ጤናማ ሕይወት ለእናትነት

የጥር ወር ለኢትዮጵያ ልዩ ወር ነው:: ደስታ እና ፌሽታ የሚበዛበት የአደባባይ በዓል እንዲሁም የሠርግ ወቅት ነው:: ይህ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ክዋኔዎች በስፋት የሚከወንበት ወር በጤናውም ዘርፍ ‹‹የጤናማ እናትነት ወር›› ተብሎ ተሰይሟል:: በዚህ ልዩ ወር ጥንዶች ስለ ጋብቻ ሲያስቡ ጤናማ ቤተሰብ እና ጤናማ ልጅ እንዲኖራቸው ግንዛቤ እንዲያገኙ የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ::

እንደ ሀገር ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረው ‹‹የጤናማ እናትነት ወር›› ዘንድሮም «ፍትሀዊነት፣ ተደራሽነት እና ጥራት ያለውን የቅድመ ወሊድ ክትትል በወቅቱ በማስጀመር ጤናማ እናትነትን እናረጋግጥ» በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ኩነቶች እየተከበረ ይገኛል::

የጤናማ እናትነት ወርን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት በ1990ዎቹ የነበረው የእናቶች ሞት ምጣኔ በአሁኑ ሰዓት መቀነሱን የተናገሩት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የጤናማ እናትነት ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው:: የጤናማ እናትነት እ.አ.አ በ2030 ለማሳካት ከተያዙት የልማት ግቦች አንዱ ሲሆን፤ በዘንድሮው በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ተጎጂ የሆኑ እናቶችን በማሰብ፣ በአካባቢያቸው የጤና አገልግሎትን መልሶ ማቋቋምን ትኩረት አድርጎ እየተከበረ ይገኛል::

ሚኒስትሯ እንደጠቆሙት፤ እርግዝና ተፈጥሯዊና በራሱ ለአንዲት ሴት እና ቤተሰብ አስደሳች የሕይወት ምዕራፍ ቢሆንም ወቅቱን የጠበቀ የሕክምና ድጋፍና ክትትል ካልታከለበት ደስታው ዘላቂ ላይሆን ይችላል።

የቅድመ ወሊድ ክትትልን በጊዜ መጀመርና ቢያንስ ለስምንት ጊዜ በመከታተል፣ በሰለጠነ ባለሙያና በጤና ተቋም መውለድ መከላከል በምንችላቸው ምክንያቶች በሕይወት የምናጣቸው እናቶች እንዲሁም ጨቅላ ሕፃናት ሞትን በከፍተኛ ቁጥር እንዲቀንስ ያግዛል:: የአንድ እናት ሕይወት ህልፈት ለመላው ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ ብሎም በሀገር ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር ሊያ፤ በሀገራችን በ2015 ዓ.ም የቅድመ ወሊድ ክትትልን ከ12 ሳምንት በፊት የጀመሩ እናቶች ምጣኔ 22 በመቶ ብቻ ሲሆን፤ ክትትላቸውን ስምንት ጊዜና ከዚያ በላይ ያደረጉት ደግሞ 15 በመቶ ብቻ መሆናቸው አክለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፤ ጤናማ እናትነት ወር የሚከበረው የእናቶችን ሞት ለመከላከልና ጤንነታቸው እንዲጠበቅ ለማድረግ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በንቃት እንዲሠሩበት ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስቴር የእናቶችን ጤንነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን እንዲተገበር በማድረግ፣ የቅድመ ወሊድ ክትትልን ተደራሽነትን በሁሉም ጤና ተቋማት በማረጋገጥ፣ በጤና ጣቢያዎች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት በማስፋፋት፣ ከጤና ጣቢያዎች ርቀት ላይ ለሚገኙ እናቶች ደግሞ በጤና ተቋማት የእናቶች ማቆያ ቤቶችን በመገንባት ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ዶክተር ደረጄ አብራርተዋል።

በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የማህጸን እና የጽንስ ስፔሻሊስት እንዲሁም የጽንስ ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ታደሰ ጉሬ እንደተናገሩት፣ በእኛ ሀገር ያሉ አብዛኛዎቹ እናቶች የእርግዝና ክትትል ማድረግ የሚጀምሩት ነፍሰጡር መሆናቸውን ካረጋገጡ ከሁለት እና ከዚያ በላይ ባሉት ወራት በኋላ ነው። እናት ጤና ልጅም ደህና እንዲሆኑ ባለትዳሮች የቅድመ እርግዝና፣ በእርግዝና ወቅት እና ድህረ ወሊድ ያሉ ክትትሎችን በተገቢው መንገድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ይመክራሉ::

በጤና ሚኒስቴር የሥርዓተ ምግብ ማስተባበሪያ ሥራ አስፈጻሚ ክፍል ውስጥ የመከላከል ተኮር ዴስክ ኃላፊ የሆኑት ቅድስት ወልደ ሰንበት እንደሚሉት፤ አንዲት እናት ከመጸነሷ በፊት አንድ ወር ቀደም ብላ እንዲሁም እስከ ሦስት ወር ድረስ የፎሊክ አሲድ እንክብል በመውሰድ፤ የሰውነት ክብደት (መጨመርም ሆነ መቀነስ) በማስተካከል እና የተመጣጠነ ምግብ መውሰድ ልጅም እናትም ጤናማ እንዲሆኑ ያግዛል:: ምግብን ማስተካከል፣ ከሁሉም የምግብ ዓይነቶች አመሳጥሮ እና አመጣጥኖ መመገብ በእናቶች ላይ የሚደርሰውን ችግር አስቀድሞ ለመከላከል ያግዛል ይላሉ::

በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ የሕፃናትና የአፍላ ወጣቶች መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር መሠረት ዘላለም በበኩላቸው፤ የጤና ሚኒስቴር የጤና አገልግሎቱን ከማስፋፋት ጎን ለጎን በጤና ኤክስቴንሽኖች አማካኝነት እናቶች ስለ ጤናቸው ሙሉ መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ የተሠራው ሥራ ውጤታማ እንደሆነ ይናገራሉ::

በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች በተከሰቱ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ለእናቶችና ሕፃናት የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች ፈተና የገጠማቸው መሆኑን በመጠቆም፤ በተለይም በትግራይ ክልል በጦርነት እና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ምክንያት መጠነ ሰፊ የአገልግሎት መስተጓጎል እንዳለና ችግሮቹን ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከር በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል:: ከዚህ ጋር ተያይዞም የእናቶች ጤና አገልግሎትን ለማሻሻል የጤናማ እናትነት ወር የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ በትግራይ ክልል መደረጉም አንዱ ማሳያ ነው ይላሉ::

የጤናማ እናትነት ወር ዘመቻ ዓላማ ታሳቢ በማድረግ እናቶች የቅድመ ወሊድ ክትትልን በጊዜ ካለመጀመር ጋር በተያያዘ ያሉትን ችግሮች በተገቢው መንገድ መከላከል እንዲቻል፣ ብሎም በባለሙያ የታገዘ የወሊድ እና የድህረ ወሊድ እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማገዝ የትግበራ አቅጣጫዎች ላይ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን ወስደው መሥራት እንደሚገባቸውም አስቀምጠዋል::

ዶክተር መሠረት እንደሚስረዱት፣ እናት ጤናማ ሳትሆን ስለሀገር ጤናማነት ማሰብ ይከብዳል:: ከዚህ ጋር ተያይዞም ስለ ሀገር እድገትም ሆነ ብልጽግና ማሰብ ከቶ አይቻልም:: የእናቶች ሞት እየቀነሰ ቢመጣም ብዙ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው።

በትግራይ ክልል የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል የመድኃኒትና የሕክምና ግብአቶች ድጋፍ በማድረግ፣ ሥልጠና በመስጠት፣ የሥነ ልቦናና የአእምሮ ጤና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑና በሂደት ላይ ያሉ ሰፊ ሥራዎች መኖራቸውን የተናገሩት ዶክተር መሠረት፤ የጤናማ እናትነት ወር ምክንያት በማድረግ ጤና ሚኒስቴር በርካታ አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር 12ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የሕክምና ግብአቶችን ድጋፍ እንዳደረገም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የስምምነት ሰነድ ከተፈራረመችባቸው ቁልፍ ጉዳዮች መካከል የእናቶች የጤና ጉዳይ አንዱ ነው:: «የእናቶችን ሞት መቀነስ ቁልፍ የሆነ ሀገራዊ አጀንዳ ነው» ያሉት ዶክተር መሠረት፣ በመሆኑም በቅድመ ወሊድ፣ በወሊድ ጊዜና በድህረ ወሊድ ተደራሽ የሚደረጉ መረጃዎችና አገልግሎቶች መኖራቸውን ያስረዳሉ:: አብዛኛውን የሀገራችን ሕዝብ በገጠር የሚኖር እንደመሆኑ በተለይም በጤና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብር በኩል አገልግሎቱ ተደራሽ እየተደረገ እንደሚገኝም አክለዋል።

እንደ ዶክተር መሠረት ገለፃ፤ በገጠሩ የሀገራችን ክፍል እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች መካከል እናቶች ከመውለዳቸው በፊት ጥቂት ጊዜ ሲቀራቸው የሦስት ዓመትና ከዚያ በታች ልጅ ካላቸው ልጆቻቸውን ይዘው በአቅራቢያቸው ባለ ጤና ጣቢያ ቆይተው ክትትልና ድጋፍ ተደርጎላቸው፤ ምግባቸው ተሟልቶላቸው፣ ጤናቸው ተጠብቆላቸው ልጅ ወልደው እንዲሄዱ ይደረጋል:: በተጨማሪም እናቶች ከጤና ኬላ ተነስተው ፣ ጤና ጣቢያ እንዲሁም ሆስፒታል ድረስ በሚያደርጉት የጤና ክትትል የግንኙነት መስመሩ የተመቻቸ እንዲሆን በሙያው የተሻሉ የጤና ባለሙያዎች በአቅራቢያቸው በሚገኝ የጤና ተቋማት ተገኝተው ድጋፍ የሚያደርጉበት የአጥቢያ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ አሠራርም ተፈጥሯል።

በሀገራችን ያሉ ሁሉም ወረዳዎች በአስፋልት ወይም በመንገድ የተገናኙ እና ምቹ እንዳልሆኑ ይታወቃል:: በዚህ ረገድ የመሠረተ ልማት ማስፋፋት ላይ ብዙ መሥራትን ይጠይቃል የሚሉት ዶክተር መሠረት፤ የእናቶች ጤና መሠረታዊ ከሆኑ አገልግሎቶች ጋር በእጅጉ የተገናኘ መሆኑን ነው የሚያብራሩት:: ለአብነት ከመንገድ፣ ከስልክ፣ ከመብራት፣ ከውሃ፣ ከትራንስፖርት እና ከሌሎችም ጋር የተያያዘ ነው:: በተለይም ነፍሰጡር ለሆነች ሴት የመውለጃ ጊዜዋ ሲደርስ በመኪና አልያም የአምቡላንስ አገልግሎት በመስጠት የእናትንም የሕፃናትን ጤና ለማስጠበቅ ብዙ መሥራት እንደሚስፈልግ አጽንኦት ሰጥተውታል።

ዶክተር መሠረት ሲያብራ፤ እናቶችን ከሞት ለመታደገ በሚሠሩ ሥራዎች ከሌሎች ሥራዎች ጋር መጋቢ ወይም አብሮ ከሚሠሩ ፕሮግራሞች ጋር አያይዞ መሥራትን ይጠይቃል:: ዛሬም ቢሆን ቤታቸው የሚለወልዱ እናቶች አልጠፉምና የመረጃ ተደራሽነት ላይ በስፋት መሠራት አለበት። የመረጃ እጦት እናትንም ልጅንም አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ፤ መሠረተ ልማት ያልተስፋፉባቸው አካባቢዎች ላይ አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ከማድረግ አንፃር ሰፊ ሥራዎች ይሠራሉ።

እንደ ጤና ሚኒስቴር ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል የተሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን የሚገልጹት ዶክተር መሠረት፤ በደም መፍሰስ የሚሞቱ እናቶችን ለመታደግ በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ ሥራዎች መሠራቱን ያወሳሉ:: በመረጃ እጦት፣ የጤና ተቋማት ዝግጁ አለመሆን እና በመሠረተ ልማት ችግር በደም መፍሰስ ሕይወታቸው የሚያልፉ እናቶችን ሕይወት ለመታደግ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ70 ሆስፒታሎች የመለስተኛ የደም አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲኖራቸው የግብአት ድጋፍ መደረጉንም ያስረዳሉ::

በአጠቃላይ በእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎት እንደ ሀገር ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎት መሻሻል የታየበት መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር መሠረት ፤ በቀጣይም በሚከናወኑ ተግባራት የሁሉም አጋር አካላት በትብብር እና በቅንጅት መሥራት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ባይ ናቸው::

 እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ጥር 18/2016

Recommended For You