ሰሞኑን ጆሯችንም ዓይናችንም ከስካር ተላቋል ብንል ማጋነን ይሆንብኝ ይሆን? እኔ በብዙሃን መገናኛዎች ብቻም ሳይሆን በየህንጻው እና በየጎዳናው የተሰቀሉት የመጠጥ ማስተዋወቂያዎችም መነሳታቸውን ታዝቤያለሁ። እናንተም ይህንኑ አስተውላችሁ ይሆናል።
ይህ መልካም ሆኖ ሳለ ግን «ማነህ ባለተራ?» ማለቱ ሳይበጀን አይቀርም እላለሁ። ምክንያቱም በቆረጡት ቁጥር እንደሚያቆጠቁጥ ዛፍ በመጠጦች እግር የመተካት ፍንጭ የሚታይባቸው ሌሎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። እንደ ደራሽ ሳያጥለቀልቀን በፊትም፤ በጠላ እና ጠጅ ጀምረን ወደ ውስኪ እና ሌሎች የአልኮል መጠጦች እንዴት ደረስን? የሚለውን መመርመርና ትናንትን ማስታወሱ መልካም ነው።
በቀደመው ዘመን ማስታወቂያው ሽክና፣ ቅል አሊያም ጣሳን በእንጨትና ሸንበቆ ላይ በመሻጥ ነበር። በዛሬው ዘመን በየጎዳናው ባሉ «ቢልቦርዶች» ፎቷቸውን፣ በቴሌቪዥን ምስላቸውን፣ በራዲዮ ድምጻቸውን፣ በጋዜጣ ሃተታቸውን፣ በድረ- ገጾችም ግልጋሎታቸውን ማሳየት እንዲሁም የተንቆጠቆጡ ቀለማት ባሏቸው መብራቶች እና በተጌጡ ጽሁፎች ጠጪን ይጣራሉ።
አንዳንድ ምንጭ ጅረት እንደሚፈጥር፣ ጅረትም አጋዥ አግኝቶ ወንዝ እንደሚሆን፣ አልፎ ሂያጅ ሲሆን ከባህር እንደሚቀላቀል አሊያም ያገኘውን እንደሚያጥለቀልቅ ማለት ነው። ማስታወቂያውም እንዲያ ነበር፤ ከቤቶች ደጃፍ ጣሳ ሲሰቀል፤ «ጠላ አለ» የሚል ምልክት ነበረው። በቆይታም ጠላው በፈረንጅ መጠጥ ተተክቶ በየመሸታ ቤቱ ጎላ ባለ መልኩ ጠጪዎችን መሳብ ጀመረ።
አለፍ ሲልም ባገኙት የህዝብ መገናኛ ዘዴዎች ሁሉ «ጠጡልን» ማለታቸውን ተያያዙት። በቆይታም ይኸው ማስታወቂያ ጽንፍ ወጥቶ ምርር አድርጎን ነበር። ከህጻን እስከ አዋቂ ለአልኮል ተገዢ እንዲሆን እና በሂደት ጎጂ የሆነውን መጠጥ እንደ ሞት መድሃኒት እያጋነኑ ማሳየታቸውን ተከትሎ ልጓም እንዲይዙ በህግም ተገደዋል።
አንዳንድ መነሻዎች ግብ ያላቸውን ያህል ሌሎች ደግሞ ዘፈቀዳዊ ይሆናሉ። የእነዚህ አካላት ግብም ገቢ መሰብሰብ እንጂ ከዚያ ባሻገር ያለውን ባለመመልከታቸው፤ የብዙዎች ተስፋ መክኗል፣ ጓዳዎች ተራቁተዋል፣ ትዳሮች ፈርሰዋል፣ ቤተሰቦች ተበትነዋል፣ ዕድሜም አጥሯል።
ነገር ግን የዚህ ምክንያት «ተግ በል!» የተባለው መጠጥ ብቻም አይደለም። ይልቁኑ ቀድሞ በድብቅ ይደረጉ የነበሩ፣ በህዝቡ ዘንድ እንደ ነውር የሚታዩ፣ በህብረተሰቡም ዘንድ እምብዛም ያልተለመዱ ሌሎች አሁን ገሃድ እየወጡ ይገኛሉ። ለዛሬም እንደ ጠላ ደጃፋቸው ላይ ኮባ መሳይ ቅጠሎችን በመስቀል ጀምረው አሁን ቤት ለቤት ማደል ላይ ስለተደረሰው ጫት እናንሳ።
ይህ ቅጠል በፊት በፊት ከአምራቾች እንዲሁም ከአከፋፋዮች በቀር በግልጽ የሚሸጥ አልነበረም። መቃሚያ ቤቶች እንዲሁም የችርቻሮ መሸጫዎችም ቢሆኑ ድብቅ በመሆናቸው ተጠቃሚው እንጂ ሌላው ህብረተሰብ አያውቃቸውም ነበር። ተጠቃሚዎቹም ቢሆኑ ከሰው ፊት የሚጠቀሙበት ድፍረት አልነበራቸውም።
አሁንስ? አሁንማ በተለይ አፍላ ወጣቶች በግልጽ ሲጠቀሙት ነው የሚስተዋለው። እንደ ድሮው በድብቅ መሆኑም ቀርቷል፤ ሻጮች ጉልህ ማስታወቂያ ይለጥፋሉ፣ የንግድ ደረጃ አውጥተውም በግልጽ ይቸበቸባሉ፣ አድራሻቸውንም በየቦታው መስቀል ጀምረዋል፣ የሞተር ተሽከርካሪዎችም ቤት ለቤት ያቀርባሉ፣ መኪኖችም ቢሆኑ ሁለመናቸውን በጫት ማስታወቂያ አሽሞንሙነው በየአደባባዩ መሸጥ ጀምረዋል።
እህሳ፤ በዚህ ሁኔታችን ነገ በመገናኛ ብዙሃን «ለብሩህ ተስፋ፤ ቃሙ¡» መባላችን ይቀራል? አስተውላችሁ ከሆነ በህዝብ መጓጓዣዎች ላይ እኛን አሳፍረው ሲያመነዥጉ እኮ ማስቲካ (ማስቲካም ልክ የማይሆንበት ሁኔታ መኖሩን ልብ ይሏል) የሚያኝኩ ነው የሚመስለው።
የኮሌጅ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችም ህይወታቸው በጫት የቆመ ይመስል ገንዘባቸውን ለዚህ ማዋላቸው ተስፋ አስቆራጭ ነው። ጎዳና አዳሪዎችና የአይምሮ ህሙማኑም ከየቦታው ለቃቅመው ወደ አፋቸው ሲከቱት ቅጠል በል እንስሳ እንጂ ሰው መሆናቸውን ያጠራጥራል።
በአልኮል እና በትንባሆ ምርቶች ላይ ስለጉዳታቸው በግልጽ እንዲጻፍ ህግ ያስገድዳል። በውስጣቸው ስላለው የንጥረ ነገር ልክ፣ በየትኛው እድሜ እንደሚፈቀድ እንዲሁም በምን ያህል መጠን መወሰድ እንዳለበት ያሳያሉ። ጫት ግን ይህንን የሚያሳይበት ዕድል ስለሌለው፤ በፈለጉትና በቻሉት መጠን ተጠቅሞ ግራ መጋባት ብቻ።
እርግጥ ነው፤ የተለያዩ ጥናቶች በዚህ ተክል በርካታ አርሶ አደሮች እየተዳደሩ መሆናቸውን እንዲሁም ሃገር በከፍተኛ መጠን የውጪ ገቢ የምታገኝበት ዘርፍ መሆኑን ያሳያሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የዚህ ቅጠል ተጠቃሚዎች በሂደት ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እንዲሁም በጤናቸው ላይ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑንም ያሳያል። ጉዳትና ጥቅሙ በእኩል ሚዛን ላይ የሚቀመጡ ከመሆኑ አኳያም ይሁን ከትኩረት ማነስ ግልጽ ባይሆንም ግን እገዳ አሊያም በምን መልኩ ይንቀሳቀስ የሚለው አሰራር እስካሁን አልተበጀለትም።
አሁን ባለበት ሁኔታም ካወገዝነው የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያ እግር የተተካ ይመስላል። ይህንን ተከትሎም የታዳጊና ወጣቶች እጣ ፋንታ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ማስላት ቀላል ነው። ጋዜጣ እና መጽሄት ቤት ለቤት መድረስ ሲገባው ጫት የሚቀርብልን ከሆነም ነገ የት እንደምንደርስ ማሰብ ነው።
እናማ፤ «አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ» ዓይነት ስራ «አድበስብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ» ወደሚለው ሌላ ስራ ማሸጋገሩ አይቀርም። ጥቅምና ጉዳታቸው አንድ ተርታ ላይ የሚገኝን ነገር ነጥሎ እያወጡ መፍትሄ አመጣለሁ ማለትም ትርፉ ልፋት ይሆናል። ስለዚህም «ማነህ ባለ ተራ?» ከማለት በፊት እርምጃውን በጥቅል ማድረግ አሊያም ችግሩ ሳያቆጠቁጥ ከስር ከስር መግታቱ መልካም ይሆናል፤ መልዕክታችን ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2011
ብርሃን ፈይሳ