ኢትዮጵያ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው መሬቷ ቆላማና እርጥበት አጠር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ለድርቅ አደጋ ተጋላጭ ናት። በአንፃሩ ደግሞ ሰፊ የከርሰ ምድርና ገፀ ምድር ውሃ ሀብት ያለው በዚሁ አካባቢ ነው። ይሁንና ያለውን የውሃ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ባለመቻሉና በቂ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራ ባለመከናወኑ ኑሮውን እንስሳት እርባታ ላይ ያደረገው አርብቶአደር ተከታታይነት ባለው ድርቅ የመጋለጥ አደጋ ተጋርጦበታል።
ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግሥት በአካባቢው ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት አቅም ጥቅም ላይ በማዋል የአርብቶአደሩን የአደጋ ስጋት ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየሠራ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት እንዲሁም የመኖ ልማት ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም የእንስሳትን ጤና የሚያስጠብቁ የጤና ማዕከላትን ከመገንባት ባለፈ የጤና ባለሙያዎችን በስፋት በማሠልጠንና ግብዓቶችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች የሚባል ነው።
ከዚህ በተጓዳኝም ከምትዋሰናቸው ጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ዲፕሎማሲ ግንኙነት በማጠናከር የእንስሳት ግብይቱን የማዘመን፤ የግብይት ማዕከላትን የመገንባትና ሕገወጥ ንግድን ለመከላከል የተጀመሩት ሥራዎችም ይበል የሚያሰኙ ናቸው።
በአጠቃላይ የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር የአርብቶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻል እያከናወናቸው ባሉ ተግባራትና ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የምሥራቅ አፍሪካ አርብቶአደሮችን በሚያሳትፈው 19ኛው የአርብቶአደሮች በዓል ዙሪያ ከመስኖና ቆላማ ሚኒስትር ዴኤታ ከዶክተር እንድሪያስ ጌታ ጋር ያደረግነው ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር ከተቋቋመበት ዓላማ አንፃር ምን ያህል ተልዕኮውን አሳክቷል ተብሎ ይታመናል?
ዶክተር እንድሪያስ፡- እንደሚታወቀው የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በ2014 ዓ.ም በአስፈፃሚ አካላት መልሶ ለማደራጀት በወጣው አዋጅ መሠረት ነው በአዲስ መልክ የተደራጀው። ተቋሙ ቀደም ሲል በውሃ፤ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ስር በነበረው የመስኖ ልማት ኮሚሽን የጀመራቸውን ሥራዎች እንደዚሁም ደግሞ በሰላም ሚኒስቴር የአርብቶአደር ዳይሬክቶሬት ስር ይሠሩ የነበሩ ሥራዎችን በማሰባሰብ በአዋጅ የተሰጡንን ኃላፊነቶችን በሚገባ በመተንተን፤ በአዲስ መልክ መዋቅሩን አዘጋጅቶ የሰው ኃይሉን አሟልቶ ወደ ሥራ ገብቷል።
ሚኒስቴሩ በመስኖ ፕሮጀክቶች ልማት እና ቆላማ አካባቢ ምርምርና ልማት በተባሉ ሁለት ዘርፎች ነው የተደራጀው። እነዚህ ዘርፎች በቅንጅት የአርብቶአደሩንና የቆላማ አካባቢውን ልማት ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየሠሩ ይገኛሉ። አብዛኛው ሰፊና ሊታረስ የሚችል መሬት ያለው በቆላማ አካባቢ ትልቅ የከርሰ-ምድርና ገፀ-ምድር የውሃ ሀብት ያለበት በመሆኑ ይህንን የውሃ ሀብት ለመስኖ በማዋል፤ ለላቀ ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅኦ ሊውል በሚችል ሁኔታ ውሃን ማዕከል ያደረገ የልማት ሥራ እንዲሰራ ጥረት አድርጓል።
በዋናነትም ቆላማ አካባቢዎች ያላቸውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን፤ የቆዩ ሀገር በቀል እውቀቶችን ተጨባጭ በማድረግ የአስር ዓመት የልማት እቅድ መነሻ በማድረግ የሦስት ዓመት እቅድ አዘጋጅተን ወደ ሥራ ገብተናል። ይህንን እቅድ መሠረት በማድረግ በቆላማው አካባቢ ሰፋፊ የሆኑ የመስኖ ልማት ጥናትና ዲዛይን ሥራዎች ተሠርተዋል። ከእነዚህም መካከል ገናሌ 58 ሺ ሄክታር መሬት ሊያለማ የሚችል ጥናትና ዲዛይን ተጠቃሽ ነው። እንዲሁም ዋቢ ሸበሌ 27 ሺ ሄክታር ሊያለማ የሚችል ፕሮጀክት ከዚህ በፊት ተጀምሮ በተለያየ ምክንያት ጥቅም ሳይሰጥ ረጅም ጊዜ ቆይቷል። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ውጤት እየታየበት ነው። በአዋሽ ተፋሰስም እንደዚሁ የአዋሽ ወንዝ ላይ የነበረ ሰፊ የእርሻ ልማት ‘ፕሮሶፊስ’ በተባለ መጤ እፅዋት ምክንያት ከጥቀም ውጪ የነበሩትን የመስኖ መሠረተ ልማቶች በመጠገንና በማስተካከል ሰፊ የእርሻ መሬት ወደ ልማት መግባት የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል።
በተጨማሪም አነስተኛና መካከለኛ መስኖ ልማት ሥራዎች ላይ ክልሎችን በማገዝ ጥሩ ውጤቶች እየታየ ነው። በዚህም በሀገራችን የነበረውን የመስኖ መሠረተ ልማት ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል። ከዚህ በፊት እንደሚታወቀው በአብዛኛው በዝናብ ላይ የተመሠረተ ግብርና የምንከተል በመሆኑ ምርታማነታችን ከእጅ ወደአፍ በሚባል ደረጃ ነበር። በአሁኑ ወቅት ይህንን አሠራር ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። በዚህ ረገድ በተለይም የበጋ ስንዴ ልማት ጋር በተያያዘ ሰፊውን መሬት ለማልማት ጥረት ተደርጎ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ተገኝቷል።
በሌላ በኩል በቆላማ አካባቢዎች የሚኖረው ማኅበረሰብ የኑሮ መሠረት በእንስሳት እርባታ ላይ በመሆኑ የእንስሳት ምርታማነት ሊያሻሽሉ በሚችሉ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት ትኩረት ተደርጓል። ክልሎች፤ በየደረጃው ያሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የተጀመሩ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ ነው። በዋናነትም የኢትዮጵያ አርብቶአደሮች ካውንስል እንዲደራጅ በማድረግ፤ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሙሉ የአርብቶአደር የልማት ክፍቶችን በመለየት የእቅዶቻቸው አካል አድርገው ክትትልና ድጋፍ ተደርጎ ሥራዎች እንዲሠሩ ጥረቶች ተደርገዋል።
አዲስ ዘመን፡- የእንስሳት ሀብት ምርታማነት ለማሻሻል ስለተሠሩት ሥራዎች ቢያብራሩልን?
ዶክተር እንድሪያስ፡– የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል የመጀመሪያው ሥራ የእንስሳት ውሃ አቅርቦትን ማሳደግ ነው። ምክንያቱም ትልቁ ችግር ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘም የአርብቶ አደር አካባቢ በተደጋጋሚ ድርቅ ይከሰታል። ድርቅ ደግሞ የመኖ አለኝታ እንዲመናመንና የእንስሳት እልቂት እንዲከሰት ያደርጋል፤ የኅብረተሰቡ አጠቃላይ የኑሮ መሠረት እንዲናጋም ምክንያት ይሆናል። በዚህ ረገድ በእነዚህ ዓመታት በሕይወት ላይ አደጋ እንዳይደርስ መንግሥትና ኅብረተሰቡ ርብርብ አድርገዋል። የአርብቶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ መሠረት ያደረጉ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ በቀጣይም ከችግር መውጣት የሚችልበትን አቅም ማጎልበትን መሠረት ያደረገ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። ስለዚህ የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማሻሻል አንደኛ የውሃ አቅርቦትን ከፍ ማድረግ ይገባል።
ለኅብረተሰቡ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ከማቅረብ አኳያም በርካታ ፕሮጀክቶች ተነድፈው ወደ ሥራ ተገብቷል። በተለይም የከርሰ ምድር ውሃ ባለባቸው አካባቢዎች ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ ተሞክሯል። በተጨማሪም ከዚህ በፊት የነበሩ የውሃ ተቋማትን ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርገዋል። ዝናብ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ደግሞ ዝናብ በኩሬ መልክ አቆይቶ ጥቅም ላይ የሚውልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የወንዞች አቅጣጫን በመቀየስ (በመጥለፍ) የመስኖ ልማት ተሠርቷል። በእርግጥ ከችግሩ ስፋት አኳያ የተሠራው ሥራ ገና ቢሆንም ጥሩና ተስፋ ሰጪ የሆኑ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ማንሳት ይቻላል።
ሌላው የእንስሳት ሀብት ልማት ለማሻሻል የተፈጥሮ ግጦሽ፤ አያያዝና አስተዳደር የመኖ ልማት ሥራ ነው። እነዚህ የግጦሽ ቦታዎች ከአየር ንብረት ተፅዕኖም ሆነ ከእፅዋት ዝርያም ጋር በተያያዘ ምርታማነታቸው እጅግ እየቀነሰ ስለሆነ የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን ከልሎ እንዲለሙ የማድረግ፤ መጤ የዕፅዋት ዝርያን የማስወገድ የመመንጠር ሥራ ሲካሄድ ቆይቷል። ምርታማና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ዝርያዎችን ዘር አቅርቦ ሕዝቡ እንዲያለማ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ መኖን በትርፍ አምጥቶ እንዲሁ እንዲባክን መፍቀድ ሳይሆን ለክፉ ጊዜም ማቆየት የሚችሉበትን ባንኮች በየአካባቢው እንዲገነቡ እየተደረገ ነው። በተጨማሪም ለገበያ አውጥቶ ኅብረተሰቡ ገንዘብ ማግኘት እንዲችል ሥራዎች ተሠርተዋል። በዚህም የጋራ ፍላጎት ያላቸው መኖ አምራች አርብቶአደሮች በአፋር፤ በደቡብ፤ በኦሮሚያ በሱማሌ ክልሎች ተደራጅተው ገቢ የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በተመሳሳይ የተፈጥሮ ግጦሽን የማስተዳደር ሥራውን የማሻሻል፤ የአካባቢ ጥበቃውን የማጠናከርና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የማጎልበት ሥራዎች አበረታች የሚባሉ ናቸው። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ኅብረተሰቡን በየክላስተሩ አደራጅቶ በልማቱ ተሳታፊ የማድረጉ ሥራም ጥሩ ውጤት እየተገኘበት ነው። ለአብነት ያህልም በአፋር፣ በሱማሌ፣ በቦረና፤ በደቡብ ክልሎች መኖ ልማት ላይ የተሰማሩ አርብቶአደሮች ከፍተኛ ውጤት ማግኘት መቻላቸው ተጠቃሽ ነው። ይህም መኖ አለኝታን በማረገገጥ የእንስሳት ሀብት ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ያግዛል።
ከዚህ ባሻገርም የእንስሳት ሀብት ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል ከግብርና ሚኒስቴርም ጋር በቅንጅት እየተሠራ ያለው የእንስሳት ጤና አገልግሎትን የማሻሻል ሥራ ነው። እንግዲህ አርብቶአደሩ የኑሮ መሠረቱ እንስሳት እንደመሆኑ የእንስሳት ጤናን ለማስጠበቅ ክሊኒኮችን በየአካባቢው ተደራሽ እንዲሆኑ፤ የሕክምና ቁሳቁሶች እንዲሟሉ፤ የማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት ሠራተኞችን አሰልጥኖ ከኅብረተሰቡ የኑሮ ዘይቤ ጋር ተንቀሳቀስው የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ በብዙ ቦታዎች ውጤት ተገኝቷል። በተጨማሪም በቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ተቀርፀው እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ።
በተጨማሪም የኅብረተሰቡን የኑሮ መሠረት ማስፋት ያስፈልጋል የሚል እምነት ተይዞ እየተሠራ ያለ ሥራ አለ። እንደሚታወቀው የአርብቶአደሩ ኑሮ በእንስሳት እርባታ ላይ ብቻ የተመሠረተ እንደመሆኑ በተለያዩ አደጋዎች ምክንያት ለከፋ ችግር የሚጋለጡበትን ሁኔታ ለመቀነስ የተለያዩ የገቢ አማራጮችን ማስፋት ያስፈልጋል በሚል የተለያዩ ሥራዎች ተጀምረዋል። በመሆኑም የጋራ ፍላጎት ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማደራጀት በተለያዩ የሥራ መስኮች እንዲሰማሩና ተጨማሪ የገቢ አማራጮችን እንዲያገኙ ለማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። በተጓዳኝ ሰብል፤ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተደራጅተው እንዲሰማሩ ድጋፍ ተድርጎላቸዋል። በዚህም ጥሩ የሚባል ውጤት ተገኝቷል።
ከዚህም ባሻገር እንደየዝንባሌያቸው በአነስተኛ የሥራ መስክ መሰማራት እንዲችሉ የቢዝነስ ፕላን ተዘጋጅቶ፤ የፋይናንስ አቅርቦት ተመቻችቶላቸው፤ በድጋፍ መልክ ተሰጥቶቸው ወደ ሥራ የገቡ አሉ። ለአብነት በእጣንና ሙጫ፣ በእንስሳት ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በወተት ግብይት ሰንሰለትም የተሰማሩትን መጥቀስ ይቻላል። በተለይ ለወጣቶች ተደራጅተው የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ተሞክሯል። ባለፈው ዓመትም ከ50ሺ በላይ የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአነስተኛ የሥራ መስክ እንዲገቡ ተደርጓል። አሁንም አማራጭ የገቢ ምንጮችን ለማስፋት፤ የፋይናንስ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ ለማድረግ ከፍ ባለ ደረጃ እየተሠራ ነው።
ለምሳሌ አርብቶአደሩ እንስሳቱን አሲይዞ ከፋይናንስ ተቋማት ብድር ማግኘት እንዲችል ድጋፎች እየተደረጉ ነው። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ብሔራዊ ባንክ አካታች የፋይናንስ ሥርዓት መመሪያ አውጥቷል። ይህም የአርብቶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል ከፍተኛ አቅም ይሆናል ተብሎ ይታመናል።
በነገራችን ላይ፤ የቆላማና አርብቶ አደር አካባቢ የሀገራችንን 60 በመቶ ያህል የቆዳ ሽፋን የሚይዝ፤ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማኅበረሰብ የሚኖሩበት በመሆኑ መሠረተ ልማቶችን ተደራሽ ማድረግ በእጅጉ ያስፈልጋል። በተለይ የመንገድ፣ የውሃ፣ የትምህርትና ጤና ተቋማት ተደራሽነት ከማረጋገጥ አኳያ የኅብረተሰቡን ኑሮ መሠረት ያደረገ ምቹ ለማድረግ በአርብቶአደር ካውንስል አማካኝነት በጋራ ሥራ እየተሠራ ነው። በአጠቃላይ ግን የአርብቶአደር አካባቢ የልማት ክፍተቶች ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ እንዲሟሉ ለማድረግ በቅንጅት ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንጻር በቆላማና አርብቶአደር አካባቢ ያለውን ሰፊ የውሃ ሀብት ጥቅም ላይ ከማዋል አኳያ የተሠራው ሥራ አመርቂ ነው ማለት ይቻላል?
ዶክተር እንድሪያስ፡- እንደተባለው የከርሰ-ምድርና የገፀ-ምድር ውሃ ሀብት በአካባቢው በስፋት ይገኛል። በተጨማሪም ከደጋማ አካባቢዎች የሚዘንበው ዝናብ ተጠራቅሞ ወደ ቆላማ አካባቢዎች ነው የሚፈስሰው። ይሁንና በእነዚህ አካባቢዎች ሰፊ ሀብት ቢኖርም ሀገሪቱ በሚፈለገው መጠን አልተጠቀመችም። ሰፊ የሆነ ማልማት የሚቻል መሬት አለ። የሕዝቡ የአሰፋፈር ሁኔታ ከጤና
አገልግሎትም፤ ከአየር ንብረትም ጋር በተያያዘ በአብዛኛው ወደ ደጋው አካባቢ የሚያመዝነው። ስለዚህ ቆላማ አካባቢ ያለው ቦታ ሰፊና ያልተነካ ነው። ከደጋማ አካባቢዎች ጋር ሲነፃፀር በጣም ለም የሆነ፤ ብዙ ምርት ማምረት የሚቻልበት፤ ለኢኮኖሚው ትልቅ ተስፋ የሆነ አካባቢ ነው። ስለዚህ ይህንን አካባቢ ማልማት ትልቅ የእድገት አማራጭ አድርጎ መውሰድ ያስፈልጋል። በእነዚህ አካባቢዎች ያለውን የውሃ ሀብት አልምቶ ለመስኖ፣ ለእንስሳት፣ ለሰብልና ለመኖ ልማት ማዋል ይገባል።
በዚህ ረገድ እስካሁን የተሠሩት ጅምር ሥራዎች ናቸው። የጥናትና ዲዛይን ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን ለምሳሌ ገናሌ ትልቅ ወንዝ ነው፤ አቋርጦ የሚሄድበት አካባቢ ሰፊ ነው፤ ይህንን አጥንቶና ኢንቨስት አድርጎ የሀገሪቱን የመስኖ ልማት መገንባት በጣም ከፍተኛ የሆነ አቅም ይጠይቃል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ስለተቋቋመ ብቻ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሠራ አይደለም፤ ሂደትን የሚጠይቅ ነው። አሁንም ቢሆን በርካታ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ሲሆን ብዙዎቹ የሚዘገዩት ደግሞ ከሀገራችን የመፈፀም አቅም ጋር በተያያዘ በሚፈጠር ችግር ነው።
ይህም ሲባል የኮንትራክተሮችና የአማካሪዎች አቅም፤ የአጠቃላይ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪያችን ገና ያላደገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተጀመሩ ሥራዎች በፍጥነት የመጨረስ ችግሮች በመኖራቸው ነው። ሆኖም የነበሩና የተበላሹ መሠረተ ልማቶችን ጠግኖ ወደ ሥራ እንዲገባ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው። ለምሳሌ በጋምቤላ ክልል አልዌሮ ግድብ ወደ 12 ሺ ሄክታር ማልማት የሚችል ቢሆንም እስካሁን አገልግሎት ሳይሰጥ ነው የቆየው። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ይህንን በፕሮጀክት ይዘን ቶሎ መሠረተ ልማቱን ተሟልቶ አካባቢውን ማልማት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
በተመሳሳይ በጎዴ አካባቢ ዋቢ ሸበሌ ወንዝን መሠረት በማድረግ 27ሺ ሄክታር ማልማት የሚችል ሰፊ አቅም አለ። ይህንን ጥቅም ላይ ለማዋል በፕሮጀክት ተደግፎ ወደ ሥራ ተገብቶ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ወደ አምስት ሺ ሄክታር መሬት ወደ ልማት ገብቷል። እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች ውሃን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረጉ ጥረቶች አሉ። በገናሌ ወንዝ ላይ 58ሺ ማልማት የሚችል የጥናትና የዲዛይን ሥራ ኮንትራት ተሰጥቶ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። የአዋሽ ተፋሰስን ተከትሎ ተጨማሪ የመስኖ ልማት ሥራዎች እየተሠሩ ነው። በኦሮሚያም የከርሰ-ምድር ውሃ አውጥቶ ለንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትም፤ ለመስኖም መጠቀም የሚችሉበት ሁኔታ ለመፍጠር የተጀመረ ሥራ አለ።
በሌላ በኩል ተፋሰስን ተከትሎ የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ተጀምሮ ረጅም ርቀት ሳይሄድ ተስተጓጉሎ መቅረቱ ይታወሳል። ይህ በጣም ሰፊ ቦታ ማልማት የሚችል የመስኖ አውታር ወደ ልማት ለማስገባት የአዲስ ኮንትራት ውል ተፈራርመን ሥራ እየተሠራ ነው። ኦሞ ላይ ደግሞ ወደ 200ሺ ሄክታር ማልማት የሚችል አቅም አግኝተናል። በተጨማሪም የቆላማ አካባቢ በክልሎች አቅም የሚሠሩ አነስተኛና መካከለኛ ፕሮጀክቶችን የመደገፍ፤ የማስተባበር ሥራ እየሠራን ነው። በጥቅሉ ውጤት በአንድ ጊዜ አይመጣም፤ ግን ደግሞ ደረጃ በደረጃ ለመለወጥ እየተሠራ ነው። መካድ የማይቻለው ግን የአቅም ውስንነት መኖሩን ነው። እነዚህ ፕሮጀክቶች በመንግሥት በጀት የሚከናወኑ በመሆኑ በአንድ ጊዜ ለሁሉም ፋይናንስ ማድረግ አይቻልም። በደረጃ በደረጃ እየተጠናቀቀ ሲመጣ ብዙ ለውጥ ይታያል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ የመስኖ ፕሮጀክቶች ይገነባሉ ተብለው ሳይገነቡ የቆዩ፤ ሌሎች ደግሞ ተገንብተው አገልግሎት ሲሰጡ አይታዩም፤ ከሚጠበቀው በታች እያለሙ ያሉ እንዳሉ ይታወቃል። ለምሳሌ የርብ ግድብንና አፋር አካባቢ ያሉ ፕሮጀክቶችን መጥቀስ ይቻላል። ይህ የሆነበትን ምክንያት ቢያስረዱን?
ዶክተር እንድሪያስ፡- በእርግጥ የመስኖ ፕሮጀክቶችን የሚመራ ሌላ ዘርፍ ቢኖርም እንደተቋም ግን በተወሰኑት ላይ ምላሽ ልስጥ። እነዚህ የመስኖ ፕሮጀክቶች ሚኒስቴሩ ከተቋቋመ በኋላ አዲስ የተጀመሩ አይደሉም። አዲስ ያስጀመርናቸው በጣም ጥቂት ናቸው፤ ከዚያ በላይ በስፋት የሠራነው ጥናትና ዲዛይን ነው። እንደተባለው ፕሮጀክቶቹ ተጀምረው በተለያዩ ችግሮች የሚቋረጡበት ሁኔታ አለ። ብዙ ጊዜ በቂ ጥናትና ዲዛይንም ሳይደረግ በፖለቲካ ውሳኔ ብቻ ተጀምረው የቆሙ፤ መሠረተ ድንጋይ ተቀምጦላቸው ወደ ሥራ ያልገቡ፤ ብዙ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ የገቡ ናቸው። ለአብነት መገጭን ማንሳት ይቻላል፤ በሌሎች አካባቢ ያሉ ፕሮጀክቶችም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ገብተው ተደነቃቅፈው የቀሩ ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ የእነዚህን ፕሮክቶች ችግር ማወቅ ያስፈልጋል።
በሀገሪቱ ከፍተኛ አቅም አላቸው የተባሉ ባለሙያዎች ቀጥረን ችግሮችን እንዲለዩ የማድረግ፤ አንዳንዶቹም በአዲስ መልክ የዲዛይን ማሻሻያ የሚደረግላቸው ሲሆኑ ሌሎቹ ከመቆየታቸው ጋር ተያይዞ በአዲስ የዋጋና የጊዜ ለውጥ ያስከተሉ በመሆኑ እነዚህ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው። ግን ኅብረተሰቡ እነዚህ ፕሮጀክቶች አልቀው ልማት ካልዋሉ እርካታ ሊኖር አይችልም። ከዚህ አንፃር ለምሳሌ ኦሮሚያንና ሲዳማን የሚያዋስነው ጊዳቦ ግድብ ፕሮጀክት ሳይጠናቀቅ በ2010 ዓ.ም መመረቁ ይታወሳል። ሲመረቅ ግን ውሃ ብቻ ተገደበ እንጂ የመስኖ ልማት ሥራ አልተሠራለትም ነበር። በዚህም ምክንያት ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል። አሁን ግን ያሉት ችግሮች ተለይተው ወደ ሥራ ተገብቷል ፤ የቀሩት ሥራዎች ወደ መጠናቀቁ ነው ያሉት።
አዲስ ዘመን፡- በኦሮሚያ፣ ሱማሌና ሌሎች አካባቢዎች ጭምር በተከታታይ የሚከሰተው ድርቅ የሚያስከትለውን ችግር ለመቋቋም በመስኖ ልማት ላይ መሥራት እንደሚገባ ቢታመንም ባለፈው ዓመት በቦረና፤ በደቡብ ክልልና በሱማሌ ክልሎች ድርቅ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። ዘንድሮ ደግሞ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ድርቅ ተከስቷል። ይህንን ችግር በዘላቂነት መፍታት ለምን አልተቻለም?
ዶክተር እንድሪያስ፡– የድርቁ መንስኤ የአየር ንብረት ለውጥ እንደሆነ ይታወቃል። ይህም ዓለም አቀፍ ክስተት ነው። ይሁንና ከዚህ በፊትም ቢሆን እነዚህ አካባቢዎች እርጥበት አጠርና የሚያገኙትም ዝናብ ዝቅተኛ ነው። እንደተባለው ቀደም ባሉት ጊዜያት የድርቅ ክስተቱ አሁን እንደሚታየው በተደጋጋሚና በአጭር ጊዜ ልዩነት የሚከሰት አልነበረም። አሁን ላይ በየዓመቱ የሚከሰትበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። እነዚህ ቆላማ አካባቢዎች ድርቅ ብቻ ሳይሆን ለጎርፍ ተጋላጭ ናቸው። ባለፈው ዓመት ብቻ በአፋር፣ በሱማሌና በጋምቤላ ክልል የተከሰተው ጎርፍ አስከፊ ጉዳቶችን አምጥቷል።
እንደአጠቃላይ ግን ድርቅም ሆነ ጎርፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መሆናቸው እሙን ነው። በመሆኑም እንደሀገር ይህንን መከላከል የሚቻልበትን አቅም መፍጠር ያስፈልጋል። ይህንን መፍጠር የሚቻለው ደግሞ በዘላቂ ልማት ማምጣት ሲቻል ነው። በዚህ ረገድም የድርቅ አደጋ ስጋቶችን በየጊዜው እየተከታተለ የሚገመግም፤ በርካታ ባለድርሻ አካላትን ያቀፈ፤ ክልሎችንም ጭምር የያዘ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ምክር ቤት በመንግሥት መቋቋሙ ይታወሳል። ምክር ቤቱ ገምግሞ ከሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ነው።
ድርቁ የተፈጥሮ ክስተት ስለሆነ አስቀድሞ ድርቅ ሲከሰት የምናውቅበት አቅም ሊኖር ይገባል። ተከስቶ ከተገኘም ቶሎ ከችግር መውጣት የሚቻልበት የኅብረተሰቡ የኑሮ መሠረት መስፋት አለበት። በዋናነት የውሃ መሠረተ-ልማትን በተለይ መስኖ በስፋት ተደራሽ ማድረግ፤ ሕዝቡ መኖንም ከሁለት ጊዜ በላይ ማምረት የሚችልበት፤ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስፋት የግሉም ዘርፍ ማሳተፍ ይገባል። ለዚህም ሦስትና ከዚያ በላይ ዓመታትን የሚወሰድ የጥናትና ዲዛይን ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።
የአዋጭነት ጥናቶች የሚፈልግ በመሆኑ ጊዜ የሚወስድ ነው። ዘላቂ የልማት ግቦችን አስቀምጠን መሥራት ይጠይቃል። በተጨማሪም ድርቅን በዘላቂነት መከላከል የአርብቶአደሩን አደጋ የመቋቋም አቅም ማሳደግ ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ 2017ዓ.ም የሚጠናቀቅ የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ድርቅና ጎርፍን ታሳቢ አድርጎ ነው የተጀመረው። ይህንን ለማሳካት የአደጋ ስጋት ኮሚሽን፤ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ አገልግሎት ጋር ተናቦ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው። ምክንያቱም ድርቅ ከተከሰተ በኋላ መሮጥ አይጠቅምም፤ የዕለት ደራሽ እርዳታ ማድረግ ብቻ ትርጉም ለውጥ ሊያመጣ አይችልም። በእርግጥ የሰው ሕይወት ለማዳን ጠቃሚ ነው። ግን አስቀድሞ ለመከላከል መዘጋጀት ላይ ነው ትኩረት ማድረግ የሚገባው። በዚህ ረገድ በቅንጅት የተጀመሩ ሥራዎች እየተሠሩ ያሉት ሥራዎች አበረታች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የአርብቶአደሩ ሕይወት የተመሠረተው በአብዛኛው የከብት እርባታ ላይ እንደመሆኑ ከብቶቹን የሚያረባበትን መንገድ ከማዘመን አኳያ ምን እየተሠራ ነው?
ዶክተር እንድሪያስ፡- እንደተባለው የአርብቶአደሩ የኑሮ መሠረት በእንስሳት ላይ የተመሠረተ ነው። እንስሳቱ አብዛኞቹ ለዚህ አካበቢ የሚሆኑ ድርቅን ፤ የመኖና የውሃ እጥረትንም ተቋቁመው መቆየት የሚችሉ እንዲሆኑ ነው የሚፈለገው። አሁን ከሚከሰተው ድርቅ አኳያ ብዙ ጉዳት እየደረሰ እንደሆነ ይታወቃል። በተለይ ቦረና እና ሱማሌ ክልል ተከስቶ የነበረው ድርቅ አብነት አድርጎ ማንሳት ይቻላል። በተደጋጋሚ ድርቅ በሚከሰትባቸው በእነዚህ አካባቢዎች ውሃ መኖሩ ብቻውን ትርጉም የለውም። የመኖ ልማትም በስፋት ማከናወን ካልተቻለ የእንስሳቱ ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም።
በመሆኑም በእነዚህ አካባቢዎች ያለውን የማይቋረጥ ውሃ ተጠቅመን መኖን ብናለማ ኖሮ ድርቁን መቋቋም በቻልን ነበር። ግን ያለንን አቅም አልተጠቀምንበትም። የእንስሳት መኖ አቅርቦትን ለማሻሻል የመኖ ልማትን የማረጋገጥ፤ የተፈጥሮ ግጦሽ ምርታማነትን የማሻሻል፤ የአካባቢ ጥበቃንና የተፋሰስ ልማትን ማጠናከር ሥራዎች ድርቅን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ወሳኝ ናቸው። አስቀድሜ እንዳልኩት ግን ችግሮች ተከስተው ሲገኙ ከዚያ ለመውጣት የሚቻልበት አቅም በማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች መሥራት ያስፈልጋል። እስካሁን በተሠሩት ሥራዎች ጅምር ውጤቶች አሉ። ግን ችግሩ በጣም ሰፊ በመሆኑ ደረጃ በደረጃ መፍታት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- የአርብቶአደሩ ከብቶች በሕገወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት ሀገራት እየተወሰዱ መሆናቸው ይታወቃል። ሚኒስቴሩ ለአርብቶአደሩ ቅርብ እንደመሆኑ በከብት ግብይትና ጤና፣ በኳረንቲን አገልግሎት ማስፋፋት ላይ ምን እየተከናወነ ነው?
ዶክተር እንድሪያስ፡– ከግብይት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች በዋናነት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ከኅብረት ሥራ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው። ሆኖም የካውንስሉ አባልና አርብቶአደሮችን ጉዳይ እንደሚመራ ተቋም አይመለከተንም ማለት አይደለም። ምክንያቱም የቁም እንስሳት ሕገወጥ ግብይት አርብቶአደሩን ሕይወት በቀጥታ የሚነካ መሆኑ ግልፅ ነው። አንዱ ችግር የገበያ ማዕከላት ያለመኖር ሲሆን በተጨማሪም አርብቶአደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸጥበት ሁኔታዎች ምቹ ያለመሆናቸው ነው። በእኛ በኩል የገበያ ማዕከላቱን የማስፋት ጉዳይ ትኩረት የተሰጠው ነው። ጎን ለጎንም የግብይት ሥርዓቱን የማሳለጡ፤ ቀጣናዊ ትስስሩ የበለጠ ሕጋዊ እንዲሆን የሚመለከተው አካል ይሠራል። ግን በእኛ በኩል ጉድለቱ የት ጋር ነው ያለው? የሚለውን ጥያቄ መፍታት ያስፈልጋል። የእሴት ሰንሰለቱ የተጠናከረ ሥርዓት መፍጠር ይገባል። ሕገወጥ ንግዱን ከመከላከል አኳያ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን፤ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጋራ በመሆን እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ።
በእኛም በኩል ከእንስሳት ግብይት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተጀመረ ሥራ አለ። የእንስሳት ግብይቱ ሲከናወን የነበረው መደበኛ ባልሆነ መንገድ ነበር። አርብቶአደሩ ከእንስሳቱ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም በአግባቡ ማግኘት የማይችልበት፤ ለሕገወጥ ንግድ የሚዳረግበት፤ ድንበር አቋርጦ ወደ ውጭ ሀገር የሚሄድበት ሁኔታ ስለነበር በተረጋጋ ሁኔታ የመደራደር አቅም አልነበረውም።
በመሆኑም አርብቶ አደሩ የእንስሳት ውጤቶችን መሸጥና ገቢ ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ ውስን መሆን እንደአንድ ችግር ተለይቷል። ይህንንም ለመፍታት ዘመናዊ የእንስሳት ግብይት ማዕከላት ግንባታ በበርካታ አካባቢዎች ተከናውኗል፤ እየተገነቡም ነው። በእነዚህ ማዕከላት መኖና ውሃ ማግኘት የሚችል በመሆኑ በተረጋጋ ሁኔታ ከተረካቢዎች ተደራድሮ በአጥጋቢ ዋጋ መሸጥ የሚችልበትን ሁኔታ ፈጥሯል።
አዲስ ዘመን፡- ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ በሚከበረው የአርብቶአደሮች ቀን የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን ተሳታፊ ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያትና ስለተደረገው ዝግጅት ቢያብራሩልን?
ዶክተር እንድሪያስ፡– ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ በሚከበረው የአርብቶ አደሮች ቀን በዓል ከወትሮው በተለየ መልኩ የምሥራቅ አፍሪካ አርብቶ አደሮች የሚሳተፉበት ሲሆን በዚህም የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ ነው። ከዚህ ቀደም በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከበር የነበረው የአርብቶአደሮች ቀን ዘንድሮ በተለየ ሁኔታ በሁሉም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት አርብቶአደሮች፤ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ዲፕሎማቶች ባሳተፈ መልኩ ይከበራል። በበዓሉ በዋናነትም የሀገራቱን የቀደመ ታሪካዊ ፤ ባህላዊ ፤ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክሩ አውደ ትዕይንቶች፤ ኤክስፖና የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ።
የአርብቶ አደር በዓል እንደሀገር መከበር መጀመሩ አርብቶአደሩ ሕይወቱን ለማሻሻል ትልቅ አቅም ፈጥሯል። በተለይ ማኅበረሰቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን ጉዳዮች ትኩረት እንዲያገኙ ብሎም በፖሊሲና ስትራቴጂ ማዕቀፍ እንዲደገፉ አወንታዊ ሚና ተጫውቷል። የሚኒስቴሩም መቋቋም የዚሁ ትኩረት አካል ሲሆን፤ ተቋሙ የአርብቶአደሩን ሕይወት ከማሻሻል ባለፈ በአካባቢዎቹ ያሉ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት እምቅ አቅሞች ለሀገር ልማት በተገቢው መልኩ እንዲውሉ ለማድረግ የተሰጠውን ተልዕኮ እየፈፀመ ይገኛል።
በየሁለት ዓመቱ በሚከበረው የአርብቶ አደር ቀን በዓልም በዋናነት የአርብቶ አደሩ ጉዳይ እንደመንግሥት እውቅና እንዲሰጠው፤ ያሉበት ውስብስብ ችግሮች እንዲፈቱና ተግባራዊ የመፍትሔ አቅጣጫዎች እንዲቀመጡ ከማድረግ አኳያ አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል። በዘንድሮውም በዓል በተለይ የአርብቶአደር ሕይወት ድንበርና ወሰን የማያግደው እንደመሆኑ፤ በቀጣናው ያሉ አርብቶአደሮች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ማኅበራዊ ግንኙነት ለላቀ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ታሳቢ ተደርጎ ዝግጅት ተደርጓል።
የአፋር ክልላዊ መንግሥት 19ኛውን የአርብቶአደሮችን ቀን በዓል አዘጋጅ የነበረ ቢሆንም በዓሉ ቀጣናዊ ትስስር በሚፈጥር መልኩ እንዲከበር በመንግሥት አቅጣጫ መሰጠቱን ተከትሎ ዘንድሮ ‹‹አርብቶአደርነት የምሠራቅ አፍሪካ ኅብረ-ቀለም›› በሚል መሪ ሃሳብ ከጥር 17 እስከ ጥር 23 በሚሊኒየም አዳራሽ እንዲካሄድ ተወስኗል።
በእነዚህ ቀናትም የሁሉንም አርብቶአደር አካባቢዎች ባህላዊ፤ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቱፊቶች የሚያንፀባርቁ አውደ ትዕይንቶች፤ ኤክስፖና የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ። ከእነዚህም መካከል የግመል ግልቢያና የግመል ወተት የመቅመስ ትዕይንቶች ተካተዋል። በፓናል ውይይቶቹም በኢጋድ በኩል የተጋበዙና ቁጥራቸው ከ250 የሚልቁ የየሀገራቱ አርብቶ አደር ተወካዮች፤ ዲፕሎማቶችና የግብርና ባለሙያዎች ይሳተፋሉ።
መሪ ሃሳቡ አርብቶአደርነት ሁሉም ሀገራት ሕዝቦች የሚያዋህድና ኅብረቀለም የሚፈጥር መሆኑን ለማሳየት ታሳቢ ተደርጎ ነው የተቀረፀው፤ በበዓሉ የሚታደሙ አርብቶ አደሮች ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን ከማጠናከር ጎን ለጎን የጋራ በሆኑ እንደ ድርቅ፤ የጎርፍ አደጋ እንዲሁም ኮንትሮባንድ ንግድ በመሰሉ ችግሮች ዙሪያ እንዲሁም የልማት አማራጮች ላይ ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሠሩ ምቹ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል።
በመክፈቻው ዕለት ብቻ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ከ500 በላይ አርብቶአደሮች ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆን በየአካባቢያቸው የሚገኙ የተፈጥሮ ፀጋዎች ለታዳሚው የሚያሳዩበት መድረክ ተመቻችቷል። በበዓሉ የአፋር አርብቶአደሮች ከጅቡቲ፤ በሱማሌ ክልል አርብቶአደር ከሱማሌ ላንድና ከሱማሌ፤ በኦሮሚያና ደቡብ ያሉት ከኬንያ፤ ጋምሌ ያሉት ከደቡብ ሱዳን እንዲሁም ቤኒሻንጉል አርብቶአደሮች ጋር የባህል፣ የታሪክ፣ የኢኮኖሚ፣ የገበያ ትስስራቸውን ይበልጥ የሚያጠናክሩበት መንገድ ውይይት ያደርጋሉ።
የአርብቶአደር አካባቢዎችን የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማሳየት ጥረት ይደረጋል። የቀጣናው አርብቶአደሮች ልምድና ተሞክሮቻቸውን በመለዋወጥ የንግድ ትስስራቸውን ይበልጥ እንዲያሳልጡ፤ ብሎም የሚያጋጥሟቸውን የጋራ ችግሮች በጋራ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያገለብቱ ዕድል ይፈጥራል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር እንድሪያስ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥር 16/2016