የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች በውስጥ ጉዳያችን የሚገቡትን እረፉ ልንላቸው ይገባል!

 የባሕር በር ለአንድ ሀገር ምን ያህል አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ሊረዳው የሚችል የአደባባይ ምስጢር ነው። በተለይም 120 ሚሊዮን ሕዝብ ይዞ ያለወደብ መኖር ማለት ምን ያህል የህልውና ጉዳይ እንደሚሆን መገመት ይከብደዋል ብሎ ማሰብ አይቻልም።

ዓለም በተለያዩ ፍላጎቶች በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎች እየከፈለች ባለበት አሁናዊ እውነታ፤ ኢትዮጵያውያን አስተማማኝና ቀልጣፋ የወደብ አገልግሎት የሚያገኙባቸውን አማራጮች ተጨባጭ ለማድረግ የጀመሩት ጉዞ የዚሁ ዓለም አቀፍ እውነታ አካል ነው፤ ነገዎቻቸውን ብሩህና ተስፋ ሰጪ ለማድረግም ወሳኝ ነው።

በየዕለቱ በሚፈጠሩ ዓለም አቀፍ ክስተቶች በብዙ እየተፈተነ ባለው ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ እና የደህንነት ሁኔታ ውስጥ፤ ያደሩ እና የዋሉ ብዙ ያልተሠሩ የቤት ሥራዎችን እንደ ሀገር ይዞ የ120 ሚሊዮን ሕዝብን ሕይወት ማስቀጠል ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ መገመት አይከብድም።

ችግሩ ዛሬ ላይ የአንድ ሀገር/የኢትዮጵያውያን ተደርጎ ቢወሰድም፤ ነገ ላይ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው ሀገራት አለመረጋጋት የስጋት ምንጭ ሊሆን የሚችል ነው። ይህን ችግር ቀድሞ ተገንዝቦ ከወዲሁ የጋራ መፍትሔ በጋራ ለማፈላለግ የኢትዮጵያ መንግሥት እየሄደበት ያለው መንገድ የሚበረታታ ነው።

ችግሩን እንደ ሀገር ሰጥቶ በመቀበል መርህ፤ የጋራ ተጠቃሚነት መሠረት ባደረገ መንገድ ለመፍታት መንግሥት እየሄደበት ያለው መንገድ ዘመኑን የሚዋጅ፤ ለቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች የነገ ተስፋ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባ፤ የኢትዮጵያውያንን አርቆ አሳቢነት አመላካች ነው።

በተለይም የቀጣናው ሀገራት ካሉበት ድህነትና ኋላቀርነት ፈጥነው መውጣት የሚችሉበትን የጋራ አቅም መገንባት የሚያስችል ነው። አዲስ የትብብር ምዕራፍ በመክፈት፤ ለቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች ብሩህ ተስፋ ፈንጣቂ ተደርጎ የሚወሰድ፤ የአካባቢውን ሕዝቦች ከትናንቶች ጥላ የሚታደግ ነው።

ሀገራቱ ያላቸውን ተፈጥሯዊ ጸጋ አውቀውና አቀናጅተው ከቅኝ ግዛት ዘመን ማግስት ለሕዝቦቻቸው ተስፋ ያደረጉትን ልማት እውን ለማድረግ ትልቅ ስትራቴጂካዊ ጎልበት ተደርጎ የሚወሰድ፤ የአካባቢውን ሀገራት ሕዝቦች ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ የሚያስችል ነው።

ብዙዎች ዋጋ ከከፈሉለት የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ የተቀዳ፤ ወንድማማችነትን እና ከዚህ የሚመነጭ አብሮ የመልማት መሻትን ታሳቢ ያደረገ ነው። ከስድስት አስርት አመታት በፊት የብዙ አፍሪካውያን ታጋዮች ድምጽ የነበረ፣ ዛሬም በብዙ ጫና ከታፈነበት ወጥቶ የሚሰማ የአፍሪካውያን የተስፋ ድምጽ ነው።

በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ሕዝብ ጥያቄ ልማትና ከልማት የሚገኝ ትሩፋት ነው፤ በተለይም ድህነትና ኋላ ቀርነት ከሁሉም በላይ ብዙ ዋጋ እያስከፈላቸው ለሚገኙ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሕዝቦች ልማት ትልቁና መሠረታዊ ጥያቄያቸው ነው። ነገዎቻቸው ከዛሬ ሊለዩ የሚችሉት በልማት ብቻ ነው።

ይህ የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች ፍላጎት የመሪዎቻቸው ፍላጎት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፤ አሁን ባለው ዓለምአቀፋዊ እውነታ፤ ይህንን አካባቢያዊ የልማት መሻት እውን ለማድረግ ተያይዞና ተደጋግፎ ከመሄድ ውጪ ወደ ስኬት የሚወስድ ሌላ አማራጭ የለም። ያለውም ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮ ይኸው ነው።

ከዚህ ውጪ ማንንም ተጠቃሚ ሊያደርግ የማይችለውን የሴራ መንገድ መከተልም ሆነ ለመከተል መንደርደር ፤ ከጥፋት ውጪ ሊያስገኝ የሚችለው ነገር የለም፤ በአካባቢው ገዝፎ የሚታየውን ድህነትና ኋላቀርነት ከማስቀጠል ያለፈ ሚና አይኖረውም።

በተለይም በሀገራቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት በቀጣናው የተጀመረውን አዲስ የጋራ ተጠቃሚነት ጉዞ ለማሰናከል ጥረት የሚያደርጉ ኃይሎችና ሀገራት የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን አቅም ስላላቸው ካልተገባ እንቅስቃሴያቸው ሊታቀቡ ይገባል።

እነዚህ ኃይሎች እና ሀገራት ቀደም ባሉት ጊዜያት የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች የነበራቸውን ሰላምና ጉርብትና በማበላሸት ያልተገቡ ዋጋዎችን እንዲከፍሉ ከማድረግ ባለፈ የፈጠሩት ነገር የለም። ዛሬም ከዚህ የተለየ ዓላማ ስለሌላቸው ፤ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ከትናንቶቻችን ተምረን እረፉ ልንላቸው፤ ከተስፋችን እንዲርቁ ልናሳስባቸው ይገባል።

 አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You