በ2016 ዓ.ም ወደ ተግባር የተገባባቸው የለውጥ ስራዎች

 ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮና በትኩረት መስክ ተለይተው እንዲሰሩ ማድረግ ለትምህርት ጥራትና በአገራችን እንዲገነባ ለምንፈልገው ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ወሳኝ መሆናቸውን ሳይታክት ሲናገር የቆየው የትምህርት ሚኒስቴር በያዝነው ዓመት ቃሉን አክብሮ ወደ ስራ የገባ መሆኑን፤ ቃልን ወደ ተግባር በመቀየር የለውጥ (ሪፎርም) ስራውን በማስኬድ ላይ እንደ ሆነ እየተናገረ ይገኛል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሐምሌ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ከለቀቀው መረጃ መረዳት እንደሚቸለው፣ እንደ አገር ያጋጠመንን የትምህርት ጥራት መጓደል ለማረም በሁሉም የትምህርት እርከን የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች ተቀርፀዋል። መቀረፅ ብቻም ሳይሆን፣ ወደ ሥራም ተገብቷል። ሪፎርሞቹ በትምህርት ዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለማረም መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች፤ በትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ የተሰነዱ ናቸው፡፡ በባለፉት አምስት ዓመታት ይህንኑ ፍኖተ ካርታና የለውጥ ምክረ ሃሳቦች በመከተል በአጠቃላይና በከፍተኛ ትምህርት ዘርፎች የሪፎርሙ ስራዎች የተተገበሩና በመተግበር ላይ ናቸው፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ እነዚህን ለውጦችና የሪፎርም ሃሳቦች በመከተል እየተተገበሩ ካሉ ጉዳዮች መካከል፤ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አመራር ብቃትን መሰረት ባደረገ መልኩ የዩኒቨርሲቲዎቹ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈውበት እንዲመረጡና እንዲሾሙ ማድረግ፤ አነስተኛው ሶስት ዓመት የነበረውን የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እርዝማኔ ወደ አራት ዓመት በማሳደግ የአንድ ዓመት የፍሬሽማን ፕሮግራምን በሥርዓተ ትምህርቱ ማካተት፤ በዩኒቨርሲቲዎች በመሰጠት ላይ የሚገኙትን ፕሮግራሞች በመገምገም የማጣጣም ሥራ፤ ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮና በትኩረት እንዲለዩ ማድረግና ወደ ተለዩባቸው የትኩረት መስኮች እንዲሸጋገሩ የሚረዳቸው የትግበራና የሽግግር እቅድ ማዘጋጀት፤ በዩኒቨርሲቲዎች ለመማር ማስተማር፣ ምርምርና ጥናት፣ ተቋማዊ አስተዳዳር እና የወል አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶችን ማጥናት፤ በተደረገው የትኩረትና ተልዕኮ ልየታ መሰረት ጉድለቶችን ለመሙላት መስራት፤ ተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎችን የማስፋፋት ስራን ለጊዜው መግታት፤ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ-ገዝነት እንዲሸጋገሩ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ምን ስልት መከተል እንደሚያስፈልግ መለየት፤ ለሁሉም የቅድመ ምረቃ ድግሪ ፕሮግራሞች የመውጫ ፈተና መተግበር፤ እንዲሁም፣ በኢንዱስትሪዎችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ጠንካራ ትስስርና ትብብር እንዲኖር መስራት እና የመሳሰሉት ይገኙበታል።

ከተቋሙ ተለቅቀው የነበሩ ጥናታዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የጥናቱን ውጤትም Springer የተባለው ዓለም አቀፍ አሳታሚ ድርጅት (https://link.springer.com/book/10.1007/978-3-658-39082-2 ድረ-ገጽን ይጎብኙ) በቅርቡ በመጽሐፍ መልክ አትሞታል። ይህን አገራዊ ጥናት መሰረት በማድረግ በሁሉም የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተልዕኮና የትኩረት መስክ ልየታ (Differentiation) በማድረግ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር መግባታቸው ይታወሳል።

እንደ ትምህርት ሚኒስቴር እምነት፣ ቀደም ሲል የነበረው የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች አደረጃጀትና ትግበራ ተጨባጭ በሆነ ሀገራዊና ክልላዊ ፍላጎት ጥናትን መሰረት ያደረገ ባለመሆኑ የሚመረቀውና የሚፈለገው የሰው ኃይል ሊጣጣም አልቻለም፡፡ በመሆኑም ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮና የትኩረት መስክ ለይተው ወደ ተግባር እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

* የሚከፈቱ የትምህርት ክፍሎችና ፕሮግራሞች የዩኒቨርሲቲዎችን ውስጣዊ አቅም (የመምህራን፣ ትምህርት ግብአቶች፣ መሰረተ ልማትና ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶችን ያማከሉ ያሟሉ ለማድረግ)፤

* ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢዊ ጸጋን መሰረት አድርገውና ተጠቅመው የመስራት ባህላቸው ለማሳደግ፤

* ዩኒቨርሲቲዎች ባላቸው ነባራዊ የትኩረት መስክ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ለማስቻል፤

* ከተለመደውና ባህላዊ ከሆነው የአደረጃጀትና ትግበራ ለመላቀቅ ፤

* ዩኒቨርሲቲዎች ከሚታይባቸው የትምህርት ክፍሎችና ፕሮግራሞች መደጋገምና መደራረብ ለማላቀቅ፤

* ደረጃውን የጠበቀ የመማር-ማስተማር ሂደት ለማስፈን፤

* አስፈላጊ የሆኑና የተመረጡ የትምህርት ክፍሎችና ፕሮግራሞች ላይ በማተኮር እንዲጠናከሩ ለማስቻል፤

* የሚከፈቱ የትምህርት ክፍሎችና ፕሮግራሞች ሀገራዊና ክልላዊ ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ ማስቻል በዋነኝነት የተመላከቱ ጉዳዮች ናቸው።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኮና የትኩረት መስክ ልየታ አስፈላጊነትና በዩኒቨርሲቲዎች ለትምህርት ጥራት ያለውን አስተዋፅኦ አስመልክቶ በተዘጋጀውና ይፋ በተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደ ሰፈረው፣ ዩኒቨርሲቲዎች በተልዕኮና ትኩረት መስክ ተለይተው ወደ ትግበራ መግባታቸው የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅና አለማቀፋዊነትን ከማረጋገጠ አኳያ አዎንታዊ ለውጦች እየተመዘገቡ ነው፡፡ በዚህም የተደጋገሙና ተመሳሳይ የሆኑ የትምህርት ክፍሎችና ፕግራሞችን የማጠፍ፤ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑትን ደግሞ የማስፋትና የማጠናከር፤ አማራጮችን የማስፋት፤ ያለውን ሀገራዊ እና ክልላዊ ፍላጎት መሰረት የማድረግ፤ የአቅም ግንባታና ሌሎች የማደራጀት ስራዎች በትኩረት በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ፣ ተልዕኮና የትኩረት መስክን ለይቶ መፈጸምን በተመለከተ ተቋማቱ ግንባር ቀደም ሆነው እንዲወጡ፤ ተቋማዊ ነጻነታቸው እንዲጎለብት፤ እንዲሁም በምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎቻቸው ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ፋይዳው የጎላ መሆኑን በትግበራ ሂደት ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ይሁን እንጂ በትግበራ ወቅት በትምህርት ማህበረሰቡ በኩል አልፎ አልፎም ቢሆን ተገቢ ያልሆኑ ስጋቶች እየተስተዋሉ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል የሚለው የሚኒስቴሩ የወቅቱ መግለጫ፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዩኒቨርሲቲዎች በተልዕኮና የትኩረት መስክ ለይተው ወደ ተግባር መግባታቸው ለዩኒቨርሲቲውም ይሁን ለአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ እድል እንጂ ስጋት የሚሆንበት ጉዳይ የለም በማለትም አስፍሯል፡፡

በተለይም ከላይ ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮና ትኩረት መስክ መለየት ያስፈለገበት ዝርዝርና ምክንያታዊ እሳቤዎች በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን፤

እነዚህን ጥናታዊ ተግባራትና አስተያየቶች ተግባራዊ ለማድረግ የሚሰሩ ስራዎች በተለመደው መልኩ ይቀጥላሉ ማለት ሳይሆን ምቹ የሆነ አደረጃጀት ፈጥሮ መጠቀም እንደሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል። በተጨማሪም ትግበራው ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው የትግበራ ስትራቴጂ መሠረት እየተፈጸመ ያለ ሲሆን፣ በተቋማቱ ሲተገበሩ የነበሩ፤ ነገር ግን የዩኒቨርሲቲዎቹ ትኩረት መስክ የማይሆኑ ፕሮግራሞች ቢያጋጥሙ በሌሎች አማራጮች የሚቀርቡበት እድል ዝግ አይደለም የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና ብቃት ማሻሻያ ዴስክ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሰይድ መሀመድ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት ከሆነ፣ የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኮና የትኩረት መስክ ልየታ ማሳያ በጥናቱ መሰረት ዩኒቨርሲቲዎች ከሚኖራቸው ዓለም-አቀፋዊ፣ ሀገራዊና ክልላዊ ጠቀሜታ አንጻር ከዚህ በሚከተሉት ዋና ዋና ተልዕኮዎች ተለይተዋል።

1. የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች (Research Universities)

2. አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች (University of Applied Sciences)

3. የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች

4. አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎች (Comprehensive Universities) ሲሆኑ፣ በ2014 አንድ ተጨማሪ ልዩ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ (ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ) እንዲለይ ሆኗል።

በላይኛው ልየታ መሰረት (ዝርዝሩን ከሌሎች የተቋሙ ሰነዶች ነው ያገኘነው)፣ 1. አዲግራት ዩኒቨርሲቲ 2. ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ 3. ቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ 4. ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ 5. እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ 6. ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ 7. ደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ 8. ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ 9. ጂንካ ዩኒቨርሲቲ 10. ቀብሪድሃር ዩኒቨርሲቲ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ 12. መቅደላምባ ዩኒቨርሲቲ 13. መቱ ዩኒቨርሲቲ 14. ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ 15. ኦዳቡልቱም ዩኒቨርሲቲ 16. ራያ ዩኒቨርሲቲ 17. ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ 18. ወራቤ ዩኒቨርሲቲ 19. ወልድያ ዩኒቨርሲቲ 20. ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ 21. ቦረና ዩኒቨርሲቲ በ“አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎች፡፡

1. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 2. ጅማ ዩኒቨርሲቲ 3. ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 4. ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ 5. ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ 6. ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ 7. መቀሌ ዩኒቨርሲቲ 8. አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ“የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች።

አምቦ ዩኒቨርሲቲ 2. አርሲ ዩኒቨርሲቲ 3. አሶሳ ዩኒቨርሲቲ 4. አክሱም ዩኒቨርሲቲ 5. ዲላ ዩኒቨርሲቲ 6. ድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ 7. ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ 8. ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ 9. ወሎ ዩኒቨርሲቲ 10. ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ 11. ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ 12. ሰመራ ዩኒቨርሲቲ 13. ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ 14. ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ 15. ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በ“የተግባር ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ስር፤ እንዲሁም፡፡

አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በ“ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች (STUs) ስር እንዲያርፉ ተደርጎ የመማር ማስተማሩ ስራ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና ብቃት ማሻሻያ ዴስክ ኃላፊው አቶ ሰይድ መሀመድ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደ ተናገሩት ይህ ልየታ ያስፈለገው ከትኩረት መስክና ተልእኮ አኳያ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት የነበረው የመማር-ማስተማር ሁኔታም ይሁም የዩኒቨርሲቲዎቹ አደረጃጀት ከተልእኮና የትኩረት መስክ አኳያ ሳይሆን ሁሉም አንድ አይነት የትምህርትና ጥናት መስኮችን የሚያቀርቡበት፤ ተመሳሳይ የትምህርት ፕሮግራሞችን የሚሰጡበትና የአገርና ሕዝብ ፍላጎቶችን ያላገናዘቡ ነበሩ። በመሆኑም ይህ ልየታ አስፈልጓል። በልየታው መሰረትም በጥልቅ ጥናትና ተግባር ላይ የተመሰረተ የተቋማቱ ድልድል ተከናውኗል።

ኃላፊው እንደነገሩን ከሆነ ከ2014 ዓ∙ም ጀምሮ ሲጠና የነበረው መሰረታዊ ጉዳይ፣ በልየታው መሰረት በዚህ ዓመት ወደ ተግባር የተገባ ሲሆን፣ የየተቋማቱ ስርዓተ ትምህርቶችም (ካሪኩለም) በዚሁ መሰረት እየተዘጋጁ ይገኛሉ። ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በልየታው መሰረት ካላቸው ማንነት አኳያ የየራሳቸውን ስርዓተ ትምህርት በመከለስ በማዘጋጀት ላይ ናቸው።

አቶ ሰይድ እንደሚሉት፣ በተልእኮና ትኩረት መስክ ከመደራጀት አኳያ የቀድሞዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች የተሻሉ ነበሩ። ለምሳሌ እርሻ ወይም ግብርና ሲባል በእያንዳንዳችን አእምሮ ውስጥ የሚመጣው የቀድሞው አለማያ የዛሬው ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ነበር። አንድ ተማሪ ውሀ ቴክኖሎጂን ለማጥናት ካሰበ አስቀድሞ በአእምሮው የሚመጣው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንጂ ሌላ አይደለም። ሌሎቹንም በዚሁ መልክ ማሰብ ይቻላል። ስያሜያቸው ራሱ ይናገራል። አሁን ግን ያ የለም። ሁሉም ሁሉንም ይሰጡ ዘንድ የተቋቋሙ ናቸው። የየራሳቸው ልህቀት (ኤክሰለንስ) የላቸውም። ያ ደግሞ የሚያስኬድ ባለመሆኑ በሪፎርሙ (ለውጡ) እንዲታይ ተደርጓል። በተልእኮና ትኩረት መስክ መለየቱ አስፈላጊ ስለሆነም ነው ወደ እዚህ አሰራር መምጣት የተፈለገው። ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱም እንደዛው።

ሌላው በዚሁ በ2016 ወደ ተግባር የተገባበት ጉዳይ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች የመግቢያ ፈተና (GAT) ሲሆን፣ እንደ አቶ ሰይድ ማብራሪያ ተግባሩ በጥሩ ሁኔታ ተከናውኗል። ተቀባይ ተቋማትም የየራሳቸውን ፈተና በመስጠት ተፈላጊውን ውጤት ያመጡትን እየተቀበሉ በማስተማር ላይ ናቸው።

ለረዥም ጊዜ ሲጠና የቆየውና ዘንድሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደ ስራ የተገባበት የራስ ገዝ (ኦቶኖሚ) አወቃቀር ሲሆን፣ ወደ ፊት ሁሉም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ወደዚሁ ራስ ገዝ አወቃቀር እንዲገቡ እንደሚደረግ አቶ ሰይድ ተናግረዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ዓመት የተጀመረው የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናም በዚህ ዓመትም ቀጥሎ የተማሪዎች ውጤትና ለፈተናው እያደረጉት ያለው ዝግጅት እየተሻሻለ በመምጣት ላይ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል። ይህ “ለመጀመሪያ ጊዜ ቢባልም፣ የመውጫ ፈተናው ድሮ ለሕግና ለህክምና ተመራቂዎች ይሰጥና ውጤታማ ስራም እንደ ነበር አስታውሰዋል።

በአጠቃላይ፣ ትምህርት ሚኒስቴር በ“አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ስም ከመሰረቱ የተበላሸውን የአገሪቱን የትምህርት ስርዓት ከመሰረቱ ለማሻሻል በርካታ የማሻሻያና የለውጥ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ስንገልፅ መቆየታችን ይታወቃል። ዛሬም ከላይ የጠቀስናቸውና መሰረታዊ ለውጦች የሆኑትን፣ ጥቂቶቹን ይዘን መቅረባችን ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊታይ የሚችል ነው። ወደ ፊትም ሌሎች ከለውጡ (ሪፎርም) ጋር በተያያዘ የተከናወኑ ስራዎችን ይዘን የምንቀርብ መሆናችንን በመግለፅ የዛሬውን ዝግጅታችንን እናጠናቅቃለን።

 ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You