ጥምቀትን የሚያስታውሱኝ ሙስሊም አባት

ከሦስት ዓመታት በፊት የጥምቀት ዕለት ነው። ከወሰን ወደ ሲኤምሲ ሚካኤል የሚወርደው ሰፊ አስፋልት መንገድ ግራ ቀኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዓርማ ያለባቸው ባንዲራዎች ተሰቅለዋል፡፡ ከሰዓት፣ 8፡00 አካባቢ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ከሲኤምሲ ወደ ወሰን በሚወስደው አስፋልት በእግር እየወጣን ነው፡፡ ሰዓቱ ታቦታት ከማደሪያቸው ወደ መንበራቸው ገብተው መንገዶች ፀጥ ረጭ ያሉበት ነው፡፡ ድምቀቱ ያለው በቤተ ክርስቲያናቱ አካባቢ ነው፡፡ መንገዶች የሚደምቁት ምዕመኑ መመለስ ሲጀምር ነው፡፡

በዚህ ፀጥ ረጭ ባለ ጎዳና ላይ እየወጣን ሳለ ከላይ አንድ ሙስሊም አባት ወደ ታች ይመጣሉ፡፡ አንድ ቦታ ሲደርሱ ከመንገዱ ግራና ቀኝ ያሉ፣ ባንዲራ የተሰቀለባቸው ምሰሶዎች ወድቀዋል፡፡ ከላይ እየመጡ የነበሩት ሙስሊም አባት እነዚያን የወደቁ ምሰሶዎች እያነሱ፣ ከሥር በሚገኘው ማስደገፊያ እያስደገፉ ባንዲራዎችን ሲያቆሙ ተመለከትን፡፡

ሙስሊም ሆነው ይህን በማድረጋቸው ምንም አልገረመንም፡፡ አብሮኝ ያለው ልጅ አብሮ አደጌ ስለነበር እያየነው ያደግነው ነገር ነው፡፡ ከዚህ ጓደኛዬ ጋር አጀንዳ አድርገን እየተጨዋወትን የሄድነው የእንዲህ አይነት አባቶች ንጹህ ልቦና በብዙዎች ዘንድ የማይታወቅ መሆኑን ነው፡፡ ይህን እንድናስብ ያደረገን ደግሞ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚደረግ ነው የሚባሉ ሰሞንኛ አጀንዳዎች ነበሩ፡፡

እንደ ጥምቀትና መስቀል ያሉ የከተራና የደመራ በዓላት በመጡ ቁጥር ሙስሊሞች መንገድ አጸዱ፤ እንደ ሮመዳን ያሉ በዓላት ሲመጡ ክርስቲያኖች እንዲህ አደረጉ …›› የሚሉ ዜናዎች ሲሰሩ በአንዳንድ ሰዎች የሚሰጡ አስተያየቶች አሉ፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ ነው፤ በመንግሥት ካድሬዎች ታዝዘው ነው፤ እንዲህ አድርጉ ተብሎ ነው … እየተባለ ይወራል፡፡ እርግጥ ነው እንደዚያ ሊሆንም ይችላል፡፡ በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ ያሉ ባለሥልጣናት የሚያደርጉት አርዓያ ሆኖ ለመታየት፣ ምናልባትም ለፖለቲካ ፍጆታ ሊሆን ይችላል፡፡ እውነታው ግን በማህበረሰባችን ውስጥ ይህ ልማድ ያለ እና የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊ የአገሩ ሕዝብ የሚያደርገውን ነገር ቢያደርግ፣ የአገሩን ሕዝብ እሴቶች ቢያንፀባርቅ ምንም ችግር የለውም፡፡ ችግር የለውም ብቻ ሳይሆን ግዴታው ነው፡፡ ችግሩ ግን ለፖለቲካ ፍጆታ ተብለው የሚደረጉ ሌሎች ነገሮች ስላሉ እንዲህ አይነት በጎ ነገሮችን ጭምር በቅንነት እንዳይታዩ ያደርጋል፡፡ በዘመቻ የሚደረገውን እንተወውና እውነታው ግን በማህበረሰባችን ውስጥ ያለ መሆኑን ማወቅ ነው፡፡

ለምሳሌ የጥምቀት ዕለት የወደቀ የባንዲራ ምሰሶ እያነሱ ሲያቃኑ የነበሩት ሙስሊም አባት ማንም አዝዟቸው አይደለም፡፡ እየሄዱ የነበረው ብቻቸውን ነው። ማንንም ለማስደሰት ብለው አልነበረም፤ በአካባቢው ሰው የለም፡፡ ከታች እየመጣን የነበረውን ሁለት ሰዎች አይተው ይሆናል ብሎ መገመት በጣም የለየለት ጅልነት ይሆናል፡፡ ጭራሹንም ያዩን አይመስለኝም፡፡ አጠገባቸው ደርሰን፣ እርሳቸውም አቃንተው ጨርሰው ስንተላለፍ ነው ምናልባትም ልብ ብለውን ከሆነ፡፡ ያንን ሲያደርጉት የነበረው ለህሊናቸው ነው፡፡ ያ ባንዲራ የተሰቀለው ለበዓሉ ድምቀት መሆኑን ያምናሉ፤ ስለዚህ ወድቆ ሲያዩት አላስቻላቸውም ማለት ነው፡፡ ምን አገባኝ በሰው ሃይማኖት አላሉም ማለት ነው፡፡ በቅን ልቦና እና ህሊና ሲታሰብ እንዲህ ነው፡፡

አሁንም እደግመዋለሁ፤ ገጠመኙን ያነሳሁት ምንም የሚገርም ነገር ኖሮት አይደለም፡፡ ከፖለቲካ ውጭ ያለው የአገራችን የሕብረተሰብ ክፍል እየኖረው ያለው ሕይወት ነው፡፡ ይህን በማድረጋቸው መደነቃችንን ቢያውቁ ምናልባትም ሊስቁብን ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ለእነርሱ የዕለት ከዕለት ሕይወት ነው፡፡ አንድ ሰው መሰረታዊ ነገሮችን ማድረጉ የተፈጥሮ ግዴታ ነውና የሚደንቅ ነገር የለውም፤ እነርሱም ልክ እንደዚያ ነው የሚያዩት፡፡

ገጠመኙን ያነሳሁበት ምክንያት፤ እንዲህ አይነት ሃይማኖታዊ በዓላት ሲመጡ የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ ወገኖች እንዲህ አደረጉ የሚለው እንደ ትልቅ ዜና በመታየቱ ነው፡፡ ልክ ያልተደረገ ነገር፣ ወይም ሊደረግ የማይችል ነገር የተደረገ በማስመሰል ማዳነቅ ስህተት ይመስለኛል፡፡ በዚያ ልክ የማዳነቅ ሽፋን ሲሰጠው ነው ሰዎች ተጨማሪ ትርጉም ለመስጠት የሚገደዱት። እንዲህ ከሆነማ ሊያጸዱ የወጡት ሰዎች “‹እንዲህ አድርጉ› ተብለው ተገደው ነው ለሚል አተያይ ያጋልጣል፡፡ በአጭሩ የአንድ ሃይማኖት በዓላት ሲከበር የሌላኛው ሃይማኖት ተከታዮች ድጋፍ ማድረግና አብሮ ማክበር በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ውስጥ ያለ እና የሚኖሩበት ነው፡፡

እንዲህ አይነት ዜናዎችን ስመለከት ወደ ልጅነቴ እመለሳለሁ፡፡ ተወልጄ ባደኩበት አካባቢ ሙስሊሞች በቁጥር ትንሽ ናቸው፡፡ አብዛኛው ኦርቶዶክስ ነው። ታዲያ ከሃይማኖታዊ በዓላት ይልቅ ሰርግ ሲደረግ የነበረው ነው ትዝ የሚለኝ፡፡ እንደ ልማድ ሆኖ ይሁን ሃይማኖታዊ አስተምህሮው ባይገባኝም ‹‹የሙስሊም እና የክርስቲያን ሥጋ›› የሚባል አለ፡፡ ሌላውን ምግብ አብረው እየበሉ የሥጋ አይነት ሲሆን ይለያያል፡፡ ማረድ ያለበትም የእምነቱ ተከታይ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡

በዚህ ሁኔታ ሰርግ ሲደረግ፤ እንደ ባለ ሰርጉ አቅም ሁለትና ከዚያ በላይ ነው የሚታረደው፡፡ ሁለት ግን ግዴታ ነበር፡፡ አለበለዚያ እርድ የሌለበት ሰርግ (በፆም ምግቦች) ይደረጋል እንጂ አንድ ብቻ ሊታረድ አይችልም። የቻለ ሁለት ከብት፣ ያልቻለ ሁለት ፍየል ነው ሊያርድ የሚችለው፡፡ አንዱን ክርስቲያን ያርዳል፣ አንዱን ሙስሊም ያርዳል፡፡ በተለያየ ድስት ይሰራል። ሙስሊም ከሙስሊሙ፣ ክርስቲያን ከክርስቲያኑ ይበላሉ ማለት ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ አስተናጋጅ ተሳስቶ ከአንዱ ሃይማኖት ለሌላኛው ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህኔ ‹‹ኧረ ይሄኛው የሙስሊም ነበር›› ወይም ‹‹ኧረ ይሄኛው የክርስቲያን ነበር›› ይባላል፡፡ ይሄኔ በቀልድ እያዋዙ ‹‹ባክህ ሁለቱም ከሰኞ ገበያ ነው የተገዙት›› በማለት በሬዎች የተገዙበትን ሰኞ ገበያ የምትባል የአካባቢያችንን ገበያ ይጠቅሳሉ፡፡ አንድ አይነት በሬ ወይም ፍየል ናቸው፤ ምንም ልዩነት የለውም ማለታቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል በሬው ወይም ፍየሏ ሃይማኖት የሌላቸው ፍጡር ስለሆኑ ምንም ልዩነት የለውም እያሉ ፍልስፍና አከል ጨዋታዎችን ይጫወታሉ።

እንግዲህ እነዚህን ሰዎች ‹‹ሙስሊምና ክርስቲያን እኮ አንድ ነው›› ብለን ብንነግራቸው ‹‹እና ታዲያ ድሮስ ስንት ሊሆኑ ነበር?›› በማለት ነው የሚስቁብን። ለእነርሱ ዜና አይደለም ማለት ነው፡፡ ‹‹ሙስሊምና ክርስቲያን እኮ ተከባብሮ ነው የሚኖር›› ብንላቸው ‹‹እና ታዲያ ከመከባበር ውጭ ምን ሊሆን ነበር?›› ብለው ነው የሚመልሱልን፡፡ ወይም ‹‹አንተ ነህ እሱን የምትነግረኝ?›› ብለው ሊገረሙብን ይችላሉ፡፡

በተለይም እንዲህ እንደ ጥምቀት ያሉ በዓላት ደግሞ እንዲህ አይነት ማህበራዊ እሴቶችን አጉልተው ያሳያሉና እውነተኛውን የማህበረሰብ መስተጋብር እናይባቸዋለን፡፡

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You