በውጭ ሀገራት የሚኖረው ሁለተኛ ትውልድ ለሀገሩ ልማት የሚጠበቅበትን ሚና ሊወጣ ይገባል!

ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ካሳየቻቸው እምርታዎች አንዱ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መከተሏ ነው፡፡ አዲስ በሆነው በዚህ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው በክብር ለመመለስ ከመቻሏም በላይ በአሁኑ ወቅት በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መጥተው ታሪካቸውን፤ ወግና ባሕላቸውን እንዲያውቁ መንግሥት ጥሪ አቅርቧል፡፡ ይህንኑ ጥሪ ተቀብለው እየመጡት ላሉትም የአየር ትኬትና የሆቴል መስተንግዶ ቅናሽ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ማበረታቻዎች እየተደረጉ ነው፡፡

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በሦስት ዙሮች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ጥሪ ቀርቧል፡፡ በመንግሥት የተደረገውን ጥሪ ተከትሎም ከታኅሣሥ 20 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ መስከረም ወር 2017 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት በሦስት ዙሮች በርካታ ቁጥር ያላቸው የሁለተኛው ትውልድ አባላት ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ የሁለተኛው ትውልድ ወደ ሀገር ውስጥ መምጣትም በርካታ ትሩፋቶችን ይዞ የሚመጣ ነው፡፡

የመጀመሪያውና ዋነኛው በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እንዲያውቁ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ፤ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ብቸኛዋ ሀገር እና የጥቁር ሕዝቦች ኩራት፤ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች፤ በዩኒስኮ 16 ቅርሶችን ያስመዘገበች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር፤ የአፍሪካ ዋንጫ መሥራች፤ በኮርያ ፤ በኮንጎ እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሰላም በማስከበር አንቱታን ያገኘች ሀገር ነች፡፡ ይህ ታሪክ ደግሞ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የሁለተኛው ትውልድ መኩሪያ ታሪክ ጭምር ነው፡፡

ሁለተኛው ትውልድ በማኅበራዊም ሆነ በሥነ ልቦና ረገድ ጠንካራ ማንነት ሊገነባ የሚችለው ታሪኩን፤ ባሕልና ወጉን መረዳት ሲችል ነው፡፡ ይህ ትውልድ ከኢትዮጵያ ይዞት የሄደ ባሕልና ማኅበራዊ ሕይወት ስለሌለው እና ሙሉ ለሙሉ በውጭ ባሕል ያደገ በመሆኑ እንደ ቀደመው ትውልድ ጠንካራ ስብዕና አይኖረውም፡፡ ስለዚህም ጥሪውን ተከትሎ ሲመጣ የሀገሩን ታሪክ፤ ወግና ባሕል እንዲሁም ማኅበራዊ ሕይወት በቀላሉ በመረዳት ከማንነት ቀውስ ይላቀቃል፤ በራሱና በሀገሩ ይኮራል፡፡ ይህ ዕድልም ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ከወላጆቻቸው ሀገር ጋር ቁርኝት እንዲፈጥሩ፣ መነሻ ሀገራቸውን በአግባቡ እንዲረዱና በማንነታቸው እንዲኮሩ ያስችላቸዋል፡፡

ማንኛውም ትውልድ መነሻ ያስፈልገዋል፡፡ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ውስጥ መምጣት ከሀገራቸው ጋር ቋሚ ግንኙነት እንዲፈጥሩ እና መነሻቸውንም እንዲያውቁ ያደርጋል፡፡ ሁለተኛው ትውልድ ከኢትዮጵያ ይዞት የሄደ ባሕልና ማኅበራዊ ሕይወት ስለሌለው ለጊዜው ለመኩራት የሚሞክረው የሚችለው ባለበት ሀገር ታሪክና ባሕል ነው፡፡ ይህ ደግሞ የራስ ባልሆነ ታሪክ፤ ወግና ባሕል ለመድመቅ መሞከር ግንጥል ጌጥ ከመሆን አያልፍምና አሁን የተሰጠው ዕድል ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በአባት አያቶቹ ታሪክ እንዲኮራ ዕድል ይፈጥርለታል፡፡

በሦስት ዙር ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውም የሁለተኛው ትውልድ አባቶቻቸውና አያቶቻቸው ያቀኗትን ሀገር እንዲያውቁና የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ የወላጆቻቸው ሀገር ክብርና ዝና በአካል ተገኝተው እንዲረዱ ያስችላል፡፡ ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ የጸናች ሀገር ናት፡፡ የትላንቱ ትውልድ በከፈለው መስዋዕትነት የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት አክሊል ሆና ዘለቀች ሀገር ነች፡፡ ይህችን ድንቅ ሀገር በአካል ተገኝቶ ማየትና መረዳት ከዕድልም በላይ ነው፡፡

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መግባት ሀገራቸው ላይ ዕውቀታቸውንና ገንዘባቸውን እንዲያፈሱ ዕድል ይሰጣል፡፡ አዲሱ ትውልድ በሠለጠኑት ዓለማት ያገኘውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት ወደ ሀገሩ በማምጣት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩትን ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታትም ዕድል ይሰጠዋል፡፡

ሁለተኛው ትውልድ ሀገሩን የማወቅ ዕድል ማግኘቱ ትልቅ ዕድል ከመሆኑም ባሻገር ለኢትዮጵያም ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ ትምህርት ለማስፋፋት፤ መንገዶችን ለመሥራትና ተደራሽ ለማድረግ፤ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በአጠቃላይ የተጀመረውን ልማት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡

ስለሆነም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ የተደረገው ጥሪ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ የተገኘውን ዕድል በመጠቀም በሀገሩ ልማት ላይ የማይተካ ሚና መጫወት ይጠበቅበታል!

አዲስ ዘመን ጥር 17/2016

Recommended For You