የብረት መቁረጫ ማሽን የሠሩት እንስቶች

በሀገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የመተካት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ሀገር በቀል እውቀትን በመጠቀም በራስ አቅም ለሚሠሩ የፈጠራ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷል። በዚህም ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ቴክኖሎጂዎቹን ለማስመጣት ይወጣ የነበረውን ውጪ የሚያስቀሩ እና ጊዜ የሚቆጠቡ የፈጠራ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።

አሁን በተለይ በሀገራችን ይሠራሉ ተብለው የማይታሰቡት ቴክኖሎጂዎች ጭምር በሀገር ውስጥ ማምረት እየተቻለ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነውን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገባውን የብረት መቁረጫ ማሽን በሀገር ውስጥ መሥራት ተችሏል። ይህም የተሰራው በሀገሪቱ የፈጠራ ባለሙያዎች ነው። ይህ ማሽን የተሠራው በመካኒካል ኢንጂነሮቹ ቤቴል ተስፋሁን እና ኢንጂነር ጥሩ ዓለም ተሾመ ነው። እነ ኢንጂነር ቤቴል ‹‹ሲኤምሲ ፕላዝማ ማሽን›› በመባል የሚታወቀውን ይህን ማሽን ለመሥራት መነሻ የሆናቸው ሁለቱም የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ምሩቃን መሆናቸው፣ ከማሽኖች ጋር በቅርበት የመገናኘት ዕድሉ ስላላቸው እንዲሁም ፍላጎቱ ስላደረባቸው መሆኑን ይናገራሉ።

ይህን ማሽን ለመሥራት አንዱ መነሻ ሃሳብ የሆናቸው የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በመባል ይጠራ የነበረው ድርጅት በባሕርዳር ይሠራ በነበረበት ወቅት ፕሮጀክቶች ለመሥራት በገቡበት ወቅት ያጋጠሟቸው ችግሮች መሆናቸውን ኢንጂነር ቤቴል ታስታውሳለች። እሷ እንዳለችው፤ በማዕከሉ በተለያዩ የብረት ሥራዎች ላይ የተሰማሩ አብዛኞቹ ባለሙያዎች የብረት መቁረጫ ማሽን ቢፈልጉም፣ ለብረት መቁረጫ የሚውሉ ማሽኖችን ማግኘት ግን አልቻሉም። ለዚህ ችግር መፍትሔ መፈለግ የጀመሩት እነ ኢንጂነር ቤቴል በኮምፒዩተር በመታገዝ ብረትን መቁረጥ የሚችል የብረት መቁረጫ ማሽን የመሥራት ሃሳብ በውስጣቸው ይጠነሰሳል።

በወቅቱ በኮምፒዩተር እየታገዙ የሚሠሩት ስ ሪዲ (3ዲ) ፕሪንተር እና ሌሎች ለእንጨት መቁረጫ የሚውሉ ሲኤምሲ ማሽኖች ነበሩ፤ በዚህ ቴክኖሎጂ የሚታገዝ ለብረት መቁረጫ የሚውል ማሽን ግን አልነበረም። በዚህ የተነሳ ከእንጨት የተቆረጠ ፕሮቶታይፕ ብቻ ነበር መሥራት የቻሉት። ግዴታ ከብረት ተቆርጠው መሥራት ያለባቸውን ለመሥራት ባለመቻላቸው የብረት መቁረጫ ለመሥራት እንደቻሉ ኢንጂነር ቤቴል ታብራራለች።

እነ ኢንጂነር ቤቴል፤ በተማሩት የሙያ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ነቅሰው በማውጣት ይህንን ማሽን መሥራት ችለዋል። አሁን ‹‹ችቦ ሲኤምሲ ኢንጂነሪንግ›› የተሰኘ ድርጅት ከፍተው የተለያዩ የሲኤምሲ ፕላዝማ ምርቶችን እየሠሩ ይገኛሉ። የእነ ኢንጂነር ቤቴል የፈጠራ ሥራ የሆነው ‹‹ሲኤምሲ ፕላዝማ ማሽን›› ተሠርቶ ያለቀ ሲሆን፤ የሙከራና ፍተሻ ሂደቶችንም አልፎ አሁን አገልግሎት እየሰጠ ነው፤ የማሽኑ የአጠቃቀም መመሪያም እየተዘጋጀ ነው።

ኢንጂነር ቤቴል እንደምትለው፤ የፈጠራ ውጤቱ ለሀገሪቱ መካኒካል ኢንጂነሪንግ ችግሮች መፍትሔ ይሆናል የተባለ ሲኤም ሲ ማሽን ነው። ማሽኑን በዲጅታል መንገድ መቆጣጠር ይቻላል። ብረትን በቀላሉ በሚፈለገው ዓይነት ቅርጽ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቆርጦ ለማወጣት ያስችላል። አሁን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዋና ዋና ችግሮች ከሚባሉት አንዱ በተለምዶ (በማንዋል) የሚሠራበት መሆኑ ነው። ለምሳሌ አንድ ብረት ለመቆረጥ የሚቻለው በማንዋል መንገድ ነው፤ በዚህ መንገድ የሚፈለገውን ቅርጽ ምንም እንከን በማይወጣለት መልኩ በትክክል ማምጣት ግን አይቻልም በማለት ታብራራለች።

ማሽኑ በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ማዕከል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የምትናገረው ኢንጂነር ቤቴል፤ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ብረቶችን በሚፈልጉት ዓይነት መቁረጥ እያስቻላቸው እንደሆነም ትገልጻለች። የብረታ ብረት ቅርጾችን በትክክል ያለምንም እንከን ለማውጣትና ለመቁረጥ የግዴታ በኮምፒዩተር የሚታገዙ ማሽኖች እንደሚያስፈልጉ ጠቅሳ፤ ለዚህ ሥራ ትክክለኛው መሣሪያ ይህ ማሽን እንደሆነ አመላክታለች።

በሲኤምሲ ፕላዝማ ማሽን የሚፈለጉት ዲዛይኖች በተለያዩ ቅርጾች ከተሠሩ በኋላ ብረቱ በማሽኑ እንዲቆረጥ ይደረጋል። ይህም የሚያገለግለው በብረት ላይ ለሚሠሩ የሜታል የአርት ሥራዎች ነው። የበር፣ የመስኮት እና ለተለያዩ ነገሮች የሚውሉ አካላትን ለማምረት ያስችላል። እነ ኢንጂነር ቤቴል ማሽኑን ለመሥራት በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ወርክሾፕ ውስጥ ያሉ ማሽኖችን በብዛት ተጠቅመዋል፤ ፕሪንተር፣ ሌሎች የሲኤምሲ ማሽኖችን የእንጨት መቁረጫዎችን እና ፕላስቲኮችን ተገልግለዋል።

አብዛኛው የማሽኑ አካል የተሰራው ከእንጨት ነው። ዲዛይኑን ለመሥራት ደግሞ የተለያዩ ሶፍትዌሮች በመጠቀም የራሳቸው የሆነ ዲዛይን አውጥተው ሠርተዋል። ኤሌክትሪካል ክፍሎቹን ለመሥራት ቀደም ሲል በመደበኛ ትምህርት ካገኙት እውቀት ውጪ የተለያዩ መጻሕፍትን በማንበብ የሠሩ ሲሆን፤ ኤሌክትሪካልና መካኒካል አካላቱን የሚያገናኙ ሶፍት ዌሮችንም ፈጥረው ሠርተዋል። ማሽኑን በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ውስጥም መጠቀም ይቻላል። ለምሳሌ በግብርናው ዘርፍ ዘር ለመዝራት የሚያስፈልጉ ማሽኖችን ሲሰሩ የሚያስፈልጓቸውን አካላት ለማምረት የመጀመሪያውን ሥራ ብቻ ከመስራት ውጪ መቀጠል አይችሉም። የዚህ ችግሩ ይህን ማሽን ማምረት የሚያስችሉ አካላትን መቁረጫ ማሽን አለመኖሩ ላይ ነው። እነዚህ ማሽኖች ግን የግዴታ በማሽኑ የሚቆረጡትን በመቁረጥ በፍጥነት ያለምንም እንከን ለመሥራት ያስችላሉ።

በተመሳሳይ በጤናው ዘርፍ የ‹ኤክስሬ› ማሽን ሳጥኑን ለመሥራት ያስችላል። ሳጥኑ ከብረት የሚሠራ ሲሆን፣ ለእዚህ የሚያስፈልገውን ብረት በትክክል ያለምንም እንከን ለመቁረጥ የግዴታ ይህን ዓይነት ማሽን መጠቀም ያስፈልጋል፤ አለበለዚያ ብረቱን በአጭር ሰዓት እንዲሁም በትክክል መቆረጥ አይቻልም። በማኒፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ውስጥም እንዲሁ ብዙ ዓይነት ማሽኖች አሉ። የሳሙና ማምረቻ እና መፍጫዎችን ለመሥራት ማሽኑ ያስፈልጋል። በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ውስጥ የመኪና አካላትን ለመቁረጥ በእጅጉ ያስፈልጋል። በእጃችን ቅርጾችን በትክክል ማውጣት አንችልም፤ የሚፈልገውን ቅርጽ በትክክል ለማውጣት እንደዚህ ዓይነት ማሽኖች የግድ ያስፈልጋሉ።

ማሽኑ በፍጥነት መሥራት በማስቻል ጊዜን መቆጠብ ከመርዳቱም በላይ፣ ምንም እንከን የማይወጣላቸውን ሥራዎች ለመሥራት ይረዳል የምትለው ኢንጂነር ቤቴል፤ ዲዛይኑ በኮምፒዩተር ተሠርቶ ካለቀ በኋላ ማሽኑ ይህ ዲዛይን እንዲወጣ እንደሚያደርግ ትገልጻለች። ‹‹ማሽኑን በኮምፒዩተር ስለምንቆጣጠረው ምንም እንከን የማይወጣለት ሥራ መሥራት ያስችላል። እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች በእጅ ሲሰሩ ሁልጊዜም አንዱ  ከአንዱ ይለያያል፤ ዲዛይኑ ተጠብቆ በትክክል ካልተሰራ የምንፈልገውን ቅርጽ ለማግኘት አያስችለንም›› ስትል ታብራራለች።

ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚመጣው ‹‹ሲኤምሲ ፕላዝማ ማሽን›› በሀገር ውስጥ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የምትጠቁመው ኢንጂነር ቤቴል፤ ‹‹የእኛ ማሽን ከዚህ ይለያል፤ ፍሬሙ ፣ ዲዛይኑ በራሳችን የተሠራ ነው። ከውጭ የሚመጣውን ማሽን በማሻሻል በቀላሉ እንዲንቀሳቀስና እንዲያመርት፣ በአነስተኛ ዋጋ ሀገር ውስጥ ማምረት እንዲቻል አድርገን ሠርተናዋል›› ትላለች። እሷ እንዳብራራችው፤ ከውጭ የሚመጣው ማሽን ዋጋው በጣም ውድ ነው። ሁለት በአንድ ሜትር ስፋት ያለው ሲኤምሲ ፕላዝማ ማሽን ከውጭ ተገዝቶ ወደ ሀገር ውስጥ እስከሚገባ ድረስ ያለው እያንዳንዱ ውጪ ሲሰላ ዋጋው አራት ሚሊዮን ብር አካባቢ ይደርሳል።

በሀገር ውስጥ ተሻሽሎ የተመረተው ይህ ሲኤምሲ ፕላዝማ ማሽን ግን ዋጋው ተመጣጣኝ ሲሆን፣ 300 ሺ ብር ቢያስወጣ ነው። ማሽኑ ይህንን ብዙ ወጪ ማስቀረቱ ብቻ ሳይሆን ተመራጭ የሚያደርገው፣ ጊዜና ጉልበት ያለአግባብ እንዳይባከን ማድረጉም ሌላው ፋይዳው ነው። ኢንጂነር ቤቴል፤ አሁን አንድ ሲኤምሲ ፕላዝማ ማሽን መሥራታቸውን ጠቅሳ፣ ሌሎች ማሽኖችን ለማምረት በሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁማለች። እነ ኢንጂነር ቤቴል የማሽኑን አገልግሎት ለሚፈልጉ ሰዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። በማሽኑ መገልገል የሚፈልጉ አካላት ወደ እነርሱ መጥተው አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉም አስታውቃለች።

‹‹ የብረታ ብረት ሥራዎችን የሚሠሩ አካላት የሚፈልጉትን ዲዛይን ይዘው ከመጡ ዲዛይኑን ማምረት እንችላለን። አለበለዚያም የፈለጉትን ዲዛይን ሠርተን መስጠት እንችላለን›› የምትለው ኢንጂነር ቤቴል፤ ከዚህ በተጨማሪም ለማስታወቂያ አገልግሎት የሚውሉ እንደ ሎጎ፣ መለያ (ብራድ) የመሳሰሉትን ለመሥራትም ደንበኞችን እየፈለጉ መሆናቸውን አመላክታለች ። ኢንጂነር ቤቴልና ኢንጂነር ጥሩ ዓለም ይህንን የፈጠራ ሃሳባቸውን ይዘው ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በ2015 ዓ.ም ባዘጋጀው ‹‹ብሩህ ተስፋ›› ውድድር ላይ ተሳትፈው አሸንፈዋል። በውድድሩ ያገኙትን የገንዘብ ድጋፍ ፕሮጀክታቸው ላይ አውለውታል።

ድጋፉ በፕሮቶታይፕ ደረጃ ያለውን ማሽን ለመሥራት እንዳስቻላቸው ኢንጂነር ቤቴል አስታውቃለች። ከውድድሩ በኋላም ከሚመለከታቸው አካላት ብዙ ድጋፎችና ትብብሮች ማግኘታቸው ጠቅሳ፤ ማሽኖቹን በማምረት ወደ ቢዝነስ ለመግባት ያስችላቸው ዘንድ የልማት ባንክን ስልጠና መውሰዳቸውንም ተናግራለች። ‹‹በብሩህ ተስፋ›› ውድድር ላይ ከተሸለመን በኋላ የባሕርዳሩ የሥራና ክህሎት ተቋም መስሪያ ቦታና ተጨማሪ ብድር እንዲሰጠን መነጋገራቸውን ገልጻ፣ ተቋሙ ይህን እስኪያመቻችላቸው ድረስ እየጠበቁ መሆናቸውን አመላክታለች።

ማሽኑ አሁን በባሕር ዳር ለአስራ ሁለት ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ተናግራ፣ ማሽኑን የማምረቱ ሥራ ሲጀምር ደግሞ ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችሉ ትገልጻለች። አሁን ዲዛይኖችን በመሥራት ከሌሎች ኢንጂነሮችና የማሽን አገልግሎት ፈላጊ አካላት ጋር በአጋርነት በመሥራት ላይ እንዳሉ ጠቁማለች። የማሽኑን የፈጠራ የባለቤትነት መብት ለማግኘት በአእምራዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በማስመዝገብ ሂደት ላይ መሆናቸውን አመላክታለች።

እሷ እንዳለችው፤ ተጨማሪ ብድርና የመስሪያ ቦታ ሲመቻች ማሽኑን ወደ ማምረት ሥራ ይገባል። ወደፊት ለብረት መቁረጫ የሚውል ማሽን ብቻ ሳይሆን፣ ለእንጨት፣ ለፕላስቲክ እና ለሌሎች ዓይነት ሥራዎች የሚያስፈለጉ ማሽኖችን ለመሥራት እቅዱ አላቸው። ቁጭ ብሎ ሥራ መጠበቅ እጅግ ያስቸግራል የምትለው ኢንጂነር ቤቴል፤ ወጣቶች በየሙያ ዘርፍቸው ያሉ ችግሮችን በመለየት ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን ለመሥራት ተነሳሽነት ሊኖራቸው እንደሚገባም መክራለች። ይህ ሲሆን መፈታት የማይቻሉ የሚመስሉ ችግሮች ሁሉ መፍትሔ ያገኛሉ ስትል ጠቅሳ፣ ወጣቱ ከራሱ አልፎ በዙሪያው ላሉ ሰዎች ሆነ ለሀገሩ የሚጠቅም ሃሳብ አመንጪ ይሆናል ትላለች።

 ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ጥር  14/2016

Recommended For You