‹‹ገዳዮችን የመውደድ የፖለቲካ ባህላችን መለወጥ አለበት›› -የተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አንጋፋው ፖለቲከኛ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር)

በ1965 ዓ.ም ከቀድሞ ቀዳማይ ኃይለስላሴ ከአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ እና በመንግስት አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በጊዜው የመጨረሻው የንጉሱ ዘመን የድግሪ ተመራቂ ሆነው ከንጉሱ እጅ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተማሪ ሕብረት ላይ ከመሳተፍ በተጨማሪ ትምህርታቸውን በትጋት እየተከታተሉ ኦነግን ለመመስረት ከእነ ሌንጮ ለታ ጋር ብዙ ሠርተዋል፡፡ እስከ አሁን ድረስም በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል የፖለቲካ ትግል ውስጥ በመሳተፍ ከግንባር ቀደሞቹ መካከል ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡

የኦነግን የፓርቲ ፕሮግራም ከመቅረፅ ጀምሮ ሴሎችን በማደራጀት ለፓርቲው መመሥረት ሠፊውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ንቃት ተከታትለው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ውጤት ቢያጠናቅቁም ሥራ ማግኘት ቀላል አልሆነላቸውም። ከእርሳቸው በታች ነጥብ ያስመዘገቡ ተመራቂዎች በጊዜው ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሌሎችም ከእርሳቸው ሞያ ጋር የተያያዘ ሥራ የሚያሠሩ ተቋማት ውስጥ ሲቀጠሩ እርሳቸው ግን ማንም ሊቀጥራቸው ፈቃደኛ አልሆነም ነበር፡፡

ሳይታክቱ የተለያዩ ተቋማት እየሄዱ ቢያመለክቱም ሥራ አላገኙም፡፡ ሥራ ያጡባቸው የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ ዋነኛው ግን የመመረቂያ አጠቃላይ ነጥባቸው ታይቶ፤ የፅሁፍም ሆነ የቃል ፈተና ተፈትነው ሁሉንም ካለፉ በኋላ፤ የመመረቂያ ፅሁፋቸውን ሲጠየቁ የሚያቀርቡት የወቅቱን የመሬት ሥርዓት አካሔድ ትክክል አለመሆኑን የሚያመላክት በመሆኑ በተቋማት ለመቀጠር ተቸገሩ፡፡ ለስምንት ወራት ሥራ አጥተው ቢንከራተቱም፤ ሥራ አለማግኘታቸው ግን በሌላ በኩል ኦነግን በደንብ ለማደራጀት ዕድል ሰጣቸው፡፡

በኋላም ወደ ወለጋ ሥራ አግኝተው እንደሄዱ ብዙም ሳይቆዩ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በሕዝብ ትግል ስልጣናቸውን ለቀቁ፡፡ ደርግ መምጣቱን ተከትሎ እርሳቸው የመሬት አስተዳደር ሥራ ላይ በመሠማራት ጭሰኛው የመሬት ባለቤት እንዲሆን በመስራት መሬት ላራሹን በፈለጉበት መንገድ እንዲተገበር ከጓደኞቻቸው ጋር ከፍተኛውን ሚና ተጫወቱ፡፡

ቀጥለው ደርግ የእርሳቸውን እና የኦነግን ፍላጎት መፈፀም እንደማይችል በመገንዘብ የኦነግ ጦርን ለማጠናከር ሱዳን እና ኤርትራ ድረስ ሔደው ብዙ ሥራዎችን ሰርተዋል። የኦነግ መስራች እና የመጀመሪያው የፓርቲው ፕሬዚዳንት የዛሬው የወቅታዊ እንግዳችን ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በጫካ ሲታገሉ ቆይተው ደርግ ሲወድቅ፤ ኢህአዴግ ሙሉ ለሙሉ በደርግ እግር ተተክቶ አገር ማስተዳደር ከመጀመሩ በፊት በነበረው የሽግግር ጊዜ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚንስትር ሆነው ሠርተው ነበር፡፡ በኋላም በነበረው የፖለቲካ ሴራ ተሰደው በውጪ ከቆዩ በኋላ፤ ከአምስት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ በተደረገው የመንግሥት ለውጥ በስደት ከሚኖሩበት አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት፣ ይመሩት የነበረውን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በመተው፤ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በግል ተወዳድረው በማሸነፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው። ሰላም ላይ በማተኮር እየተደረገ ያለውን ጥረት እና አጠቃላይ የወቅቱን የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ እንዲሁም ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን ሀገራዊ ምክክር በተመለከተ ከእኒሁ አንጋፋ ፖለቲከኛ ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡ መልካም ንባብ፡-

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ጉዳት እያስከተሉ ካሉ የተለያዩ ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛው በጦርነት አልሸነፍም በማለት ከመነጋገር እና ተደራድሮ ችግርን ከመፍታት ይልቅ በስሜት ወደ ጦርነት እና ግጭት ፊትን ማዞር የተለመደ ስለመሆኑ ይነገራል። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ዲማ:- ከመንግስት አንፃር ካየነው ይህ በየትኛውም ዓለም ያለ የመንግስት ፀባይ ነው። ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ማንኛውም መንግስት ‹‹ሁሉንም ኃላፊነት የምወስደው እኔ ነኝ፡፡ ማሸነፍ እና ማንበርከክ እችላለሁ›› ብሎ ይገምታል፡፡ በእርግጥ መንግስት ማንበርከክ ይችላል። ነገር ግን ቢችልም አገሪቱ ትጎዳለች። ሕዝብ ይጎዳል፡፡ ስለዚህ የግድ አንዳንድ ነገሮችን ተቀብሎ ለሰላም መድረኩን መክፈት እና ለሰላማዊ አማራጭ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡

የመንግስት ኃላፊነት ከሁሉም አንፃር የሚታይ ነው። ይህ እስከ ሆነ ድረስ ማሸነፍ እና ማንበርከክ እችላለሁ ብቻ ብሎ በማመን የኃይል አማራጭን ብቻ እንደመፍትሔ መውሰድ ከመንግስትነት አንፃር ተገቢ አይሆንም፡፡ ለመፍትሔ የኃይል አማራጭ ብቻውን በቂ አይሆንም። በፖሊስ ብቻ አገር አይመራም፡፡ የፖለቲካ ቅቡልነት ለማግኘት ሕዝቡን የግድ በሰላማዊ መንገድ ማሳመን ያስፈልጋል፡፡ የሚያዋጣው ኃይል ሳይሆን ተቀባይነት የሚገኝበትን መንገድ መፈለግ ነው።

ሌላው ታጣቂም በመሳርያና በግጭት ለውጥ አመጣለሁ ብሎ ከማሰብ መራቅና በውይይትና በምክክር ዓላማን ከግብ ማድረስ እንደሚቻል ሊረዳ ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የፌዴራል መንግስት በተደጋጋሚ ሠላም ለማምጣት ጥረት አድርጓል፡፡ ለምሳሌ ከሕወሓት ጋር ያካሄደውን የፕሪቶሪያውን ስምምነት መጥቀስ ይቻላል። እንደውም ስምምነቱን ተከትሎ ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን አቋቁሟል፡፡ ኮሚሽኑ ከሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየተወያየ እየሠራ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ዲማ:– በአገሪቱ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ከዚህ በፊትም ውይይት ይደረጋል፡፡ አሁን ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ የልዩ ልዩ አገሮችን ተሞክሮ እና ልምድ ለማግኘት እና የወደፊቱ የአገራችን ዕጣ ምን ይሆናል? የሚለው ላይ ከፓርቲዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ጥሩ ጅማሮ እየታየ ነው፡፡ ይህ በመንግስት በኩል ብቻ የሚሠራ ሥራ ሳይሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ማህበራዊ ተቋማትም አስተዋፅኦ ያስፈልጋል፡፡ የእነርሱንም ሃሳብ መውሰድ ጥሩ ነው፡፡

በእርግጥ የተሃድሶ ኮሚሽን የተቋቋመው የሰሜኑን ጦርነት ያቆመውን የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ ነው። ጦርነት ከቆመ በኋላ ታጣቂ የነበሩ ሰዎች ወደ ሕብረተሰቡ መመለስ አለባቸው ዋናው ተግባሩ ይህንን ማድረግ ነው። ስለዚህ ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ማለት መጀመሪያ ጦርነቱ ውስጥ ገብተው የነበሩትን ተቀናጅተው የሚዋጉትን እንዳይዋጉ መሳሪያ ፈተው ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ የእርሱ ተግባር ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች ለብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ምን መሆን አለበት ?

ዶ/ር ዲማ:– እነዚህ ተደራጅተው ቡድን ፈጥረው ለፖለቲካ ዓላማቸውን በመሳርያ ኃይል ለማስፈጸም የሚታገሉ ቡድኖች የቀድሞ አካሄዳቸውን ትተው በሰላማዊ መንገድ ለመኖር እና ለመታገል እምነት ሊያድርባቸው ይገባል፡፡ አሁን ባለው የፖለቲካ ሥርዓት እምነት እንዲያድርባቸው የመንግስት ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ እምነት በማሳደር በኩል የእነዚህ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚና ቀላል አይሆንም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ምን መሆን አለበት?

ዶ/ር ዲማ:– እውነት ለመናገር በአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ ለማለት አልደፍርም። በአገራችን የፖለቲካ አደረጃጀት የተጀመረው በ1970ዎቹ ነው። የተጀመረበትም ሁኔታ ሕዝብን በግልፅ አደራጅቶ ለፖለቲካ ዓላማ ለማሰለፍ ሳይሆን በድብቅ ተደራጅቶ የፖለቲካ ዓላማን ለማራመድ ነው። አደረጃጀቱ በጫካ ወይም በድብቅ በከተማ ነበር። የመጀመሪያዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በእዚህ መልክ መደራጀታቸው ለፖለቲካ ፓርቲዎች በበቂ መጠን አለመጠናከር የራሱን አሉታዊ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

ሌላኛው ደርግ የመጀመሪያው ያቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲ ነው፡፡ ደርግ አስር ዓመት ሥልጣን ላይ ወጥቶ ከተቀመጠ በኋለ ፓርቲ አደራጀ፤ ብዙም ሳይቆይ ወደቀ፡፡ ያ ፓርቲ ዛሬ የለም፡፡ ሕዝባዊ ሳይሆን መንግስታዊ ፓርቲ ነበር ማለት ነው፡፡ እነዚህ ልምዶች በአገራችን የፖለቲካ ፓርቲ እድገት ላይ የራሳቸውን ተፅዕኖ አሳርፈዋል፡፡ ወደ ፊት የፖለቲካ ምህዳሩ እየሠፋ የሕዝቡም ፍላጎት እና ንቃተ ህሊና እያደገ ሲሔድ፤ ከዚህ በተሻለ መንገድ በሰፊው ሕዝብ ላይ የተመሠረቱ ፓርቲዎች ወይም በፖለቲካ ዓላማ የተደራጁ ግለሰቦች እና ፓርቲዎች እየተጠናከሩ ይሔዳሉ ብዬ እገምታለሁ።

አሁን የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖች አሉ፡፡ እነዚህ ቡድኖች መንግስት ውስጥ የሌሉት፤ ሥራቸው ስለመንግስት ማማረር ነው፡፡ መንግስት ይህን አላደረገልንም፤ የፖለቲካ ምህዳሩን ክፍት አላደረገም ይላሉ፡፡ መቼም ቢሆን ፖለቲካ ውስጥ መግባት መስዋትነትን ይጠይቃል፡፡ በፖለቲካ ትግል ውስጥ መግባት ብዙ መስዋትነት ያስከፍላል፡፡ መስዋትነትን ፈርቶ ትግል ማድረግ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ከሁለቱ አንዱን መምረጥ የግድ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከላይ ከጠቀሷቸው ምክንያቶች በተጨማሪ ሁሉንም ሊገዛ የሚችል የፓርቲ ፕሮግራም ይዘው አለመምጣታቸው በፓርቲዎች ዕድገት ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ የለም?

ዶ/ር ዲማ:- አዎ! ነገር ግን አሁን የፖለቲካ አመራር ላይ ያሉትን ብዙዎቹን ሰዎች ብንወስድ ላለፉት ሰላሳ እና አርባ ዓመታት የነበሩ ሰዎች ናቸው። ብዙ አይለወጡም፤ እየተተካኩ አይሄዱም። እንደማስበው ከመጀመሪያው ጀምሮ የሆነ ውስንነት አለ፡፡ ውስንነቱ በአጠቃላይ አገሪቱን እና ሕዝቡን የተመለከተ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጥ የሚያመጣ ፕሮግራም ነድፈው ዓላማቸውን ለማሳካት ሕዝብን ምን ያህል አንቀሳቅሰዋል? ምን ያህልስ አባል አላቸው? የሚለው ወሳኝ ነው።፡ አሁን እያንዳንዱ ፓርቲ ምን ያህል አባል አለው መልሱ ያጠያይቃል፡፡ ብልፅግና 14 ሚሊየን የፓርቲ አባል አለኝ ይላል፡፡ ያን ያህል ቁጥር ያለው አባልን በዲሲፕሊን በአንድ ፕሮግራም እየመራ ነው ወይ የሚለው ግራ ያጋባል፡፡ ነገር ግን ሲበዛም ጥሩ አይደለም፡፡

በምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች 10 ሺህ ወይም 20ሺህ አባል ሊኖራቸው ይገባል ሊል ይችላል፤ ምርጫ ቦርድ በሚያስቀምጠው የአባል ቁጥር መጠን 120 ሚሊየን ሕዝብ ባለበት አገር ውስጥ 100 ፓርቲ ማቋቋም ይቻላል፡፡ ነገር ግን በእኔ እምነት ፓርቲ ፓርቲ መሆኑ የሚታወቀው በምርጫ ተፈትኖ ነው፡፡ ይሔ ፓርቲ ስንት መቀመጫ አገኘ ሲባል ይፈተናል። በፌዴራል ምክር ቤት ውስጥ ከ12 አባላት ውጪ ሁሉም መቀመጫዎች የገዢው ፓርቲ ናቸው፡፡

እነዚህ 12 መቀመጫዎች ትንሽ እየበዙ፤ ፓርቲዎች እየጠነከሩ ከሔዱ፤ የሌሎች ፓርቲዎች አደረጃጀት እየተጠናከረ ሊሔድ ይችላል፡፡ አንዳንዴ ተመሳሳይ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ብዙ ከሚሆኑ እየተዋሃዱ እና አንዱን እያጠናከሩ መሔድ ይችላሉ።

አዲስ ዘመን፡- በተለይ ሰላም ላይ በማተኮር እየተደረገ ያለውን ጥረት እና አጠቃላይ የወቅቱን የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ዲማ:– የሰላም ስምምነት ተካሂዶ የሰሜኑ ጦርነት ካበቃ በኋላ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በተወሰነ መልኩ ሠላም ተስተውሏል፡፡ ስምምነት መፈጠሩ በራሱ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን መቋቋሙም መልካም ነው። እንዲህ ዓይነት የሰላም ስምምነት ሌሎቹንም እያካተተ በአጠቃላይ በአገሪቱ ሰላማዊ የሆነ የፖለቲካ ሕይወት ይኖራል የሚል ተስፋ እየታየ ነው፡፡ በእኔ እምነት መልካም የሰላም ሁኔታ አለ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የትግራይ በስምምነት ቢቋጭም በአማራም ሆነ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት ይስተዋላል፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ዲማ:– በአንፃራዊነት ስንመለከተው በሰሜኑ ክልል በትግራይ አካባቢ የነበረው ጦርነት በሁለት ጦሮች መካከል የተካሔደ ነበር፡፡ ለእዛውም አንድ ጦር የነበረ ማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የነበረ ለሁለት ተከፍሎ እርስ በእርስ ውጊያ ላይ መቆየታችን የሚካድ አይደለም። ያ ጦርነት ከባድ ነበር፡፡ ብዙ ሰው ተሳትፏል፤ ጉዳቱም በሁለቱም በኩል ቀላል አልነበረም። ይህ ማለት ግን በዛ ጊዜም ቢሆን በሌሎች አካባቢዎች ሰላም ነበር ማለት አይደለም፡፡

በአንፃራዊነት ስናየው በተለያዩ አካባቢዎችም ግጭቶች ነበሩ፡፡ ግጭቶቹ አሁንም የሚታዩ ሲሆኑ፤ መልካቸውን እየቀያየሩ የሚሔዱበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ በተቻለ መጠን እነዚህ ግጭቶች ሰላማዊ እልባት እንዲያገኙ ለማድረግ በዋናነት ኃላፊነቱን ሊወስድ የሚገባው መንግስት ነው። መንግስትም ጥረት እያደረገ ይመስለኛል፡፡ መንግስት በኦሮሚያ ክልል አካባቢ ያለውን ችግር ለመፍታት አንድ ሁለቴ ድርድር ለማድረግ መሞከሩን እናውቃለን፡፡ ከዚህ በኋላም ድርድሩ ይቀጥላል፤ ቀጥሎ ወደ እልባት ይደርሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ መንግስት ለድርድር በሩ ክፍት መሆኑን እየገለፀ ይገኛል። በተቃራኒው ደግሞ በትግራይ ክልል ዙሪያ የነበረውን ጦርነት በድርድር ማስቆም ቢቻልም፤ በኦሮሚያ ክልል ለሚስተዋለው ችግር ግን የተሳካ ውይይት እንዳልተካሔደ ታውቋል። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ዲማ:- መንግስት የሚጠበቅበትን አንዳንዴም አልፎ እየሔደ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ አለበት። መንግስት ተቃዋሚው እምነት እንዲያድርበት ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ሲያደርግ ዛሬ መሳሪያ አንስተው ጫካ የገቡትም እምነት አድሮባቸው መሳሪያቸውን ጥለው ‹‹ነገ የማምንበትን ዓላማ በሠላማዊ መንገድ ላካሄድ እችላለሁ›› ብለው ከህብረተሰቡ ጋር ይቀላቀላሉ፡፡ ይህን የመሰለ እምነት ላይ እንዲደርሱ መንግስት አሠራሩን ሊያይ እና ሊያሻሻል ይገባል፡፡ አያያዙ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን በሚያሳምን መልኩ መሆን አለበት፡፡

መሳርያ ያነሱትም ቢሆኑ በውይይት ማመን አለባቸው። መሳርያ አንስቶ ውጤት ማምጣት እንደቀድሞው አዋጭ ላይሆን ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ተቀራርቦ ለመስራት መሞከር ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለአገር ዘላቂ ሰላም ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡ በብሔራዊ ምክክር ዙሪያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ?

ዶ/ር ዲማ:- የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋነኛ ዓላማው የአገሪቱን ዋና ዋና ችግሮች ከዚህ በፊት አንዳንዶች ትጥቅ ያነሱባቸው ጉዳዮችን በምክክር መድረክ እልባት ሰጥቶ ወደ በለጠ ሰላማዊ የፖለቲካ ሕይወት አገሪቱን መምራት ነው፡፡ ውይይቱ ዋና ዋና አጨቃጫቂ በሆኑ ጉዳዮች ሲሆን፤ ለምሳሌ ሕገመንግስቱ ይቀየር የሚሉ ሰዎች አሉ። ይቀየር ብለው ጠመንጃ ያነሱ ሰዎች ቢኖሩም፤ የለም መቀየር የለበትም ብለው የሚከራከሩም አሉ፡፡ መጀመሪያ ይቀየር የሚለው ላይ መስማማት ያስፈልጋል፡፡ ከዛም ምን ምን ዓይነት ቦታ ላይ ይቀየር? የሚለው ላይም መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ድርድር የሚያስፈልገው ለእዚህ ነው፡፡

ምክክሩ በኋላ ወደ ድርድር ይሔዳል፡፡ እኔም የተወስነ የምሠጠው አለ፤ ሌላውም የሆነ የሚሠጠው ነገር ይኖረዋል። እኔ ያልኩት ብቻ ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት። ብዙ ፍላጎቶች አሉ። በብሔር እና በሃይማኖት ብቻ አይደለም፡፡ በዕድሜ፣ በፆታ፣ በሥራ ለምሳሌ አንዱ አራሽ ሲሆን፤ ሌላው ከብት አርቢ ነው፤ በዚህ እና በሌሎችም በብዙ ጉዳዮች ልዩነቶች ይኖራሉ። ሁላችንንም የሚያስማማን ነጥብ ላይ መድረስ ይኖርብናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በብዙ ጦርነት እና ግጭቶች ውስጥ አልፈናል፡፡ በእዚህ በድህረ ጦርነት ማግስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአገር ሰላም እና ዕድገት ምን ማድረግ አለባቸው?

ዶ/ር ዲማ:- ዋነኛው ዓላማችን እና ምኞታችን ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊት አገር ማድረግ ነው። የፖለቲካ ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መንግስት ተጠያቂነት ያለበት የሚሆንበትን ሥርዓት መመሥረት ነው፡፡ ለእዚህ አንዱ ቁልፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር ነው፡፡ የመንግስትን ተጠያቂነት ማረጋገጥ የሚቻልበት አንዱ ነፃ ፕሬስ፣ ነፃ ፍርድ ቤት እና ነፃ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመሳሰሉት መኖራቸው ወሳኝ ነው፡፡

ምኞታችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት በመሆኑ በዚህ ሂደት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ትልቅ ነው። ሕዝቡ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሻለውን የመምረጥ እና የመጣል መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል፡፡ ይሔ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

 አዲስ ዘመን፡- ከጥንት ጀምሮ በአብዛኛው በቡድን ብረት ይዞ ወደ ትግል የመግባት ዝንባሌ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በተደጋጋሚ ይታያል። ይህ እንዳይሆን ሕዝቡ መነጋገር ላይ እንዲያተኩር ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ዶ/ር ዲማ:– ይህንን ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነው። እኛ ጋንዲ የለንም፡፡ የምናምነው እና የምንወደው ገዳይን ነው፡፡ በአመዛኙ ባህላችን በገዳዮች የሚያምን ነው። ገዳዮችን የመውደድ የፖለቲካ ባህላችን መለወጥ አለበት። ይህ እስካልተለወጠ ድረስ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡

አዲስ ዘመን፡- የፓርቲዎች እንቅስቃሴ እና የፖለቲካ ሁኔታ ሲነሳ የተቋማት አደረጃጀት እና ነፃነት ጉዳይ ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ዙሪያ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ዲማ:- እንደውም መጀመሪያ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲጠናክሩ፤ ተቋማት ገለልተኛ እና ሞያ ላይ የተመረኮዙ ለማንም የማይወግኑ መሆን አለባቸው። ተቋማት አንድ ፓርቲም ሆነ ማንኛውም ሰው ስልጣን ላይ ይኑር አይኑር ለማንም የማይወግኑ ተልዕኳቸው አገራዊ እና ሕዝባዊ ብቻ መሆን አለበት። ለምሳሌ የፍትሕ ተቋማት፣ መከላከያ፣ ደህንነትን የመሳሰሉት ተቋማት አገራዊ መሆን አለባቸው፡፡

ይሔ እየተደራጀ የሚሔደው በሒደት ነው። አሁን ላይ ካየናቸው አጀማመራችን ጥሩ ነው፡፡ ባለፉት ዓምስት ዓመታት ብዙ መሻሻሎች አሉ፡፡ ብዙ ለውጦች ተደርገዋል። ነገር ግን ይሔ እየተጠናከረ መሔድ አለበት የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ሌላኛው በፓርቲ እና በመንግስት መካከል ድንበር መኖር አለበት፡፡ ይሔ ድንበር ካልተስተካከለ ለሌሎችም በፖለቲካው ዘርፍ ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ተስፋ እና አመኔታን ያሳጣል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ እናመሰግናለን፡፡

ዶ/ር ዲማ:- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

 ምሕረት ሞገስ

 አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You