የፎረሙ መመስረት ዳያስፖራው ለሀገሩ እድገት የአቅሙን እንዲያበረክት የሚረዳው ነው!

በተለያዩ ምክንያቶች ከትውልድ ሀገራቸው ወጥተው በሌላ ሀገር ለመኖር የተገደዱ የአንድ ሀገር ዜጎች /ዳያስፖራዎች ለሀገራቸው እና ለህዝባቸው ካላቸው ፅኑ ፍቅር የተነሳ ስለ ሀገራቸው ብዙ ዋጋ የሚከፍሉበት ሁኔታ የተለመደ ነው። ለሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።

በተለይም በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ዳያስፖራዎች በሚኖሩባቸው ሀገራት ሆነው የሀገሮቻቸውን እና ህዝቦቻቸውን ህይወት ለመቀየር በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ ዋነኛ ተዋንያን ሆነው ማየት የተለመደ ነው፤ በዚህም ውጤታማ በመሆን በሀገራቸው እድገት ውስጥ አሻራቸውን በስፋት ማሳረፍ ችለዋል።

እነዚህ ዳያስፖራዎች ለሀገራቸው በጎ ከማሰብ ጀምሮ በገንዘባቸውና በእውቀታቸው ለሀገራቸው እና ለህዝባቸው ነገዎች የሚቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ፤ ለህዝባቸው ያላቸውን አጋርነት በተጨባጭ በማሳየት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እያተረፉ ያለበት እውነታም ሰፊ ነው። ለዚህ ደግሞ እንደ ህንድና ፊሊፒንስ ያሉ ሀገራት ተጠቃሽ ናቸው።

በኛም ሀገር ያለው እውነታ ቡራቡሬ መልክ ቢኖረውም፤ አብዛኛው የዳያስፖራ ማህበረሰብ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና የሀገር ፍቅር ለሀገሩና ለወገኑ ባለው አቅም ሁሉ የተቻለውን ለማድረግ የሚጥር ነው። በዚህም፤ በተለይም ሀገሪቱ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በምትገኝበት ሁኔታም ሆነ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የነበረው እና ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

ይህም ሆኖ ግን ዳያስፖራው ማህበረሰብ ካለው ሁለንተናዊ አቅም አንጻር፤ እስካሁን ያለው ሀገራዊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳጥፎ በቂ ነው የሚባል አይደለም። በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ ሀገሪቱ ያሏትን ጸጋዎች ለማልማት የሚያስፈልጋትን ሀብት በማፈላለግ ሆነ የሀብት ምንጭ በመሆን በሚጠበቀው መልኩ እየተንቀሳቀሰ አይደለም።

ከዚህም ባለፈ በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ዘመን በሚዋጅ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተሳታፊ በመሆን፤ ሀገር አሻጋሪ የለውጥ አስተሳሰቦች በማህበረሰብ ውስጥ ጉልበት አግኝተው ፤ሀገር እንደ ሀገር ወደተሻለ የፖለቲካ ምእራፍ የምትሸጋገርበትን እድሎች በመፍጠርም ሆነ የተፈጠሩትን በማጎልበት ሂደት ውስጥ ውስንነቶች ይታዩበታል።

በማህበራዊ ሆነ በቴክኖሎጂ ዘርፎችም ቢሆን፤ ዳያስፖራው ሀገርን ሊጠቅም የሚችል የዳበረ እውቀትና ክህሎት ባለቤት ቢሆንም፤ በተለያዩ ምክንያቶች ይህንን አቅም በተደራጀ መንገድ ለሀገር ልማት፤ ለዜጎች ማህበራዊ እድገት በመጠቀም ሂደት በተመሳሳይ መልኩ ሰፊ ክፍተት የሚታይበት ነው።

በአጠቃላይ እስካሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ ዲያስፖራው በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ውስጥ በተደራጀ መንገድ የሚጠበቀውን ያህል አዎንታዊ ተሳትፎ እያደረገ አይደለም፤የዚህን ኃይል አቅም በአግባቡ ለመጠቀም ሰፊ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል።

በተለይም ዳያስፖራው ማህበረሰብ ስለሀገሩና በሀገሩ እየተካሄዱ ስላሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች ተገቢም መረጃ እንዲያገኝ በማድረግ፤ ከውዥንብሮች ነጻ ሆኖ የለውጡ አካል እንዲሆን በስፋት መንቀሳቀስ ፤ ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት መፍጠር ያስፈልጋል።

ዳያስፖራው ማህበረሰብ በራሱ ተነሳሽነት በየዘርፉ ያለውን አቅም አቀናጅቶ ፣ለሀገሩና ለወገኑ አቅም የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠርም አስፈላጊ ነው። ከዚህ አንጻር ሰሞኑን ዳያስፖራው ባለው አቅም ስለ ሀገሩ የሚቻለውን ሁሉ እንዲያበረክት፤ የዳያስፖራ ዲፕሎማሲ አማካሪ ፎረም መመስረቱ እንደ ትልቅ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ፎረሙ ዳያስፖራው ማህበረሰብ ሀገራችን አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያጋጠሟት ያሉትን ጫናዎች ለመቋቋምም ሆነ በቀጣይ ሊያጋጥሟት የሚችሉትን ተግዳሮቶች ሰብራ ለመውጣት ተጨማሪ አቅም ሊሆን የሚችልበትን እድል የሚፈጥርበት እንደሆነም ይታመናል።

በተለይም ሀገር ብሄራዊ ጥቅሞችን መሰረት ባደረጉ ንቅናቄዎች ውስጥ የዳያስፖራውን ሁለንተናዊ አቅምና ተሳትፎ በምትፈልግበት አሁናዊ ሁኔታ ፎረሙ መመስረቱ፤ ዲያስፖራው ማህበረሰብ በዘርፉ ያለውን አቅም ለሀገሩ ብሩህ ነገዎች በተሻለ መንገድ እንዲያውል ይረዳዋል።

መንግሥት የሁላችንም ሀገር በሆነችው በኢትዮጵያ ጉዳይ በመነጋገርና በመግባባት ለሁለንተናዊ ዕድገቷ አብረን እንስራ፤ ለትውልዶች አመቺ የሆነች ሀገር እንገንባ በሚል ተደጋጋሚ ጥሪዎችን እያደረገች ባለበት ወቅት የፎረሙ መመስረት፤ዲያስፖራው ለሀገሪቱ እድገት የሚኖረውን ስትራቴጂካዊ አስተዋፅኦ የሚያሳድግ ነው፤የራሱን ታሪክ እንዲሰራም መልካም እድል የሚፈጥርለት ነው።

አዲስ ዘመን ጥር 15/2016

Recommended For You