“ሀዘን አታብዙ። ሀዘን ሲበዛ ሀዘንን ነው የሚወልደው” የሚል ዘመን የተሻገረ አባባል አለ። አባባሉ “እውነት” ስለመሆኑ ዘመን ጠገብነቱ ብቻ በራሱ ማረጋገጫ ነው።
ከሰው ልጅ ቁጥጥር ውጭ ከሆኑት ባህርያት አንዱ ሀዘን (ማዘን) ነው። ማንም ሰው ወዶ አያዝንም፤ ማንም ሰው፣ አላዝንም ቢልም እንኳን፣ ከማዘን አያመልጥም። መደሰትም እንደዛው ሲሆን፣ በግድ መደሰት እንደ ሌለ ሁሉ፣ በውድ አለመደሰትም አይቻልም። በመሆኑም፣ ሁለቱም ውስጣዊ በመሆናቸው ፈንቃይ ናቸው።
ምንም ሆነ ምን፣ የሰው ልጅ አንድ ማድረግ የሚችለው ነገር ያለ ሲሆን፣ እሱም ምንም ይሁን ምን “መቆጣጠር መቻል” ነው። አዎ፣ ደስታንም ቢሆን ካልተቆጣጠሩትና በአግባቡ ካልያዙት ጦሰኛ ነው። ሀዘንም እንደዛው ሲሆን፣ ቻል ካላደረጉት የሚያስከትለው ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ከመሪር ሀዘን (ትካዜ፣ ቁዘማ፣ ሙሾ ∙ ∙ ∙ን ይጨምራል) ምንም አይገኝም። ከፈጣሪ በስተቀር፣ እኛ ጸጉር በመንጨትም ሆነ ደረትን በመድቃት ማንንም ከሞት ወደ ሕይወት መመለስ አይቻለንም። በመሆኑም፣ ዝቅ ብለን እንደምንመለከታቸው አስተዋይ ሰዎች ራሳችንን መግዛት ግድ ይለናል።
2016 ዓ∙ም ከገባ ወዲህ አንድ ለየት ያለና ሰው ተኮር የሆነ አቢይ ጉዳይ ተከናውኗል። ዝቅ ብለን ታሪካቸውን የምንመለከትላቸው ሰው እንዳሉት “የምናለቅሰው ለሀገራችን ሞት እንጂ፣ ለልጃችን አይደለም” እስከ ማስባል ድረስ የዘለቀ ክስተት ነው።
ሰኞ፣ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ∙ም “የትግራይ ክልላዊ ሐዘን ሦስተኛ ቀን” በሚል ርዕስ ለንባብ የቀረበ ዘገባ “ትግራይ የቀድሞ ተዋጊዎች የህልፈት መርዶ ለቤተሰቦች መነገሩን ተከትሎ ከፍተኛ ሐዘን ላይ ናት። በከተሞች እንቅስቃሴዎች ተገድበዋል፣ በክልሉ ብሔራዊ ሐዘን ከታወጀ ሶስተኛ ቀኑ ላይ ይገኛል። ለወትሮው በሰዎችና ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ፣ በግብይት እንዲሁም ሌሎች ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ትደምቅ የነበረችው መቐለ ዛሬ እንደ ሁልጊዜው አይደለችም።” ይላል።
ሌላው የወቅቱ ዜና ደግሞ የሶስት ቀን (ከጥቅምት 3 – 5 ቀን፣ 2016 ዓ∙ም) “ብሔራዊ ሀዘን በታወጀባት ትግራይ፥ በተለያዩ የጦር ግንባሮች ያለፉ የቀድሞ ተዋጊዎች መርዶ ለቤተሰቦቻቸው ተነግሮ ከፍተኛ የሐዘንና ፀጥታ ድባብ ሰፍኖባት ይገኛል።” ይላል።
ለጀርመኑ ዶቸቨሌ ዘጋቢ አስተያየቱን የሰጠው፣ የመቐሌው ነዋሪ ወጣት አማኑኤል ኃይለ “ትግራይ ሐዘን ላይ ናት። በትግራይ የሶስት ቀናት ክልላዊ ሀዘን ታወጀ። ትልቁ ትንሹ፣ ወንዱ ሴቱ ሁሉም ነጠላ ለብሶ፣ እያለቀሰ ነው የምታየው። እኔ በርካታ አብሮ አደጎቼ፣ የሰፈሬ ልጆች፣ አብረውኝ የተማሩ አጥቻለሁ። የትኛውን ሀዘን ደርሰህ የትኛውን መተው እንዳለብህ እስኪጠፋብህ ድረስ በአንድ ጊዜ መርዶው መጥቷል። እንደዚህ ዓይነት ፈታኝ ጊዜ የለም። ለቅሶ በመድረስ ደከምን። አሁን እኔ ዕዳጋዓርቢ ሄጄ የዘመድ ለቅሶ መድረስ ነበረብኝ። ግን እዚህ ያሉትስ ብዬ ተውኩት። ለትግራይ ሕዝብ መፅናናትን ነው የምመኘው።”
ሌላው አስተያየት ሰጪ ዳንኤል መብራህቱ “በርካታ ጓደኞቻችን፣ የዕድሜ እኩዮቻችን፣ በርካቶችን አጥተናል። አሳዛኝ ድባብ ነው ያለው። እናቶች ልጆቻቸውን አጥተው ሲያለቅሱ እንደ ማየት የሚያም ነገር የለም። ብዙ ብርቅዬ ወንድሞቻችን አጥተናል። ትግራይ በየጊዜው በርካቶችን እየገበረች መኖር የለባትም። ያለፈው ይበቃል። ከእኛ ጀምሮ፥ ይህ እንዳይደገም ጥረት ይፈልጋል” ማለቱም ተዘግቧል። “ትግራይ ሐዘን ላይ ናት።” የሚለውም የዚሁ ንግግር አካል ነው።
ለሁለት ዓመት በመንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች መካከል የተደረገው ጦርነት፤ በተለይም በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሱ ሲገለፅ ቆይቷል። በትግራይ ኃይሎች በኩል በውጊያ ግንባሮች ያለፉት ቁጥር ስንት መሆኑ እስካሁን በግልፅ ባይቀመጥም (የተለያዩ አስተያየቶች እንዳሉ ሆነው)፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በሀዘኑ ሳምንት ሰጥተውት በነበረ መግለጫ “ከፍተኛ ኪሳራ” መድረሱ ተነግሯል። ሁለት ዓመት ወደኋላ እንሂድ።
“የሕወሓት ቡድን በአፋር ክልል፣ በፈንቲ ረሱ በጋሊኮማ ጊዚያዊ መጠለያ በነበሩ ንፁሃን ዜጎች ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ አስመልክቶ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት (ከነሐሴ 05 /2013 እስከ ነሐሴ 07/2013 ዓ∙ም) የሀዘን ቀን እንዲሆን የአፋር ክልል መንግስት አውጇል።” መባሉ የሚረሳ አይደለም።
እንዲህ እንዲህ እያልን ብንቀጥል ነገሩ ሁሉ ቀልድ እስኪመስለን ድረስ ሊገርመን ይችላል። “የሀገሪቱ ሕዝቦች አብደዋል እንዴ፣ የጦርነት ሱስ አለባቸው እንዴ? ምነው መተላለቅ ሥራቸው ሆነ?” ሊያስብለን ሁሉ ይችላል። ወደድንም ጠላንም ግን፣ በሀገራችን እየሆነ ያለው፤ እየተደረገ ያለው፤ መቆሚያ ያልተበጀለት ይሄ ነው።
ሀዘንን በተመለከተ በሀገራችን የነበረውን ታሪካዊ ዳራ እንመልከት፤ ከመሪዎችም እንጀምር።
አፄ ኃይለሥላሴ በልጃቸው ልዕልት ዘነበወርቅ ሞት እጅጉን አዝነው እንደነበረ፤ ለቅሷቸውም ከ“ስቅስቅቅቅቅቅ ∙ ∙ ∙”ም አልፎ ከቁጥጥራቸው ሁሉ ውጭ ሆኖ ያየ የተመለከታቸውን ሁሉ ሲያስለቅስ እንደነበረ በበርካታ ድርሳናት ውስጥ ተሰንዶ ይገኛል። ምክንያታቸውንም “አሁን፣ ዛሬ በልጄ በዘነበወርቅ ሞት ሀዘን የፀናብኝ ስለ ሶስት ነገር ነው፤ 1ኛው በሕፃንነቷ፣ 2ኛው ባዲስ ሙሽርነቷ፣ 3ኛው ነፍሰ ጡር ሆና ሳትገላገለው በመሞቷ ነው።” በማለት መናገራቸው እንዲሁ የታሪክ እውቅና ተቸሮት በድርሳናት አማካኝነት ለምስክርነት በቅቷል።
“እነዚህ እጅግ የከበዱ ሶስት ነገሮች ባንድ ጊዜ ስለደረሱብኝ ሀዘኔን እያፀናሁ ብቆይ እወድ ነበር፤ ነገር ግን በአንድ ወገን ፅኑ ሀዘን አድርጎ መቆየት ተስፋ የሌላቸውን አሕዛብን መምሰል ነው ተብሎ በመጽሐፍ መከልከሉን ስላወቅሁ፤ በሁለተኛውም ወገን ለእናንተ፣ ለሁላችሁም የጉዳት አብነት (ምሳሌ) ማሳየት የማይገባኝ መሆኑን ስላወቅሁ ሀዘኔን ትቼዋለሁ።” ማለታቸውም እንደዚሁ ስለ ሀገርና ሕዝብ በተጻፉ ድርሳናት (ለምሳሌ፣ የብላታ መርስኤ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ፣ “ዝክረ ነገር” (1942 ዓ∙ም)) ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ስለ ንጉሡና ንጉሠ ነገሥታቸው በተነገሩ ታሪኮች ላይ ሁሉ ተገቢውን ስፍራ ይዞ እንመለከታለን።
በንጉሡ ጊዜ በተለያዩ ሀገራዊ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲሰሩ ወደ ነበሩትና እውቅ ደራሲና ዲፕሎማት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ (1870 − 1931) እንሂድ።
እራሳቸው ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ “የልቅሶ፣ ዜማ ግጥም፤ ምስጢሩ ከመጻሕፍት ጋት የተስማማ”(1910 ዓ∙ም) በሚል ርዕስ ባሳተሙትና በወዳጅ ዘመዶቻቸው አማካኝነት በ2001 ዓ∙ም በድጋሚ በታተመው መጽሐፋቸው ላይ “የዚህችኛዋ እትም አጭር መግቢያ” ስር ስለ እሳቸው በሰፈረው ጽሑፍ ላይ “ታላቁ ሰው ህሩይ ሞትን፣ ሀዘንን፣ ልቅሶን በተመለከተ፣ ከነበሩበት ዘመንም ሆነ፣ አሁን ከአለው የሀገራችን ማህበረሰብ ከአብዛኛው በተለየ መልኩ የሚመለከቱበት የራሳቸው የሆነ ፍልስፍና አላቸው። አንዱ፦ ‘ለሞተው ወዳጅህ ከምታልቀስ ይልቅ በሕይወት ሳለ የክፋት ሥራ ለሚሰራ ወዳጅህ አልቅስለትʾ የሚል ነው።” (ገጽ 4 – 5) የሚል ሰፍሮ እናነባለን።
“በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ከአባቱ ስር ሆኖ፣ ያላንዳች የደመወዝ ክፍያ እናት ሀገሩን በነፃ ያገለገለው፣ ከማይጨው ጦርነትም በኋላ፣ የጥቁር አንበሳን ጀግኖች አርበኞች የተጋድሎ ማህበር ከመሰረቱት አባሎች አንዱ የሆነው ልጃቸው፣ የኬምብሪጅ ምሩቅ ልጅ ፈቃደ ሥላሴ ህሩይ ከቤቱ በጠቋሚ ተወስዶ በየካቲቱ ጭፍጨፋ መገደሉን፣ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በተገኙበት፣ በእንግሊዝ ቤተመንግሥት በተረዱ ጊዜ ምን ነበር የተሰማቸው?” የሚል ጥያቄ ከሰፈረ በኋላ፦
“እንኳን ለተወለደው-ለተዛመደው፣ እንኳን ለቀረበ-ላወቀው ይቅርና ፎቶግራፉን [ፎቷቸው አለ] ብቻ እንኳን፣ እንዲሁ ላየው፣ የሚያሳሳ፣ አንጀት የሚበላ፣ ይህ መለሎ ወጣት፣ ሕይወቱ በአጭር መቋጨቷ የሚያስከትለው መሪር ሀዘን፣ እንዳለ ይቆይና በፋሽስቶች እብሪትና ጥጋብ በከባድ ጭካኔ፤ ሊያውም በግፍ የመገደሉ ነገር ታውሷቸው ሀዘናቸውን አላከበዱትም፤ እንባቸው ፈንቅሎ እንዲወጣ እንኳን እሺ-በጅ አላሉትም፤ የእንጉርጉሮ ስንኝም አልቋጠሩለትም። ሀዘናቸውን የገቱት በአንዲት ዘለላ እንባና በአንዲት ዓረፍተ ነገር ብቻ ነበር፤ ‘የምናለቅሰው ለሀገራችን ሞት እንጂ፣ ለልጃችን አይደለምʾ ” ተብሎ ተጽፎላቸው እናገኛለን።
ይህ ብቻም አይደለም፤ ሀዘን ስለደጋገማቸው ህሩይ የሚከተለውም ሰፍሮ ይገኛል።
“ወ/ሮ አምሳለ ህሩይ የተባለች የመጨረሻ ልጃቸውን በ11 ዓመትዋ ለትምህርት ወደ አውሮፓ ልከዋት ትምህርትዋን አጠናቅቃ ከተመለሰች በኋላ ትዳር ይዛ በወሊድ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ስትለይ ገና የት ትደርሳለች ብለው ያሰቧት ልጃቸው እንዲህ ባጭሩ በመቀጨትዋ ለሀዘኑ፣ ለልቅሶው አልተንበረከኩለትም፤ ሀዘኑንም ልቅሶውንም ባጭሩ ገትተውታል።
“ከቀብር መልስም ባደረጉት ንግግር፣ እንደ ኢዮብ ‘እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔር ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን።ʾ ካሉ በኋላ ስለ አቃበራችሁኝ አመሰግናችኋለሁ፤ ቀባሪ-አቃባሪ አያሳጣችሁ። ሀዘኑም፣ ልቅሶውም እዚሁ አብቅቷል፤ ስለ ሀዘኑ ቤት አንቀመጥም፤ የሰልስት ልቅሶም የለንም፤ ስለዚህ አላደክማችሁም፣ ወዳጆቼ ከዚሁ እንድትሰናበቱልኝ እለምናችኋለሁ።” በማለት መናገራቸው ተሰንዷል።
በመጨረሻም፣ ነገሩ ሁሉ፦
የገደለው ባልሽ፤
የሞተው ወንድምሽ
ሀዘንሽ ቅጥ አጣ፣
ከቤትም አልወጣ።
እንደተባለው ነው – የእኛ ነገር። ሟችም ገዳይም የአንድ ቤት ሰዎች ሆነውብን ተቸግረናል። በሶስቱ የአፋር ሀዘን ቀናት የተቸገርነው ይህንኑ ሆኖ ሳለ፣ አሁንም፣ በሶስት የትግራይ የሀዘን ቀናት የተቸገርነው በተመሳሳይ የላይኛውን፣ የአልቃሿን ግጥም የሚያስታውስ ነው። በመሆኑም ዘላለማዊ በሆነ መልኩ “መቸም መቸም አይደገምም” ካላልን እና በቃላችን ካልፀናን በስተቀር፣ እየገደልንና ተገዳደልን፤ ለሟች ቤተሰብም “∙ ∙ ∙ የሞተበት ሰርተፊኬት” እየሰጠን መቀጠላችን ነው።
እዚህ ላይ ምህላን በተመለከተ አንድ ነገር ብሎ ማለፍ የሚገባ ሲሆን፣ እሱም “መቸም መቸም አይደገምም” የሚለው ነው።
የአብዮቱን መፈንዳት ተከትሎ፣ በቀይ እና ነጭ ቀለሞች አሳብበን መተላለቃችንን መቸም ላለመድገም በመማል የሰማእታት ሀውልት ማቆማችን፣ አቁመንም እላዩ ላይ “መቸም መቸም አይደገምም” ብለን መጻፋችን የሚታወስ ብቻ አይደለም የሚታወቅ ነው። ይሁን እንጂ “መቸም መቸም አይደገምም” ባልንበት አንደበታችን መፅናት አቅቶን ስሙን እየቀያየርን መተላለቃችንን አላቆምንም። ጭራሽ ወደ ለየለት ጦርነት ውስጥ በመግባት በሚሊዮኖች እንዲያልቁ እያደረግን እንገኛለን። ዛሬም ድረስ። ታዲያ፣ ይህ የጤና ነውን???
ምንም ሆነ ምን፣ ያለን እድል አንድ ነው። ሀዘንተኞች ከላይ እንደተመለከትናቸው ሁለት አንጋፋ ሰዎች ሁሉ፣ ራሳችንን ተቆጣጥረን ሀዘናችንን ቻል ማድረግና ወደ መደበኛ ሕይወታችን መመለስ ነው። ሌላውም፣ በትግራይ ክልል ሀዘኑን አስመልክቶ በተሰጠው የሀዘን መግለጫ “ለሁሉም የትግራይ ሕዝብ መጽናናቱን ይስጥህ፣ መጽናናቱን ይስጠን። የልጆቻችን እና ወንድሞቻችን መስዋዕትነት የሁላችንም መስዋዕትነት ነው። ይህ ዓይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ እንዳይደገም የፖለቲካ አመራሩም፣ ሁሉም ራሱን መፈተሽ አለበት።”
መቸም በየትኛውም የከፋ ሀዘን ውስጥ ድምፃቸው ጎልቶ የሚሰማው፣ ሀዘናቸው ጠልቆ የሚጎዳቸው ∙ ∙ ∙ እናቶች ናቸውና በ“የራሔል እንባ” መፅናናትን እንመኝላቸው፤
«እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የኀዘን የልቅሶና የጩኸት ድምጽ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ድምጽሽን ከለቅሶ ዓይኖችሽንም ከእንባ ከልክይ፤ ለሥራሽ፤ ዋጋ ይሆናልና፥ ይላል። እግዚአብሔር፤ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ። ለፍጻሜሽም ተስፋ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ልጆችሽም ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ።» ኤር 36፥15።
ቅዳሜ ጥቅምት 3/ 2016 ጀምሮ በትግራይ ክልል የታወጀውን የሀዘን ቀን እና የመርዶ ሥነ ሥርዓት ተከትሎ፤ አዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት እና ፖለቲከኞች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሕይወታቸውን ላጡ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጸሎት እና የጧፍ ማብራት ሥነ ሥርዓት አከናውነው እንደነበር ይታወሳል። በሥነ ሥርዓቱ ላይም የሰባት ሀገራዊ እና ክልላዊ ፓርቲዎች አመራሮች እና አባላት ተገኝተው ሀዘናቸውን ገልጸዋል። ይህ መሆን ያለበትና ሁሉም ሊያደርገው የሚገባ ጉዳይ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ ሀዘኑ የሁላችንም ስለመሆኑ ጥሩ ማሳያ ነው።
በእለቱ ከተገኙት አንዱ የሆኑት፣ የመኢአድ ሊቀመንበር አቶ ማሙሸት አማረ “የዛሬው ቀን ምን ተብሎ እንደሚሰየም ባላውቅም፤ ትግራይ፣ አፋር፣ አማራ ላይ ላለቁት ወገኖቻችን፣ አጠቃላይ እንደ ሀገር በወደቁት ወንድሞቻችን የመከላከያ ሠራዊት ጭምር እንዳናስበው፣ የጋራ እንዳናደርገው ሌላ ደግሞ ችግር አለብን። ሌላ ችግር ውስጥ ነው ያለነው። ከአንዱ ችግር ወደ [ሌላ] ችግር ነው እንጂ፤ ከአንዱ ችግር ወደ ተሻለ ነገር መሸጋገር አልቻልንም [∙ ∙ ∙] ይሄ ሁሉ ሕይወት፣ ይሄ ሁሉ ዋጋ የተከፈለበት ዓላማው ምንድነው? ግቡ ምንድነው? በውጤቱስ ምን ተገኘ? ብለን ብናስብ፤ ምንም የለም። ዜሮ እንኳ አይሆንም” ያሉትም ሊዘለል የሚገባው አይደለም።
በእለቱ (እሑድ ጥቅምት 4/ 2016 ዓ∙ም) የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት፤ በትግራይ ክልል የደረሰው ሀዘን የጋራ መሆኑን ጠቅሰዋል። በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሕይወታቸውን ያጡ የአማራ እና የአፋር ዜጎችንም ጭምር ለማሰብ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሀዘን ቀናት ሊታወጅ ይገባ እንደነበርም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት የነበረው “የእርስ በእርስ መገዳደል” በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎች ቦታዎች መቀጠሉ የሚያሳዝን እና መፍትሔ ሊበጅለት የሚገባ እንደሆነም አሳስበዋል። ይህም ሌላው የሀዘኑ የጋራ መሆን አመላካች ነውና ተሳታፊዎቹ ሊመሰገኑ ይገባል።
በወቅቱ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለንባብ እንዳበቃው፣ በመርሀ ግብሩም “ሁላችንም ያለፈውን መመለስ አንችልም፤ ግን ከዚህ በኋላ የተሻለ ሥርዓትን በመገንባት ሕዝቡን መካስ መቻል አለብን።” የሚለው ሃሳብ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ሲንሸራሸር መቆየቱ፤ “ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለገባችበት ውድቀት ተጠያቂው ሕዝቡ ሳይሆን ፖለቲከኞች መሆናቸው፤” “የፖለቲካ ኤሊቱ” ነው የሚለው የውይይቱ ማዕከላዊ ነጥብ ሆኖ የነበረ መሆኑ ስለ ወደፊቷ ኢትዮጵያ ሲባል ተስፋን የሚያጭር ነው።
በመጨረሻም፣ ሀዘኑ የሁላችንም ነውና ነፍስ ይማር እንላለን። ለወዳጅ ዘመዶች፣ በአጠቃላይም ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ መጽናናትን እንመኛለን። ይህንን ስንል ግን አሁን እየሆነ ያለው፤ ፍፁም ኢትዮጵያዊ ባህልና ወግ ያልሆነው መገዳደልም እንዲቆም፤ ፊታችንን ከጦርነት ይልቅ ወደ ሰላም እንድናዞር በመማፀን ጭምር ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም