ጎዳና ኑሮ ወደ ስኬት ጉዞ

ሕይወት ብዙ ፈተና እና ትግል የሚታለፍባት ተግባራዊ ትምህርት ቤት ናት። ብዙዎች ሲወድቁ አንዳንዶች ግን በድል ያልፋሉ። የሕይወት ፈተና ወደ መሬት ሲጥለን በወደቅንበት ቦታ ሆነን ማማረር ማጉረምረም ለመውደቁ ለመደናቀፉ ምክንያት የሆኑትን ሰዎች ሁኔታዎች እና ዕድለቢስነትን እየደጋገሙ ከማብራራት ይልቅ ወደላይ መመልከት ብቸኛው መፍትሔ ስለመሆኑ እሙን ነው።

የእዚች ዓለም ውጣ ውረድና የሕይወት ውስብስብ ፈተና አያልቅም። ሁሌም ቢሆን በሕይወት ውስጥ ክፍተት አለ። ሁልጊዜ ደስተኛ መሆን አይቻልም፤ አንዳንዴ መከፋት፣ ኀዘን ይኖራል፤ አንዳንዴም ማጣት ይከሰታል፣ ሁሉም ነገር አይሰጥም፤ ሁሉም ነገር ደግሞ አይታጣም። በሕይወት ውስጥ ሁሌም ክፍተት አለ፤ ግን ሕይወት ያመጣችውን ፈተና ተጋፍጦ ውጤታማ መሆን ለብርቱዎች የተሰጠ ፀጋ ነው።

የዛሬ የአዲስ ዘመን ወጣቶች አምድ እንግዳችን ወጣት ሽኩር አብደላ ይበላል። በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ ተወልዶ ያደገው ወጣቱ፤ ዛሬ እዚህ ስኬት ላይ ከመድረሱ በፊት እጅግ አስቸጋሪ የሕይወት ፈተና እንዳሳለፈ ይናገራል፡፡ ለረዥም ዓመታት በጎዳና ላይ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች እየተዘዋወረ ኑሮውን ያደረገው ሽኩር፤ ለመረማመጃነት እንጂ ለሰው ልጅ መኖሪያነት ባልተፈጠረ ቦታ ኑሮን መግፋት ከሚገመተው በላይ ስቃዩ ከባድ ስለመሆኑ ይናገራል።

ሕይወት ፊቷን አዙራበት ሳያስበው የጎዳና ተዳዳሪ የሆነው ሽኩር በክረምት ብርድ በበጋ በሐሩር ፀሐይ መሰቃየት የጎዳና ሕይወት የዕለት ተዕለት ዕጣ ፈንታ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በጎዳና ለሚኖሩ ወጣቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት ማለትም ዱርዬ፣ ሌባ ብቻ አድርጎ ማየቱ በከፍተኛ ደረጃ የሥነልቦና ጫና የሚያሳድር እንደሆነ ይገልፃል።

ወጣት ሽኩር እንደሚለው፤ የጎዳና ሕይወትን ለብዙ ዓመታት ሲያሳልፍ ፈታኝና ስቃይ የተሞላበት ሕይወት ስለመግፋቱ በምሬት ያስታውሳል። «እንደ ወንጀለኛ ስለምታይ ፖሊሶች ያባርሩኛል፤ ስታመም የምተኛበት ሕክምና የማገኝበት ሁኔታ አልነበረም፤ ከተገኘ የጉልበት ሥራ እሠራለሁ፣ ሥራ ሲጠፋ ደግሞ የሰው ፊት አያለሁ፤ የሆቴሎች ትራፊ ምግብ እበላለሁ፤ በቆሻሻ ገንዳ እየዞርኩ የሚሸጡ ዕቃዎች እየፈለግኩ እውላለሁ፡፡» የሚለው ወጣቱ የጎዳና ሕይወት እሱንም ሆነ ሌሎች ጓደኞቹን የሲጋራና የጫት ሱሰኛ አድርጓቸው እንደነበር ይናገራል።

ከእዚህ ሕይወት ለመውጣትና ሥራ በመሥራት እራሱን ለመለወጥ የወሰነው ወጣቱ፤ በቀላሉ ምን መሥራት እችላለሁ? ብሎ እራሱን ሲጠይቅ ወደ አዕምሮ የመጣው ብዙ ርቀት ሳይጓዝ በአካባቢው የሚገኘውን የደረቅ ቆሻሻ በመሰብሰብ መሸጥ ነበር። ይህንን ሥራ ከትንሽ ጀምሮ መሥራት ሲጀምር ውጤታማ እንደሚያደርገው በመገንዘቡ ሌሎች ጓደኞቹን በማስተባበር ሽኩርና ጓደኞቹ የተሰኘ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ላይ የተሰማራ ማኅበር መስርቶ ሥራውን እንደቀጠለ ይናገራል።

‹‹ወደዚህ ሥራ ስገባ ብዙዎች ውጤታማ አትሆንም ከማለት ባለፈ ይሳለቁብኝ ነበር›› የሚለው ሽኩር፤ ለራሱ ዛሬ ያለው ሁኔታ ጠንክሮ በመሥራት የሚለወጥ እንደሆነ በማመን ሰዎች ለሚሰጡት አሉታዊ አስተያየት ጆሮ ሳይሰጥ ሥራው ላይ ብቻ በማተኮር ስኬታማ መሆን እንደቻለ ይናገራል። በሀገሪቱ ሕዝብ አብዛኛውን የሰው ቁጥር የሚይዘው ሠርቶ ለመለወጥ አቅምና ጉልበቱ ያለው ወጣቱ ስለመሆኑ የሚናገረው ሽኩር፤ አብዛኛው ወጣት ግን ሥራ ሳይንቅ ሠርቶ እራሱን ለመለወጥ ያለው ፍላጐት የቀዘቀዘ ስለመሆኑ ይናገራል። ለእዚህ ማሳያው የሚለውንም ሲናገር፤ ብዙውን ጊዜ ከእርሱ ጋር ወጣቶች አብረውት እንዲሠሩ ለማድረግ ጥረት ቢያደርግም ሥራውን በመናቅና ስልቹ በመሆን እንደተለዩት ያስረዳል።

የደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ሥራው እነርሱ ከሚያገኙት ገቢ ባለፈ ከተማውን ውብና ፅዱ ለማድረግ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ሽኩር፤ ይህንን ሥራውን እርሱ በሚፈልገው ልክ መሥራት እንዳይችል ብዙ ተግዳሮት እያጋጠመው እንደሆነ ይገልፃል። አሁን ያሉበት በብዙ መልኩ ለሥራው አስቸጋሪ በመሆኑ ማለትም ለዚህ የሚሆን ቦታ አለማግኘታቸው ትልቅ ችግር ሆኖ ከፊታቸው እንደተጋረጠ ይናገራል።

በቀን ደረቅ ቆሻሻ እያቀረቡ የሚከፈላቸው ወጣቶችንና በወር ደሞዛቸውን የሚያገኙ ግለሰቦችን ሳይጨምር እስከ 20 የሚሆኑ ወጣቶችን በቋሚነት በስሩ የሚያስተዳድረው ወጣት ሽኩር፤ አሁን ላይ ደረቅ ቆሻሻን መልሶ አገልግሎት ላይ ለሚያውሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች እንዲሁ ጥሬውን ከማቅረብ ፈጭቶ የተሻለ ገቢ የሚገኝበት ለማድረግ ለመሣሪያ ግዥ የሚሆን ፋይናንስ አለመኖር ሌላኛው የማኅበሩ ተግዳሮት እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ይህ ችግራቸው ቢቀረፍ ከዚህ የበለጠ በመሥራት ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችሉ እራሳቸውም አሁን ካለው በተሻለ ሁኔታ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ይናገራል።

‹‹እዚህ ደረጃ ላይ የደረስነው ከምንም ተነስተን ነው፡፡›› የሚለው ወጣት ሽኩር፤ የጉለሌ ክፍለ ከተማን ጨምሮ የወረዳ ሦስት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ማኅበሩ ሌሎች ተሞክሮ ሊወስዱበት የሚችሉት ዓይነት ማኅበር በመሆኑ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ለውጤታማነታቸው አወንታዊ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ተነግሯል።

ማኅበሩ አሁን ላይ 85 ሺህ ብር የሚሆን የቁጠባ ተቀማጭ ገንዘቡን ሳይጨምር ከ150 ሺህ ብር በላይ ካፒታል እንዳለው የተናገረው ወጣት ሽኩር፤ ከምንም ላይ ተነስተን ይህንን ሀብት ማፍራት መቻል እንደቀላል የሚታይ አይደለም፤ ነገር ግን ከዚህ በላይ ውጤታማ ለመሆንና አሁን ካለው የሠራተኛ ቁጥር በላይ በመቅጠር መስራት እንዲችሉ መንግሥት ከጎናቸው ሊቆም ይገባል ይላል። ‹‹ተነሳሽነት ከተላበስንና ውስጣችንን በማሳመን ያለመታከት ከሠራን ከባዶ ነገር በመነሳት ወደተሻለ ደረጃ መድረስ ይቻላል።›› የሚለው ወጣቱ፤ እርሱ የመጣበት መንገድ ለዚህ ማሳያ ሆኖ ማቅረብ እንደሚቻል ይገልፃል።

እንደወጣቱ ገለፃ፤ በየዓመቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ከሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለያየ የሙያ መስክ ይመረቃሉ፡፡ ነገር ግን የሥራ ዕድሉ አነስተኛ ነው። ሥራ ፈጠራ ደግሞ በትምህርት ብቻ የሚገኝ ነገር አይደለም፡፡ ተቀጣሪ ከመሆን ደግሞ የራስን ሥራ መስራት የተሻለ በመሆኑ ወጣቶች ሥራ ሳይንቁ መንቀሳቀስ አለባቸው።

ወጣት ሃዋ አብደላ ደግሞ ሌላኛዋ የእዚህ ማኅበር መሥራች አባል ናት። እርሷ እንደምትናገረው ወደዚህ ሥራ ከመምጣቷ በፊት እራሷንና ቤተሰቦቿን ለመደገፍ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት ሞክራለች፤ ቆሎ አዙሮ መሸጥ፣ የሰው ቤት በመዞር ልብስ ማጠብ፣ ጉሊት መሸጥ ሃዋ እራሷን ለመለወጥ ጥረት ያደረገችባቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈ ስደትን አማራጭ በማድረግ በውጭ ሀገር ቆይታ አድርጋ እንደመጣች ትናገራለች።

ብዙ ነገር ለመሥራት ብትሞክርም ‹‹ውጤታማ መሆን የቻልኩት በዚህ ሥራ ነው›› የምትለው ሃዋ፤ ጫናው ቢበረታም ከሌላ ሥራ ከሚገኘው ገቢ ይልቅ፤ ይህ ሥራ ካለው ፋይዳ አንፃርም ከመንግሥት አካላት ጀምሮ የማበረታታት እንጂ እንቅፋት የሚኮንበት ሁኔታ ባለመኖሩ አዋጭ እንደሆነ ትገልፃለች።

በዓይን ሲታይ የሚሠራው ሥራ ቆሻሻ ሊመስል ይችላል፡፡ ቀርቦ ላየው ሰው ግን ገንዘብ ነው የምትለው ሃዋ፤ ሁሉም ነገር ወደ ገንዘብ የሚቀየር እንደሆነ ትናገራለች። በሀገር ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን ከመሥራት ጀምሮ ባሕር ተሻግራ የሰው ሀገር በመጓዝ ለሦስት ዓመታት ኑሮን ለማሸነፍ ጥረት ያደረገችው ሃዋ፤ «በዚህ ሁሉ ደስተኛ አልነበርኩም አሁን ግን በዚህ የሥራ ቦታ ስውል ቤቴ ሁለ ትዝ አይለኝም፤ ከተማውን ፅዱ በማድረግ ገቢ እያገኘን መሆኑ ደስተኛ አድርጎኛል»ትላለች።

‹‹ሥራን ባለመፀየፍ ከሠራን ፈተና የሚሆን ነገር ቢኖርም እርሱን አሸንፎ በመውጣት ካለሙበት መድረስ እንደሚቻል አምናለሁ» የምትለው ሃዋ፤ በፍቅር በጋራ መሥራት ደግሞ ይበልጥ ለውጤታማነት አጋዥ መሆኑን ታስረዳለች። ማኅበሩም በጥቂት ጊዜ ትርፋማ እንዲሆን በአባላቱ መካከል ቤተሰባዊ ግንኙነት መኖር በእጅጉ እንደጠቀማቸው ታስረዳለች።

ሃዋ እንደምትናገረው፤ በአካባቢዋ ለምታው ቃቸው ጓደኞች በማኅበራቸው ስር ከሚሠሩ ሥራዎች በአንፃራዊነት ቀላል የሆነውን የፕላስቲክ ክዳን በመፍታት አንድ ኪሎ የሚሆን በመሰብሰብ ገንዘብ እንዲያገኙ ለማድረግ ጥረት ብታደርግም ይህንን እንኳ ለማድረግ ብዙዎቹ ቆሻሻ ነው ብለው ስለሚያስቡ እንደሚፀያፉት ትናገራለች።

ከዚህ በፊት እርሷም ሥራውን እሩቅ ሆና ስታየው የነበራት አመለካከት የንቀት እንደነበር የምትናገረው ወጣት ሃዋ፤ የቆሻሻ ክምችት ብቻ እንደሚመስላት፣ ቀርባ ስትመለከተው ግን ገንዘብ የሚገኝበት ሆኖ እንዳገኘችው፤ ይህም ሥራውን እንድትወደው ምክንያት እንደሆናት ተናግራ፤ ስለዚህ ማንኛውም ወጣት በእሩቁ ውጤታማ አያደርገኝም ብሎ ከመበየን ቀርቦ አይቶ መወሰን እንዳለበት ትመክራለች።

አቶ ሀብታሙ አያሌው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት የፅዳት አስተዳደርና መልሶ መጠቀም ባለሙያ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊነት ወረቀት፣ ካርቶን፣ ሌሎች የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ነው። ይህንን ሥራ ለማከናወን ሥራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ሥራ ማሰማራት ነው።

ባለሙያው እንደሚሉት፤ ወጣቶችን አደራጅተው ይህንን ሥራ እንዲሠሩ ለማድረግ በተለያየ ጊዜ እንደ ወረዳ ባደረጉት ጥረት ሁለት ሦስት ማኅበራት አንደኛ ሥራውን ባለማወቅ፣ ሁለተኛ ደግሞ ስልቹ በመሆንና ለሥራው ባላቸው ዝቅተኛ አመለካከት ምክንያት ሥራውን አቁመው የተበደሩትን ገንዘብ እንኳ መክፈል ሳይችሉ ተበትነዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ሽኩርና ጓደኞቹ የእንደራጅ ጥያቄ ሲቀርብ በሙሉ እምነት ወደ ሥራው እንዲገቡ ለማድረግና መለወጥ እንደሚችሉ ለወራት ስለሥራው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እንደተሠራ ይናገራሉ።

የተለያዩ ተቋማትን በር በማንኳኳት ለዚህ ማኅበር ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥረት ማድረጋቸውን የሚገልፁት አቶ ሀብታሙ፤ ከክፍለ ከተማ፣ ከማኅበራት ማደራጃ ኤጀንሲ፣ ከወረዳ ጨምሮ ድጋፍ አድርገው አሁን የሚሠሩበትን ኮንቴነር እንዲያገኙ ተሠርቷል ይላሉ። አሁን ላይ ግን የሚሠሩት ሥራ ከመስፋቱ የተነሳ ያሉበት ቦታ ለሥራው አመቺ ባለመሆኑ ከዚህ የተሻለ ቦታ እንዲሰጣቸው እየጠየቁ መሆኑን ተናግረዋል። ለእዚህ ችግራቸው መፍትሔ ለመስጠት ከተማ አስተዳደሩ ወይም ክፍለ ከተማው ቢሠራ መልካም ነው ይላሉ።

አሁን በአጠቃላይ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ስር ያሉ በተናጠል የደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ላይ የተሰማሩ ማኅበራት ለሽኩርና ጓደኞቹ ማኅበር እንዲያስረክቡ ለማድረግ እየተሠራ ነው የሚሉት ባለሙያው፤ ይህም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ በፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ስለመጀመሩ ይገልፃሉ።

እንደ አቶ ሀብታሙ ገለፃ፤ በኢትዮጵያ በዓመት እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣቶች ወደ ሥራ ዓለም ይቀላቀላሉ ወይም ሥራ ፈለጊ ይሆናሉ። ለእዚህ ብዙ ቁጥር ላለው ዜጋ በመንግሥት ወይም በግል ተቋማት እና ድርጅቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ባለመቻሉ ደግሞ አብዛኛዎቹ ለሥራ አጥነት ይዳረጋሉ። ይህንን ችግር ለመፍታት ደግሞ ሥራ ጠባቂ ከመሆን ይልቅ ሥራ ፈጣሪ ሆኖ መገኘት የሚጠበቅ ሆኗል ይላሉ።

በሀገሪቱ በርካታ ወጣቶች የሥራ ፈጠራ ባለሙያዎች ቢሆኑም የፈጠራ ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ለማዋል የመሥሪያ ቦታ እጥረት፣ የብድር አቅርቦት አለመመቻቸት፣ የገበያ ትስስር አለመኖር እና የክህሎት ክፍተቶች እንቅፋት ስለሆነባቸው፤ ይህንን ችግር ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You