ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የመንግሥትን ጥረት ለመደገፍ ፈጥኖ ሊንቀሳቀስ ይገባል!

በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተ የድርቅ አደጋ እና ግጭቶች የምግብ እህል እጥረት ማጋጠሙ የሚታወስ ነው። መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ”አንድም ዜጋ የሚበላው አጥቶ መሞት የለበትም” በሚል ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ያሉትን አቅሞች አቀናጅቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

በዚህም ችግሩ የክብደቱን ያህል ጥፋት እንዳያስከትል ማድረግ ተችላል፤ በቀጣይም ችግሩ ዜጎችን ዋጋ እንዳያስከፍል በመንግሥት በኩል ዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ከማስተባበር ጀምሮ ሀገራዊ አቅሞችን አቀናጅቶ ችግሩን ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሰሞኑን እንዳስታወቀው፤ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ የድርቅ አደጋ እና ግጭቶች ከጥር እስከ መጋቢት ወር 2016 ዓ.ም ድረስ 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ለሚጠጉ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ የዕለት ደራሽ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

ከዚህ ውስጥ የፌዴራል መንግሥት በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አማካኝነት ከጥር ወር 2016 እስከ የካቲት ወር 2016 ዓ.ም ለሚኖረው የአስቸኳይ ጊዜ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ምላሽ 500 ሺህ ኩንታል ስንዴ በመመደብ የቅድሚያ ቅድሚያ ምላሽ ለሚሹ ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ወገኖች ተደራሽ ያደርጋል ፡፡ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው አጠቃላይ ዜጎች ውስጥ 4 ሚሊዮኑ በአፋር፣ ትግራይና አማራ ክልሎች እንዲሁም በኦሮሚያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ የድርቅ እና የግጭት አደጋ ተጎጂዎች ናቸው። 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚሆኑት በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በጎርፍ፣ ግጭት እና የድርቅ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው ፡፡

ለአስቸኳይ ጊዜ የዕለት ደራሽ ርዳታ የሚያስፈልገው የምግብ መጠን አንድ ሚሊዮን 118 ሺህ 700 ኩንታል ነው፣ ይህም በብር ሲሰላ 9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት ነው፡፡ እስካሁን ካለው ተጨባጭ እውነታ አንጻር ይህንን ሀብት በማፈላለግ ሂደት ውስጥ የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ሚና የጎላ እንደሚሆን ይታመናል ። በርግጥ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ ወር 2016 ዓ.ም ባሉት ስድስት ወራት ከመንግሥትና አጋር አካላት በተገኘ 15 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ለሦስት ተከታታይ ዙሮች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ ተደርጓል። ከዚህም ውስጥ አንድ ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምግብ በዓይነት እና ሁለት ቢሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ የቀረበ ነው ፡፡

ከተሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ውስጥ 77 በመቶ በመንግሥት /11ቢሊዮን ብር አካባቢ/ ፣ 23 በመቶ /4 ቢሊዮን ብር አካባቢ/ በአጋር አካላት የተሸፈነ ነው፤ ከተሠራጨው ሁለት ቢሊዮን ብር ውስጥ 40 በመቶ /2 ቢሊዮን ብር / በመንግሥት 60 በመቶው ደግሞ ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ የተሸፈነ ነው ፡፡ መረጃዎች መንግሥት ለችግሩ የቱን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ በተጨባጭ የሚያሳዩ ፣ ሀገራዊ አቅሞችን አቀናጅቶ በመንቀሳቀስ ችግሩ እንደሀገር ሊያስከትል ይችል የነበረውን የከፋ አደጋ ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ እንደቻለ አመላካች ናቸው።

መንግሥት እስካሁን ባለው የርዳታ አቅርቦት ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን መታደግ ፣ በዚህም ለዜጎች ህይወት ያለውን ትልቅ ከበሬታ በተጨባጭ ማሳየት ፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት በተመሳሳይ መልኩ የተከሰቱ ችግሮች ያስከተሉትን የከፋ አደጋ መቀልበስ ችሏል። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ የሠራቸው የልማት ሥራዎች እንደ መንግሥት ለፈጠረው ጥንካሬ ፣ እንደ ሀገርም ለተገኘው አደጋዎችን የመቋቋም ብሔራዊ አቅም ትልቅ መሰረት ሆነውታል። በቀጣይም ችግሩን ለዘለቄታው ለመቋቋም ለሚደረጉ ጥረቶች ዋነኛ ጉልበት እንደሚሆኑ ይታመናል።

ይህንን የመንግሥት አደጋ የመቋቋም አቅም በማሳደግ ሂደት ውስጥ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ከፍ ያለ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት አስካሁን የሄደባቸው ርቀቶች የሚጠበቀውን ያህል አይደሉም። የአስቸኳይ ጊዜ የዕለት ደራሽ ርዳታ በባህሪው ፈጥኖ መንቀሳቀስን የሚጠይቅ ከመሆኑ አንጻር፤ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ባልተገቡ ጉዳዮች ጊዜ ከመውሰድ መውጣት ፣ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት የሚያስችል ቁርጠኝነት ፈጥሮ ፈጥኖ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።

በአጠቃላይ መንግሥት ”አንድም ዜጋ የሚበላው አጥቶ መሞት የለበትም ” በሚል ችግሩ ሰብአዊ ጥፋት ሳያስከትል ለመከላከል እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ጥረት በሚጠበቀው ደረጃ በዓለም አቀፍ አጋሮች መደገፍ ይኖርበታል። ይህንን የማድረግ የሕግም የሞራልም ግዴታ አለበት!

አዲስ ዘመን ጥር 18/2016

Recommended For You