በአርብቶ አደሮች መኖሪያነት ተጠቃሽ ከሆኑ የዓለም አካባቢዎች የአፍሪካ ቀንድ (ምሥራቅ አፍሪካ) አካባቢ አንዱ ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙት ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሶማሌ ላንድ ጅቡቲና ደቡብ ሱዳን የአያሌ አርብቶ አደሮች መኖሪያ ናቸው።
የአርብቶ አደርነት ሕይወት በአብዛኛው በእንስሳት እርባታ ላይ የተመሠረተ፤ ሁሌም ቢሆን ከውሃና ከግጦሽ ሳር ፍለጋ ጋር በተያያዘ እንቅስቃሴ የሚበዛበት ነው፤ በዚህ የተነሳም በሀገራቱ አርብቶ አደር ማኅበረሰብ መካከል ያሉ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች ከድንበር መስመር ያልፋሉ።
በተለይም የምሥራቅ አፍሪካ አርብቶ አደር ማኅበረሰቦች ከአንድ ቤተሰብ የሚቀዱና፤ ማኅበራዊ ፣ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ መሠረታቸውም አንድ ሊባል የሚችልም ነው፡፡ ዕጣ ፈንታቸው በብዙ መልኩ የተሳሰረ መሆኑም የአንድ ቤተሰብ አባል ያህል ሆነው የሚታዩበትን እውነታ ፈጥሯል። ይህም ሁኔታ አሁናዊ ብቻ ሳይሆን ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው በብዙ መልኩ የተሳሰረ እንዲሆንም አድርጎታል።
የቅኝ ግዛት የሴራ አስተሳሰብ እነዚህ ሕዝቦች በተለያዩ የድንበር መስመሮች ተከፋፍለው እንዲኖሩ ቢያስገድዳቸውም፤ ተጨባጭ የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ግን ከድንበር መስመሮች በዘለለ፤ በወንድማማችነት መንፈስ ዘመናትን መሻገር የቻለና ዛሬም ቤተሰብ ሆነው እንዲኖሩ ያደረጋቸውም ነው።
የአርብቶ አደሮቹ ሁለንተናዊ የሕይወት መስተጋብር፤ ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸውን በጋራ ለመቅረጽ እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ ተደርጎ ቢወሰድም፤ ዓለም እየተመራችበት ባለችው የሴራ ፖለቲካ መንገድ የተነሳ መልካም አጋጣሚውን ወደ ተጨባጭ እውነታ መቀየር ሳይቻል ዘመናት አልፈዋል፤ አካባቢው በዚህ መልካም አጋጣሚ ተጠቃሚ መሆን ሲገባው፣ ከዚህ ይልቅ የግጭት ማዕከል ለመሆን ተገዷል።
በዚህም የአካባቢው አርብቶ አደር ማኅበረሰቦች የብዙ የተፈጥሮ ጸጋዎች ባለቤት ቢሆኑም ፤ ለከፋ ድህነትና ኋላ ቀርነት፤ ከዚህ ለሚመነጭ ስደት ተዳርገዋል፤ አካባቢው በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ በድርቅ በተደጋጋሚ የሚመታ መሆኑም ሌላው የአካባቢው ፈተና ሆኗል፤ ይህ ሁሉ ችግር አርብቶ አደሮቹ ሕይወታቸውን በጠባቂነት እንዲያሳልፉ ፣ አንገት የሚያስደፋ ሕይወት እንዲመሩ ተገደዋል።
የአርብቶ አደሮቹ አሰፋፈርም ሆነ፤ ድንበር ተሻጋሪ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብራቸው ፤ስለጋራ ዕጣ ፈንታቸው ቁጭ ብለው መወያየት እንዲችሉ፤ ለጋራ ፍላጎቶቻቸው እውን መሆን ትኩረት ሰጥተው በጋራ የሚሠሩበትን መንገድ እንዲቀይሱ፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የሚወስኑበትን የተሻለ ዕድል መፍጠር የሚያስችላቸው አልሆነም፡፡
ከዚህ አንጻር ከጥር 17 እስከ ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ‹‹አርብቶ አደርነት የምሥራቅ አፍሪካ ኅብረ- ቀለም›› በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው 19ኛው የአርብቶ አደሮች ቀን በዓል ፋይዳው ከፍተኛ ይሆናል፤ የቀጣናው አርብቶ አደር ማኅበረሰቦች ነገዎቻቸውን ብሩህ ለማድረግ የሚወያዩበትን የተሻለ ዕድል ይፈጥራል።
የአካባቢው ሀገራት አርብቶ አደሮችን ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር ከማጠናከር ጎን ለጎን የጋራ በሆኑ እንደ ድርቅ፤ የጎርፍ አደጋ እንዲሁም ኮንትሮባንድ ንግድ በመሳሰሉ ችግሮች ዙሪያ በጋራ በመምከር መፍትሔ ለማመላከት፤ በልማት አማራጮች ላይ ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠርም ይረዳቸዋል።
ልምድና ተሞክሮቻቸውን በመለዋወጥ የንግድ ትስስራቸውን ይበልጥ እንዲያሳድጉ፣በጋራ ችግሮቻቸው ዙሪያ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያገለብቱ፣ ከሁሉም በላይ ዘላቂ በሆኑ የጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ላይ በመሥራት የተሻሉ ነገዎችን ለመፍጠር ትልቅ አቅም እንደሚሆናቸው ይታመናል።
በተለይም የተፈጥሮ ጸጋዎቻቸውን አቀናጅተው፤ ካሉበት እና ለረጅም ዘመን አብሯቸው ከዘለቀው ድህነትና ኋላቀርነት የሚወጡበትን ስትራቴጂክ እሳቤ በመፍጠር ዘመኑን የሚመጥን ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር መፍጠር የሚያስችላቸውን፤ በዚህም መጪውን ዘመናቸውን ለራሳቸውና ለመጪዎቹ ትውልዶች ብሩህ አድርገው ማስረከብ የሚያስችላቸውን ተግባር ከወዲሁ ማከናወን ለመጀመር ምቹ መደላድልንም ይፈጥርላቸዋል።
ከዚህም ባለፈ የቀጣናውን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችል፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ሰጥቶ በመቀበል መርህ ከአካባቢው ሀገራት ጋር አብሮ ለማደግ በጀመረችው የልማት ስትራቴጂ ዙሪያ ለዋና ባለጉዳዮቹ የጠራ መረጃ ለማስተላለፍ ትልቅ መድረክ ሆኖ ሊያገለግልም ይችላል!
አዲስ ዘመን ጥር 16/2016