፍሪካ ገናና አገር ናት:: ይህ ‹‹ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ›› የሚባል አይደለም፤ ምክንያቱም ራሳቸው የአፍሪካ ሀገራት የሚመሰክሩት ነው:: ለዚህም ነው በመሪዎቻችን ስም ጎዳናዎችን እና የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰይሙት:: ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሀገራት ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ናት:: ይህን የኢትዮጵያን ገናናነት ዓለም ያውቀዋል፤ የአፍሪካ ሀገራትም እነሆ እያከበሩን ነው:: ለመሆኑ ግን እኛ ራሳችንን አክብረናል? ውጭዎች ያከበሩልንን ያህል መሪዎቻችንን አክብረናል? እነርሱ የሰየሙትን ያህል ሰይመናል? የእነርሱን ያህል ውለታቸውን ዘክረነዋል?

ብዙ የሚያስተዛዝቡ ነገሮች አሉ:: መሪዎች በዘመናቸው ዘመኑ የሚፈቅደውን ከፉም ሆነ ደግ ነገር አድርገዋል:: ከመቶ ምናምን ዓመታት በፊት የነበሩ መሪዎችን ዴሞክራሲያዊ አልነበሩም ብሎ መውቀስ በጣም ሲበዛ የዋህነት ነው:: መሠልጠን ማለት ከዘመናት በፊት የነበሩ ነገሮችን በዘመኑ ዓውድ በማየት ዛሬ ላይ ያለውን መሥራት ነው:: ከዚህ በፊት የነበሩ ታሪካዊ ተሳትፎዎቻችንን ማክበር ለዛሬው ዲፕሎማሲ ትልቅ ዋጋ አለው:: ከዚህ በፊት የነበሩ ዓለም አቀፍ ተሳትፎዎቻችን ደግሞ በዘመኑ በነበሩ መሪዎች የተገኙ ናቸው::

የወቅቱን የኢትዮጵያ የብሽሽቅ ፖለቲካ ካስተዋልን ግን አንዱ የደገፈውን ሌላው መቃወም ግዴታ የሆነ ይመስላል:: እንዲህ አይነት ብሽሽቅ የሀገርን የውስጥ ገመና ለውጭ ኃይል ማጋለጥ ይሆናል:: ስለዚህ፤ ዓለም እያከበረን ነውና እኛም ራሳችንን እናክብር! ‹‹ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ›› የሚለው የአፍሪካ ኅብረት መሪ ቃል እርስ በርስ መከባበርን በማስቀደም ሊተገበር ይገባል።

 ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ጥር 18/2016

Recommended For You