የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በበርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች የበለጸገ ነው፡፡ በክልሉ ከፍተኛ ክምችት ያለው የማዕድናት ሀብት ይገኛል፡፡ እንደ ወርቅ ያሉ የከበሩ ማዕድናት፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለኮንስትራክሽን እና ለመሳሳሉት በግብአትነት ሊውሉ የሚችሉ እንደ ድንጋይ ከሰል ያሉ በርካታ ማዕድናት በስፋት አሉት፡፡ ክልሉ በአሁኑ ወቅት በተለይ በድንጋይ ከሰል ማአድን ባለቤትነቱ ብቻ ሳይሆን በምርቱም መታወቅ ችሏል፡፡
ከክልሉ የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው፤ የክልሉን ማዕድናት በጥናት ለመለየት በተከናወነ ተግባር በርካታ ማእድናት መኖራቸውን ማረጋገጥ ተችሏል፤ በአንጻሩ ገና ያልተለዩ ማእድናትም አሉ፡፡ በጥናት የተለዩትን ማዕድናት በማልማት ረገድ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡
የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተርና የማዕድን ዘርፍ ኃላፊ አቶ መንገሻ መዳልቾ ክልሉ እንደ ውሃ አካላት፣ ማዕድን ሀብት እና ደን ሀብት ባሉት የተፈጥሮ ሀብቶች የበለጸገ መሆኑን ይገልጻሉ። በክልሉ በርካታ የማእድን ሀብቶች ቢኖሩም አልምቶ ከመጠቀም አንጻር ቀደም ሲል ክልሉ ውስንነቶች ነበሩበት የሚሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር እምብዛም እንዳልተሰራም ይገልጻሉ፡፡ የማዕድን ዘርፍ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በመንግስት ታምኖበት ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ተከትሎ በክልሉ የማእድን ሀብቶች ላይ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ይናገራሉ፡፡
ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚውሉ ማዕድናት
በክልሉ የማዕድን ዘርፍ እየተከናወኑ ካሉ ተግባሮች መካከል ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑ ማእድናት ልማት በሰፊው እየተሰራበት ይገኛል፡፡ ለኢንዱስትሪ ኃይል ማመንጫነትና ለመሳሰሉት ግብዓት ሊውል በሚችለው የድንጋይ ከሰል ልማት ላይ በስፋት እየተሰራበት ነው፡፡ የድንጋይ ከሰል ጥራትን መጨመር የሚያስችል ፕሮሰሲንግ ማሽን በዳውሮ ዞን የተከላ ሥራው እየተጠናቀቀ ይገኛል። ሌሎች የድንጋይ ከሰልን በሰፊው ለማምረት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችና ፍላጎቶችም አሉ፡፡
ለሴራሚክ ማምረት ስራ ግብዓት የሚውሉ ካዮሊን፣ ግራናይት፣ እምነበረድ፣ የኖራ ድንጋይ እና የመሳሳሉት ማዕድናት በክልሉ በስፋት ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ማዕድናት ለማልማት አልሚዎች ማዕድኑን በጥናት በመለየት ወደ ምርት ፈቃድ ደረጃ እየተሸጋገሩ ይገኛሉ፡፡ ይህም አሁን የማዕድን ዘርፉ ልማት ተጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ ለውጥ አምጥቷል የሚባል ባይሆንም፣ ተስፋ ሰጪ ነገሮች ስለመኖራቸው ግን አመላካች ነው፡፡ ለሴራሚክ ማምረት ስራ ግብዓትነት የሚውሉ ማዕድናት ሰፊ ክምችት መኖሩ ወደፊት በክልሉ ፋብሪካዎችን የመቋቋም ተስፋ እንዳለ ያሳያል፡፡
ሌላኛው የኖራ ድንጋይ ሲሆን፣ ይህም ከ50 ዓመትና ከዚያ በላይ ሊመረት የሚችል ክምችት መኖሩ ከተረጋገጠ በክልሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የማቋቋም እድል ይፈጥራል፡፡ አሁን የእነዚህን ማዕድናት ክምችት በደንብ ለማወቅ ጥናቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፤ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች መኖራቸውም ለማዕድን ዘርፉ ተስፋ የሚሰጥ እድል መኖሩን እንደሚያመላክት ነው ምክትል ዳይሬክተሩ የጠቆሙት፡፡
የኮንስትራክሽን ማዕድናት
ክልሉ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ሊውሉ የሚችሉ ማዕድናት መገኛም ነው፡፡ እምነ በረድ፣ ግራናይት፣ የኖራ ድንጋይ (ለሕንጻና ለግርግዳ ምንጣፍ የሚውል በመሆኑ) እና ሌሎች ማእድናትን የመለየት ስራ እየተከናወነ ነው፡፡
ብረትና ብረትነክ ማዕድናት
በክልሉ ከሚገኙት ማእድናት መካከል ብረትና ብረትነክ ማዕድናት ይጠቀሳሉ፡፡ በአዋጁ መሠረት ብረትና ብረትነክ ማዕድናት ፈቃድ የሚሰጠው በማዕድን ሚኒስቴር አማካኝነት ነው፡፡ በመሆኑም በምርመራ ሥራ ፈቃድ ያገኙ ባለሀብቶች በክልሉ በዳውሮ ዞን፣ በኮንታ እና በከፋ ኮሪደሮች ላይ ፈቃድ አግኝተው በእነዚህ ማእድናት ላይ ጥናት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ብረትና ብረትነክ ማዕድናትን በባሕላዊ መንገድ ለሚያወጡ የአካባቢው ሰዎች ማእድናቱን የማውጣት ፈቃድ ተሰጥቷቸው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡
የከበሩና በከፊል የከበሩ ማዕድናት
የከበሩና በከፊል የከበሩ ማዕድናትም በክልሉ ይገኛሉ። ከከበሩ ማዕድናት ውስጥ አንዱ የወርቅ ማእድን ሲሆን፣ በክልሉ በወርቅ የማምረት ሂደት የአፈጻጸም ውስንነት ቢኖርም ወርቅ የማምረት ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡ ወርቅ ለማምረት በማዕድን ሚኒስቴር ፈቃድ የተሰጣቸው በምርመራ ላይ የሚገኙም ኩባንያዎች አሉ። በክልሉ ፈቃድ የተሰጣቸው ባሕላዊና አነስተኛ የወርቅ አምራቾች ደግሞ በማምረት እንቅስቃሴ ላይ ናቸው፡፡
የወርቅ ማውጣቱ ስራ በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት ከወትሮ በተለየ መልኩ ድጋፍና ክትትል እየተደረገበት መሆኑን ተከትሎ ወርቅ የማምረት ሂደቱ አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ምክትል ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ የጌጣጌጥ ማዕድናትም ከከበሩ ማዕድናት መካከል የሚመደቡ ናቸው፡፡ ክልሉ የተለያየ ቀለም ያላቸው የአጌት፣ ኦፓል እና የመሳሳሉት ማዕድናት መገኛም ነው፤ በቤንች ሸኮ ዞን አካባቢ አንድ አልሚ የኦፓል ማዕድን ማልማት ፈቃድ አውጥቶ ወደ ምርት ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ነው፡፡
በማዕድን ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች
በምዕራብ ኦሞ ዞን በኮንስትራክሽን ማዕድናት ላይ ሁለት ባለከፍተኛ ፈቃድ አልሚዎች ፈቃድ ወስደው በእምነበረድ ልማት ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በዳውሮ ዞን ሁለት አምራቾች በግራናይትና በኖራ ድንጋይ ልማት ላይ የተሰማሩ ሲሆን፤ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውለው የካዮሊን ማዕድንን ለማምረት አንድ ባለሀብት ፈቃድ ወስዷል፡፡
‹‹የድንጋይ ከሰል ማዕድን በማምረት ሂደት 18 የሚሆኑ አምራቾች ተሰማርተዋል›› ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ ‹‹አሁን ብዙዎቹ በቅኝትና በምርመራ ሂደት ላይ ይገኛሉ›› ብለዋል፡፡ በማዕድን ቅኝትና ምርመራ ስራ ለመሰማራት 178 ያህል ፍላጎቶች እንዳሉም ጠቅሰው፣ በክልሉ ያለው የማዕድን ሀብት ውስን እንደመሆኑ በዘርፉ ተሰማርተው የነበሩትን አምራቾች በአግባቡ ተቆጣጥሮ ወደ ሥራ ለማስገባት ስለተፈለገ አዲስ ፈቃዶችን የመስጠቱ ሥራ መታገዱን ምክትል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዝናባማ አካባቢ እንደሆነና ከባለፈው ዓመት የካቲት ወር እስከ ኀዳር ወር ድረስ በክልሉ ዝናብ ይጥል እንደነበር አስታውሰው፤ አምራቾች አሁን ፈቃዳቸውን አድሰው ወደ ምርት ሥራ ለመግባት እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑንም አመላክተዋል። በበጀት ዓመቱ ያለው የምርት አፈፃፀም በጣም ውስንና ማምረት ከተፈለገው አቅም በታች መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የገበያ ትስስር
በአንዳንድ አምራቾች በኩል የሚቀርቡ የገበያ ትስስር ችግሮች እንዳሉም ምክትል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። እነዚህም ከጥራት ጋር ተያይዘው የሚነሱት ችግሮች መሆናቸውን ይገልጻሉ፤ በክረምት ምክንያት ምርቶችን ከቦታ ወደ ቦታ ለማንቀሳቀስ ከመንገድ ጋር ተያይዞ መስተጓጎል እንደሚታይ ጠቅሰው፤ አምራቾች በተፈጠረው የገበያ ትስስር መሠረት ምርቶችን በፍጥነት ማቅረብ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ ምርቱን የሚፈልጉት ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ምርቶቹን ከሌላ ቦታ በማምጣት እየተጠቀሙ መሆናቸውን ተከትሎ የአካባቢው አምራቾች በድጋሚ የገበያ ትስስር ለማግኘት እንደሚቸገሩ አመልክተዋል፡፡
የሥራ እድል ፈጠራ
በማዕድን ዘርፉ የሥራ እድል ፈጠራን በተመለከተ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ ለሦስት ሺ607 ሥራ አጥ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ፤ ለሁለት ሺ 711 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡
ያጋጠሙ ተግዳሮቶች
በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት 15 ኪሎግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ መቻሉን ጠቅሰው፣ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በሰራው ሥራ አሁን በወር 22 ኪሎግራም የወርቅ ምርት ወደ ብሔራዊ ባንክ ማስገባት ተችሏል ብለዋል፡፡ የወርቅ ወርሃዊ ምርት መጠን እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ቀጣይነቱ ላይ ግን ስጋቱ እንዳላቸውም ምክትል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። ‹‹ጥብቅ ቁጥጥር ሲደረግ የተወሰነ መሻሻሎችን ያሳያል፤ ቁጥጥሩ ሲላላ ደግሞ ምርቱ በዚያው ልክ ያሽቆለቁላል›› ይላሉ፡፡
የወርቅ ሕገወጥ ዝውውር በወርቅ ምርት ላይ የተጋረጠ ከባድ ፈተና መሆኑን ጠቅሰው፣ በኮንትሮባንድ የመሸጥና ወደ ጋምቤላ ክልል ይዞ የመውጣት ችግሮች ይስተዋላሉ ብለዋል፡፡ በዚህ የተነሳ አነስተኛ የወርቅ አምራቾች ማህበራት የፈረሱበት ሁኔታ እንዳለም ገልጸዋል፡፡ ይህን ሕገወጥ የወርቅ ዝውውር ለመቆጣጠር ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፣ የወርቅ ማምረቻ ቦታው ወደ ድንበር አካባቢ ስለሆነ ለክትትል አመቺ አይደለም ይላሉ፤ ክትትሉ በዘላቂነት እንዳልቀጠለም ጠቅሰው፣ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከክልሉ ከጸጥታ መዋቅር ጋር እየተሰራ ያለው ሥራ ይጠናከራል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ በ2016 በጀት ዓመት 400 ኪሎግራም ወርቅ ለማምረት የታቀደ ሲሆን፤ በግማሽ ዓመቱ 200 ኪሎ ግራም እንደሚመረት ይጠበቅ ነበር፡፡ እስካሁን ያለው አፈጻጸም 36 ነጥብ 6 ኪሎ ግራም ነው። ይህ ትልቅ ክፍተት እንደሆነም ይገልፃሉ፡፡ በ2014 በጀት ዓመት እስከ 400 ኪሎ ግራም የወርቅ ምርት የተገኘበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን የሚታዩት ብልሹ አሠራሮች ከተቀረፉና ትኩረት ተሰጥቶት በደንብ ከተሰራ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ምክትል ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በኢንዱስትሪ ማዕድንም በግራናይት፣ ዳሜንሽን ስቶን እና ካዮሊንን በማምረት ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፤ ካዮሊን 90 በመቶው ለሴራሚክ ፋብሪካ የሚፈለግ ማዕድን ነው፡፡ ሆኖም ግን በአካባቢው ኢንዱስትሪው ስለሌለ አምራቾቹ ይህንን አፈር ጭነው፣ ረጅም ርቀት ተጉዘው ኢንዱስትሪው ወዳለበት ቦታ ማድረሱ አዋጭ አልሆነላቸውም። የማዕድኑ በዚህ ልክ መገኘት በክልሉ የሴራሚክ ፋብሪካዎች የሚከፈቱበትን እድሉ ያሰፋዋል፡፡ በዚህ ማዕድን ፈቃድ የወሰደው አምራችም ፈቃዱን ይዞ ሌላ አማራጭ እየጠበቀ እንደሚገኝ ምክትል ዳይሬክተሩ አመላክተዋል፡፡
የግራናይትና የኖራ ድንጋይ ማዕድናትን ለማምረት የሚፈልጉ አካላት ፈቃድ ያገኙት በዚህ ዓመት በመሆኑ፤ በዚህ በኩል ያሉት ሥራዎች ገና በጅምር ላይ ናቸው። ብረትና ብረትነክ ማዕድናትንም በተመለከተ እስካሁን ምርመራውን ጨርሶ ወደ ምርት የገባ የለም፡፡ በማዕድኑ ዘርፍ እየተሰሩ ያሉት ሥራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የትኩረት አቅጣጫውን ተከትሎ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ ሀገር ውስጥ ያለውን ሀብት በመለየትና በማልማት ለኢኮኖሚ እድገት በገቢ ምንጭነት ወይም በግብዓትነት መጠቀም ምርጫ እንደሌለውም አስታውቀዋል፡፡
መፍትሔዎች
ከድንጋይ ከሰል ምርት ጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት በማዕድን ሚኒስቴር ኢንዱስትሪ ኢንሼቲቭ አማካኝነት ኢንዱስትሪዎች ምን አይነት የድንጋይ ከሰል ምርት ያስፈልጋቸዋል? ምን አይነት ምርትስ አለ? በሚለው ላይ ጥናት ማካሄድ መጀመሩን ምክትል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ጥናቱ ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን የድንጋይ ከሰል ካሎሪ መጠን ለመለየት የሚያስችል ነው፡፡ አሁን በአብዛኛዎቹ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከስድስት ሺ በላይ ካሎሪ መጠን ያለው የድንጋይ ከሰል ነው የሚቀበሉት፡፡ ከዚህ በታች ካሎሪ ያለውን የድንጋይ ከሰል አንቀበልም የሚሉበት ሁኔታ አለ፡፡ የጨርቃጨርቅ፣ የቀለም እና የመሳሰሉት ፋብሪካዎች ደግሞ ከዚህ ዝቅ ያለ የካሎሪ መጠን ይጠቀማሉ፡፡ ይህን ፍላጎት በመለየት አስተማማኝ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ ነው፡፡
እስከዚያ ግን በዳውሮ ዞን የተተከለው የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ /ፕሮሰሲንግ/ ማሽን በቀን አንድ ሺ500 ቶን የድንጋይ ከሰል ማጠብ ይችላል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ፋብሪካው በድንጋይ ከሰል ምርት ላይ ያለውን የጥራት ችግር ሊፈታ እንደሚችል ታምኖበት እየተሰራ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ተጨማሪ የማጣሪያ ማሽን ለመትከል ፍላጎት ያላቸው ሌሎች አምራቶች መኖራቸውንም ጠቅሰው፤ አሁን ላይ እየታየ ያለው ጅምር ጥሩ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
የወርቅ ማምረትን በተመለከተም ወርቅ በሚመረትበት ቤሮ ወረዳ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ መክፈቱን ጠቅሰው፣ አምራቾች የወርቅ ምርቱን ለባንኩ እንዲያስገቡ የሚደረግበት ሁኔታ መፈጠሩን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም በተወሰነ መልኩ ችግሩን ለመቅረፍ ተችሏል ብለዋል። አሁን እንደ ችግር የሚነሳው የኔትወርክና የመንገድ መሰረተ ልማት አለመኖር መሆኑን ጠቅሰው፣ የጸጥታ ችግር ሌላው የልማቱ ተግዳሮት መሆኑን አስታውቀዋል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች
በማዕድን ዘርፍ በክልሉ ይህ ሁሉ ሀብት መኖሩ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እንዳሉ ያመላክታሉ ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይ የተሻለ ጥናት ቢደረግ ሰፊ ሥራዎች መስራት እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡ የክልሉ የማእድን ሀብት ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪና የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካትና ምርቶቹን ወደውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት በኩል ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ምክትል ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።
በቀጣይ በማዕድን ዘርፉ ላይ የሚደረገው ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ በወርቅ ላይ ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች በተጨማሪ ልዩ አነስተኛ ባለ ፈቃድ የሚባሉትም ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ እነዚህ አምራቾች ማሽን ተጠቅመው የሚያመርቱት የወርቅ ምርት የተሻለ ውጤት ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ያመለከቱት፡፡
ይህ ሁኔታ በድንጋይ ከሰል አምራቾች ዘንድም መነቃቃት እንዲፈጠር ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የበጋ ወቅት ለማዕድን ሥራዎች ምቹ መሆኑን ጠቅሰው፣ አምራቾቹ በዚህ ወቅት በሙሉ አቅም ወደሥራ እንዲገቡ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የተሻለ አምርቶ የተሻለ ገቢ እንዲገኝ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጥር 10/2016