ሀገራት ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን አስጠብቀው ለማስቀጠል በብዙ መልኩ ይንቀሳቀሳሉ። ይህ ዓለም አቀፋዊ እውነታ ዛሬ ላይ የተጀመረ ሳይሆን ከሀገራት መፈጠር ጋር አብሮ ሊተሳሰር እንደሚችል ለመገመት የሚከብድ አይደለም። እውነታው በየዘመኑ የተለያዩ ቅርጾችን እየተላበሰ አሁን ላይ ደርሷል ።
በተለያዩ ወቅቶች ሀገራት ጡንቻቸውን እየመዘኑ ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ያሳጡናል ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ በግልጽም ሆነ በስውር ጦርነቶችን በማካሄድ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ ረጅም ርቀት ሄደዋል። በዚህም ዓለም ብዙ ዋጋ ለመክፈል የተገደደችባቸው አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል ።
ከዚህ በተለየ ሁኔታ ሀገራት የሕዝቦቻቸውን የጋራ ተጠቃሚነት መሠረት ባደረገ መንገድ፤ ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን ሰጥቶ በመቀበል መርሕ፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በፈገግታና በእንኳን ደስ ያለን መንፈስ በእጃቸው በማስገባት የሕዝቦቻቸውን ነገዎች ብሩህ ማድረግ የሚያስችሉ ርምጃዎችን ሲወስዱም ተስተውሏል ።
አሁን አሁን ቀጣይ ዘመናት ይዘውት ሊመጡ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ታሳቢ በማድረግ ችግሩን በጋራ መሻገር የሚቻልበትን አቅም ለመገንባት አካባቢያዊ ኅብረትን በመፍጠር ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን በተሻለ መንገድ ለማስጠበቅ መሥራት እየተለመደ መጥቷል። ለማሳያም የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ የተለያዩ አካባቢያዊ ኅብረቶችን ማንሳት ይቻላል።
ከዚህም ባለፈ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅሜን ይጎዳል ብለው ባመኑ ቁጥር፤ ከድንበሮቻቸው በሚሊዮን ኪሎ ሜትሮች ርቀት በመጓዝ ወታደራዊ ሰፈሮችን ማቋቋም፤ አስፈላጊ ነው ብለው ባመኑ ቁጥርም፤ ኃይልን መጠቀም እንደ አንድ ስትራቴጂክ አማራጭ መውሰዳቸውም የአደባባይ ሐቅ ነው።
በቀይ ባሕር አካባቢ የተገነቡ የጦር ሰፈሮችን ማየት በራሱ በቂ ነው። ኃያላን የሚባሉት ሀገራትን ጨምሮ በአካባቢው ሊኖር የሚችለው የትኛውም ስጋት ብሔራዊ ጥቅሜን አደጋ ውስጥ ይከታሉ ያሉ ሀገራት ዓይናቸውን በአካባቢው ላይ ጥለዋል። በአካባቢው ወታደራዊ ሰፈሮችን የመገንባት ፍላጎታቸውም ከፍ እያለ መጥቷል።
በርግጥ አካባቢው በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው ስትራቴጂክ ጠቀሜታ አንጻር የብዙዎችን ትኩረት መሳቡና ብዙዎች አካባቢው ከብሔራዊ ጥቅሜ አንጻር የዕይታዬ ማዕከል ነው ማለታቸው እንግዳ ጉዳይ አይደለም፤ የነበረና የሚጠበቅ፤ በአካባቢው ለሚስተዋለውም አለመረጋጋት አንዱ ምክንያት ነው ።
በአካባቢው ሊከሰት የሚችል የትኛውም ዓለም አቀፍ ስጋት የቀጣናውን ሀገራት ሕዝቦች የማይመለከት አድርጎ የማሰብ፤ የአካባቢው ሀገራት የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ የሚያደርጓቸውን ጥረቶች ያልተገቡ በማድረግ ዓለም አቀፍ አጀንዳ አድርጎ ለማሳየት የሚደረጉ ሙከራዎች ብዙ ናቸው ።
የቀጣናው ሀገራት ካሉበት አሁናዊ ሁኔታ አንጻር፤ በአካባቢው ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን በተናጠል መቋቋም የሚችሉበት አቅም የላቸውም። በአካባቢው ከስድስት አስርተ ዓመታት በላይ የቆየው አካባቢያዊ የፖለቲካ ባሕልም ሆነ የውጪ ጣልቃ ገብነት ሀገራቱ ኅብረት ፈጥረው ስጋቶቻቸውን በጋራ መከላከል የሚችሉበትን አቅም ማጎልበት የሚያስችል አይደለም ።
ይህ ተጨባጭ የሆነው አካባቢያዊ እውነታ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዛ ወደብ አልባ ለሆነችው ኢትዮጵያ የቱን ያህል ፈተና እንደሚሆንባት፤ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ሊፈጥርባት እንደሚችል ለመገመት ከፍ ያለ የዳበረ እውቀት የሚጠይቅ አይደለም። የትኛውም ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው ሊረዳው የሚችል ነው።
ሀገራችን ይህ ችግር ይዞባት ሊመጣ ከሚችለው የከፋ ፈተና አንጻር እንደሀገር አስተማማኝ አማራጭ የባሕር በር የማግኘት የሕግ፣ የታሪክና የሞራል መብት አላት። ይህንን መብቷን ተጨባጭ ለማድረግ የምትሄድባቸውን የሰላም አማራጮች ሁሉ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ተቀብሎ የማስተናገድ ኃላፊነት አለበት።
ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ በሚል ባሕር ተሻግረው፤ ወታደራዊ ሰፈሮችን እየገነቡ ፤ከዚያም አልፈው የኃይል አማራጮችን ታሳቢ ያደረጉ ርምጃዎችን በአደባባይ ተግባራዊ እያደረጉ ባሉበት በአሁኑ ወቅት፤ ብሔራዊ ጥቅሞችን በሰላማዊና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት በማድረግ ለማስጠበቅ የሚደረግን ጥረት ላለመቀበል የሚያስችል ምንም ምክንያት የለም!
በተለይም የአካባቢው ሀገራት የሕዝቦቻቸው ነገዎች በተጨባጭ ተስፋ የተሞሉ እንዲሆኑ፤ የጋራ ተጠቃሚነት በጋራ ከመንቀሳቀስ ውጪ አማራጭ እንደሌለ በአግባቡ ሊረዱት ይገባል። ለዚህም ላለፉት ስድስት አስርተ ዓመታት በቀጣናው የነበረውን ዛሬም ያለው እውነታ ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ሊያጤኑት ያስፈልጋል።
የቀጣናው ሀገራት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሚተርፍ የብዙ ሀብት ባለቤቶች ሆነው ባሉበት ተጨባጭ እውነታ፤ ለከፋ ድህነትና ኋላቀርነት ተዳርገዋል። እንኳን ነገ እና ከነገወዲያን ቀርቶ ዛሬን የሚያሸንፉበት አቅም አጥተው በጠባቂነት ዓመታትን ለማሳለፍ ተገድደዋል ።
ይህ እውነታ ባለንበት ዘመን በየትኛውም መንገድ ሊቀጥል የሚገባ አይደለም። ሀገራቱ የሕዝቦቻቸውን ነገዎች ብሩህ ለማድረግ፤ ሕዝቦቻቸውን ከከፋ ድህነትና ኋላቀርነት፤ ከዚህ ከሚመነጭ ጠባቂነት ለመታደግ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ አዲስ እሳቤ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል ።
ይህንን እውነትም ለማድረግ ሁሉም የአካባቢው ሀገራት ያላቸውን አቅሞች አቀናጅተው ለሕዝቦቻችው ተስፋ ኢንቨስት ማድረግ፤ ሕዝቦቻቸው ቀና ብለው የሚሄዱበትን ማንነት መገንባት ይጠበቅባቸዋል፤ ኢትዮጵያም አሁን ላይ ኃላፊነቱን ወስዳ እንደሀገር በቀጣናው እያራመደችው ያለው ይህንኑ ነው !።
አዲስ ዘመን ጥር 12 ቀን 2016 ዓ.ም