የኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ ዶ/ር ከትናንት በስቲያ በሀገር አቀፍ ደረጃ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዙሪያ ያለውን ሀገራዊ እውነታ ፤ ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገዋል ፤ የቃለ መጠይቁን ሙሉ ቃል እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ጥያቄ፡- እንደ ሀገር ለቴክኖሎጂ የተሰጠው ትኩረት ምን ይመስላል?
ዶ/ር በለጠ፦ እንደ ሀገር ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች የኢኖቬሽን፣ የቴክኖሎጂና የአይሲቲ ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ አንዱ ነው። ይህም በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ ውስጥ እንዲሁም በሀገር በቀል ኢኮኖሚው፣ በደንብ ተሰምሮበት የተቀመጠ ነው። በቀጣይ ለሚገነባው ሀገራዊ ኢኮኖሚ እንደምሰሶ ሆነው ይቆማል ተብለው ከተለዩ አምስት /የማዕድን፣ የግብርና፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ ቱሪዝምና አይሲቲ /ዘርፍ አንዱ ነው። ይህም መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው በተጨባጭ የሚያሳይ ነው።
በቅርብ ጊዜ ሁላችንም እንደምናውቀው መንግሥት ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ዘርፉን ሊብራላይዝድ አድርጓል። ለዚህም የቴሌ ካም ኢንደስትሪው ማንሳት ይቻላል፣ ዘርፉ በሀገራችን ከመቶ ዓመት በላይ አንድ ለእናቱ ነበር። አሁን ሊብራላይዝድ ተደርጓል፤ ይህ በመንግሥት በኩል የተወሰደው ርምጃ በጣም ትልቅ ነው።
ከዚህም ሳፍሪኮም ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ገበያ ውስጥ እንዲሳተፍ ተደርጓል። አሁን በኢትዮጵያ በቴሌኮሙ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሥራ እየሰራ ነው። ይሄ ዘርፉን ሊብራይዝድ በመንግሥት በኩል የተወሰደው ርምጃ በርግጥም መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን የሚያሳይ አንድ ቀዳሚ ምሳሌ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።
ሌላው የአይሲቲ መሠረተ ልማቶች ግንባታ ላይ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። መሠረተ ልማቶቹ አቅም በፈቀደ መልኩ እንዲስፋፉ እንዲገነቡ፤ የኮኔክቲቪቲ ተደራሽነት እንዲስፋፋ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። በዚህም በአጠቃላይ በሀገራችን 35 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሕዝብ የብሮድባንድ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ሆነዋል።
ይሄ ቀላል ቁጥር አይደለም። 35 ሚሊዮን ሕዝብ ማለት እኛ ዝቅ ብለን ስለጀመርን ብዙ ላይመስል ይችላል። ግን በጣም ትልቅ ነው ። 35 ሚሊዮን የሦስት የአራት የአፍሪካ ሕዝብ በአንድ ላይ ተደምረውን እንደ ማለት ነው። ይሄ በጣም ከፍተኛ እመርታ ነው። ከዚህም ባለፈ መረጃዎች እንደሚያሳዩት 73 ነጥብ1 ሚሊዮን ሕዝብ የሞባይል ተጠቃሚ ነው።
ሌላው የክፍያ ሥርዓቱን ካየን ፤ ጎልህ በሚባል መልኩ ብዙ ለውጦች እየታዩበት ነው። ባንኮቻችንን “ከአናሎግ” አሠራር እየወጡ አሁን ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጅታል አሠራር እየገቡ ነው። የክፍያ ሥርዓቶች ዲጂታላይዝድ ሆኗል። በዚህም በትሪሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ውስጥ እየተዘዋወረ ነው።
ይሄ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ የመጣ ውጤት ነው። በርግጥም ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ መሆኑን በተጨባጭ መመልከት የተቻለበት ውጤት ነው።
ጥያቄ፡- በዘርፉ እየተካሄደ ያለው የመሠረተ ልማት ግንባታ ከዘርፉ የአስር ዓመት ዕቅድ አንጻር ምን ያህል በዕቅድ ተጉዘናል የሚያስብል ነው ?
ዶ/ር በለጠ፦ በዘርፉ እየተካሄደ ያለው የመሠረተ ልማት ግንባታ በጥሩ ደረጃ ላይ ነው ማለት ይቻላል። ይሄ ማለት ተግዳሮት የለም ማለት አይደለም። የቴክኖሎጂና የአይሲቲ ጉዳይ እንደሚታወቀው ኮፒታል መሠረት ያደረገ ነው። በመንግሥትም በግሉም ዘርፍ በሚደረግ ጥረት ብቻ ሳይሆን ኢንቨስትመንት ከውጭ መሳብን የሚጠይቅ ነው።
በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ ውስጥ እናሳካቸዋለን ብለን ካስቀመጥናቸው ግቦች አኳያ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ጥሩ ውጤት እያመጡ ነው። በቀጣይ የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች እየፈተሽንና እየገመገምን ፤ በማስተካከያ ርምጃዎች እየወሰድን እና ክፍተቶቻችንን እየሞላን ከሄድን በዘርፉ ያስቀመጥነው የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ በሙሉ የሚሳካበት ዕድል አለ። ተግዳሮቶችም አሉ። እነሱን በቀጣይ መቋቋም እየቻሉ መሄድ ያስፈልጋል።
ጥያቄ፡- እርስዎ ከሚመሩት ዘርፎች አንዱ ኢትዮጵያ ትልቅ ኢንቨስትመንት ያወጣችበት የአይ.ሲ.ቲ ፓርክ ተጠቃሽ ነው። ፓርኩ እስከ አሁን ድረስ በሙሉ አቅሙ እየሠራ አይደለም ። ፓርኩ በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ ሚኒስቴሩ ምን እየሠራ ነው?
ዶ/ር በለጠ፦ የአይ.ሲ.ቲ ፓርክ ግዙፍ መሠረተ ልማት ነው። ከጎሮ አልፈን ወደ ደብረዘይት መንገድ ላይ የሚገኝ ፤ ወደ 200 ሄክታር ላይ ያረፈ ነው። ከተመሠረተ 15 ዓመት ሆኖታል። በእነዚህ ዓመታት የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት እንዲያስተዳድሩት ተደርጓል። መጀመሪያ ሲመሠረት በኤምሲ አይቲ ስር ነበር። ለውጡን ተከትሎ ደግሞ የአይ.ፒ.ዲ.ሲ የኢንደስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን ወደምንለው ተላልፎ አምስት ዓመት በዚህ ሲመራ ቆይቷል።
እኛ ባለፈው ዓመት ከፍተኛ የሆነው የመንግሥት አካል ጠይቀን ፖሊሲና ስትራቴጂ እናወጣለን፤ እነዚህን ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ለመፈፀም አስቻይ ከሆኑ መሠረተ ልማቶች አንዱ እንደዚህ ዓይነት የቴክኖሎጂና የአይሲቲ ፓርኮች መኖር ነው። በሚል ጥያቄ አቅርበን ወደ እኛ መጥቷል። ወደኛ ለማምጣት የነበረው ተግዳሮት ግን ቀላል አልነበረም።
ፓርኩ አንደኛ ሙሉ ለሙሉ እንዲለማ የተደረገ አይደለም፤ ከአንዱ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም እንዲሸጋገር በተደረገው ውሳኔ መሠረት ከሞላ ጎደል ያለሥራ ቆይቷል። ስለዚህ ወደ እኛም ተቋም ሲመጣ ገና ግልፅ ያልተደረጉ፤ አሁንም ድረስ ብዙ ጥረት እየጠየቁን ያሉ የሰነዶች፤ የውሎች ፤ የአስተዳደር ጉዳዮች አሉ።
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራን ነው። ስለዚህ አሁን ላይ የቢዝነስ እቅዱን በመከለስ እዚያ የነበሩ፤ ግን የወጡ የግል ኩባንያዎች እንዲመለሱ፤ እዛ ያሉትም ተበራርተው ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ እና አጠቃላይ የማደስ ሥራ እየተሰራ ነው።
በአሁኑ ወቅት የግሉ ዘርፍ እንደ አዲስ የሚሰብ የአሰራር ሥርዓት እንዲሁም ሥራዎች እየተሰሩ የግል ኩባንያዎች እየገቡ ነው። የብሬክ ሊዝ ያመለከቱ ኩባንያዎች እየገቡ ነው። እንደሚታወቀው ደግሞ ፓርኩ ሕንፃዎች አሉት፤ ሕንፃዎቹን ተከራይቶ ለመሥራት ጥያቄ አቅርበው የተቀበልናቸው አሉ፤ በቀጣይ በግምገማ የምንቀበላቸው አሉ።
ሌላው የኃይል አቅርቦት ጉዳይ ቁልፍ ችግር ነበር። እዚያ ውስጥ ትልልቅ የመረጃ /ዳታ ማዕከሎች፤ አገልግሎት የሚሰጡ የውጭ ኩባንያዎች ሀገር ውስጥ ገብተው ብዙ ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት አካሂደው መሠረተ ልማቶችን የገነቡ አሉ። ለምሳሌ ዊንጎ አፍሪካ የምንለው እነራክሲዩ፤ ሬድ ፎክስ፤ ሳፋሪ ኮም የመሳሰሉት በትልልቅ ካፒታል እየገነቡ ነው። ሌሎችም የግል ድርጅቶች እንዲገቡ እየጋበዝን ነው። እየገቡ ነው።
ወደ ሥራ ሲገባ የኃይል ጉዳይ አንዱ እጥረት ስለሚሆን ለዚህ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው። በፊት የነበረው ወደ 2 እስከ 3 ሜጋ የማይበልጥ ነበር። አሁን ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግረን 10 ሜጋ አድርሰናል። አሁን ላሉት በቂ ነው፤ ግን ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ለምቶ እንደ‹ማይክሮሶፍት›፣ ‹አይቢኤም›፣ ‹ኦራክል› ያሉ ብዙ ታላላቅ ዓለም አቀፍ የግል ኩባንያዎች እንዲመጡ እየሠራን እንገኛለን።
ተሳክቶልን እነዚህ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከመጡና ሀገር በቀል ድርጅቶችም ወደሥራው ሲገቡ ብዙ ኃይል ይፈልጋል። አሁን ላሉት አስሩ በቂ ቢሆንም በቀጣይ ወደ 200 ለማሳደግ ከአንድ የቻይና ኩባንያ ጋር በመነጋገር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል። የራሱን ማከፋፈያ ጣቢያ ገንብቶ ይህን ያህል ኃይል ለአይሲቲ ፓርኩ ማቅረብ የሚችልበት ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል። ይህ አንዱ ተግዳሮት ስለነበር መስመር ዘርግተን 10 አድርሰናል።
የኢንተርኔት ግንኙነት (ኮኔክሽን) ችግርም ነበር። ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ባደረግነው ምክክር የኢንተርኔት ግንኙነት ፍጥነቱ ከፍተኛ ፍጥነት ወዳለው (High Speed Connection) እንዲሸጋገር ተደርጓል። የውሃ አቅርቦት እና የካፍቴሪያ ችግሮችም ነበሩ። እነዚህን ችግሮች ደረጃ በደረጃ እየፈታን ጥሩ ውጤቶችን አይተናል። ነገር ግን ግዙፍ አቅም ያለው በመሆኑ፣ አቅሙን ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም እየተከታተልንና እየሠራን እንቀጥላለን። ስፋቱ 200 ሄክታር ነው። ቀጣይ ሥራዎችን የሚጠይቁ ብዙ ተግባራት አሉብን።
ጥያቄ፡- ስለሊበራላይዜሽን ሲነሳ በአንድ በኩል ‹‹መንግሥት ለብዙ ዓመታት ዝግ አድርጎ ያስቀመጣቸውን ተቋማትን አሳልፎ ለውጭ ሊሰጥ ነው›› የሚሉ ወገኖች ነበሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ሊበራላይዜሽን ጥሩ ነው፤የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ኢንቨስትመንት መስፋፋትና ዘርፉ ማደግ አለበት›› የሚል አቋም ያላቸው ወገኖች አሉ። በዚህ ረገድ የመንግሥት እንቅስቃሴና ጥንቃቄ ምን ይመስላል? ሌሎች ተቋማት ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሳተፉስ ምን እየተሰራ ነው?
ዶ/ር በለጠ፦ በመንግሥት ጥረት ብቻ ሀገር ሊያድግ አይችልም። ያደጉ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ በአንዳንዶቹ መንግሥት የመሪነት ሚናውን ወስዶ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ፣ በሌሎቹ ደግሞ የግሉ ዘርፍ መሪ ሆኖ መንግሥት የቁጥጥር ሥራውን በመሥራት እድገት አስመዝግበዋል። የኢትዮጵያ ተሞክሮ የሚያሳየው መንግሥት ብዙውን ነገር እንደሚመራና እንደሚቆጣጠር ነው። የግሉን ዘርፍ እያሳተፍን ቢሆንም አሁንም በቂ አይደለም።
የግሉ ዘርፍ አቅሙ ጎልብቶ የመሪነት ሚናውን እንዲወስድ ታስቦ እየሰራ ነው። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት የሊብራላይዜሽን ጉዳዮች ብዥታ መፍጠራቸው አይቀርም። ነገር ግን ሊብራላይዝ ከማድረግ ውጭ ያለው አካሄድ አዋጭ አይመስለኝም። አንዳንድ ተቋማት ለመንግሥት ሸክም የሚሆኑበት አጋጣሚ ይፈጠራል፤ መንግሥትም ሙሉ በሙሉ ድርሻውን ሳያጣ፣ የግሉ ዘርፍ የተወሰነውን ድርሻ እንዲይዝና ተቋማቱ የሕዝብን ተጠቃሚነት የበለጠ የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ መንግሥት የወሰደው ርምጃ ትክክለኛ ነው።
ሰዎች ስለሂደቱ ጥያቄ ቢያነሱ፣ እንረዳቸዋለን። የቴሌኮም ኢንደስትሪውን ካየን እንደውም የተሻለ ሆኗል። ተወዳዳሪ ሲመጣ ለሕዝቡ የተሻለ አፈፃፀም እያስመዘገበ እና የተሻለ አገልግሎትን እና አማራጮችን እየፈጠረ ነው። በአፍሪካ ቀዳሚ፤ በጣም ንቁ (ቫይብራንት) ሆኖ የቆመ የቴሌኮም ካምፓኒ እንዳለን በዚህ ሰዓት እያየን ነው። በጣም ተዓምር የሚባሉ ሥራዎችን እየሠራ ነው።
ይህ ውድድሩ የፈጠረበት መነቃቃት ነው ተብሎ ሊቀርብ ይችላል። የሚገባኝ በዛ መልኩ ነው። አገልግሎቶችን ከማስፋት አንፃር እና ተደራሽነትን ከማስፋት አንፃር፣ አዳዲስ አገልግሎቶችን ከማምጣት አንፃር፣ ለሕዝብ ከማቅረብ አንፃር፣ አማራጮችን ከማስፋት አንፃር በጣም ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው።
ሊብራላይዜሽን በአጠቃላይ ጥሩ ነገር ነው። ውድድርን ያመጣል። የተሻለ ምርት ለሕዝብ እንዲደርስ ያደርጋል፤ አማራጭ ያሰፋል፤ የተሻለ የኑሮ ደረጃ እንዲፈጠር አስቻይ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። እንዲህ ዓይነት የተለያዩ ነገሮች ሲመጡ፤ ዕድገትን ያፋጥናል፤ ጥራት ያለው ወይም የተሻለ የኑሮ ደረጃን እየጨመረ ይሄዳል። የሚገባኝ እንደዛ ነው።
ጥያቄ፡- በፈጠራ ላይ የሚደረጉ ምርምሮችን ማጠናከር ፤ በተለይ ተቋማት ያላቸውን አሠራር ዲጂታላይዝድ እንዲያደርጉ የተጀመረ ጥረት ነበር። ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል ?
ዶ/ር በለጠ፦ ምርምርን ከመደገፍ አንፃር ኃላፊነቱን ወስደናል። እንደ ኢኖቬሽን እና እንደምርምር እንደ ቴክኖሎጂ እንደ ዲጂታል ተቋም አጠቃላይ የኢትዮጵያን ሀገራዊ የምርምር ሥነ ምህዳር እንዲመራ ባለቤትነትን እንዲያረጋግጥ ኃላፊነት እና ሥልጣን ተሰጥቶታል።
ምርምሮች መደገፍ አለባቸው፤ የሚደገፉ ምርምሮችም ውጤታማ ሆነው በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ራሱን የቻለ አስተዋፅኦ መጫወት መቻል አለባቸው። እስከ ዛሬ ይህ ተቋም ምርምሮችን ይደግፍ ነበር። ነገር ግን አጠቃላይ የምርምር ሥርዓቱ መፈተሸ አለበት። የተበታነ ነገር አለ። እዚህ እና እዚያ የምርምር ጥረቶች አሉ።
ምርምርን በመደገፍ ጅምር ነገር አለ። እኛ አሁን ላይ እንደተቋም የግምገማ ሥራ እየሠራን ነው። ከአሁን በፊት ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በዚህ ተቋም የተደገፉ የምርምር ሥራዎች ምን ላይ ደርሰዋል? ስንቶቹ ውጤታማ ሆኑ? ምን ዓይነት ውጤት አሳዩ? ስንቶቹስ ቀሩ ለምንስ ቀሩ? የሚሉትን ሥራ እየሠራን እና እየለየን ነው። በደንብ ከለየን በኋላ ወደ ድጋፍ ሥርዓቱ እንመጣለን። ይሄም ሆኖ ግን ከአጋሮች በሚደረግ ድጋፍ አሁንም እየደገፍን ነው።
ለምሳሌ በዚህ ግማሽ ዓመት ውስጥ ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (ከዩኤንዲፒ) በተገኘ ድጋፍ አስር ምርምሮችን ደግፈናል። ይህ ብቻ አይደለም፤ ናይሮቢ ኬንያ ውስጥ ከሚገኝ ፤ አፍሪካ ውስጥ የሚደረጉ ምርምሮችን በገንዘብ ከሚደግፍ የቴክኖሎጂ ጥናት ማዕከል ጋር ባደረግነው ስምምነት ፤ ወደ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ዶላር ድጋፍ አግኝተን ስድስት ምርምሮችን እያካሄድን እንገኛለን።
በአጠቃላይ በጤና፣ በግብርና እና በኢንደስትሪ ዘርፎች ላይ የሚመራመሩ ሰዎችን አወዳድረን ለይተን ለእያንዳንዳቸው 35 ሺህ ዶላር ሰጥተናል። በዚህ ሰዓት እነዚህ ተመራማሪዎች ሥራ እየሠሩ ነው። ሌላው በተጠሪ ተቋሞቻችን የምርምር ማዕከላት ላብራቶሪዎች ተገንብተው ሥራ እየሠሩ ነው። ጥሩ ጥሩ ሥራዎች አሉ።
ከዲጂታላይዜሽን አንፃር እዚህም ላይ ጥሩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። የመንግሥት ሥራዎችን በቴክኖሎጂ ታግዞ የመሥራት እና የኢንተርኔት አገልግሎት ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። በአጠቃላይ አገልግሎቶች ዲጂታላይዝድ እንዲሆኑ እየሠራን ነው። ወደ 528 የሚሆኑ በሀገር ደረጃ የለሙ የዲጂታል አገልግሎቶች አሉ።
ከእነዚህ ውስጥ 321 የሚሆኑት በእኛ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን የለሙ ሥራዎች ናቸው። ይህንን አጠናክረን መቀጠል አለብን። አጠቃላይ የአሠራር ሥርዓቱ ዲጂታላይዝድ እንዲሆን እንድናደርግ ለዘርፉ ኃላፊነት ተሰጥቷል። ስለዚህ እኛም እንደዘርፍ ሌሎችም የመንግሥት ተቋማትም በየድርሻቸው በሚመለከታቸው አገልግሎታቸውን እንዲያዘምኑ እኛ ድጋፍ እንሰጣለን፤ እየሰጠን ነው። ስለዚህ ጥሩ ነገር አለ። ነገር ግን ተግዳሮቶች አሉት።
ከሚለሙ ሥርዓቶች ሙሉ ለሙሉ ወደ ተግባር የማይገቡ አሉ። አንዳንዴ ግምገማ እናካሂዳለን። በሚለሙ ሥርዓቶች ድጋፍ ያደረግንላቸው በርግጥ ሥራ ላይ እየዋሉ ነው ወይ? ብለን ፍተሻ እናደርጋለን። ከዲጂታል አጠቃቀም ትምህርቱም አንፃር ዝቅተኛ እንደመሆኑ መጠን እዚህ ላይ በደንብ ግፊት መደረግ አለበት።
የለሙ ሥርዓቶች በሙሉ ጥቅም ላይ የማይውሉበት ሁኔታ እንዳለም ጭምር እናያለን። ነገር ግን ዞሮ ዞሮ ይሄ እንዲቀረፍ ከትምህርቱ ማለትም ከማንበብ እና ከመፃፉ ፤ ከትምህርት ሥርዓቱ ሆነ ከክህሎት አንፃር ስልጠናዎች በየወቅቱ እንዲሰጡ ፓኬጆችን እየቀረፅን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው። በዚህም ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው።
ጥያቄ፦ አዲስ አበባ ከተማን “ስማርት ሲቲ” የማድረግ እቅድ ነበር። እቅዱ ከምን ደረሰ?
ዶ/ር በለጠ፦ አዲስ አበባ ከተማን ስማርት ሲቲ የማድረግ እንቅስቃሴ እንደነበር፤ ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ስድስት ቦታዎችን ለይቶ “ስማርት አካባቢ”፣ “ስማርት ኢኮኖሚ”፣ “ስማርት ሞቢሊቲ ትራንስፖርት ሲስተም” ፣“ስማርት ሊቪንግ”፣ “ስማርት ፒውፕል” የሚሉ ኢኒሼቲቮች እንዳሉ እናውቃለን።
የኢኒሼቲቮቹ አላማ የነዋሪውን ሕይወት ምቹና ቀላል ለማድረግ ፤ጥራት ያለው ሕይወትን እንዲኖራቸው ለማስቻል ነው። በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ በዲጂታል አይሲቲ “ፕሮቮክድ” የሆነ የሕይወት እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው ነው። ከዚህ ውስጥ እኛ እንደ ተቋም “ስማርት ስቲ” የሚለውን ወስደን ወደ “ስታርትአፕ ሲቲ” ማዕቀፍ በመቅረጽ ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክብርት ከንቲባዋ ጋር በቅርቡ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል።
ስምምነቱ “የስታርትአፕ ሲቲ” እንዲገነባ ነው። ከተማዋ “ቫይብራንት” የሆነ “የስታርትአፕ” ከተማ ሆና “ስታርትአፖች” እየተደገፉ፣ ካምፓኒ ሆነው የሚወጡበትና ኢኮኖሚውን የሚያግዙበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው። “ስታርትአፕ” በተፈጥሮው ከከተማ ወደ ገጠር የሚሄድ በመሆኑ በቀጣይ ወደ ክልሎች የሚሰፋ ይሆናል።
ከተማ ላይ ጎልብቶ ውጤታማ ሲሆን፣ የሚገኙ ውጤቶች ተቀምረው ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ይወሰዳሉ። ይሄንን /በአዲስ አበባ ጀመርነውን/ ኢኒሼቲቭ ተግባራዊ ካደረግን በኋላ ወደ ክልል ከተሞች የምንሄድ ይሆናል።
ጥያቄ፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ብዙ ቴክኖሎጂዎችን ለዓመታት ከውጭ ስንቀዳ ነው የቆየነው፤ ይህንን ከመቀየር አንጻር የሚሰሩ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?
ዶ/ር በለጠ፦ ከዚህ አንጻር እኛ “የኢንኩቤሽን” ማዕከላት እየገነባን እንገኛለን። በጥቂት ጊዜ ውስጥ የምናስመርቀው፤ በአይሲቲ ፓርክ ውስጥ የኮሪያ መንግሥት ድጋፍ አድርጎልን እስከ ሶስት ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት በጣም ዘመናዊ የሆነ “የኢንኩቤሽን” ማዕከል ገንብተን ጨርሰናል። ሃሳብ ያላቸው “ስታርትአፖች ” በማዕከሉ ልምምድ እንዲያደርጉና ጎልብተው እንዲወጡ ለማድረግ የሚያስችል ነው።
ሌላው የሳይንስ ካፌዎች በዘጠኝ ክልሎች በመገንባት ላይ ናቸው። በአማካሪዎች ፍተሻ እየተደረገላቸው ነው። ካፌዎቹ የሳይንስ እና ኢኖቬሽን ባህል እንዲስፋፋ ወጣቶችም እነዚህን ማዕከላት ተጠቅመው ፈጣሪ የሚሆኑበትና የሚለማመዱበት ነው። የታለንት ማዕከልም ገንበተናል።
በቴክኖሎጂ የተደገፈ ኢኮኖሚ እውን እንዲሆን ጥረቶች አሉ። ለዚህም ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በጋራ ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን። ከኛ ተጠሪ ተቋማት መካከል አንዱ ፣ የስፔስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ነው። ከእነርሱ ጋር በመሆን ከተሞች አድራሻ ሥርዓታቸውን ዲጂታላይዝ እንዲያደርጉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ፕሮጀክቱ በዓለም ባንክ የሚደገፍ እና በጅምር ያለ ነው። በቀጣይ እሱን ጨርሰን የተወሰኑ ከተሞች ቢያንስ ቢያንስ ዋና ዋና የምንላቸውን ከተሞች የአድራሻ ሥርዓታቸው ዲጂታላይዝድ እንዲሆን ሥራዎች እንሠራለን። ይሄ ሁሉ ተደምሮ ከኢኖቬሽንና ዲጂታላይዜሽን ጋር የሚያያዝ እንደመሆኑ መጠን በዚህ መንገድ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።
ጥያቄ – በቡራዩ የተሰጥኦ ማበልጸጊያ ማዕከል ፍላጎቱ ያላቸው፣ አቅሙ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው የሚሰለጥኑበት አቅማቸው የበለጠ የሚጎለብትበት ለኢትዮጵያ ግብዓት እንዲያመጡ የሚጠበቅ ማዕከል ነው። ይሄ ማዕከል አሁን ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል? ምን ምን ሥራዎች እየሠራ ነው?
ዶክተር በለጠ፡ – በጣም ጥሩ! ስለራዕዩ ትንሽ ልበል፤ ቡራዩ ስንል ዝም ብሎ ትምህርት ቤት አይደለም። ቡራዩ የተሰጥኦ ማበልጸጊያ ማዕከል ወይም ትምህርት ቤት ነው። ትምህርት ቤት ስንለው እንደሌሎች ትምህርት ቤት አይደለም። ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው የኢትዮጵያ ልጆች ተሰጥዎአቸውን የሚያበለጽጉበትና የሚያዳብሩበት ዕድል በየቦታው የለም፤ መቸገር አለ። ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው አንደኛ በማህበረሰባቸው አንደርስታንድ አይደረጉም፤ ይህ ችግር አለ። ልዩ ተሰጥኦ አላቸው ማለት ትንሽ ወጣ ያለ ባህሪ ሊያሳዩ ይችላሉ።
እንደዛ ባይሆን እንኳን ልዩ ተሰጥኦ ካላቸው ያንን ወደ ውጤት መቀየር እንዲችሉ እንዲያዳብሩት ሁኔታዎች እንዲመቻችላቸው ይፈልጋሉ። የባከነ ተሰጥኦ፣ የባከነ ክህሎት፣ የባከነ ዕውቀት እንዳይኖር ከማሰብ አንጻር ቡራዩ ታለንት ማዕከል መገንባት አለበት ተብሎ ታስቦ በዚህ ተቋም ተገንብቷል። በጣም ዘመናዊ ነው። አንድ ሺህ አልጋዎች አሉት፤ እስከ አንድ ሺህ ተማሪ ያስተናግዳል። ቀጣይ ታለንት ሥራዎች እየተሠሩ በሀገሪቱ ታለንት ያላቸው ልጆች መጥተው እንዲሰለጥኑ እንድንሠራ ነው።
እስካሁን በሶስት ዙር ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ ከስፔስ ሳይንስ ጋር በመተባበር እነዚህን ታለንት ያላቸውን አስገብተን እያሰለጠንን አውጥተናል። አሁን ላይ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያሉ ታለንቶችን ደርሰን እዚህ መጥተው ሰልጥነው ክህሎታቸውን አዳብረው ምናልባትም ከተሳካላቸው ፕሮዳክት ይዘው ካምፓኒ መመስረት የሚያስችላቸው ሁኔታ እንዲኖር የመለያ መስፈርት ጨርሰናል። ፕሮግራም እየሠራን ነው በአሁኑ ሰዓት በዓለም ባንክ አማካሪ ቀጥረን ይህን ሥራ እንዲረከብ እያደረግን ነው።
በአጠቃላይ ይሄ እንዳለ ሆኖ በጥቆማም እንቀበላለን። ከቤተሰቦች ሊሆን ይችላል። ከትምህርት ቤቶች ሊሆን ይችላል። ልዩ ክህሎትና ተሰጥኦ አለው ብለው የሚያስቡት ልጅ ካለ በጥቆማ እየመጣ እየፈተሽን የዚህ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እናደርጋለን። በቀጣይ ይፋ ጥሪዎች ይኖራሉ። በሚዲያ ማስታወቂያው ይገለጻል። ከየትም ቦታ ያሉ ኢትዮጵያውያን አመልክተው የዚህ ሥራዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሥራዎች ይሠራሉ። በዓለም ባንክ አማካሪ ቀጥረን ይህ ሥራ ተጀምሮ እንዲሠራ እዛ ላይ ነው ያለነው።
ጥያቄ – ኢኖቪሽን በፈጠራ በቴክኖሎጂ የተሻለ ቦታ ለመድረስ የኢትዮጵያውያንን ሕይወት ለማሻሻል የዲጂታላይዜሽን ኢትዮጵያ 2025 ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። የዕቅዱ አመጣጠም ምን ይመስላል?
ዶክተር በለጠ፡- መጀመሪያ ላይ ያልኩት ከዚህ ጋር ይያያዛል። ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እስትራቴጂ ተቀርጾ ትግበራ ላይ ነው ያለው። ሶስት ዓመት ከስድስት ወር መጥተናል። 2012 ዓ.ም. ሰኔ አካባቢ ነው ወደ ሥራ ተገብቷል። የግማሽ ጊዜ ግምገማ አካሂደናል። ውጤቶችን አይተናል። እዛ ላይ የተገኙትን ውጤቶች ቆጥረናል። የታዩ ተግዳሮቶችንም ለይተናል። የኢንተርኔት ብሮድባንድ ተጠቃሚ መብዛቱ የሊብራላይዜሽኑ አሁን ላይ ሁለት ኦፕሬተሮች አሉን። የተገነቡ ኢንፍራስትራክቸሮች፣ መሠረተ ልማቶች የሞባይል ቁጥር ተጠቃሚ እያደገ መምጣቱ የክፍያ ሥርዓቱ እያደገ መምጣቱ ይሄ ሁሉ ዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂው ሲነደፍ አሳካቸዋለሁ ካላቸው ግቦች ውስጥ እየተሳኩ ያሉ ውጤታቸው ሊጠቀስ የሚችል ነው።
አሁን ላይ እንዳልኩት ገምግመናል አፈጻጸሙ ምን ይመስላል ብለናል። ክፍተቶችን አይተናል፤ የተገኙ ውጤቶችንም አይተናል። በቀሪ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ውስጥ ያየናቸውን ግምገማዎች መሠረት አድርጎ ክፍተቶችን ለመሙላት ሥራዎች ይሰራሉ።
በግምገማው ችግር ያለባቸውን ጥለን አዳዲስ ሃሳቦችም ካሉ እነርሱን ከስትራቴጂው አኳያ አያይዘን እንሄዳለን። በዚህም እንደ ሀገር የሚኖረን የዲጂታል ላንድ እስኬፕ ከቀደመው እጅጉን የተሻለ ውጤት የሚታይበት ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ጥሩ ነገሮች አሉ፤ ግን ይህ ሂደት ተግዳሮት ያልነበረው አይደለም። አንደኛ የመሠረተ ልማት ግንባታው ከፍተኛ ወጪን ይጠይቃል። ለሀገር ቀላል አይደለም። የግሉ ዘርፍ መጥቶ ከውጭም ኩባንያዎች ተጋብዘው የሚሠሩት ሥራ እንዳለ ሆኖ፤ ይህ በደንብ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ቀጣይ ተግዳሮት ሊሆን ይችላል። የፋይናንስ አቅርቦት ውስንነትም ራሱን የቻለ አንድ ሌላ ተግዳሮት ነው።
ሌላው የክህሎት ውስንነት ነው። በፈጻሚውም፣ በተጠቃሚውም፣ በአልሚውም የክህሎት ውስንነት ይታያል። ይህ ብቻም አይደለም፤ ከዲጂታል እውቀት ጋር በተያያዘም ውስንነቶች አሉ። ይህንን ለመሙላት አስፈላጊ የስልጠና ማዕቀፎች (ፓኬጆች) እየተቀረጹ ሥራዎች ይከናወናሉ።
ዲጂታል አካታችነትን ለማረጋገጥ ስትራቴጂ እየቀረጽን ነው። ስለዚህ ያሉትን ክፍተቶች እየሞላን የአምስት ዓመቱ የስትራቴጂ ዘመን ሲጠናቀቅ ከአምስት ዓመት በፊት የነበርንበት ሁኔታ ላይ እጅጉን ወደፊት የተራመደ ውጤት ይኖራል ብለን እንጠብቃለን።
ጥያቄ፡- ዘርፉ ሕይወትን እንደሚያቀለው ሁሉ ብዙ አደጋዎች/ ስጋቶች ያሉበት ነው ፤ እነዚህን አደጋዎች ለመቋቋም ምን እየተሠራ ነው ?
ዶክተር በለጠ፡- ሥጋቱ ሁሌም ሊኖር የሚችል ነው። አይደለም እኛ ገና ወደ እዚህ ዘርፍ እየገባን ያለነው ፤ በር እያንኳኳን የምንገኘውና ብዙ ርቀት መጓዝ ያለብን ሀገር ይቅርና ሙሉ ለሙሉ ዲጂታሉን የሚጠቀሙ ሀገራት እንኳን አደጋው ሊያጋጥማቸው ይችላል።
ከዚህ አንጻር በጣም የተጠናከረ የጥበቃ ሥራ፤ ተከታታይነት ያላቸው ፍተሻዎች ይደረጋሉ፤ የተሻለ ቴክኖሎጂዎች እየበለጸጉ የሥራ ሂደቶችን የሚያግዙበት ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
ሥጋቶች እንደ ሀገር ሁልጊዜ ይኖራሉ፤ ለዚህም ተብሎ የተቋቋመ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም አለ። እኛም በተሰጠን ኃላፊነት ልክ እንሠራለን። የጥበቃ ሥራውም አንዱ ኃላፊነታችን ነውና እርሱንም ጨምረን እንሠራለን። ወደ ቴክኖሎጂው እየገባን እንደመሆናችን መጠን የሚጠበቅ ተግዳሮት ይኖራል።
አዳዲስ ባህል ሲገነባ ፈተና (resistance) እንደሚኖር ሁሉ፤ ያሉ ክፍተቶችን የሚጠቀም የማስተካከያ ተግባራት ይኖራሉ። እነሱን በቀጣይነት ወይም በወጥነት እየተከታተሉ የእርምት ርምጃ እየወሰዱ፤ ቴክኖሎጂው የተሻለ የሚቋቋም እንዲሆን ሥራ እየተሠራ ነው።
ጥያቄ፦ እንደ ማህበረሰብ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጉዳዮችን የመረዳት የግንዛቤያችን ምን ላይ ነው? ግንዛቤውን ለማሻሻል ምን ዓይነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ትሠራላችሁ ?
ዶክተር በለጠ፡- የግንዛቤ ሥራ በሰፊው መሥራት ይጠበቅብናል። እንዳልኩት ያለነው በቴክኖሎጂ በበለጸገ ሀገር አይደለም። አብዛኛው ማህበረሰባችን በግብርና ላይ ተሰማራ (agrarian) ነው። ለቴክኖሎጂ ያለው ምልከታ ተግዳሮት ይኖራል።
የምናለማቸው የዲጂታል ሥርዓቶች በትልልቆቹ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ችግር ያጋጥማቸዋል (resistance) በዚህ የተነሳም የለሙ ሥርዓቶች ወደ ሥራ ወዲያውኑ የማይገቡበት ሁኔታ አለ። እንደ ሀገር ደግሞ ስንወስደው አዲስ ነገርን ቶሎ ያለመቀበልና ያለመላመድ ባህል (retention culture) አለ።
በታሪክ እንደምናውቀው በፊትም የቀደሙ መሪዎች ቴክኖሎጂን ሲያስተዋውቁ ማህበረሰቡ እንደ ማህበረሰብ ቴክኖሎጂዎችን ለመላመድ እና ለመቀበል ጊዜ የሚወስድበት ሁኔታ ነበር። አሁንም እንደዚሁ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በገጠርና በከተማ ያለው ልዩነት ቀላል አይደለም። ከተሞች እየቀደሙ እየሄዱ ነው፤ ወደ ባህሉ ውስጥ እየገቡ ነው፤ እራሳቸውን ከዓለሙ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ለማስኬድ ጥረቶች አሉ።
ከተሞች እየቀደሙ እየሄዱ ነው። ገጠሩ ደግሞ ገና ያልተነካ ነው። ቴክኖሎጂውን በገጠሩ ተደራሽ ለማድረግ ብዙ ሥራ እየተሠራ እና ጥሩ ውጤትም እየተመዘገበ ነው፤ ይህም ሆኖ ግን በገጠርና በከተማ ያለው ልዩነትና በዚህ ምክንያት እየተፈጠረ ያለው ተግዳሮት ሰፊ ነው። ይህንን ችግር ለመፍታትና ለማሻሻል የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነት ብቻ አይደለም።
ስለ ቴክኖሎጂ፣ ዲጂታላይዜሽን ስናወራ ሁሉንም ይመለከታል። ሚኒስቴሩ እንደ መንገድ ጠራጊ (polish) እቅዱን ያዘጋጃል። ፖሊሲዎች እንዲቀረጹ ያደርጋል። ያንን መሬት ማውረድና ፖሊሲዎቹ በጠቆሙት ልክ ሥራ ላይ ማዋል የሁሉንም ጥረት የሚጠይቅ ነው።
የሚመለከታቸው ሁሉም የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም የግል ዘርፉ በጋራ በምንሠራው ሥራ ነው ቴክኖሎጂን ለማወቅና ለመጠቀም ከፍተኛ ጉጉት ያለው (inspired) ማህበረሰብ መፍጠር የሚቻለው። ተግዳሮቱ አለ ፤ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ሰፊ ሥራ ይጠብቀናል። ሁላችንም ተረባርበን ውጤታማ ማድረግ አለብን።
ጥያቄ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት ከሩሲያ መንግሥት ጋር የኒውክሌር ኃይልን ለሰላም ጥቅም ለማዋል የሚያስችል ስምምነት ተፈራራሟል። ይህ ስምምነት ከምን ደረሰ?
ዶክተር በለጠ፡- እዚህም ላይ ብዥታው መጥራት አለበት። ኒውክሌር ሲባል የብዙ ሰው አይምሮ ላይ የሚመጣው የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ነው። እንደዚያ አይደለም። ኢትዮጵያ ለመገንባት ስምምነት ላይ የደረሰችውና እቅዷም ኒውክሌርን ለሰላማዊ አላማና ለልማት ለማዋል ነው።
በዓለም ላይ በስፋት እየዋለ ያለውም ለዚሁ ነው። ኒውክሌር በሕክምና፣ በእርሻው በኢንዱስትሪው አለ። በብዙ ዘርፎች አለ። የጨረራ ሕክምና አለ። በራዲየሽን ቴክኖሎጂ አለ። እነዚህ ሁሉ በኒውክሌር ፓኬጅ ውስጥ ያሉ ናቸው።
ስለዚህ እኛ ለኃይል እና ለተለያዩ ሰላማዊ ተግባራት የሚውል የኒውክሌር ፓወር ግንባታ ከሩሲያ ጋር ተፈራርመናል። ከሩሲያ የኒውክሌር ዋና ተቋም/ ሮሳቶ ጋር ባለፈው ሐምሌ በቅዱስ ፒተርስፐርግ ከተማ የሮድ ማፕ ስምምነት አድርገናል። የኃይል አማራጭን ማስፋት ስለሚያስፈልገን ።
ኢነርጂ ከውሃ ፣ ከንፋስ ፣ ከጂኦተርማል ኢነርጂን ማልማት ያስፈልጋል። ልክ እንደነዚህም ኒውክሌር የሚሠጠውን የኢኮኖሚ ትሩፋትም መጠቀም ያስፈልጋል። ስለዚህ ከኒውክሌር ኃይል እንድናገኝ የኃይል አማራጮቻችንን ምንጮች በማስፋት በማቀድ ይህን ፋሲሊቲ ለመገንባት በማቀድ በአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ውስጥ ተካቷል።
በአሁኑ ወቅትም የአዋጭነት ጥናት እንዲጠና ለማድረግ የግዢ ፈቃድ የሚሠጥ አካል ፈቃድ እንዲሰጠን ሥራዎች እየሠራን ነው። እዚህ ላይ ነው ያለው። የአዋጭነት ጥናቱ ተጠንቶ በዓመታት ይህን ገንብተን እውን በማድረግ ሀገራችን ከዚህ ዘርፍ ማግኘት ያለባትን እድል እንድታገኝ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በሰው ሀብት ልማት ረገድ ሥራዎች እየሠራን ነው። አምስት ተማሪዎች ወደ ቻይና ሀገር ልከን በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ በኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ላይ ናቸው። ሩሲያም፣ ጣሊያንም እንደዚሁ ተማሪዎቹ አሉን።
ኒውክሌር ከተነሳ አይቀር ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በቅርበት እንሠራለን። እነሱም የጨረር ሕክምና “የራዲየሽን ትሪትመንት” ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲኖር በተለይ ዩኒቨርሲቲዎቻችንና ሆስፒታሎች ከዚህ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ባደረግነው ሥራ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች ተመርጠው፤ በአሁኑ ሰዓት በጥቁር አንበሳ ዩኒቨርሲቲ የካንሰር ትሪትመንት መስጠት የሚያስችል መሳሪያ ተተክሎ ሥራ ላይ ነው።
በቀጣይም ጅማ ፣ ጎንደር፣ ሀዋሳ ፣ አለማያ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የካንሰር ትሪትመንት ፣ የራዲየሽን ትሪትመንት ማዕከል እንዲገነባ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ይህንንም የሚደግፈው የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ነው። ይህም በኒውክሌር ማዕቀፍ ውስጥ የሚታይ ነው። ኒውክሌር ለሰላማዊ አላማ ይውላል ስንል ከጤናም አንፃር የሚታይ ስለሆነ ይህንን አጠናክረን የምንሄድበት ይሆናል ማለት ነው።
ጥያቄ፡- የስድስት ወር የሥራ አፈፃፀማችሁ ምን ይመስላል?
ዶክተር በለጠ፡- እንደ አጋጣሚ ትላንትም ይሄንን በማኔጅመንት ገምግመናል። በመጀመሪያው ሩብ የእቅድ አፈጻጸም ጥሩ ውጤቶች ነበሩ። ቅድም ስገልጸው የነበረው በኛ ሆነ በተጠሪ ተቋማት በስድስት ወር አፈፃፀማችን ላይ የታዩ ናቸው። ጥሩ ሥራዎች አሉ ፤ በመሃል የገጠሙን ተግዳሮቶች አሉ፤ እነዚህን በአግባቡ ገምገማናል። በቀጣይ ስድስት ወር የግምገማ ውጤቶቻችንን ታሳቢ ባደረገ መንገድ ማሻሻያዎችን አድርገን የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችል አቅጣጫዎች አስቀምጠናል። በዚህ ላይ ነው ያለነው፤ ጥሩ ነው።
ጥያቄ፡- ለሰጡን ጊዜ እጅግ በጣም እናመሰግናለን።
ዶክተር በለጠ፡- እኔም እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም