አንዳንዴ ነገሮች ከመስመር ባለፉ ጊዜ በእጅጉ ያስተዛዝባሉ፡፡ እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች ደግሞ የሰውን ልክና ማንነት ጭምር የሚጠቁሙ ናቸው። ሁሌም ቢሆን ለአንድ ጉዳይ ልኬታ ሲበጅለት፣ መስመር ሲዘረጋለት አመኔታው ይጎላል፡፡ አንዳንዶች ግን አጋጣሚውን ባገኙ ጊዜ ገደብ ይሉትን አያውቁም። ከንግግር ሳይቆጠቡ፣ የሚያወጡትን ቃል ሳይመርጡ እንዳሻቸው ይሆናሉ፡፡
ይህኔ ጆሮ አግኝተው ሊደመጡ የሚችሉት ለጥቂት አፍታዎች ብቻ ይሆናል፡፡ ከዚህ ያለፈው ጊዜ ግን ከመተዛዘብ አያልፍም፡፡ ሁሌም እነሱን ከሚሰሟቸው መሀል አብዛኞቹ ጉዳያቸውን ፍሬ ነገሬ አይሉትም። እንደውም አንዳንዶቹ የታዘቡትን በውስጣቸው ይዘው ስለ ድርጊት፣ ምግባራቸው ያፍሩላቸዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ስማቸውን እያነሱ መቀለጃ ፣ መዘባበቻ ያደርጓቸዋል፡፡
ሰሞኑን ከአንድ የማህበራዊ ገጽ ላይ አንድን ጉዳይ ስታዘብ ከረምኩ፡፡ እንደው ለቃሉ ያህል ‹‹ትዝብት›› ልበለው እንጂ ለሃሳቡ ከዚህም በላይ መገለጫ ቢኖረው እወድ ነበር፡፡ የትዝብቴ መነሻ በማህበራዊ ገጹ ላይ የተቀመጠው ዝርዝር ሃሳብ ነው፡፡ ይህ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ‹‹ይድረስ ›› የሚለው መልዕክት ለእኔ ከጥቅሙ ጉዳቱ፣ ከግንዛቤው ይልቅ በሀፍረት አፍ ማስያዙ አመዝኖብኛል፡፡
በየአፍታ ልዩነት በየቦታው ተሰንቅሮ የሚገኘውን መልዕክት አሁንም ማንበብ ይዣለሁ፡፡ ያለ አንዳች ከልካይ እርግጠኛ በሆነ ስያሜ ‹‹የጥበብ አገልግሎት›› የሚል ቃል የተቸረው ይህ መልዕክት መሰል ማስታወቂያ በምን አጋጣሚ በግል ቴሌግራሜ ገፄ ላይ እንደደረሰ አላውቅም፡፡ ለእኔም ቤተኛ ከሆነ ግን ከራርሟል፡፡ በየጊዜው አዳዲስ ሃሳቦችን ከምስል ጋር አቀናብሮ ብቅ እያለ ያስደንቀኛል፡፡
ከተጻፉት ዝርዝሮች መሀል ጥቂቱን እያነበብኩ በግርምታ ማስተዋሌን ቀጥያለሁ፡፡ በዚህ ገጽ ላይ ለመቁጠር የሚያዳግቱ ዝርዝር ሃሳቦች ተቀምጠዋል። አንዳንዶቹ የተለመዱና የሚታወቁ ናቸው፡፡ እኔን ያስገረሙኝ ግን ከተለመዱት ሁሉ ይለያሉ፡፡ አንደኛው እንዲህ ሲል ይጀምራል፡፡ ‹‹ለጥበብ ቤተሰቦች ከምንሰጣቸው አገልግሎቶች መሀል እነዚህ ይጠቀሳሉ››፡
ለግርማ ሞገስ፡-ይህ የጥበብ አይነት ግርማ ሞገስ የሌላቸውን በሙሉ ክብር የሚያላብስ፣ ከሌሎች በተለየ እይታን እንዲስቡ የሚያደርግ መስሎ የቀረበ የጥበብ አይነት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ለግርማ ሞገስ ተብሎ የተቀመጠው ሃሳብ አንድ ሰው በሚገኝበት ስፍራ ሁሉ ዓይነ ግቡ ሆኖ፣ ሚዛን ደፍቶ፣ ከሌሎች ሁሉ ልቆና በልጦ እንዲታይ የሚያደርግ ኃይል መሆኑ ነው። እንግዲህ በዚህኛው የጥበብ መንገድ አምኖ የሚጓዝ ቢኖር ‹‹ጥላ ቢስ ›› ይሉት ቃል በአጠገቡ ዝር አይልም ማለት ነው፡፡ በዚሁ እየተገረምኩ ወደ ሌላው ነጥብ ተሻገርኩ፡፡
የታሰረ ሰው እንዲፈታ ለማድረግ
ይህኛው ነጥብ እንደሚጠቁመው የታሰረ ሰውን በጥበብ የማስፈታት ኃይል የመኖሩን ሀቅ ነው፡፡ ማንም ሊናገረው እንደሚችለው የሚታሰር ሰው አስቀድሞ ወደ ቦታው ሲገባ በህግ አግባብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ጥበብ የሚባለው መላ ግን የተቀመጠውን ደንብና መመሪያ ሁሉ ጥሶና በጣጥሶ ታሳሪውን የማስፈታት ኃይል እንዳለው በግልጽ አስቀምጧል፡፡
ጉዳዩ በዚህ ብቻ አይቋጭም ፡፡ የጥበብ ጉዞው ቀጥሎ ራስን ወደ መከላከል ኃይል ይሻገራል፡፡ በዚሁ ማህበራዊ ገጽ በግልጽ እንደተቀመጠው ራስን በጥበብ የመከላከል ኃይል ለጥበበኞቹ ቀላል መሆኑ ሰፍሯል፡፡ ጉዳዩ በግልጽ እንደሚያሳየውም ሃሳቡ እንዲህ በሚል መገለጫ ሰፍሯል፡፡
ጠላት እንዳይጎዳ የሚያደርግ
ጠላት ምን ጊዜም ጠላት ነው፡፡ ራሱን ከመከላከል አልፎ ተቃራኒውን ለመጉዳት ወደ ኋላ የሚል አይደለም፡፡ አስቀድሞ እንደተጠቀሰው ግን የዚህ ጥበብ ኃይል የጠላት ተብየውን ጉልበት ውሃ አድርጎ የተቀናቃኙን ወገን ብርታት የሚረታ ነው፡፡ ይህም ጉልህ ርዕስ ተሰይሞለት በግልጽ ተቀምጧል፡፡
የጥበበኞቹ ራስን የማስተዋወቅ መንገድ በተለመደው አግባብ ቢሆን ኖሮ ይህ ጉዳይ ተነስቶ ሊያስተዛዝበን ባልቻለ ነበር፡፡ እስካሁን የተለመደውና አብዛኛው ሰው የሚረዳው በአንዳንዶች ፍላጎትና ስሜት ላይ የተመሰረተ አሰራር መኖሩን ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ለህመም፣ ለመስተፋቅር፣ ለዓይነጥላ፣ ለመፍትሄ ስራይ፣ ለዛር ውላጅ፣ ለኪንታሮት ህመምና ለመሳሳሉት እየተባሉ የሚዘረዘሩ ሃሳቦች ተለምደዋል፡፡ አሁንም ይህን አምኖ መቀበል ያለመቀበል የግለሰቦች ፍላጎትና ምርጫ ይሆናል ፡፡
ዘንድሮ ግን ጨዋታው ሁሉ ከነበረው ገፅታ በእጥፍ ተለውጦ በአስገራሚ መልኩ ለገበያ ይቀርብ ይዟል፡፡ አንድ በእጅጉ የደነቀኝን ጉዳይ ደግሞ ልምዘዝ፡፡ በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ የሀገር ልጆች የተቀመጠውን የጥበብ ነገር፡፡
የጥበበኞቹ ኃይል ወንዝ ተሻግሮ፣ ባህር ሰንጥቆ ሌሎች ዓለማት ላይ ጭምር መከሰት ጀምሯል፡፡ በተለያዩ ገፆች ላይ በግልጽ እንደሰፈረው ይህ ጥበብ ውጭ ሀገራት ለሚኖሩ ወገኖች ሳይቀር መድረስ ችሏል፡፡
አሁንም የህግና የአሰራርን ጉዳይ መጥቀስ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ “ህገወጥ የሚለውን ጉዳይ እንተወውና ‹‹ህጋዊ›› የሚለውን ነጥብ እናንሳ፡፡ ማንኛውም ሰው ከሀገር ሲወጣና በውጭ ሀገራት ሲኖር በተቀመጠው የህግ አሰራር ላይ ተመስርቶ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
የመኖሪያ ፈቃድም ይሁን የዜግነት መብት ይሏቸው አሰራሮች ሊከወኑ የሚችሉትም ህጉንና ህጉን ብቻ መሰረት አድርገው ነው፡፡ የጥበበኞቹ መላ ግን ይህን እውነታ ከስሩ የመመንገል ኃይል እንዳለው የሚጠቁም ሆኗል፡፡ በውጭ ሀገራት የሚገኙ የሀገር ልጆች የመኖሪያ ፈቃድ ባያገኙ፣ የሥራ ዕድልን ቢያጡ የጥበበኞቹ ጥበብ ተአምር ሰርቶ ሁሉንም በእጃቸው፤ በደጃቸው ያደርሳል።
ወዳጆቼ! በተለያዩ የማህበራት ገጾች ላይ በተደጋጋሚ እየተሰራጨ ያለው መረጃ በአስገራሚነቱ ወደር የለውም፡፡ አሁንም ይሆነኛል፣ ይጠቅመኛል የሚል ጠያቂ ቢኖር ፍላጎቱ የግሉ መሆኑ እንዳለ ይሁንና ሌሎችን ጉዳዮች ላንሳቸው፡፡
በነዚህ ገፆች ላይ እየተዋወቁ ካሉና ‹‹ጥበብ›› ናቸው ከተባሉ ጉዳዮች ውስጥ ብዙዎቹ እንዳስገረሙኝ ቀጥለዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ለህዝብ መስተፋቅር፣ ለመክሳት፣ ለገበያ፣ ለዕቁብ፣ ለሎተሪ፣ ለዱላ፣ ለስልጣን፣ ለቁማር፣ ለክርክር፣ ለድምጽ፣ ጠላትን ለማፍዘዝ በሚል የተቀመጡት የጥበብ አይነቶች፡፡
እነዚህ ጉዳዮች ታአማኒነታቸውና በድፍረት የመውጣታቸው እውነታ አስገራሚ የሚባል ነው። እንደውም አንዳንዴ ‹‹ዓይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛችሁ›› የሚሉ ይመስላሉ፡፡
እንደ እኔ ሃሳብና አስተያየት ግን ማንም ሰው አንድ ጉዳይ በድምቀት ስለተባለና ስለተነገረለት ብቻ የመቀበል አመኔታ ሊኖረው አይገባም፡፡ እርግጥ ነው ሰዎች ሲጨንቃቸው፣ ሲቸገሩና መላ ሲያጡ ከእንዲህ አይነቶቹ አጋጣሚዎች ጋር ሊገናኙ ይችላሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ውሃውን ከእሳቱ፣ ምርቱን ከግርዱ፣ ጥቅሙንም ከጉዳቱ መለየት ግድ ይላል፡፡
አሁን ላይ እየተያዘ ያለው ዘዴ የሰዎችን ደካማ ጎን በመሻት በፍላጎቶቻቸው ላይ አስልቶ መስራት ነው። ይህን ዘዴ አስቀድሞ መጠርጠር ያልቻለ ደግሞ ገንዘቡንና ጊዜውን በግልጽ ከማስረከብ ውጪ ምርጫ አይኖረውም፡፡ ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ተግባራት ሲከወኑ በግልጽ ካለመሆኑ ጋር በርካቶች ኪሳራቸውን የሚያዩት በስተመጨረሻ ይሆናል፡፡ እናም ወዳጆቼ! ‹‹ጠርጥር! ከገንፎም ውስጥ አለ ስንጥር›› የሚለውን አባባል ቀድሞ ማስታወሱ ይበጃል፡፡ አበቃሁ፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 15 ቀን 2016 ዓ.ም