ኢትዮጵያውያን የረጅም ሀገረመንግስት ባለቤት የሆኑበት ሆነ ሀገረ መንግስቱን አጥንተው ማቆየት የቻሉበት ትልቁ ሚስጥር ብሄራዊ ጥቅሞቻቸው በየትኛውም ሁኔታ አሳልፎ ያለመስጠት ማኅበራዊ ማንነት ባለቤት መሆናቸው ነው። ይህ በብዙ ጥንቃቄ እና እንክብካቤ /አስተምሮ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ማንነት የዚህ ትውልድም መገለጫ ነው።
የቀደሙት ትውልዶች በየዘመኑ የተከሰቱ ሀገረ መንግስቱን ሆነ ብሄራዊ ጥቅሞቻችንን የሚፈታተኑ የውስጥና የውጪ ፈተናዎች፤ የሀገርና የሕዝብን ጥቅም ባስቀደመ መንገድ ከፍ ባለ መስዋዕትነት መሻገር ችለዋል፤ በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያተረፈ ማንነት ፈጥረው አልፈዋል።
ይህ የፈጠሩት ማንነት ቀጣዩ ትውልድ አንገታቸውን አቅንተው እንዲሄዱ አስችሏል፤ በብዙ የማንነት ቀንበር ጎብጠው ዘመናት ላስቆጠሩ ሕዝቦች መንፈሳዊ መነቃት በመፍጠር ቀና ብለው የሚሄዱበትን፤ ዕጣፈንታቸውን በራሳቸው የሚወስኑበትን እድል በመስዋዕትነታቸው ህያው ማድረግ እንዲችሉ ረድቷቸዋል።
ይህ ትናንቶቻችንን ያደመቀው፤ ለዛሬያችን አቅም የሆነንና ነገዎቻችንን በብዙ ተስፋ እንድንጠብቅ ያደረገን ጥቅሞቻችን ላይ ያለመደራደር ብሔራዊ ማንነታችን፤ የዚህ ትውልድ መገለጫ ሆኖ ስለመቀጠሉ በዓባይ ግድብ ግንባታ ላይ በተጨባጭ የታየ ” ይቻላል ”በሚል አዲስ ትርክት ትውልዱን ያንቀሳቀሰ ነው።
ይህ ትርክት ትውልዱ ሀገሪቱ አስተማማኝ እና ፈጣን የወደብ አገልግሎት የምታገኝበትን አዲስ ተጨማሪ የታሪክ ምዕራፍ እንዲጽፍ አቅም ፈጥሯል። የዝምታን መጋረጃ ገፍፎ፤ ከራሱ አልፎ የትውልዶችን ዕጣ ፈንታ ሊቀይር በሚችል ብሩህ ተስፋ መንቀሳቀስ እንዲችል ረድቶታል።
በቀደሙት ዘመናት ሀገራችን እንደ ሀገር ከአንድም በላይ የባህር ወደብ ባለቤት እንደነበረች የታሪክ ሰነዶች ያረጋገጡት፤ ወደፊትም ሊያረጋግጡት የሚችሉት እውነታ ነው። በነዚህ ዘመናት ለነበሩ መንግስታት ግዝፈትም እነዚህ ወደቦች በአንድም ይሁን በሌላ የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍያለ እንደነበር ይገመታል።
ለሀገረ መንግስቱ ጥንካሬ የወደቦቹ ግልጋሎት የቱን ያህል ከፍያ እንደሆነ፤ ከሁሉም በላይ እንደ ሀገር ወደብ አልባ በሆንባቸው ስስት አስርት ዓመታት ያጋጠሙን ችግሮች፤ ችግሮቹን ለመሻገር እየከፈልነው ያለው ዋጋም ሆነ፤ ችግሮቹ ተስፋ ባደረግናቸው ነገዎቻችን ላይ ያጠሉትን ጥላ በአግባቡ መመልከት ተገቢ ነው።
ሀገሪቱ ያለችበት የቀይ ባህር አካባቢ ካለው ጂኦ- ፖለቲካዊ ጠቀሜታ አንጻር የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነው፤ ከዚያም በላይ አሁነኛው የዓለም ፖለቲካ ተገማችነት አስተማማኝ አይደለም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ይዞ በየትኛውም መልኩ መዘናጋት በሀገር ላይ የከፋ ጥፋት የመጋበዝ ያህል ነው።
በተለይም ዓለም በብዙ ፍላጎቶች ውጥረት ውስጥ በምትገኝበትና ውጥረቶቹ እያስከፈሉ ያለው የከፋ ዋጋ በተጨባጭ እየታየ ባለበት፤ ወዳጅነትና ጠላትነት በግልጽ መስመር ተለይተው በማይታዩበት፤ ብሔራዊ ጥቅም የጥቅሞች ሁሉ ”አልፋና ኦሜጋ ” በሆነበት ዓለም ራስን በአግባቡ ማዘጋጀት ለነገ የሚባል የቤት ስራ አይደለም።
ከዚህ አንጻር መንግስት ካለበት ኃላፊነት አኳያ ዝምታዎችን እየሰበረ፣ ብሄራዊ ጥቅሞቻችንን ለማስጠበቅ፤ ከዚያም አልፎ ሀገርን እንደሀገር የህልውና ስጋት ውስጥ የሚከቱ አደጋዎችን ከወዲሁ ለመከላከል የሚያደርገው ስትራቴጂያዊ ጥረት የዜጎችን እውቅና እና ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚፈልግ ነው።
በተለይም አሁን ላይ ሀገሪቱን አስተማማኝ የወደብ ባለቤት በማድረግ፤ ከወደብ አገልግሎትም ሆነ፤ የወደብ ባለቤት በመሆን የሚገኝ ስትራቴጂክ ተጠቃሚነትን ተጨባጭ ለማድረግ የሚያደርገው በብዙ ፈተናዎች የታጀበ ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ መላው ሕዝባችን ዓባይን ለመገደብ ያደረገውን ርብርብ ያህል በተጠናከረ መንገድ ሊደግመው ይገባል።
ይህ የመንግስት ጥረት፣ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ አዲስ ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ትርክት መጻፍ የሚያስችል መልካም ዕድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ትውልዱ በ”ይቻላል” መንፈስ ለጀመረው የበለጸገች ሀገር ግንባታ ስኬት ትልቅ አቅም፣ ተጨባጭ ተሞክሮ ተደርጎ የሚወሰድ፤ የመጪዎቹን ትውልዶች ዕጣ ፈንታ ቀያሪ ነው !
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም