የጎዳና ተዳዳሪዋን ወጣት…

በአፍላው የወጣትነት እድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ከሁለቱም ፆታዎች የተሰባጠሩ ናቸው። በርከት ብለው ነው ከወዲያ ወዲህ የሚንቀሳቀሱት። በቡድን መጋዛቸው ጥቃትን ባያስቀርም ስለሚቀንስ መለያየትን አይመርጡም። ወጣቶቹ በተለመደው አጠራር ጎዳና ተዳዳሪ ይባላሉ፤ ‘ተዳዳሪ’ የሚለው ቃል እድሜ ልካቸውን የሚኖሩ ያስመስለዋል ብለው የሚቃወሙ ሰዎች ደግሞ ‘ጎዳና አዳሪዎች’ የሚለውን ስያሜ ይጠሯቸዋል። እኔም ለዚህ ፅሁፍ ጎዳና አዳሪዎች የሚለውን ምርጫዬ አድርጊያለሁ።

ልጆቹ በበጋ ወቅት የሚለበስ እንኳን ሳይፈልጉ በመሸባቸው ቦታ ማደርን ይመርጣሉ፤ ክረምት ግን እንዲህ እንደዋዛ በመሸበት ማደር አይሰራም። አጅግ በጣም ከባድም አደገኛም ሊሆን ይችላል። ለደህንነታቸው ሲሉ ዶፍ ዝናብ፣ ጎርፍ፣ ውርጭ የማይደርስበት ቦታ መምረጥ የግድ ይላቸዋል። ለብርዱ ደግሞ ከድልድይ በታች የተሻለ ቦታ አይገኝም።

ከድልድይ በታች ቦታ ለማግኘት ግን መታደል ያስፈልጋል። በክረምት ከጥጋጥጉና ከድልድዮቹ ስር ሌላ ሕይወት አለ። እንደ ነገሩ በካርቶን እና ጣውላ የታጠሩ ክፍሎች የሚመስሉ ስፍራዎች አሉ፤ መሀላቸው ቀጫጭን ፍራሾች፣ ብርድ ልብሶችና አንሶላዎች አሉ። ላስቲክም ማደበሪያም የተገኘው ነገር በሙሉ ተሸፍኖ የውሃ ነጠብጣቦች አንዳይገቡበትም መከላከል ይገባል። ያገለገሉ ሶፋዎች እና ምድጃዎችም ሌሎች ለመኝታም ለመመገቢያም የሚያገለግሉ ቁሶች ይታያሉ።

ሕፃናት ከነወላጆቻቸው አነስተኛ ቦታ ላይ ተደርድረው ይታያሉ፤ ወጣቶች በብዛት አራትም አምስትም ከዚያም በላይ ሆነው ሙቀት ለመፍጠር በሚመስል መልኩ ተጠባብቀው ይተኛሉ ሌሎች የተወሰኑ ወጣቶች ደግሞ ንጋት ላይ እሳት አያይዘው በዙሪያው ተኮልኩለው ይጨዋወታሉ።

የግንብ ስሮችና ድልድልዮቹ በጎዳና አዳሪዎቹ ዘንድ ለምን ተመራጭ ሆኑ ተብለው ሲጠየቁ የሚመልሱት “እንዴ! ድልድዮቹ ለእኛ በአጭሩ ቤታችን ናቸው። እንዲሁ ዝም ብለን በምናብ የሳልነው ቤት ሳይሆን እንደ ሀብታሞቹ በክረምት ከዝናቡና ብርዱ፤ በበጋም አልፎ አልፎ ከፀሀዩ የምናርፍባቸው ቤታችን ናቸው” ይላሉ።

ጎዳና አዳሪዎች የቀን መኝታ ብሎ ነገር አያወቁም። አይደለም ጎዳና አዳሪዎች ኑሮ የሞላላቸው ሰዎች ራሳቸው ቀን አይተኙም። ልተኛ ቢባልስ ደግሞ ሆድ ባዶ ሆኖ እንቅልፉ ራሱ ከዬት ይመጣል? ይህ ከባድ እውነታ ነው።

ከንጋት እስከ ምሽት ድረስ ያለውን ጊዜ የሚያሳልፉት ግማሾቹ የተጣሉ የፕላስቲክ ምርቶችን፣ ከፊሎቹ ደግሞ ብረታ ብረት ለቅመው ይሸጣሉ። ይህን የሚያደርጉት ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ በልቶ ለማደር ቢሆንም የሰበሰቡት ገንዘብ እንዲቀመጥላቸው ሲሉ በየምግብ ቤት እየዞሩ ‘ተመላሽ’ መፈለግም የየእለት ተግባራቸው ነው። ‘ተመላሽ’ ማለት የምግብ ቤት ደንበኞች በልተው የተረፋቸው እና ተጠራቅሞ በፌስታል የሚሰጣቸው ምግብ ነው፡፡ ተመላሽ በነፃ የሚሰጧቸው ምግብ ቤቶች እንዳሉ ሁሉ በተወሰነ ገንዘብ የሚሸጡላቸው አሉ። አንዳንዴም በጉርሻው መጠን ተመን ይወጣለታል።

ታዲያ ቀን የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ሲንጠራወዙ ከሚውሉት የጎዳና ልጆች መካከል ደመቅ ጎላ ብላ የምትታየው ወጣት ሳምራዊት ትባላለች። ሳምራዊት ከልጅነት እስከ እውቀት መሸከም የማትችለው ስቃይ ወላጆቿ ይሁኑ አሳዳጊዎቿ በውሉ በማይገቧት ሰዎች ቤት ውስጥ ደርሶባታል። ከረሀቡ ጭቅጭቁ፤ ከጭቅጭቁ ዱላው በየተራ ሲፈራረቁባት ነበር ደጁን የማተረችው። በአቅራቢያዋ ጎዳና ላይ የምታያቸው ልጆች እሷ ቤቷ ውስጥ ከሚደርስባት መከራ የተሻሉ መስሎ ታያት። እሷ መከራ ብላ የምታስበው ነገር ሲበዛ ከመሞት መሰንበት ብላ ጎዳናን ምርጫዋ ያደረገች ወጣት ናት።

ወጣቷ ሳምራዊት

ከቤቷ የወጣችው ሳምራዊት አሁን ላይ ከድልድዩ ስር ከሚኖሩት ወጣቶች አንዷ ናት፤ ከጓደኞቿ ጋር የምትኖረው ሳምራዊት ከእነሱ በእድሜ ከፍ ስለምትል ጓደኞቿን እንደ ልጆቿ ነበር የምትንከባከባቸው። እሷና እንደ ሳምራዊት አጠራር ልጆቿ የእለት እንጀራቸውን ለማግኘት አንዳንድ ስጋ ቤቶች ቅንጥብጣቢ በማምጣት እና ከሌሎች ሱቆችና አትክልት መሸጫዎች ደግሞ ሊበላሹ የደረሱ ሽንኩርትና ቲማቲም ለምነው አምጥተው እሳት አንድደው ምግብ በመስራት በጋራ ይኖራሉ።

ከምግቡም በላይ ትስስሩ አብሮ መኖሩን ተላምደውታል። አንዳቸው ለአንዳቸው ከለላ አንዳቸው ለአንዳቸው መከታ ናቸው። በእለቱ በአካባቢያቸው በሚገኘው ቀጨኔ መድሀኒዓለም ቤተክርስትያን የነፍሰ ይማር ዝክር ስለነበር ሳምራዊትና ጓደኞቿ ሲበሉና ሲጠጡ ውለው ደክሟቸው ነበር በጊዜ መጥተው የተኙት።

ልጆቹ እንቅልፍ ጥሏቸው ነበር። በጥልቅ አንቅልፍ ወስጥ በመሆናቸው የተነሳ አጠገባቸውም ቦንብ ቢፈነዳ እንኳን አይነቁም በሚያስብል ደረጃ ጧ ብለው ተኝተዋል። ይህን አጋጣሚ ሲጠብቅ የነበረው ክፉ ሰው ከመካከላቸው ከፍ ብላ የምትታየውን ሳምራዊት በአይኑ ሙሉ ተመለከታት።

ያኔ ልጆቼ የምትላቸውን ጓደኞቿን ለመጠበቅ ስትል ዳር ላይ የተኛችው ሳምራዊት ቀን በጠጡት ጠላ ምክንያት ይሁን በሌላ ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ነበረች።

ቀን ለጎደለባት የዋለ ቀነ ጎዶሎ

ዋልጌ ነው፤ ስነ ምግባር የሚባል ነገር ያልፈጠረበት። ያንንም ያንንም መዝለፍ መለያ ባህሪው ነበር። ነገሮችን በፍቃድ ከማድረግ ይልቅ ጉልበት የሚቀናው ሁሉን ነገር በሀይል ማግኘት የሚችል የሚመስለው አይነት ሰው ነው። ዝናው ተገኝ ይባላል።

በአካባቢው የተጠላም የተፈራም ሰው ነበረ። ከእሱጋ መቀራረበ አንድ ቀን ዋጋ እንደሚያስከፍል የተረዱ ሁሉ ቀስ በቀስ እየራቁት ሄደው ብቻውን ቀርቷል። በሰማኒያ ያገባት ሚስቱን እንኳን ሳይቀር በድብደባ አሰልችቶ ያባረረ ክፉ ሰው ነው።

በብቸኝነቱ የተነሳ ብስጭት እየጨመረ ቀኑን ሙሉ ሲጠጣ የሚውለው ይህ ሰው ሲመሽ ለክፋቱ ማረፊያ ሕፃናትን መመልከት ከጀመረ ሰነባብቷል። እስከ አሁን ድረስ ባይሳካለትም ለዛሬ ግን ወጥመዱ የያዘለት መስሏል።

ቀጨኔ መድሃኒዓለም አቅራቢያ ከሚገኝ አንድ ድልደይ ስር መጠለያቸውን ሰርተው ያረፉት ሕፃናት አይኑ ከገቡ ሰነባብተዋል። እነዚህ የጎዳና ልጆች ለወትሮው እርስ በእርስ መጠባበቅን መርሃቸው አድርገው ስለሚንቀሳቀሱ ክፉ ነገር ደርሶባቸው አያውቅም ነበር።

ዛሬ ግን ቤተክርስቲያን ለነፍስ ይማር የመጣ ምግብና መጠጥ ተትረፍርፎ ስላገኙ ያገኙትን በሙሉ በልተውና ጠጥተው ደክመው ስለነበር በጊዜ ነበር አንቅልፍ የጣላቸው። ይህንን የተረዳው ይህ ሰው ምሽቱ እስኪገፍና ሰው ሁሉ ቤቱ ገብቶ ጭር እስኪል አንድ ቦታ ተሸሽጎ መጠበቅ ጀመረ።

በግምት ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ሲሆን ግራ ቀኙን ተመልክቶ ሰው አለመኖሩን ሲረዳ ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰች የጎዳና አዳሪ ልጅ ላይ አስገድዶ ወንድነቱን ላከባት። በሀይል የፈለገውን ሁሉ ማድረግ የሚችል የሚመስለው ይህ ሰው ይህች ቀን የጨለመባትን ወጣት ይበልጥ ተስፋዋን አጨለመባት።

ፖሊስ

በማስፈራራት አፏን አፍኖ የፈለገውን ቢያደርግም፤ ቀድመው ጩኸቷን ሰምተው የነቁት ልጆቼ የምትላቸው ጓደኞቿ ከሸራ ቤቱ ሾልከው ወጥተው ፖሊስ በመጥራት ወደ ቦታው ይዘው መጡ። ያኔ ፖሊስ መምጣቱን የተመለከተው ተጠርጣሪ እግሬ አውጪኝ ብሎ ሊያመልጥ ቢሞክርም ፖሊስ ተከታትሎ በቁጥጥር ስር አውሎታል።

ፖሊስም ተጠርጣሪው ዝናው ተገኝ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ልዩ ቦታው ቀጨኔ መድሃኒዓለም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሕዳር 4 ቀን 2015 ዓ/ም በግምት ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ሲሆን ሆን ብሎ በመዘጋጀት ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰችን ሴት ደፍሯል በማለት ክስ መስርቶባታል።

በ1996 ዓ/ም የወጣዉን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 620/2/ሀ ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰች ልጅ ላይ በፈጸመዉ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተከሰሰዉ ሰው የአይን እማኞች፤ የሕክምና ማስረጃና የተጠርጣሪው የእምነት ከህደት ቃል የተጠናቀረበት መዝገብ አዘጋጅቶ ለአቃቤ ህግ አቀረበ።

የአቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር

አቃቤ ሕግም የክስ መዝገቡ እንደደረሰው ጉዳዩን መመልከት ጀመረ። ተከሳሽ ዝናው ተገኝ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ልዩ ቦታው ቀጨኔ መድሃኒዓለም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ህዳር 4 ቀን 2015 ዓ/ም በግምት ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ሲሆን በ1996 ዓ/ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 620/2/ሀ ስር የተደነገገዉን በመተላለፍ ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰች ልጅ ላይ በፈጸመዉ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ከሶ ፍርድ ቤት አቀረበው።

የአቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝሩ እንደሚያስረዳዉ የግል ተበዳይ ዕድሜዋ ከ16 እስከ 17 ዓመት እና የጎዳና ተዳዳሪ ስትሆን ከነበረችበት የሸራ ማረፊያ ቤት ውስጥ በማውጣት ተከሳሽ እጇን በመጠምዘዝ እና በመታገል ተበዳይ ስትጮህ መሬት ላይ ጣላት።

መሬቱ ላይ በሀይል ገፍቶ በመጣልና በኃይል በማስፈራራት ጩኸቷን ካስቆመ በኋላ አፏን አፍኖ የግብረ ስጋ ግንኙነት ፈፀመባት። ይህ በመሆኑ ዐቃቤ ህግ በ1996 ዓ/ም የወጣዉን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 620/2/ሀ ስር የተደነገገዉን በመተላለፍ ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰች ልጅ ላይ በፈጸመዉ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ክስ መስርቶበታል፡፡

ተከሳሹም ፍርድ ቤት በቀረበ ጊዜ ዐቃቤ ሕግ የተከሳሸ ጥፋተኝነት ያስረዳሉ ያላቸዉን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ የተከራከረ ሲሆን ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ቢሠጥም ተከሳሽ ጥፋቱን ባለማስተባበሉ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን ጥፋተኛ ብሎታል፡፡

በመጨረሻም የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት የቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ ሁኔታዎችን በማየት ተከሳሹ በሰባት ዓመት ፅኑ እስራት እና ከሕዝባዊ መብቱ ለአምስት ዓመት ታግዶ ይቆይ በማለት ወስኖበታል፡፡

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You