እኛ ሰፈር ብቻ ከሆነ አላውቅም እንጂ መብራት ኃይሎች ፈረቃው ራሱ የተምታታባቸው እየመሰለኝ ነው። አለ አይደለ! የእኛን ሰፈር ያጠፋው ሰውዬ ለምሳ በወጣበት አንድ ሁለት ብሎ ተጫውቶ ሲመለስ የትኛውን ጠፍቶ እንደቆየና የትኛው ሰፈር ተለቅቆ እንደነበር ረስቶት ባለበት የሚተወው። ታድያ ሙሉ ቀን መብራት የሌለው የእኛ ሰፈር ነው ብላችሁ ውሰዱት።
«ብለነው ብለነው የተውነውን ነገር!» አትበሉኝና ሰሞኑን ፈረቃውን ሳስብ ነበር። እንደውም ባይገርማችሁ ከስምንት ሰዓት አንዲት ደቂቃ ዝንፍ ብላ ሌላው ቀርቶ አብሮን የቆየው መብራት ካልጠፋ ይከፋኝ ጀምሯል። መቼም በቴሌቭዥን ዜና አልኖርንምና መብራት ቢጠፋ ግድ የለም፤ ኔትወርክ ይኑርልን እንጂ። አዎን! ቴሌም ውሎውን ፈረቃ የሚባል አመል ካወጡ ተቋማት ጋር እንዳያደርግ መምከር ነው።
ከምን የዋለች ምን… ምን ነበረ ተምራ መጣች የሚባልላት፤ ብቻ እንዳይጋባብን መጠንቀቅ ነው። አሃ! የሆነውስ ሆኖ አሁንም’ኮ ሁሉ ነገር በፈረቃ መስሏል። ፍቅርና ጸቡ ራሱ በፈረቃ ሆኗል። መቼ እለት «ኦሮማራ» ሲባል ሰምታችሁ ወር ሳይዘልቅ በሁለት ሰዎች ተራ ግጭት አገር ካልተያዘ ይባላል። ይኸው የፈረቃ ፍቅር ሄዶ ሄዶ «አማራ ትግራይ» ሆነ፤ አልቆየም በጥቂቶች ጸብ መልሶ ግልብጥ። የፈረቃ ትምህርት የቀረ ጊዜ ፍቅራችንን በፈረቃ አድርገነው ተገኘን።
እውነት ለመናገር ወቅት ሲፈራረቅ እንጂ ፍቅር ሲፈራረቅ ደስ አይልም። ስላችሁ እየተፈራረቁ የሚወዷችሁ ብዙ ሰዎችን ይስጣችሁ! እያፈራረቁ ከሆነ ግን ዋጋ የለውም። አንድ ቀን እየወደዱ ሌላ ቀን መጥላት ከዛ ደግሞ ድጋሚ መውደድ፤ «ኢትዮጵያ» የሚለውን የጥላሁን ገሠሠን ዘፈን ሲሰሙ በፍቅር አልቅሶ ከአፍታ በኋላ «አይ ይህቺ አገር!» ብሎ በቁጣ ማለቃቀስ ከዛ ድጋሚ በቴዲ አፍሮ «ኢትዮጵያ አገሬ» ማለት፤ ይሄም ያው ፈረቃ አይደለ?
በነገራችን ላይ ብልጭ ድርግም የሚል ተፈራራቂ ስሜታችን አምላኩ ይይለትና! አገራችንን የት ባደረስን ነበር። ለምሳሌ ልንገራችሁ፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበረውን የኢትዮጵያንና የጣልያንን ጦርነት አስታውሱ። ያኔ ጣልያን የቋጠረው ቂም ፈንድቶ ኢትዮጵያን የወረረ ጊዜ ነበር። በዛ ጊዜ ንጉሡም አቤቱታቸውን ለዓለም መንግሥታት ሁሉ ቢያሰሙም አድማጭ አጡ። በኋላ እነዚሁ አቤቱታውን ሰምተው እንዳልሰሙ ያለፉ አገራት የራሳቸው ጉዳይ ሲገጥማቸው ጣልቃ ሊገቡ ፈቀዱና እንግሊዝ ደረሰች።
የአገራችን አርበኞች የአምስት ዓመት መስዋዕትነትና ድካም ላይ የእንግሊዝ ጉልበት ሲጨመር ጣልያን ጨርቄን ማቄን ሳይል ወጣ። ይሄኔ እንግሊዝ ሆዬ ማንም አላወቀባት፤ ወዳጅ መስላ አገር ልትይዝ። ታድያ ንጉሡ ነገሩ ገብቷቸው ስለነበርና የወቅቱ ፖለቲከኞችም ስለባነኑ እንግሊዝም «ውለታዬ አለብሽ» ብላ ኢትዮጵያን ባርያ እንዳታደርግ መላ መላ ብለው ሸኝተዋታል።
እና በዛ ሰዓት እነዛ ሰዎች እንደዛሬው ያለ የስሜት ፈረቃ ቢኖርባቸው ከጣልያን ተርፈን የእንግሊዝ ሲሳይ መሆናችን ይቀር መስሏችኋል? በጭራሽ! «እንግሊዝዬ… አንድም ጣልያንን የሸኘነው በአንቺ ምክንያት ነው» ብለን ስንተቃቀፍና ስናቅፋት፤ አጅሪት ምናችንን ታስቀረው ነበር? «ያለሽ መስሎሻል…ተበልተሽ አልቀሻል» እንደተባለለት ጎተራ ሆነን እናርፈው ነበር።
ብቻ ግን ይህን ሁሉ የምዘባርቀው በጣም የስሜት ፈረቃ አለብን የሚለው ላይ ለማስመር ነው። አብርቶ ማሳደር፤ አጥፍቶም ማዋል እንደማይችለው መብራት ኃይል፤ ዘግቶ እንደማያከርም ለቅቆም እንደማይዘልቅ ውሃ ልማት አንዳች የፈረቃ አመል አለብን።
በምን ፍጥነት የወደድነውን እንደምንጠላ፣ በየትኛው ሌሊት አስተሳሰባችን ሁሉ ተቀይሮ እንደሚያድር፣ በየትኛው ቀን ዘር ቆጥረን ለመስደብ እንደወሰንን፣ በየት በኩል ምርቃት ባዘነበ አፋችን እርግማን እንደሚሞላ፤ ከምኔው ያጨበጨብንለት ላይ ምራቅ እንደምንተፋ አይታወቅም። ድንገት ድርግም! ድንገት ጥፍት!
ደግሞ ድንገት ብርት…ፍስስ። በአንዲት ማብሪያና ማጥፊያ እንደሚቆጣጠሩት የእልፍኝ ባልቦላ በአንዲት ጉዳይ ግልብጥ። እንደውም እነ መብራት ኃይል የፈረቃን ጸባይ ከእኛ ሳይሆን ይቀራል የተማሩት!? መድረሻውን የማያውቅ ሰው የሚሄድበትን መንገድ ያልወሰነ ነውና በወሰዱት ሁሉ ይጓዝ የለ? እኛም ልክ እንደዛው «ሆ!» ብሎ መውጣት… ግርርርር ብሎ ተስፋ ማድረግ…ተከታትሎ መፍሰስ። ተዓምር በሚሰማባት አገር ላይ እኛም ተዓምር ሆነን ቁጭ!
ጉዳዩም ሲፈራረቅ እንደዛ ነው። አንድ ሰሞን የአንዲት ሴት በ«ወድጃት ነው» ሰበብ መገደልን ስናውለበልብ ቆይተን፤ ጫፉን ሳንይዝ «የቤተመንግሥቱ ራት ላይ አርቲስቷ ተገኘች» ጉዳያችን ይሆናል። አንዱም መቋጫ ሳያገኝ በሰው አክባሪነትና ጨዋነት የተመዘገብን እኛ «ሰው በድንጋይ ተወገረ…» ዜናን እንቀባበላለን። ይህ አንገት አስደፍቶን ሳያበቃ፤ «ፕሮጀክቶቹ» እንደማለዳ ፀሐይ ርዕስ ጉዳይ ሆነው ይጠብቁናል።
ብቻ ነገሩ ሁሉ ፈረቃ ነው፤ ርዕሰ ጉዳይም ቀን ይጥለው ጀምሯል። ጉዳዮቻችን ከፍ ካለ የአንድ ሳምንት እድሜ አልያም በአንድ እጅ ጣት የማይቆጠሩ ቀናት ቆይታን ብቻ ያደርጋሉ። በፈረቃ አንዱ ሲጣል ሌላው ይነሳል። ማኅበራዊ ገጾቻችን ደግሞ ለታሪክ የሚበቃ እድሜ ይስጣቸውና «አምና በዚህ ጊዜ እንዲህ ስትሉ ነበር» ብለው አልፈው ያስታውሱናል። የእኛ ፈረቃ መች አሁን ጀመረ? ቆይቶብናልኮ!
ይሄ ተፈራራቂነታችን ይበጃል ወይ? አይመስለኝም። የእኛ ስሜት መፈራረቅ «የአሥራ ሦስት ወር ጸጋ» እንደሚባለው፤ በእነዚህ ወራት መካከል እንደሚፈራረቀው የአየር ጸባይ ቱሪስት አይስብ! ፋብሪካ እየተፈራረቁ እንደሚሠሩና እንደሚረካከቡ ባለሙያ ዎች ሥራ አያፋጥን! አያምርብን! አገራችን’ኮ በየቀኑ ሕዝብ የምትቀይር እየመሰለን ነው፤ እንደሸሚዝ።
አንድ ሰሞን ፈካ ያሉ ተስፈኞች፣ በሰሞኑ ማግስት ጠበብ ያሉ «ተስፋ የለንም» ባዮች፣ አንዳንዴ ዘናጭ ለከረባት የሚስማሙ፣ ሌላ ጊዜ ያላማረባቸው ተዛንፈው የተቆለፉ፤ አገሬ ሕዝብ እንደ ሸሚዝ እየቀየረች ይሆን? ግን እሱስ ቢሆን አያልቅባትም? አይሰለቻትም? እኛስ በየቀኑ ማለዳ ስንነሳ እናት አገራችን «አንተ የትኛው ልጄ ነበርክ?» ብላ ለመለየት ስትቸገር፤ «ዛሬስ ስለእኔ ምን ታስብ ይሆን?» ብላ ስትጨናነቅና ስትሳቀቅ፤ «ዛሬ ደግሞ ሊሰድቡኝ ይሆን ሊያሞግሱኝ» ብላ ስታስብ ስናያት አታሳዝነንም?
እንግዲህ ወቅቱም ግራ የገባው ይመስል የሚዘንብበትን ቀን እንኳ መለየት ትቷል መሰለኝ። አልያም እኛ ተኝተን ያለፈን ወቅት ሳይኖር አልቀረም አየሩም ግራ አጋቢ ሆኗል። ዝናቡ ራሱ «ከመጣሁ አይቀርማ ዘንቤ ልሂድ እንጂ» የሚል ነው የሚመስለው። በተረፈ ግን ጊዜውን ጠብቆ የሚሆን ነገር የጠፋ እየመሰለ ነው። እኔ ራሴ አበዛሁ መሰለኝ! ብቻ ፈረቃን ካልወደድንና ከጠላን እኛም ጸባያችን እንደ መብራትና ውሃ ወይም እንደ ወቅት አይፈራረቅ ለማለት ነው። በዛውም! ለባልቦላው ባለቤቶች «ኧረ የእኛ ሰፈር መብራት እየተረሳ ነው መሰለኝ!» በሉልኝ። ሰላም!
አዲስ ዘመን ዛሬግንቦት 25/2011
ሊድያ ተስፋዬ